ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9)

«ለኢየሱስ፥ እሺ! ለቤተ ክርስቲያን፥ እምቢ!» 

በ1960ዎቹ ይህ መፈክር በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የነበረበትን ጊዜ ታስታውሳለህን? በወቅቱ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በከፋ ችግር ውስጥ ስለነበረች፥ ይህን አባባል በ 56 ዓ.ም በቆሮንቶስ የነበሩት ያለ ጥርጥር በቅንነት በተጠቀሙት ነበር። የሚያሳዝነው፥ ችግሮቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰቦች መካከል የቀሩ ሳይሆኑ፥ በውጭ ባሉ በማያምኑትም ዘንድ የታወቁ መሆናቸው ነበር። 

በመጀመሪያ ደረጃ በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተክርስቲያን የረከሰች ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ከአባሎቿ አንዳንዶቹ በዝሙት ኃጢአት የወደቁ ነበሩ፤ ሌሎች ሰካራሞች ነበሩ፤ እንደዚሁም ሌሎቹ ለዓለማዊ አኗኗራቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ እንደ ማመካኛ የሚጠቀሙ ነበሩ። ከዚህም ባሻገር ይህች ቤተ ክርስቲያን በአመራር ትንቅንቅ በገጠሙ (1፡12) በትንሹ አራት የተለያዩ ቡድኖች የተከፋፈለች ነበረች። ይህም ጸጋዋ የተገፈፈ ቤተ ክርስቲያን ነበረች ማለት ነው። እግዚአብሔርን በማስከበር ፈንታ፥ የወንጌልን ግሥጋሤ የምትገታ ነበረች።  

ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነበር? የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የከተማዪቱ ኃጢአት ወደ ጉባኤያቸው ሰርጎ እንዲገባ ስለፈቀዱ ነበር። ቆሮንቶስ ሁሉም ዓይነት ክፋትና ዓለማዊ ተድላ ያጨናነቃት የረከሰች ከተማ ነበረች። በዚያን ዘመን የመጨረሻው ቀላል ክስ አንድን ሰው «ቆሮንቶሳዊ» ብሎ በመወንጀል ሊመሠረት ይችል ነበር። በአባባሉ ምን ለማለት እንደፈለገ ሰዎች ወዲያው ይገባቸዋል። 

በተጨማሪም ቆሮንቶስ ንድፈ አሳባቸውን የሚያራምዱ በርካታ ተዘዋዋሪ አስተማሪዎች የነበሩባት፥ በትዕቢቷ የተወጠረች የፍልስፍና ከተማ ነበረች። የሚያሳዝነው፥ ይህ ፍልስፍናዊ አካሄድ በወንጌል ላይም እንዲተገበር በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አማካኝነት በመደረጉ ክፍፍሉን አጧጡፎአል። ምእመናኑ ከወንጌል መልእክት በስተጀርባ በኅብረት ከመሰለፍ ይልቅ የተለያየ «የአመለካከት ጎራዎች» ባሉአቸው ቡድኖች የተዋቀሩ ነበሩ። 

ቆሮንቶስ ምን ዓይነት እንደነበረች ለማወቅ ከፈለግህ ሮሜ 1፡18-32ን አንብብ። ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ በቆሮንቶስ ነበር። በመሆኑም የዘረዘራቸውን ኃጢአቶች ሁሉ ሰመስኮቱ አሻግሮ በዓይኑ ሊያያቸው ይችል ነበር! 

በእርግጥ በሰብአዊ ጥበብ የሚመኩ፥ ዓለማዊ አኗኗርን የተላበሱ ዕቡያን ሰዎች ሲኖሩ ችግሮች እንደሚከሰቱ የታወቀ ነው። ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲችሉ ለመርዳት ጳውሎስ በክርስቶስ የተደረገላቸውን ጥሪ በማሳሰብ መልእክቱን አሃዱ በማለት የዚህን ጥሪ ሦስት ጠቃሚ ገጽታዎች አመለከተ። 

ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9) 

ጳውሎስ በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን የርኵሰትን ጽኑ ችግር አጥብቆ ተቃወመ፥ ሆኖም ግን ስለ ችግሩ የተናገረው ምንም ነገር አልነበረም። በዚህ ፈንታ አዎንታዊ አቀራረብ ተጠቀመና እማኞች በክርስቶስ ስላላቸው የከበረና የተቀደሰ ስፍራ አሳሰባቸው። ከቁጥር 1-9 ባለው ውስጥ እግዚአብሔር ስለሚያያት ቤተ ክርስቲያን ገለጸ፥ ከቁጥር 10-31 ባለው ውስጥ ደግሞ ሰዎች ስለሚያዩአት ቤተክርስቲያን አብራራ። በኢየሱስ ክርስቶስ የያዝነው ስፍራ በዕለታዊ ኑሮአችን ተተግብሮ መታየት ያለበት መሆን ሲገባው፥ ብዙ ጊዜ ግን ይህን አናደርግም። 

በኢየሱስ ክርስቶስ ከተደረገልን ቅዱስ ጥሪ የተነሣ ቤተ ክርስቲያን የሚኖሩአትን ባሕርያት ልብ በል። 

በእግዚአብሔር የተለየች (1፡1-3)። በግሪክ ቋንቋ ቤተክርስቲያን ማለት ተጠርተው የወጡ ሰዎች» ማለት ነው። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ሁለት አድራሻዎች አሉአት። መልክዓ ምድራዊ አድራሻ (“በቆሮንቶስኝ እና መንፈሳዊ አድራሻ (“በክርስቶስ ኢየሱስ ዘንድን። ቤተ ክርስቲያን የተዋቀረችው ከቅዱሳን፥ ማለትም በእግዚአብሔር «ከተቀደሱ» ወይም «ከተለዩ» ሰዎች ነው። ቅዱስ ማለት ከኖረው የተቀደሰ ሕይወት የተነሣ ሰዎች የሚያከብሩት የሞተ ሰው ማለት አይደለም። የለም፥ ጳውሎስ የጻፈው ሕያው ለሆኑ ቅዱሳን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ካላቸው እምነት የተነሣ ለእግዚአብሔር ልዩ ፍስሐ እና ግልጋሎት ለተለዩ ሰዎች ነው። 

በሌላ አባባል፥ ማንኛውም እውነተኛ አማኝ በእግዚአብሔር እና ለእግዚአብሔር ስለሆነ፥ ሁሉም አማኝ ቅዱስ ነው ማለት ነው። 

አንድ ክርስቲያን ፎቶ አንሺ ጓደኛዬ «ስላነሣው» እንድ ቆንጆ ሠርግ አጫውቶኝ ነበር። ሙሽራዪቱና ሙሽራው ከቤተክርስቲያን ተያይዘው ወጥተው፥ ወደ ተዘጋጀላቸው የሙሽራ መኪናቸው በማምራት ላይ እያሉ ድንገት ሳይታሰብ ሙሽራዪቱ ባሏን ጥላ በመንገድ ዳር ቆሞ ወደነበረ መኪና ከነፈች! ሞተሩ እየሠራ ሰውየውም መሪውን እንደ ጨበጠ ነበርና ምስኪኑን ባል ባለበት «የጨው -ዓምድ» አድርገውት ተያይዘው ፈረጠጡ። «የፈርጣጩ መኪና» ነጂ ለካስ «በፈለገው ማንኛውም ጊዜ ሊያገኛት እንደሚችል ይፎክር የነበረ» የቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ ኖሯል። በዚህም ሊገመት እንደሚቻለው ባል ጋብቻው ውድቅ ሆኖበት ቀረ። 

ወንድና ሴት ተጋቢዎች እርስ በርስ የፍቅር ቃል ኪዳን ከተለዋወጡ በኋላ አንዳቸው ለሌላቸው የተለዩ ይሆናሉ፥ በመሆኑም ከጋብቻ ውጭ የሆነ ማንኛውም ግንኙነት ኃጢአት የሞላበት ተግባር ነው። ልክ እንደዚሁ ክርስቲያን ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም የተሰጠ ነው፣ ለእርሱ እና ለእርሱ ብቻ የተለየ ነው። ከዚህም በላይ «የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሁሉ ከሚጠሩት ጋር» (ቁ2)። የዓለም አቀፍ ኅብረት ማለትም የቤተ ክርስቲያን አካልም ነው፥ የረከሰ እና ታማኝ ያልሆነ አማኝ ኃጢአት የሚሠራው በጌታ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቲያን ወገኖቹም ላይ ነው። 

በእግዚአብሔር ጸጋ ባለጠጎች የሆነች (1፡4-6)። ደኅንነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ የጸጋ ስጦታ ነው፣ ይሁንና ስትድን ወዲያው መንፈሳዊ ስጦታዎችም ታድለውሃል። (ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ በምዕራፍ 12-14 በዝርዝር ያስረዳል)። የግሪኩ ቃል ባለጠጎች እንድትሆኑ የተደረጋችሁ የሚለውን በጣም ሀብታም ሰው ብሎ ይፈታዋል። በተለይ ቆሮንቶሳውያን በመንፈሳዊ ስጦታዎች ባለጠጋዎች ነበሩ (2ኛ ቆሮ. 8፡7)፥ ሆኖም ግን እነዚህን ስጦታዎች በመንፈሳዊ መንገድ አይጠቀሙባቸውም ነበር። እግዚአብሔር እኛን የመጥራቱ፥ የመለየቱና ባለጠጋ የማድረጉ እውነት የተቀደሰ አኗኗር እንድንኖር ሊያበረታታን ይገባል። 

የኢየሱስን መገለጥ የምትጠባበቅ (1፡7)። ጳውሎስ ስለዚህ እውነት በምዕራፍ 15 የሚለው ብዙ አለው። አዳኛቸውን የሚጠባበቁ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ከነቀፋ በላይ አድርገው መያዝ ይፈልጋሉ (1ኛ ዮሐ 2፡28-3፡3)። 

በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የምትደገፍ (1፡8-9)። የእግዚአብሔር ሥራ በእነርሱ ውስጥ የጸና (ቁ.6)፥ ደግሞም በቃሉ በኩል ለእነርሱ የጸና ነበር። ይህ ቃል የንግድ ልውውጥ ዋስትና ለመስጠት የሚያገለግል የሕግ ቃልን ያመለክታል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የገባውን «ውል» እንደሚጠብቅና እስከ ፍጻሜው እንደሚያድነን 

ዋስትና የሚሰጥ የመንፈስ ምስክርነት በውስጣችን፥ የቃሉ ምስክርነት ደግሞ በፊታችን አለን። ይህ ዋስትና ያለ ጥርጥር ለኃጢአት ማመካኛ አይደለም! ይልቁኑ ለሚያድግ የፍቅር፥ የመተማመን እና የታዛዥነት ግንኙነት መሠረት ነው። 

ታዲያ፥ እነዚህ ታላላቅ እውነቶች በገሃድ እየታዩ፥ የቆሮንቶስ ጉባኤ እንዴት አድርጎ በዓለም እና በሥጋ ሊጠመድ ቻለ? ቆሮንቶሳውያን የተመረጡ፥ ባለጠጎች የተደረጉ እና የተደላደሉ ሰዎች ነበሩ። ለእግዚአብሔር ክብር የተለዩ ቅዱሳን ነበሩ ያሳዝናል፥ ተግባራቸው ከይዞታቸው የተለየ ሆነ። 

ጳውሎስ ኅብረት የሚለውን ቃል በቁጥር 9 ላይ በመጥቀስ ሁለተኛውን የክርስቲያን ጥሪ ገጽታ አስተዋወቀ።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: