ራስ ወዳድነት በ«ፍቅር ግብዣዎች» (1ኛ ቆሮ. 11፡17-22)

ከቤተ ክርስቲያን ጅማሬ ጀምሮ፥ አማኞች አንድ ላይ መብላታቸው የተለመደ ነበር (የሐዋ. 2፡42፥46)። ይህ በኑሮ አቋማቸው ደከም ካሉት ጋር አብሮ ለመሆን ና ለማካፈል ዕድል የሚሰጥ ነበር። የጌታን እራት በሚያስቡበት ጊዜ ይህን አብሮ የመብላት ነገር ወደ ከፍተኛ ደረጃ አድርሰውት ነበር። ዋናው አጽንኦት አብሮ በመከፋፈል ለቅዱሳን ፍቅርን ማሳየት ስለነበር ይህን ማዕድ «የፍቅር ግብዣ» ብለው ሰየሙት። 

የ«አጋፔ ግብዣ» (ለፍቅር የተሰጠው የግሪክ ቃል) በቆሮንቶስ የነበረው እምልኮ አንዱ አካል ነበር። ሆኖም ግን አንዳንድ ከመስመር የወጡ ነገሮች ሾልከው እየገቡ ነበር። ከዚህም የተነሣ፥ የፍቅር ግብዣዎቹ ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ነበር። አንደኛው ችግር፥ በቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ቡድኖች የነበሩ ሲሆን፥ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን መላው ቤተሰብ ጋር ኅብረት ከማድረግ ፈንታ ከገዛ «አቻዎቻቸው» ጋር አብረው ይበሉ ነበር። ጳውሎስ ይህን ራስ ወዳድ ተግባር ቢያወግዝም፥ ለውጤቶቹ ግን አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። ይኸውም እግዚአብሔር ሁኔታውን እውነተኛዎቹን አማኞች ለመግለጥ ተጠቅሞባቸዋል የሚል ነበር። 

ሌላው ጉድለት ስስት ነበር። ሀብታሞቹ ሰዎች ለራሳቸው ብዙ ምግብ ሲያመጡ ድሆቹ ይራቡ ነበር። «የአጋፔ ግብዣ» መነሻ አሳብ ፍቅርን መከፋፈል ሲሆን፥ ያ አሳብ ግን ጠፋ። ከአባላት አንዳንዶቹ ይሰክሩ ነበር። ሳምንታዊው «የአጋፔ ግብዣ » አንዳንድ ደሀ አባላት አዘውትረው የሚያገኙት ብቸኛው ደህና ምግብ የነበረ ይመስላል፤ በመሆኑም በሀብታሞቹ ወገኖች በንቀት መታየቱ የጎዳው ሆዳቸውን ብቻ ሳይሆን፥ ክብራቸውንም ጭምር ነበር። 

በእርግጥ፥ በማዕድ የሚደረጉ ክፍፍሎች በቤተ ክርስቲያን የነበሩትን ጥልቅ ችግሮች የሚያመለክቱ ነበሩ። ቆሮንቶሳውያን ራሳቸውን የተራመዱ እማኞች አድርገው ቢቆጥሩም፥ ሐቁ ግን እንደ ሕፃን የሚያደርጋቸው መሆናቸው ነው። ጳውሎስ ግብዣውን እንዲተዉት ሳይሆን፥ ወደ ትክክለኛው ትርጉም እንዲመልሱት አሳሰበ። «ሀብታሞች ከራባቸው በቤታቸው ይብሉ። እንደ እናንተ ያልደላቸውን ያለ አግባብ ስታንገላቱአቸው፥ ቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን መናቃችሁ እኮ ነው!» የ«አጋፔ ግብዣ» ለመተናነጫ ዕድል መሆን ሲገባው፥ የመቃቃሪያ ጊዜ አድርገው ተጠቀሙበት። 

ገና ወጣት ልጅ እያለሁ በእሑድ/በሰንበት ትምህርት ቤት ሽርሽር የሆነው ነገር ትዝ ይለኛል። በሽርሽር ቦታ ኃላፊ የነበረችው ሴት ጨዋታ አዘጋጅታ ነበር የመጣችው። ከዚያም ልጆቿን በቡድን አደረገች። በሁለት ረድፍ እየተያየን እንድንቆም እደረገችን። ጨዋታው ግንባር ለግንባር የሚተያዩ ልጆች እንቁላል እየተወራወሩ መቀባበል ሲሆን፥ ቅብብሎሹን በምናካሄድበት ጊዜ ወደ ኋላችንም ማፈግፈግ ነበረብን። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እየተራራቅን በሄድን መጠን እንቁላሎቹን በኃይል መወርወር ስለሚጠይቅ ጨዋታው በጣም አስደሳች ወደ ሚሆንበት ጫፍ ይደርስ ነበር። 

ይሁንና፥ ሁለት የእሑድ/የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንቁላሎችን በታላቅ ጉጉት ሲመለከቷቸው እንዳንዶቻችን ተመለከትን። እነዚህ ልጆች መግዛት ስለማይችሉ ምናልባት እንቁላል አልፎ አልፎ ከሚበሉ ደሀ ቤተሰቦች የመጡ ነበሩ። ትንሿ ልጃ ገረድ ጨዋታውን ወደምትመራው ሴት ሄደችና፥ «የተረፉ እንቁላሎች ካሉ፥ ወንድሜና እኔ ወደ ቤት እንድንወስድ ይፈቀድልናል?» ስትል ጠየቀች። ሴትየዋም ጨዋታው ከማለቁ በፊት በጥበብ አስቁማ፥ ሽልማቶቹን ከሰጠች በኋላ እንቁላሎቹን በሙሉ ለሁለቱ ልጆች ሰጠች። ሌሎች እየተከፉ አንዳንድ ቅዱሳን የመዝናኛ ጊዜ ማድረጋቸው ስሕተት መሆኑን አወቀች። 

«የጠጪዎች ማኅበር» ይዞ ለጌታ እራት መዘጋጀት ጥሩ አካሄድ ነው ለማለት አያስደፍርም። ለኃጢአተኞች ሁሉ፥ ለሀብታሙም ለድሀውም የሞተውን አዳኝ ለማስታወስ ሌሎችን መናቅ ጭራሽ መንገዱ አይደለም። ወደ ጌታ እራት በምንቀርብበት ጊዜ ልባችንን ማዘጋጀቱ ምንኛ ተገቢ ነው!

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: