ሰባኪው በገነት (2ኛ ቆሮንቶስ 12፡1-10)

ይህ ክፍል ጳውሎስ ስለ ሐዋርያነቱ ለመከላከልና ለቆሮንቶስ አማኞች የነበረውን ፍቅር ለማረጋገጥ የሚያቀርበውን አሳብ በከፍተኛ ደረጃ የሚገልጽበት ነው። ጳውሎስ ስለ እነዚህ የግል ልምምዶቹ ለመጻፍ ባይፈልግም፥ ዳሩ ግን ችግሩን ለመቅረፍ ሌላ መንገድ አልነበረውም። እንዲያውም ራሱን ከፍ ከፍ ላለማድረግ፥ ጳውሎስ ልምምዱን የገለጸው በአንደኛ መደብ ሳይሆን በሦስተኛ መደብ ነበር። ለአንባብያኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛቸውን ሦስት ልምምዶች አካፍሏል። 

ክብር – እግዚአብሔር አከበረው (2ኛ ቆሮ. 12፡ 1-6) 

የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ክብር ለማግኘት ይጣደፉ ነበርና «በድጋፍ ደብዳቤያቸው» ይመኩ ነበር(3 ከቁጥር 1 ጀምሮ)። ጳውሎስ ግን ክብርን ከሰው አልፈለገም ነበር፤ እርባና ያለው ክብር ከእግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ፥ እርሱም በዚህ መንገድ ብቻ ለመከበር ፈለገ፡፡ 

በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ራእዮችንና መገለጦችን በመስጠት አከበረው። ጳውሎስ ደኅንነትን አግኝቶ በተለወጠበት ዕለት፥ የከበረውን ክርስቶስን ተመልክቷል (የሐዋ.9፡3፤ 22፡6)፤ ሐናንያ ሊያገለግለው ሲመጣም በራእይ አይቷል (9፡ 12)፤ እንደዚሁም ለአሕዛብ እንዲያገለግል በተጠራ ጊዜም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አይቷል (22፡7)። 

በአገልግሉቱ ጊዜ፥ ለምሪትና ለብርታት እንዲሆነው፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእዮችን ይቀበል ነበር። ወደ መቄዶንያ የተጠራው በራእይ ነበር (16፡9)። የቆሮንቶስ አገልግሎቱ እንደ አቀበት አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጳውሎስን በራእይ አበረታታው (18፡9-10)። በኢየሩሳሌም ከታሰረ በኋላም፥ እግዚአብሔር ጳውሎስን በራእይ አጽናንቶታል (23፡1)። በማዕበሉ መሀል አንድ መልአክ ብቅ ብሉ እርሱና ሌሎችም መንገደኞች እንደሚድኑ አረጋገጠለት (27፡23)። 

ከጥሪውና ከአገልግሉቱ ጋር ከተያያዙ ከእነዚህ ልዩ ራእዮች ጋር፥ መለኮታዊ እውነትን የሚገልጹ መንፈሳዊ መገለጦችም ተሰጥተውት ነበር (ኤፌ. 3፡1-6 ተመልከት)። እግዚአብሔር ለአሁኑ ዘመን ትውልድ ያለውን ዕቅድ የሚያስተውልበትን ጥልቅ መረዳት ሰጠው። በመሆኑም ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ምሥጢራት ተረድቶ ነበር። 

እንዲሁም እግዚአብሔር ጳውሎስን ወደ መንግሥተ ሰማይ በመውሰድና መልሶም ወደ ምድር በመላክ አከበረው። ይህም አስደናቂ ልምምድ የተፈጸመው የቆሮንቶስ ደብዳቤውን ከመጻፉ ከ14 ዓመታት በፊት ማለትም በ43 ዓ.ም. አካባቢ ነበር። ይህም ጳውሉስ ወደ ጠርሴስ በሄደበት (የሐዋ. 9፡30) እና በርናባስን ባገኘበት (11፡25-26) ጊዜ መካከል የተፈጸመ ይሆናል። ስለዚህ ክስተት የተሰጠ ዝርዝር ነገር የለም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜን ሰውቶ መመራመሩም የሚፈይድ አይደለም። 

የአይሁድ የሃይማኖት ምሁራን (ራቢዎች) ስለ ራሳቸው ሲናገሩ፥ በሦስተኛ መደብ የመናገር ልማድ ነበራቸውና ጳውሎስም በቆሮንቶስ ውስጥ ለሚገኙ ወዳጆቹ (እና ጠላቶቹ ስለ ራሱ ልምምድ ለመግለጽ ያንኑ ልማድ ይጠቀማል። ልምምዱ እጅግ አስደናቂ ስለ ነበር፥ እግዚአብሔር በአካላዊው ሁኔታው እንዳለ ወደ ሰማይ ይውሰደው ወይም መንፈሱ ከሥጋው ተለይቶ ይሂድ ጳውሎስ እርግጠኛ አልነበረም። (እስኪ በቅርጫት «በመውረድ» እና ወደ ሦስተኛው ዓለም «በመውሰድ» መካከል ያለውን ልዩነት ያነጻጽሩ።) እዚህ ላይ ጳውሎስ የመንግሥተ-ሰማይን ኅልውናና እግዚአብሔርም ሰዎችን ወደዚያ ለመውሰድ እንደሚችል አረጋግጧል። ሦስተኛው ሰማይ ከ«ገነት» ጋር አንድ ሲሆን፥ እግዚአብሔር በክብሩ የሚኖርበት ሰማየ-ሰማይ ነው። ለዘመናዊው ሳይንስ ምስጋና ይግባውና ዛሬ ሰዎች ደመናት የሚንሳፈፉበትን ሰማያቸውን ጎብኝተዋል (ከደመናት በላይ በአውሮፕላን እንበራለን)፤ ወደ ፕላኔቶች ሰማያትም ይሄዳሉ (ሰዎች በጨረቃ ላይ ለመንሸራሸር በቅተዋል)፤ ይሁንና ሰው ያለ እግዚአብሔር እርዳታ ወደ እግዚአብሔር ሰማይ ሊደርስ አይችልም። 

የሚያስገርመው ነገር ጳውሎስ ለ14 ዓመታት ስለዚህ ልምምድ ትንፍሽም አለማለቱ ነው! በእነዚያ ዓመታት፥ ጳውሎስ «በሥጋው መውጊያ» ይሰቃይ ነበርና ሰዎች ለምን እንዲህ ያለ ሸክም እንደ ተጫነበት በማሰብ ሳይገረሙ ላይቀሩ ይችላሉ። ምናልባትም የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች እንደ ኢዮብ አጽናኞች፥ «ይህ ሥቃይ የደረሰበት በእግዚአብሔር ቅጣት ምክንያት ነው! » ሳይሉ አይቀሩም ይሆናል። (በመሠረቱ መውጊያው ከእግዚአብሔር የተሰጠው ስጦታ ነበር።) ከጳውሎስ ደህና ወዳጆች አንዳንዶቹም፥ «አይዞህ፥ ጳውሎስ፥ አንድ ቀን በመንግሥተ ሰማይ ታርፋለህ» በማለት ሊያጽናኑት ሞክረው ይሆናል። ይህን ቢሉትም ደግሞ ጳውሎስ፥ «ይህ መውጊያ የተሰጠኝ ለዚሁ ነው – ወደ ሰማይ ሄጄ ነበር» ሲል ሊመልስላቸው በቻለ ነበር። 

እግዚአብሔር ለጳውሎስ ራእዮችንና መገለጦችን በመስጠትና በተለይም ወደ ሰማይ በመውሰድ አከበረው፤ ዳሩ ግን በሰማይ ሳለ «የማይነገሩ ቃላት» በማሰማትም በተጨማሪ አክብሮታል። በሰማይ ብቻ የሚደመጡትን መለኮታዊ ምስጢራት ሰማ። እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር እና በሰማይ በሚገኙ ፍጥረታት ብቻ እንጂ፥ በሰዎች አይነገሩም ነበር። 

ለመሆኑ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎችስ እንዲህ ስላለ አንድ ልምምድ እንኳን ሊናገሩ ይችሉ ይሆን? የእግዚአብሔር ወዳጅ የነበረው ሙሴ እንኳ፥ ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኘው በተራራ ጫፍ ላይ ነበር፤ ይሁንና ጳውሎስ ጌታን በገነት ተገናኘው። ጳውሎስ ይህንን ልምምድ ለማንም ስላልተናገረ፥ በእነዚያ 14 ዓመታት ውስጥ ትልቅ መንፈሳዊ ራስን መግዛት ተለማምዷል። ይህም የእግዚአብሔርን ክብር የሚያመለክት ራእይ ጳውሎስን በሕይወቱና በአገልግሎት ዘመኑ ውስጥ በጽናት እንዲቆም ካስቻሉት ኃይሉች አንዱ እንደ ነበር የሚያጠራጥር አይደለም። የትም ስፍራ ሲኖር – በእስር ቤት፥ በባሕር ላይ፥ በአስቸጋሪ ጉዞዎች – እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ነበረና በመልካም ሁኔታም ላይ እንዳለ ያውቅ ነበር። 

እኔና አንተ ግን እስክንሞት ወይም ጌታችን እስኪመለስ ድረስ ወደ ሰማይ አንሄድም። ዳሩ ግን ዛሬውኑ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ስፍራዎች መቀመጣችንን ስናስበው በእጅጉ ያጽናናናል (ኤፌ. 2፡6)። «ከሁሉም በላይ» (ኤፌ. 2፡21-22) የከበረ የሥልጣንና የድል ሥፍራ አለን። እንደ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ክብር ባንመለከትም፥ አሁንም የእግዚአብሔር ክብር ተካፋዮች ነን (ዮሐ 17፡22)፤ አንድ ቀንም ወደ ሰማይ ደርሰን የክርስቶስን ክብር እናያለን (ቁ 24)። 

እንዲህ ዓይነቱ ክብር ብዙዎችን ያኩራራል። ሌላ ሰው ቢሆን ኖሮ ለ14 ዓመታት ዝም ብሉ በመቆየት ፈንታ፥ ከመቅጽበት ለዓለም ባሳወቀም ነበር። ዳሩ ግን ጳውሎስ እንዲህ አላደረገም። ከቆይታ በኋላም እውነቱን ገለጸ እንጂ፥ ከንቱ ትምክህት አላሳየም – እውነቶች ለራሳቸው ይናገሩ። ጳውሎስን በጣም ያሳሰበውም ማንም ሰው የእግዚአብሔርን ክብር ቀምቶ ለእርሱ እንዳይሰጠው ነበር። ሌሉች ስለ ራሱና ስለ ሥራው ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ፈለገ (ሮሜ 12፡3 ተመልከት)። 

ጳውሎስ እንደዚህ ትልቅ ልምምድ እያለው፥ እንዴት ትሁት ሊሆን ይችላል? ይህ የሆነው እግዚአብሔር በሕይወቱ ውስጥ ካስገኘለት ከሁለተኛው ልምምድ የተነሣ ነው። 

በጎነት – እግዚአብሔር ትሁት አደረገው (2ኛ ቆሮ. 12፡7-8) 

ጌታ ሕይወታችንን እንዴት ሚዛናዊ ማድረግ እንደሚቻል ያውቃል። በረከቶች ብቻ ቢትረፈረፉልን፥ ልንታበይ እንደምንችል ያውቃል፤ በመሆኑም፥ ሸክሞችም እንዲኖሩን ይፈቅዳል። ጳውሎስ በሰማይ የተመለከተው ልምምድ፥ በምድር ላይ የነበረውን አገልግሎት ሊያከስመው በቻለ ነበር፤ ዳሩ ግን፥ እግዚአብሔር በበጎነቱ ጳውሎስን ከመታበይ ለመታደግ፥ ሰይጣን መውጊያውን እንዲያሳርፍበት አደረገ። 

በዚህ ምድር ላይ የሰብዓዊ ሰቆቃ ምሥጢር ሙሉ ለሙሉ እልባት ሊያገኝ አይችልም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በመሆናችን ብቻ እንሰቃያለን። በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ፥ ሰውነታችን ለተለመዱ የሕይወት ችግሮች ይጋለጣል። ምቾቶችን ሊያመጣልን የሚችለው ይኸው አካል ሕመሞችንም ያመጣብናል። የሚያስደስቱን የቤተሰብ አባላትና ወዳጆቻችን መልሰው ልባችንን በኀዘን ሊሰብሩት ይችላሉ። ይህ «ከሰብዓዊ ተፈጥሮ አስቂኝ» ባሕርያት አንዱ ሲሆን፥ ማምለጫ መንገዱም ከሰብዓዊነት ዝቅ ማለት ነው። ይሁንና እንደዚህ ለማድረግ የሚፈልግ ሰው ደግሞ የለም። 

አንዳንድ ጊዜ ሞኞችና ለጌታ የማንታዘዝ በመሆናችን እንሰቃያለን። አንድም የራሳችን ዓመፅ ይጎዳናል፤ አሊያም ጌታ በፍቅሩ ሊቀጣን ይችላል (ዕብ 12 ከቁ 3 ጀምሮ ተመልከት)። ንጉሥ ዳዊት በኃጢአቱ ምክንያት ብዙ ተሠቃይቷል፤ የኃጢአት ውጤቶች በሥቃይ የተሞሉ ሲሆኑ፥ የእግዚአብሔርም ቅጣት እንዲሁ ነበር [2 ሳሙ. 12፡1-22፤ መዝ (51) ተመልከት]። እግዚአብሔር በጸጋው፥ ከኃጢአታችን ይቅር ይለናል፤ ዳሩ ግን በአገዛዙ፥ የምንዘራውን እንድናጭድ ያደርጋል። 

እንዲሁም መከራ እግዚአብሔር ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለበትን ባሕርይ የሚያንጽበት መሣሪያ ነው (ሮሜ 5፡1-5)። በመሠረቱ፥ ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ በተፈጸሙ አሰቃቂ ልምምዶች፥ እግዚአብሔር እንዲቀርጸውና እንዲያንጸው ስለ ፈቀደ፥ የበለጸገ የክርስቲያን ባሕርይ ነበረው። በውቂያኖስ ዳርቻ አካባቢ ስትንሸራሸር፥ ጸጥታ ባለበት ቦታዎች የሰሉትን ድንጋዮች ትመለከታለህ፤ ነገር ግን እየተላጋ ማዕበል ያለ ማቋረጥ በሚለትማቸው አካባቢዎች ያሉት ድንጋዮች ውጫዊ ክፍላቸው ለስላሳ ሆኖ ይታያል። እግዚአብሔር እኛ የምንፈቅድለት ከሆነ፥ የሕይወትን «ማዕበሉችና» ነፍሳት በመጠቀም ሊሞርደን ይችላል። 

ለጳውሎስ የሥጋ መውጊያ የተሰጠው እርሱን ከኃጢአት ለመጠበቅ ነበር። ወደ ሰማይ ደርሶ የመመለስ ዓይነት አስደናቂ መንፈሳዊ ልምምዶች፥ ሰብዓዊ ራስ-ወዳድነትን የማጎልበት ጠባይ አላቸው፤ ትዕቢት ኩራት ደግሞ ኃጢአትን ወደሚያለማምዱ በርካታ ፈተናዎች ይመራል። የጳውሎስ ልብ በትዕቢት ተሞልቶ ቢሆን ኖሮ፥ እነዚያ ቀጣይ 14 ዓመታት በስኬታማነት ፈንታ ሰውድቀት ይታጀቡ ነበር። 

የጳውሎስ የሥጋ መውጊያ ምን እንደ ነበር አናውቅም። መውጊያ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፥ «ሰውን ለማሰቃየት ወይም ለመውጋት የተበጀ ጦር» ማለት ነው። ይህም የሆነ አካላዊ ጉዳት በማስከተል፥ በጳውሎስ ላይ ሕመምና ጭንቀት ያደረሰ ነበር። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የዓይን ሕመም ነበረበት (ገላ. 6፡11 ተመልከት) ቢሉም፥ በርግጠኛነት ልናውቀው አንችልም። መከራችን ምንም ቢሆን፥ ጳውሎስ የተማራቸውን ትምህርቶች ልንማርና መጽናናትን ልናገኝ ስለምንችል፥ አለማወቃችንም መልካም ነው። 

እግዚአብሔር ልክ ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትን እንደ ፈቀደለት ሁሉ፥ ጳውሎስንም እንዲያሰቃይ ፈቀደለት (ኢዮብ 1-2 ተመልከት)። በዚህ አጥናፈ-ዓለም ውስጥ የክፋት ምንጭ ምን እንደ ሆነ ወይም እግዚአብሔር ክፋት እንዲመጣ ሲፈቅድ በልቡ ውስጥ ያለውን ዓላማ ሙሉ ለሙሉ ባንረዳም፥ እግዚአብሔር ክፋትን እንደሚቆጣጠርና ለክብሩ መግለጫ ሊጠቀምበት እንኳን እንደሚችል አሳምረን እናውቃለን። ሰይጣን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ በአማኝ ሕይወት ላይ ምንም ሥልጣን የለውም። ጠላት በኢዮብና በጳውሎስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ የመጣ ነው። 

ሰይጣን ጳውሎስን እንዲጎስም ተፈቀደለት። የቃሉም ትርጉም «መምታት፥ በቡጢ መኮርኮም» ማለት ነው። የአንቀጹ የጊዘ አመልካች እንደሚጠቁመው፥ ይህ ሕመም አንድም የማይቋረጥ አሊያም ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነው። ጳውሎስ የሚጽፋቸው ደብዳቤዎች፥ የሚሄድባቸው መንገዶች፡ የሚሰብካቸው ስብከቶች፥ የሚጎበኛቸው አብያተ ክርስቲያናትና በሚያገለግልበት ጊዜም የሚጋፈጣቸው አደጋዎች እንደ ነበሩስናስብ፥ የችግሩን ጥልቀት መረዳታችን አይቀርም። ሕመሙከእርሱ እንዲወገድ (ጌታው በአትክልት ስፍራው እንዳደረገው [ማር. 14፡32-41]) ሦስት ጊዜ መጸለዩ የሚያስደንቅ አይሆንም (2ኛ ቆሮ. 12፡8)። 

እግዚአብሔር መከራዎች ወደ ሕይወታችን እንዲመጡ በሚፈቅድበት ጊዜ፥ መከራዎቹን ልናስተናግድ የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አንዳንድ ሰዎች ነጻነትንና ምቾትን እንደ ነፈጋቸው በመግለጽ፥ ተማርረው እግዚአብሔርን ይወቅሱታል። ሌሎች ደግሞ በአስቸጋሪው ልምምድ ውስጥ ምንም ዓይነት ብርታት ስለማያክሉ፥ መከራውን ለመቋቋም በበኩላቸው ጥረት ስለማያደርጉና ተስፋ ስለሚቆርጡ ምንም ዓይነት በረከት ሳያተርፉ ይቀራሉ። የተቀሩት ደግሞ ጥርሳቸውን ነክሰው፥ «እስከ መጨረሻው ድረስ ለመጽናት» ይወስናሉ። ይህ ብርታት ያለበት ምላሽ ቢሆንም፥ ለዕለታዊ ሕይወት የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ ስለሚያሟጥጥባቸው፥ ከጊዜ በኋላ ዝለው ሊወድቁ ይችላሉ። 

ጳውሎስ ከሰይጣን ጉሰማ ነጻ ለመውጣት በመጸለዩ ኃጢአት አድርጎ ይሆን? አይመስለኝም። ከበሽታና ከሕመም ነጻ ለመውጣት ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ለክርስቲያን የተለመደ ነገር ነው። እግዚአብሔር እያንዳንዱ አማኝ በሚጸልይበት ጊዜ የግድ ላይፈውሳው ይችላል። ይሁንና ሸክሞቻችንንና ጉድለቶቻችንን ለእርሱ እንድናቀርብ ያበረታታናል። ጳውሎስ ይህ «የሥጋ መውጊያ» ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣበት ጊዜያዊ ፈተና ይሁን፥ ወይም አብሮት ለመኖር የተቆረኘው መሆኑን የማወቅ ችሎታ አልነበረውም። 

መከራ የደረሰበት ክርስቲያን በእግዚአብሔር ዘንድ አሳፋሪ ተግባር የፈጸመ እንደ ሆነ እንድናምንላቸው የሚሹ ሰዎች አሉ። «ጌታን ከታዘዝህና በክርስቶስ ያለህን ሁሉ የራስህ አድርህ ከቆጠርህ፥ በፍጹም አትታመምም» ይላሉ። ይህንን ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በፍጹም አላገኘሁም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለአይሁዶች የተለየ በረከትና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የተስፋ ቃል መግባቱ እውነት ነው (ዘዳ 7 ከቁጥር 12 ጀምሮ)፤ ይሁንና ለአዲስ ኪዳን አማኞች ከበሽታ ወይም ከመከራ ነጻ እንደሚያደርጋቸው የተስፋ ቃል አልገባም። ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ከነበረው ግንኙነት የተነሣ፥  «ቅጽበታዊ ፈውስ» የማምጣት ብቃት ቢኖረው ኖሮ፥ ለምን ፈውስን ለራሱና እንደ አፍሮዲጡ ለመሳሰሉት ለሌሎች ሰዎች አላስገኘም ነበር? (ፊልጵ. 2 ከቁጥር 25 ጀምሮ)። 

በሁለቱ የጳውሎስ ልምምዶች ውስጥ የነበረው ልዩነት ምንኛ የሚቃረን ነው! ጳውሎስ ከገነት ወደ ሕመም – ከክብር ወደ ሥቃይ ተሻገረ። በሰማይ የእግዚአብሔርን በረከት ከቀመሰ በኋላ፥ በምድር ላይ ደግሞ የሰይጣንን ጉሰማ ይቀበላል። እጅግ ከመጠቀው ደስታ፥ ወደ ሥቃይ ይሻገራል፤ ይሁንና ሁለቱም ልምምዶች ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው። እግዚአብሔር የሚያስፈልገውን ሊያሟላለት እንደሚችል ስለሚያውቅ፥ አንደኛው የክብር ልምምዱ ለማያቋርጥ የመከራ ልምምድ አዘጋጅቶታል። ጳውሎስ ወደ ሰማይ ሄዶ ነበር ከዚህም ሰማይ ወደ እርሱ ሊመጣ እንደሚችል ተማረ። 

ጸጋ – እግዚአብሔር ረዳው (2ኛ ቆሮ. 12:9-10) 

በዚህ ሕመምን ባዘለ ልምምድ ውስጥ ሁለት መልእክቶች ነበሩ። የሥጋ መውጊያው ሰይጣን ለጳውሎስ የሚያስተላልፈው መልእክት ሲሆን፥ እግዚአብሔርም ለእርሱ ሌላ መልእክት ነበረው . የጸጋ መልእክት። በቁ 9 ላይ የሚገኘው የግሡ የጊዜ አመልካች አስፈላጊ ነው:- «እርሱም (እግዚአብሔር] [ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ] አለኝ።» እግዚአብሔር ለጳውሎስ ከእርሱ ጋር የሚሰነብት መልእክት ሰጠው። ጳውሎስ በሰማይ ሳለ የሰማቸውን ቃላት ለእኛ እንዲያጋራ አልተፈቀደለትም፤ ይሁንና እግዚአብሔር በምድር ላይ የሰጠውን ቃላት ያካፍለናል – እነዚህም በጣም የሚያጽናኑ ናቸው። 

መልእክቱም የጸጋ መልእክት ነበር። ጸጋ ምንድነው? ጸጋ እግዚአብሔር ለሚያስፈልገን ነገር ሁሉ የምንፈልገው ጊዜ የሚሰጠን ስጦታ ነው። እግዚአብሔር በጸጋው የማይገባንን ነገር ይሰጠናል፤ በምሕረቱ ደግሞ የሚገባንን ነገር አይሰጠንም የሚለው አባባል ማለፍያ ነው። አንድ ሰው ጸጋ የሚለውን ቃል በክርስቶስ ከፋይነት የተገኘ የእግዚአብሔር ባለጸግነት ብሎታል። «እኛ ሁላችን ከሙላቱ [ከክርስቶስ] ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና» (ዮሐ 1፡16)። 

ይህም የበቂ ጸጋ መልእክት ነበር። ከቶውንም የጸጋ እጦት አይስተዋልም። እግዚአብሔር ለመንፈሳዊ አገልግሎታችን (2ኛ ቆሮ. 3፡4-6)፥ ለቁሳዊ ፍላጎታችንና (9፡8) ለሥጋዊ ጉድለታችን (12፡9) ሁሉ በቂ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ ሊያድነን ከበቃ፥ በመከራችን ወቅት ሊጠብቀንና ሊያበረታንም እንደሚበቃ የሚያጠራጥር አይሆንም። 

መልእክቱ የሚያበረታ የጸጋ መልእክት ነበር። እግዚአብሔር የራሱን ብርታት እንላበስ ዘንድ እንድንደክም ይፈቅዳል። ይህም የማያቋርጥ ሂደት ነው – «ኃይሌ በድካምህ] ይፈጸማል» (ቁ 9)። በጠንካራነቱ የሚተማመን ጥንካሬ፥ በመሠረቱ ደካማነት ነው፤ ዳሩ ግን ደካማነቱን የሚያውቅ ድካም ብርታት ነው። 

በክርስትና ሕይወታችን፥ ብዙዎቹን በረከተች የምንቀበለው በለውጥ እንጂ፥ በምትክ አይደለም። ጳውሎስ ሕመሙ ከእርሱ እንዲለይ ሦስት ጊዜ በጸለየበት ጊዜ፥ እግዚአብሔርን ሌላ ምትክ እንዲሰጠው እየጠየቀው ነበር፡- «በበሽታ ምትክ ጤንነትን፥ በሕመምና በድካም ፈንታ ነጻነትን ስጠኝ» ማለቱ ነበር። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ጉድላትን የሚሞላው በምትክ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ሌላ ጊዜ በለውጥ ነው። መከራውን አያስወግደውም፤ ዳሩ ግን ጸጋውን ስለሚሰጠን፥ የመከራው ጎጂ ገጽታ ወደ ጠቃሚ መልክ ይለወጣል። 

ጳውሎስ ስለ ችግሩ ሲጸልይ፥ እግዚአብሔር በሚያደርገው ነገር ላይ የጠለቀ መረዳት ሰጠው። ከዚያም ጳውሎስ ይህ የሥጋ መውጊያ ከእግዚአብሔር እንደ ተሰጠው ተረዳ። ይህ ምንኛ ያልተለመደ ስጦታ ነው! ጳውሎስ የሚያደርገው አንድ ነገር ብቻ ነበር . ስጦታውን ከእግዚአብሔር ዘንድ መቀበልና እግዚአብሔር ዓላማዎቹን ከዳር እንዲያደርስ ፈቃደኛ መሆን። እግዚአብሔር ጳውሎስ «ያለ ልክ ከፍ ከፍ» እንዳይል ስለ ፈለገ፥ ይህንኑ ፍላጎት ከዳር የሚያደርሰውም በዚሁ 

መንገድ ነበር፡፡ 

ጳውሎስ መውጊያውን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣ ስጦታ አድርጎ በተቀበለ ጊዜ፥ ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ሕይወቱ ውስጥ ዘልቆ በመግባት የሚሠራበትን ሁኔታ አመቻቸ። እግዚአብሔር ለጳውሎስ የተናገረውና የጸጋውን ዋስትና የሰጠው ከዚያ በኋላ ነበር። አንተም በመከራ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትና በማሰላሰል ተጨማሪ ጊዜ አሳልፍ፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚናገርህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ልጆቹ በችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ፥ ለእነርሱ የሚሆን የተለየ መልእክት አለው። 

እግዚአብሔር ለጳውሎስ ምንም ማብራርያ አልሰጠውም፤ ይልቁንም፥ የተስፋ ቃል ሰጠው፡- «ጸጋዬ ይበቃሀል።» የምንኖረው በማብራርያዎች ላይ ሳይሆን፥ በተስፋ ቃሎች ላይ ተደግፈን ነው። ስሜቶችን ይለዋወጣሉ፤ ዳሩ ግን የእግዚእብሔር የተስፋ ቃሎች ከቶውንም አይለዋወጡም። የተስፋ ቃሉች እምነትን ያነቃቃሉ፤ እምነት ደግሞ ተስፋን ያጠናክራል። 

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ተማመነና እግዚአብሔር ከሚያቀርብለት ጸጋ ተቀበለ፤ ይህም አሳዛኝ መስሎ የታየውን ነገር ወደ ድል ለወጠው። እግዚአብሔር መውጊያውን በማስወገድ አልነበረም ሁኔታውን የለወጠው – አንድ አዲስ ነገር – ጸጋ በማከል ነበር እንጂ! አምላካችን «የጸጋ ሁሉ አምላክ» ነው (1ኛ ጴጥ. 5፡10)፤ ዙፋኑም «የጸጋ ዙፋን» ነው (ዕብ 4፡ 16)። የእግዚአብሔር ቃል «የጸጋው ቃል» (የሐዋ. 20፡32) ነው፥ የተስፋ ቃሉም «ጸጋን አብልጦ ይሰጣል» (ያዕ. 4፡6) የሚል ነው። ችግሮቻችንን የምንመለከትበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ቢሆን፥ እግዚአብሔር ለጉድለታችን ሁሉ ብቁ ነው። 

ዳሩ ግን እግዚአብሔር ጸጋውን የሚሰጠን ዝም ብለን መከራችንን «እንድንታገሥ» ብቻ አይደለም። ደኅንነትን ያላገኙ ሰዎች እንኳ በመከራ መታገስን ሊያሳዩ ይችላሉ። የእግዚአብሔር ጸጋ ካለንባቸው ሁኔታዎችና ስሜቶች በመላቀቅ፥ መጥቀን እንድንወጣና ችግሮቻችን መልካሙን ነገር ለማከናወን ምክንያት እንዲሆኑን ሊያስችለን ይገባል። እግዚአብሔር በይበልጥ አዳኛችንን እንመስል ዘንድ፥ ባሕርያችንን ሊያንጽ ይሻል። የእግዚአብሔር ጸጋ ጳውሎስ መከራውን እንዲቀበል ብቻ ሳይሆን፥ በመከራዎቹም እንዲመካ አስችሎታል። መካራው ረግጦ የገዛው ጌታ ሳይሆን፥ መልካም ይሆንለት ዘንድ የሠራ አገልጋዩ ነበር። 

ጳውሎስ በመከራው ምክንያት ያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? አንድኛው ነገር፡ በሕይወቱ ውስጥ የክርስቶስን ኃይል መለማመዱ ነው። እግዚአብሔር የጳውሎስን ድካም ወደ ብርታት ለወጠው። «ያድርብኝ ዘንድ» ተብሎ የተተረጎመው ቃል «ድንኳንን ከላይ መዘርጋት» የሚል ትርጉም አለው። ጳውሎስ ሰውነቱን እንደ ደካማ ድንኳን ይመለከተዋል (2ኛ ቆሮ.5 ከቁጥር 1 ጀምሮ)፤ ይሁንና የእግዚአብሔር ክብር ወደዚያ ድንኳን መጥቶ የተቀደሰ ማደርያ ያደርገዋል። 

ለጳውሎስ ሌላም ነገር ተደርጎለታል – በመከራው ለመመካትችሉ ነበር። ይህም ማለት ከጤንነት ይልቅ ሕመምን መርጧል ማለት ሳይሆን፥ ዳሩ ግን መከራዎቹን እንዴት ወደ ጠቃሚ ነገሮች መለወጥ እንደሚቻል ያውቅ ነበር። እንግዲህ ለውጡን ያመጣው ምንድነው? የእግዚአብሔር ጸጋና የእግዚአብሔር ክብር። በእነዚህ መከራዎችና ችሮች «ይደሰታል»፤ ይህም ሥነ-ልቦናዊ ሚዛናዊነቱ ስለዛባና በሕመም ደስ ይለው ስለ ነበረ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን መከራውን የሚቀበለው ለኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ነው። አስቸጋሪ የሕይወት ገጽታዎችን በተቀበለበትና ባስተናገደበት መንገድ፥ እግዚአብሔርን እያስከበረ ነበር። 

ፒ.ቲ.ፎርሳይት፥ «መከራ እንዲወገድ ሳይሆን እንዲለወጥ መጸለዩ ትልቅ ነገር ነው» በማለት ጽፈዋል። እውነታቸውን ነው። ጳውሎስ ድልን የተቀዳጀው በምትክ ሳይሆን፥ በለውጥ ነበር። በዚህም የእግዚአብሔርን የጸጋ ብቃት ተረድቷል። 

ከጳውሎስ ልምምድ ውስጥ፥ በርካታ ተግባራዊ ትምህርቶችን ልንማር እንችላለን። 

1. ራሱን ለሰጠ አማኝ ከሥጋዊ ይልቅ መንፈሳዊው ነገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ይህም ሥጋዊውን ነገር ገለል እናድርገው ለማለት አይደለም – ሰውነታችን የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማደርያ ነውና። በምትኩ ሥጋችን በራሱ የነገሮች ሁሉ የመጨረሻ ግብ እንደ ሆነ አድርገን መውሰድ የለብንም ለማለት ነው። በዚህ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማከናወን የሚረጻን መሣሪያ ነው። እግዚአብሔር ክርስቲያናዊ ባሕርያችንን በማሳደግ የሚያከናውነው ተግባር፥ የባሕርይ ለውጥ ከማይታይበት የሥጋ ፈውስ እጅግ የላቀ ነው። 

2. እግዚአብሔር ሸክሞችንና በረከቶችን፥ መከራንና ክብርን እንዴት ሚዛናዊ ማድረግ እንደሚቻል ያውቃል። ሕይወት ከተለያዩ ንጥረ-ነገሮች እንደሚቀመም መድኃኒት ሁሉ፥ በውስጡ ከሚገኙት ባሕሪያት አንዳንዶቹ ሊጎዱን ይችላሉ፤ ዳሩ ግን በተገቢው ሁኔታ ሲዋሃዱ ይጠቅሙናል። 

3. ሕመም ሁሉ የኃጢአት ውጤት አይደለም። የኢዮብ አጽናኞች ሙግት፥ ኢዮብ የሚሰቃየው ኃጢአት በመሥራቱ ነው የሚል ነበር። ይሁንና ሙግታቸው በኢዮብም ሆነ በጳውሎስ ላይ የሚሠራ አልነበረም። እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ታላቅ ተግባር ለማከናወን፥ ሰይጣን መከራ እንዲያመጣብን የሚፈቅድባቸው ጊዜያት አሉ። 

4. ከሕመም የከፋም ነገር አለ – ይኸውም ኃጢአት ሲሆን፥ ከሁሉም የሚከፋው ኃጢአት ደግሞ ትዕቢት ነው። በእግዚአብሔር ላይ ከሚያምፅ ጤነኛ ሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር እየተገዛና በጸጋው ደስ እየተሰኘ የሚኖር በሽተኛ ሰው እጅጉን ይመረጣል። ልዑሉ እግዚአብሔር፥ ከሁሉም በላይ ኩሩ (ዕቡይ) በሆነው በሰይጣን በመጠቀም፥ ጳውሎስን ትሁት ማድረጉ የሚያስገርም ነው። 

5. ሥጋዊ ጉዳት ውጤታማ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ከመስጠት ሊያግደን አይገባም። የዛሬዎቹ ቅዱሳን የራሳቸውን ምቾት ወደ መጠበቅ ስለሚያጋድሉ፥ ትንሽ ሕመም በሚሰማቸው ጊዜ ሁሉ፥ ከቤተ ክርስቲያን ለመቅረት ወይም የአገልግሉትን ግብዣ ላለመቀበል፥ እንደ ማመካኛ አድርገው ይጠቀማሉ። ጳውሎስ የሥጋ መውጊያው የማሰናከያ ዓለት እንዲሆንበት አልፈቀደም። እንዲያውም እግዚአብሔር ያንኑ መውጊያ ወደ መወጣጫ ደረጃ እንዲለወጥለት ፈቀደ። 

6. ሁልጊዘም በእግዚአብሔር ቃል ልናርፍ እንችላለን። ሁልጊዘም በመከራና በሥቃይ ጊዜያት ለእኛ የሚሆን የመጽናኛ መልእከት አለው። 

ታላቋ ፈረንሣዊ የረቂቅ ምሥጢር ተከታይ የነበረችው ማዳም ጉዮን በመከራ ውስጥ ለነበረ ጓደኛዋ፥ «አሜን ብለው በተቀበሉት ኃዘን ውስጥ ያለውን ኃይል ብታውቀው ኖሮ ምንኛ በተጽናናህ! » ስትል ጽፋለት ነበር። 

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስለ ታመነና በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ስለ ተደገፈ፥ ይህንን ኃይል አውቆት ነበር። ዛሬ ያ ኃይል የአንተ ሊሆን ይችላል።

Leave a Reply

%d bloggers like this: