በጌታ ራት የነበሩ ፈር የለቀቁ ድርጊቶች (1ኛ ቆሮ.11፡23-34)

ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝቡ እንዲጠብቁአቸው ያቆሙአቸውን ሁለት ሥርዓቶች ይቀበላሉ ጥምቀት እና የጌታ እራት። (የጌታ እራት በ 1ኛ ቆሮ. 10፡ 16 ላይ እንደተጠቀሰው፥ ኅብረት በመባልም ይታወቃል። እንደዚሁም የካሪስት «አቅርቦተ ምስጋና» ተብሎም ይጠራል)። ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዋውን ና እንጀራውን አነሣእነዚህ በዘመኑ አንድ ማዕድ ተዋጽኦዎች ናቸው። ከዚያም እነዚህን ሁለት ነገሮች ለአማኞች ትርጉም ወደሚሰጡ ልምምዶች ቀየራቸው። ይሁንና የልምምዱ እሴት የሚወሰነው በተሳታፊዎች የልብ ሁኔታ ላይ ነው፤ በቆሮንቶስ የነበረው ችግርም ይኸው ነው። 

ባልተዘጋጀ ልብ ወደ ኅብረቱ መምጣት ከባድ ነገር ነው። በግድየለሽነት መንፈስም የጌታን እራት መቀበል ከባድ ነገር ነው። ቆሮንቶሳውያን በጌታ እራት አቀባበላቸው ኃጢአት ያደርጉ ስለነበር እግዚአብሔር ቀጥቶአቸዋል። «ስለዚህ በእናንተ መካከል የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል [ሞተዋል]» (ቁ 30)። 

በትክክለኛ ልብ ከቀረበው የጌታ እራት ለመንፈሳዊ እድገት ና ባርኮት ድል ይሰጠናል። ይህ እራት ቅጣት ሳይሆን በረከት እንዲያመጣልን ምን እናድርግ? 

በመጀመሪያ፥ ወደ ኋላ መመልከት አለብን (11፡23-26)። የተቆረሰው እንጀራ ለእኛ የተሰጠውን የክርስቶስ ሥጋ ያሳስበናል፤ ጽዋውም የፈሰሰውን ደሙን ያስታውሰናል። ኢየሱስ ተከታዮቹ ሞቱን እንዲያስታውሱ መፈለጉ ያልተለመደ ነገር ነው። ብዙዎቻችን የወደድናቸው እንዴት እንደ ሞቱ ለመርሳት እንጥራለን፤ ነገር ግን ኢየሱስ እንዴት እንደ ሞተ እንድናስታውስ ይፈልጋል። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያን እንደመሆናችን ያለን ነገር በሙሉ ማዕከል የሚያደርገው ይህን ሞቱን ነው። 

መሞቱን ማስታወስ ያለብን፥ የወንጌል መልእክት አንዱ ክፍል ስለሆነ ነው። «ክርስቶስ . . ሞተ፥ ተቀበረም. . .» (15፡3-4)። ኃጢአተኞችን የሚያድነው የጌታችን ሕይወት፥ ወይም ትምህርቶቹ ሳይሆኑ ሞቱ ነው። በዚህን ምክንያት ለምን እንደ ሞተ እናስታውሳለን። ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ፤ ልንከፍለው የማንችለውን ዕዳ በመክፈል፥ እርሱ የእኛ ምትክ ሆነ (ኢሳ. 53፡6፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡24)። 

እንዴት እንደ ሞተም ማስታወስ አለብን-በፈቃደኝነት፥ በየዋህነት፥ ፍቅሩን ለእኛ በመግለጥ ነው (ሮሜ 5፡8)። ሥጋውን ለክፉዎች እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ በሰውነቱም የዓለምን ኃጢአት ተሸከመ። 

ይሁንና ይህ «ማስታወስ» ታሪካዊ እውነታዎችን እንዲያው ማስታወስ አይደለም። በመንፈሳዊ እውነታዎች ውስጥ መሳተፍ ነው። በጌታ እራት ወቅት እየዞርን የምናደንቀው ሐውልት የለም። ልባችን በእምነት ሲዘረጋ ሕያው ከሆነ አዳኝ ጋር ኅብረት እናደርጋለን። 

ሁለተኛ፥ ወደፊት መመልከት አለብን (11፡26)። ይህን እራት «እርሱ እስኪመለስ ድረስ» እንወስደዋለን። የኢየሱስ ክርስቶስ መመለስ የቤተ ክርስቲያን ና የእያንዳንዱ ክርስቲያን የተባረከ ተስፋ ነው። ኢየሱስ ለእኛ የሞተ ብቻ ሳይሆን እንደገና በመነሣት ወደ ሰማይ አርጓል፤ እናም አንድ ቀን ተመልሶ መጥቶ ወደ ሰማይ ይዞን ይሄዳል። ዛሬ መሆን የሚገባንን ሁሉ አልሆንንም፤ ነገር ግን እርሱን በምናይበት ጊዜ፥ «እርሱን እንመስላለን» (1ኛ ዮሐ 3፡2)። 

ሦስተኛ፥ ወደ ራሳችን መመልከት አለብን (11፡27-28፥ 31-32)። ጳውሎስ የጌታን እራት ለመውሰድ ብቁ ሆነን መገኘት አለብን ማለቱ ሳይሆን፥ ብቃት ባለው ሁኔታ ወይም መንገድ መውሰድ አለብን ማለቱ ነው። በስኮትላንድ በተደረገ የጌታ እራት አገልግሎት ከምእመናኑ እንዲት ሴት ከሽማግሌው እጅ እንጀራውን እና ጽዋውን መቀበል ትታ ቁጭ ብላ ስታለቅስ መጋቢው አስተዋላት። መጋቢው ማዕዱን ትቶ ሄደና አጠገቧ ሆኖ « ውሰጂው የእኔ እመቤት፥ ይህ እኮ ለኃጢአተኞች ነው!» አላት። በእርግጥም ነው፤ ነገር ግን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ የዳኑ ኃጢአተኛች ይህን እራት ኃጢአታዊ በሆነ ሁኔታ ማስተናገድ የለባቸውም። 

ክቡር በሆነ መንገድ መካፈል ካለብን፥ የገዛ ልባችንን መመርመር፥ በኃጢአቶቻችን መፍረድ እና ለጌታ መናዘዝ አለብን። በሕይወታችን ንስሐ ያልገባነው ኃጢአት ይዘን ወደ ማዕዱ መቅረብ የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ተጠያቂ መሆን ነው፤ ምክንያቱም እርሱን በመስቀል ላይ የተነከረው ኃጢአት ነው። ኃጢአቶቻችንን ራሳችን ካልፈረድንባቸው፥ ንስሐ ገብተን እስከምንተዋቸው ድረስ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ፍርዱን ና ቅጣቱን ያመጣል። 

ቆሮንቶሳውያን ራሳቸውን መመርመሩን ችላ ብለው ሌላውን ሁሉ በመመርመሩ ረቀቁበት። ቤተ ክርስቲያን በምትሰባሰብበት ጊዜ የራሳቸውን ኃጢአት ማወቅ ተስኖአቸው እያለ የሌሎችን እንደሚከታተሉ «ሃይማኖታዊ መርማሪዎች» መሆን የለብንም። ክብር በጎደለው መንገድ ብንመገብ ና ብንጠጣ፥ የምንበላው ና የምንጠጣው ፍርድን ነው፤ ይህ ደግሞ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። 

ቅጣቱ እግዚአብሔር ወንድ ና ሴት ልጆቹን እንዲጠነክሩ የሚያበረታታበት የፍቅር አያያዝ ነው (ዕብ. 12፡1-11)። እርሱ በወንጀለኛ ላይ የሚፈርድ ዳኛ ሳይሆን፥ የማይታዘዙ (ምናልባትም የደነደኑ) ልጆቹን የሚቀጣ አፍቃሪ አባት ነው። ቅጣት እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያረጋግጥልናል፤ ከተባበርነው ደግሞ ቅጣት የእግዚአብሔርን ሕይወት በእኛ ውስጥ ይሠራል። 

በመጨረሻም፥ ወደ ዙሪያችን መመልከት አለብን (11፡33-34)። ዙሪያችንን መመልከት ያለብን ሌሎች እማኞችን ለመተቸት ሳይሆን፥ ነገር ግን የጌታን ሥጋ ለመለየት ነው (ቁ 29)። ይህ ምናልባት ጣምራ ትርጉም ይሰጣል። ሥጋውን በእንጀራው ውስጥ፥ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለሆነች ደግሞ በዙሪያችን ባለችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መለየት አለብን። «አንድ እንጀራ ስለሆነ፥ እኛ ብዙዎች አንድ ሥጋ ነን» (1ኛ ቆሮ. 10፡17)። የጌታ እራት የቤተ ክርስቲያን ኅብረት መገለጫ መሆን ነበረበት፤ ነገር ግን በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ኅብረት አልነበረም። እንዲያውም፥ የጌታን እራት ማክበራቸው ለክፍፍላቸው መግለጫ ሆኖ ነበር። 

የጌታ እራት የአንድ ቤተሰብ ማዕድ ነው። የቤተሰቡ ባለቤትም ልጆቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱ ና አንዱ ለአንዱ እንዲጠነቀቅ ይፈልጋል። ከአማኝ ወገኖቹ ተለያይቶ እያለ በዚሁ ጊዜ ደግሞ ወደ ጌታ መጠጋት ለእውነተኛ ክርስቲያን ሊሆንለት አይችልም። እርስ በርስ ሳንዋደድ እንዴት አድርገን የጌታን ሞት እናስባለን? «ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል» (1ኛ ዮሐ 4፡11)። 

ማንም እውነተኛ አማኝ ያልሆነ ወደ ማዕዱ መምጣት የለበትም። ይህ ብቻ ሳይሆን እውነተኛው አማኝም ቢሆን ልቡ ከእግዚአብሔር ምንም አይነት ፊንፊትም እና ከክርስቲያን ወገኖቹ ጋር ትክክል ካልሆነ ወደ ማዕዱ መቅረብ የለበትም። ከተካፋዮቹ ማንም በራሳቸው ላይ ቅጣትን እንዳይጋብዙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የጌታን እራት ከመካፈላቸው በፊት መንፈሳዊ ዝግጅት የሚያደርጉት ለዚህ ነው። አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ወደ እኔ ቀርቦ ስለደረሰበት ግላዊ ሽንፈት ያጫወተኝ ትዝ ይለኛል። ችግሩ መንፈሳዊ ሕይወቱን ከመጉዳት አልፎ በሌሎችም ዘንድ «በመለፈፉ» በእርሱ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ ነቀፋን ሊያመጣ የተቃረበ ነበር። 

«ይህን ለማስተካከል ምን ላድርግ?» አለኝ። ሁኔታው በእርግጥ ኃጢአቱን እንደፈረደበት እና ንስሐ እንደገባበት አሳመነኝ። በተከታዩ ሳምንት የጌታን እራት እንደምናዘጋጅ ነገርሁትና የጌታን ምሪት እንዲጠይቅም አሳሰብሁት። በምሽቱ የጌታ እራት ላይ፥ ከዚህ ቀደም አድርጌው በማላውቀው መንገድ አገልግሎቱን ጀመርሁ። «ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሆነ ነገር ለመካፈል የሚያስብ ሰው አለ?» ብዬ ጠየቅሁ። ንስሐ የሚገባው ወዳጄ ተነሥቶ በእግሩ ቆመና ወደፊት ተራምዶ እማዕዱ ቦታ ተገናኘኝ። በተረጋጋ፥ አጠር ባለ ቃል፥ ኃጢአት እንደሠራ እና ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ እንደሚጠይቅ ተናገረ። ከመንፈስ የመጣ የፍቅር ማዕበል በጉባኤው ላይ ሲወርድ ተሰማን። ሰዎችም በግልጽ ያለቅሱ ነበር። በዚያን ምሽት የጌታ እራት መታሰቢያ፥ በትክክል የጌታን ሥጋ ለይተን አወቅን። 

ምንም እንኳ የኃጢአት ንስሐ አስፈላጊ ቢሆንም፥ የጌታ እራት የኃጢአት መንሥኤ መንፈሳዊ የመመርመሪያ እና የልቅሶ ጊዜ እንዲሆን አይጠበቅም። የምስጋና እና ጌታን ለማየት በሐሴት የምንጠባበቅበት ጊዜ መሆን አለበት! ሥቃይ ና ሞት እየጠበቀው ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ ምስጋናን አቀረበ። እኛም እንዲሁ ምስጋና እንስጥ።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: