ሥርዓት (1ኛ ቆሮ 14፡26-40)

በዚህ ክፍል ሁለት አባባሎች አብረው ይሄዳሉ። «ሁሉ ለማነጽ ይሁን» (ቁ 26)፥ እና «ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን» (ቁ. 40)። አንድ ሕንጻ በሚሠራበት ጊዜ ፕላን ሊኖር ይገባል፤ አለበለዚያ ሁሉም ነገር ትርምስምሱ ይወጣል። የቄሶችን ቤት ለመሥራት ትልቅ ችግር ገጥሞት የነበረ አንድ ቤተ ክርስቲያን አውቃለሁ። የጣውላ ማከማቻ ክፍል ፕላን በተቋራጩ እጅ ካለው የተለየ መሆኑን አንድ ሰው እስከሚደርስበት ድረስ ናላ የሚያዞር ሆኖ ነበር። በዚህም የተነሣ ወደ ስፍራው የተጫነ ቁሳቁስ ከሕንጻው ጋር አልገጥም ብሎ ነበር። 

የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሰማኅበር ስብሰባዎቻቸው ወቅት የሥርዓት መጓደልን በተመለከተ ልዩ ችግሮች ነበሩአቸው (11፡17-23)። ምክንያቱ ለማወቅ የሚከብድ አይደለም። በመንፈሳዊ ስጦታዎቻቸው ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ሳይሆን ራሳቸውን ለማስደሰት ይጠቀሙባቸው ነበር። እዚህ ላይ ቁልፍ ቃል ማነጽ ሳይሆን ማሳየት ነበር። የአንተ የአገልግሎት ድርሻ ከወንድምህ የበለጠ የባሰ ጠቃሚ ነው ብለህ ካሰብህ፥ ወይ እስከሚጨርስ ትዕግሥት አይኖርህም፥ ወይም ታቋርጠዋለህ። በዚህ ላይ «አርነት የወጡ ሴቶች» በጉባኤው የሚፈጥሩትን ፍዳ ስትጨምርበት፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምን ሥጋዊ ውዥንብር ውስጥ እንደገባች ማስተዋል ትችላለህ። 

ቁጥር 26 በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን የአምልኮ ሁኔታ እጥር ምጥን ያለ ሥዕል ይሰጣል። እያንዳንዱ ምእመን እግዚአብሔር እንደመራው ለተሳትፎ ይጋበዝ ነበር። አንዱ የመዘመር ፍላጎት ሲያድርበት (ኤፌ 5፡19፤ ቆላ. 3፡16)። ሌላው ደግሞ ዶክትሪን ለማካፈል ምሪት ይቀበል ነበር። አሁንም ሌላው በልሳን የሚቀርብና የሚተረጎም መገለጥ ይመጣለት ነበር። እግዚአብሔር የሰጠው የሆነ ዓይነት ሥርዓት ካልነበረ በቀር ምንም ዓይነት መታነጽ ከቶውንም የማይታሰብ ነው። 

ከፍተኛውን ችግር ይፈጥሩ የነበሩት በልሳኖች የሚናገሩት እንደነበሩ ልብ በል። በመሆኑም ጳውሎስ ወደ እነርሱ በማነጣጠር በማኅበር ስብሰባዎቻቸው የሚታዘዙአቸውን በርካታ መመሪያዎች ለቤተ ክርስቲያን ሰጠ። 

በመጀመሪያ፥ መናገርና መተርጎም፥ ከመለየት ጋር ተዳምሮ (መልእክቱን መገምገም) ሥርዓት ባለው መንገድ መደረግ ነበረበት (ቁ 27-33)። በማንኛውም ስብሰባ ከሦስት የበለጡ ተናጋሪዎች መኖር አልነበረባቸውም፤ እያንዳንዱ መልእክት በቅደም ተከተል መነገርና መገምገም ነበረበት። ተርጓሚ ከሌለ በልሳኖች የሚናገር ዝም ማለት ነበረበት። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ጉባኤ የሰጠው ምክር ተግባራዊነቱ እዚህ ላይ ነው «መንፈስን እታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ» (1ኛ ተሰ. 5፡19-21)። 

መልእክቶች የተገመገሙት ለምን ነበር? ይህ ተናጋሪው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእውነት የእግዚአብሔርን ቃል ተናግሮ እንደሆነ ለማወቅ ነው። አንድ ተናጋሪ፥ በስሜቶቹ ቁጥጥር ሥር ሆኖ፥ እግዚአብሔር ለእርሱና በእርሱ በኩል እንደተናገረ አድርጎ ሊገምት ይችላል። ትንቢታዊ መልእክትን እንኳ ማጭበርበር ይቻል ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡13-14ን ተመልከት)። አድማጮች መልእክቱን ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍ፥ ከሐዋርያዊ ትውፊት እና ከግላዊ የመንፈስ ምሪት አኳያ («መናፍስትን መለየት»፥ 12፡10) መመዘን ነበረባቸው። 

አንድ ሰው እየተናገረ እያለ፥ እግዚአብሔር ለሌላ ሰው መገለጥ ከሰጠ፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ፀጥ ብሎ መገለጡ መቅረብ አለበት። ሥልጣኑን የያዘው እግዚአብሔር እስከሆነ ድረስ በመልእክቶች መካከል ውድድር ወይም ቅራኔ አይኖርም። ይሁንና፥ ልዩ ልዩ ተናጋሪዎች መልእክቶቻቸውን «እየፈበረኩት» ከሆነ ውዥንብርና ቅራኔ ይኖራል። 

መንፈስ ቅዱስ የኃላፊነቱን ቦታ ሲይዝ ልዩ ልዩ አገልጋዮች ራስን መግዛት ይኖራቸዋል። ራስን መግዛት ደግሞ ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው (ገላ 5፡23)። አንዴ «በጊዜ የመጨረስ ችግር» ካለበት ሰው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንፈረንስ አብሮ የማገልገል ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ሁልጊዜ ማቆም ከሚገባው ጊዜ 5-20 ደቂቃ ያሳልፍ ነበር። ይህ ደግሞ ለእኔ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ መልእክቴን ማጨናነቅ ማለት ነው። ራሱን ነፃ ለማውጣት «ታውቃለህ መንፈስ ቅዱስ ሲወስድህ፥ ስለ ጊዜ አትጨነቅም!» ሲል ተናገረ። የእኔ ምላሽ ለዚህ ቁጥር 32ን መጥቀስ ነበር- «የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ።» 

በእርግጥ መንፈስ በስብሰባው ወይም በጉባኤው ለመሥራቱ ከማረጋገጫዎቹ አንዱ የእኛ ራስን መግዛት ነው። ከመንፈስ አገልግሎቶች አንዱ ከትርምስ ውስጥ ሥርዓትን ማምጣት ነው (ዘፍ. 1)። ውዥንብር የሚመጣው ከሰይጣን እንጂ ከእግዚአብሔር አይደለም (ያዕ. 3፡13-18)። መንፈስ በሚመራበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መልእክት አጠቃላይ ውጤት ለቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት እንዲኖረው ተሳታፊዎቹ «አንድ በአንድ» ችሎታ ያገኛሉ። 

የተጠናቀቀው መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ የአዲስ ኪዳን ነቢያት ስለሌሉን ይህን ትእዛዝ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ የምናደርገው እንዴት ነው? 

አንደኛው መንገድ፥ እንዲመራን እየጠየቅን የምንሰማውን መልእክት ሁሉ ለመመዘን የእግዚአብሔርን ቃል መጠቀም አለብን። በዓለማችን ሐሳዊ መምሕራን ስላሉ መጠንቀቅ አለብን (1ኛ ዮሐ 4፡1-6፤ 2ኛ ጴጥ. 2)። እውነተኛ አስተማሪዎችም እንኳ ሁሉን ነገር ስለማያውቁ አንዳንድ ጊዜ ስሕተት ይሠራሉ (1ኛ ቆሮ. 13፡9፥12፤ ያዕ. 3፡1)። እያንዳንዱ አድማጭ መልእክቱን ገምግሞ ከልቡ ጋር ማዛመድ አለበት። 

የዛሬዎቹ የማኅበር ስብሰባዎቻችን ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ይልቅ መደበኛነት ወይም ወጥ አቀራረብ ስላላቸው ስለ አገልግሎት ሥርዓት መጨነቅ የለብንም። ነገር ግን መደበኛ ባልሆኑ ብዙ ስብሰባዎቻችን፥ አንዳችን ለሌላችን ማሰብና ሥርዓት መጠበቅ አለብን። በአንድ የምስክርነት ስብሰባ ላይ እንዲት ሴት አሰልቺ የሆነ ልምምዱን በመናገር 40 ደቂቃ መውሰዱና የስብሰባውን መንፈስ ማጥፋቷ ትዝ ይለኛል። 

ወንጌላዊው ዲ ኤል ሙዲ አንድ አገልግሎት ይመሩ ነበርና አንዱን ሰው እንዲጸልይ ጠየቁት። የተሰጠውን ዕድል በመጠቀም ሰውየው ያለማቋረጥ ጸለየ። ጸሎቱ ስብሰባውን በመባረክ ፈንታ እየገደለ እንደሆነ በመረዳት፥ ሙዲ ጮክ አሉና፥ «ወንድማችን ጸሎቱን እስኪጨርስ፥ መዝሙር እንዘምር!» አሉ። በማኅበር ስብሰባ ኃላፊነትን የሚወስዱ ሚዛናዊነት – እና ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። 

ሁለተኛ፥ በስብሰባው ያሉ ሴቶች መናገር አልነበረባቸውም (ቁ. 34-35)። ጳውሎስ ቀደም ሲል ሴቶች እንዲጸልዩና ትንቢት እንዲናገሩ ፈቅዶአል (11፡5)፤ ስለሆነም ይህ ትእዛዝ የትንቢት መልእክቶችን የመገምገምን ቀጥተኛ ዐውድ የሚመለከት መሆን አለበት። የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያንን ዶክትሪናዊ ንጽሕና የመጠበቁ ኃላፊነት ያረፈው በወንዶች በተለይም በሽማግሌዎች ላይ ነበር (1ኛ ጢሞ. 2፡11-12)። 

የዚህ ክልከላ ዐውድ የሚያሳየው አንዳንድ ሴቶች በጉባኤው ጥያቄዎችን በመጠየቅና ምናልባትም ክርክሮችን በማስነሣት ችግር እየፈጠሩ እንደነበር ነው። ጳውሎስ ያገቡ ሴቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙና ለጥያቄዎቻቸው በቤት ምላሽ እንዲያገኙ አሳሰባቸው። (ያላገቡ ሴቶች ከሽማግሌዎች ወይም በቤተሰቦቻቸው ካሉ ወንዶች ጋር መመካከር ይችሉ እንደነበር ይመስለናል።) ዛሬ በጣም የሚያሳዝነው፥ በብዙ ክርስቲያኖች ቤት ለባል ጥያቄዎችን የምትመልሰው ሚስት ናት-ምክንያቱም ቃሉን የተሻለ የተማረችው እርሷ ስለሆነች ነው። 

በቁጥር 34 ጳውሎስ ያጣቅስ የነበረው የትኛውን «ሕግ» ነው? ምናልባት ዘፍጥረት 3፡16 ሳይሆን አይቀርም። (ሕግ የሚለው ቃል ለብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፥ በተለይም ለመጀመሪያዎቹ አምስቱ የተሰጠ ሌላ ስያሜ ነው።) ጳውሎስ በምዕራፍ 11፥ በቤተ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ስለሚኖራቸው ግንኙነት ስላወሳ ወደ ዝርዝር ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ አልነበረም። 

ሦስተኛ፥ ተሳታፊዎች ከእግዚአብሔር ቃል የሚያፈነግጡ «አዲስ መገለጦችን» መጠንቀቅ ነበረባቸው (ቁ 36-40)። «ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም» (ኢሳ. 8፡20)። ቤተ ክርስቲያን ብሉይ ኪዳን እንዲሁም በሐዋርያት የተላለፈ አፍአዊ ትውፊት ነበራት (2ኛ ጢሞ. 2፡2)። በመሆኑም ሁሉም መገለጦች የሚመዘኑበት መለኪያው ይኽው ነበር። እኛ ዛሬ የተጠናቀቁ ቅዱሳት መጻሕፍትና እንዲሁም ለምእተ ዓመታት የተጠራቀሙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ትምህርቶች ስላሉን እውነቱን ለማበጠር ይረዱናል። በመንፈስ ምሪት የተጻፉ ባይሆኑም፥ ታሪካዊ ወንጌላውያን ክፍለ እምነቶችን ሊመራን የሚችል ጥንታዊ ሥነ መለኮት ይዘዋል። 

በእነዚህ ቁጥሮች፥ ጳውሎስ ምላሽ እየሰጠ የነበረው፥ «የጳውሎስ እርዳታ አያስፈልገንም! መንፈስ ለእኛ ይናገረናል፤ ከእግዚአብሔር አዳዲስ ድንቅ መገለጦችን አግኝተናል !» ሊሉ ለሚችሉ የቤተ ክርስቲያን አባላት ነው። ይህ አደገኛ አዝማሚያ ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል ለመተው ና የሐሰት መገለጦችን፥ የአጋንንትን ትምህርት ሳይቀር ለመቀበል የመጀመሪያው እርምጃ ስለሆነ ነው (1ኛ ጢሞ. 4፡1)። «የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን?» ሲል ጳውሎስ ምላሽ ሰጠ። «የእውነተኛ ነቢይ መለያው ለሐዋርያዊው ትምህርት መታዘዙ ነው።» ጳውሎስ በዚህ ዓረፍተ ነገሩ፥ የጻፈው አሳብ በትክክል በመንፈስ ምሪት የተገኘ «የጌታ ትእዛዝ» ነው አለ (ቁ. 37)። 

ቁጥር 38 ጳውሎስ ሰዎች እላዋቂ ሆነው እንዲቀሩ እንደፈለገ አያመለክትም። ቢሆን ኖሮ ይህን ደብዳቤ ባልጻፈና ጥያቄዎቻቸውንም ባልመለሰ ነበር። አዲሱ ዓለም አቀፍ እትም (NID መጽሐፍ ቅዱስ፥ «ይህን ባይቀበለው [የጳውሎስን ሓዋርያዊ ሥልጣን]፥ እርሱ ራሱም ይጣላል [በጳውሎስ እና በአብያተ ክርስቲያናት]።» ብሎ ይተረጉመዋል። ለኅብረት መሠረቱ ቃሉ ነው፥ እናም በፈቃዳቸው ቃሉን የሚተዉ ወዲያውኑ ኅብረቱንም ያቋርጣሉ (1ኛ ዮሐ. 2፡18-19)። 

ጳውሎስ የምዕራፍ 14 አንኳር ትምህርቶችን ከ 39-40 ባለው ክፍል ውስጥ አጠቃልሎአል። ትንቢት ከልሳኖች የበለጠ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የልሳኖች ስጦታን ትክክለኛ አጠቃቀም መከላከል የለባትም። የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ የመላው ቤተ ክርስቲያን መታነጽ ነው፤ ስለሆነም፥ ስጦታዎች ሥርዓት ባለው ሁኔታ መተግበር አለባቸው። የማኅበር አምልኮ «በጨዋ ሁኔታ» ማለትም ውበት፥ ሥርዓት እና መንፈሳዊ መነሣሣትና ደስታን በተላበሰ መልክ መካሄድ አለበት። 

ይህን ምዕራፍ ከመደምደማችን በፊት፥ ጳውሎስ ስለ ልሳኖች ስጦታ የተናገረውን ማጠቃለሉ የሚረዳ ሳይሆን አይቀርም። የልሳኖች ስጦታ ተናጋሪው ከዚህ ቀደም በማያውቀው ሆኖም ግን በሚታወቅ ቋንቋ ለመናገር ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ችሎታ ነው። ዓላማው የጠፉትን ለማዳን ሳይሆን የዳኑትን ለማነጽ ነው። ሁሉም እማኝ ይህ ችሎታ አልነበረውም፤ ወይም ይህ ስጦታ የመንፈሳዊነት ማረጋገጫ ወይም «በመንፈስ የመጠመቅ» ውጤትም አልነበረም። 

በአንድ ስብሰባ ሦስት ሰዎች ብቻ በልሳን እንዲናገሩ የተፈቀደ ነበር፤ ይህንንም ማድረግ የነበረባቸው በሥርዓትና በማስተርጎም ነው። ተርጓሚ ባይገኝ ዝም ማለት ነበረባቸው። ትንቢት የበለጠ ስጦታ ነው፤ ነገር ግን ልሳኖች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ ተፈጻሚ ከሆኑ መናቅ የለባቸውም። 

የሐዋርያትና የነቢያት የምሥረታ ሥራ በተጠናቀቀ ጊዜ የእውቀት፥ የትንቢት እና የልሳኖች ስጦታ ያስፈለገ አይመስልም። «ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ» (13፡8)። በእርግጥ እግዚአብሔር ከወደደ ዛሬም ይህን ስጦታ ይሰጣል፤ ነገር ግን ማናቸውም ልሳኖች በመለኮት ኃይል የተንቀሳቀሱ ናቸው ብሎ ለማመን ዝግጁ አይደለሁም። ወይም ሁሉም የልሳኖች ሁኔታ ሰይጣናዊ ወይም ራስ ፈጠር ናቸው እስከ ማለቱም ርቄ አልሄድም። 

አማኞች ልሳኖችን የኅብረት ወይም የመንፈሳዊነት መመዘኛ አድርገውት ሲታይ የሚያሳዝን ነው። ይህ ራሱ በእንዲህ ያለ ሁኔታ መንፈስ እየሠራ ላለመሆኑ ያስጠነቅቀኛል። ቅደም ተከተሎቻችንን እናስተካክልና የጠፉትን በማዳኑ እና ቤተ ክርስቲያንን በመገንባቱ ላይ እናተኩር።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: