ጳውሎስ ምን ጊዜም ቢሆን ክብሩን ለራሱ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ላመስጠት የፈጠነ ነበር። መተማመኛው እግዚአብሔር እንደ መሆኑ፥ ብቃቱም የሚመጣለት ከእግዚአብሔር ነበር። ጳውሎስ ንቁና በሚገባ የተማረ ሰው ቢሆንም፥ በጌታ እንጂ በራሱ ብቃት ላይ አልተደገፈም።
በርግጥ የሕግ መምህራን፥ ማንኛውም ሰው ሕግን በመጠበቅ መንፈሳዊ ሊሆን እንደሚችል አስተምረዋል። ዳሩ ግን የሕግ ትምህርት የሰዎችን ራስ-ወዳድነት አዝማሚያ የሚያጎላብት ነው። በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የምናተኩር ከሆን፥ ሰዎች ራሳቸውን ለማዳን የማይችሉ የጠፉ ኃጢአተኞች መሆናቸውን መናገር አለብን። የጳውሎስ ምስክርነት «ነገር ግን አሁን የሆንሁትን የሆንሁት በእግዚአብሔር ጸጋ ነው» (1ኛ ቆሮ. 15፡10 – አዲስ ትርጉም) የሚል ነበር፡፡ ማንም ሰው በራሱ ከሰዎች ልብ ዘልቆ የሚደርስ አገልግሎት የማቅረብ ብቃት የለውም። ያ ብቃት ሊመጣ የሚችለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው።
ይህን ምዕራፍ ስታነብ ሳለ፥ ጳውሎስ አሮጌውንና አዲሱን ቃልኪዳን በሚያነጻጽርበት ወቅት የሚሰጣቸውን ስያሜዎች በጥንቃቄ አስተውል። በቁጥር 6 ውስጥ፥ «ፊደል» የሚለው ቃል የአሮጌውን ቃል ኪዳን ሕግ የሚያመለክት ሲሆን፥ «መንፈስ» ደግሞ አዲሱን የጸጋ መልእክት ያሳያል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎሞችን ማለትም «ቃል በቃል ትርጉም» እና «መንፈሳዊ ትርጉም» እያነጻጸረ አልነበረም። በምትኩ፥ የብሉይ ኪዳን ሕግ ሕይወት ሊሰጥ እንደማይችልና የሞት አገልግሎት እንደ ሆነ ለአንባቢዎቹ እያስታወሰ ነበር (ገላ. 3፡21 ተመልከት)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከፈጸመው ሥራ የተነሣ፥ ወንጌሉ ለሚያምኑት ሕይወት ይሰጣል።
ጳውሎስ ሕግ ስህተት እንደ ሆነ ወይም አገልግሎቱ አላስፈላጊ እንዳልሆነ እየገለጸ አልነበረም። አሳቡ ከዚህ የራቀ ነው! ጳውሉስ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ጸጋ ከመዳኑ በፊት፥ በሕግ ሊገደልና ተስፋ በሌለው ሁኔታ ሊኮነን እንደሚገባው ጭምር ያውቅ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስና የሚያድን ጸጋ ላለበት መልእክቱ መንገድ የሚጠርግ፥ የፍርድ መልእክት ይዞ ነበር የመጣው።
የሕግ አገልግሎት ሞትን ያመጣል። በሕግጋት ትምህርቶች የሚመረቁ ሰባኪዎች ማህበሮቻቸውን ጽልመት ባጠላበት የበደለኛነት ደመና ውስጥ ሸሽገው ያኖራሉ፤ ይህም ደስታቸውን፥ ኃይላቸውንና ለክርስቶስ የሚኖራቸውን ፍሬያማ ምስክርነት ይገድለዋል። የየግል ችሎታቸውን ባለማቋረጥ የሚያነፃፅሩ፥ « ውጤቶቻቸውን» የሚያወዳድሩ፥ ብሉም እርስ በርስ የሚቀናኑና የሚፎካከሩ ክርስቲያኖች ብዙም ሳይቆይ በሥጋ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደማይደገፉ ይረዳሉ። አሥርቱን ትዕዛዛት ጨምሮ፥ የሰውን ሕይወት የሚለውጥ መመዘኛ ከቶውንም ሊገኝ አልቻለም። የጠፉትን ኃጢአተኞች ኢየሱስ ክርስቶስን ወደሚያስከብሩ መልእክተኞች ሊለውጥ የሚችለው፥ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚስተናገደው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው።
ጳውሎስ የአዲሱን ቃል ኪዳን ትምህርቱን ለአጋጣሚው እንዲስማማ ብሉ የፈጠረው አልነበረም። እንደ ጥንቁቅ የቅዱሳት መጻሕፍት ተማሪነቱ፥ ጳውሎስ ኤርምያስ 31፡27-34፥ እንዲሁም ሕዝቅኤል 11፡14-21ን አንብቦ ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ዕብራውያን ምዕራፍ 8-10 መጠናት ያለበት ቁልፍ ምንባብ ነው። በውጫዊ ታዛዥነት ላይ የሚያተኩረው አሮጌው ኪዳን፥ ለአዲሱ የጸጋ መልእክትና ለውስጣዊ የልብ ለውጥ ቅድመ ዝግጅት ነበር።