ቤተ ክርስቲያኒቱን አስቡ (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13)

በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለች ብቻ ሳትሆን ጸጋዋን የተገፈፈችም ነበረች። በጉባኤው ውስጥ ኃጢአት ነበረ፥ የሚያሳዝነው ደግሞ ሁሉም ስለ ኃጢአቱ ያውቅ ነበር። ነገር ግን ማንም ስለዚህ ጉዳይ ምንም ለማድረግ የፈለገ አይመስልም። 

የትኛውም ቤተ ክርስቲያን ፍጹም አይደለም፥ ነገር ግን የሰው ፍጹም አለመሆን መታጣት ለኃጢአት ማመካኛ ሊሆን አይገባውም። ወላጆች ልጆቻቸውን በፍቅር መቅጣት እንዳለባቸው ሁሉ፥ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም በምእመናኖቻቸው ላይ የሥነ ሥርዓት እርምጃ መውሰድን መለማመድ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ማለት ወንጀለኛን ለመያዝ የተሰማሩ «ትሕትና የጎደላቸው የፖሊሶች ቡድን» ተግባር ማለት አይደለም። ይልቁኑ ልባቸው የተሰበረባቸው የባዘነውን የቤተሰብ አባል ለመመለስ የሚሹ የወንድሞችና እኅቶች ቡድን ነው። 

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት አንዳንድ አባላት ሁኔታውን ተጋፍጠው ለመለወጥ ስላልፈለጉ፥ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሦስት ጠቃሚ እሳቤዎችን አቀረበ። 

ቤተ ክርስቲያኒቱን አስቡ (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13) 

«ይህ ኃጢአት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ያስከትላል?» የሚለው በእርግጥ ጠቃሚ እሳቤ ነው። ክርስቲያኖች «ቅዱሳን ለመሆን የተጠሩ» ናቸው (1፡2) እናም ይህ ማለት ለእግዚአብሔር ክብር የተቀደሰ ሕይወት ማለት ነው። አንድ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያኑን የሚወድድ ከሆነ፥ ኃጢአት እንዲያደክማት እና ምስክርነቷን እንዲያበላሽባት ዳር ቆሞ አይመለከትም። 

እንዴት ነው ምላሽ የምንሰጠው? ጳውሎስ ሦስት ወጥ መመሪያዎችን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትከተል ሰጣት። 

በኃጢአታቸው እንዲያዝኑ (5፡1-2)። ይህ ቃል የሚያገለግለው ለሞተ ሰው፥ ሰው ሊገልጸው የሚችለውን ምናልባትም በጣም ጥልቅ እና የሚጎዳ የግል ኃዘን ለማመልከት ነው። በማዘን ፈንታ በቆሮንቶስ የነበሩ ሰዎች በትዕቢት ተነፉ። ቤተ ክርስቲያናቸው በጣም «ክፍት አቋም» ስለነበራት፥ ዘማውያን እንኳ በጥሩ ይዞታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት መሆን መቻላቸውን ይመጻደቁበት ነበር! 

የወቅቱ ኃጢአት በቤተሰብ መካከል የተፈጸመ ወሲብ ነበር። የታወቀ ክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን አባል የነበረ) በዘላቂ የወሲብ ኅብረት ከእንጀራ እናቱ ጋር ይኖር ነበር። ጳውሎስ በሴቲቱ ላይ ፍርድ ስለማያስተላልፍ (ቁ 9-13)፥ ይህች ሴት የጉባኤው አባል፥ ምናልባትም ክርስቲያን እንኳ ያልነበረች እንደሆነ እንገምታለን። እንዲህ ዓይነቱ ኃጢአት በብሉይ ኪዳን (ዘሌ 18፡6-8፤ 20፡11) እና በአሕዛብ ሕዝቦች ሕጎችም የተወገዘ ነው። ጳውሎስ «የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ የማይገኝ ነው!» በማለት ቤተ ክርስቲያንን አሳፈራት። 

ክርስቲያናዊ ሕይወት ደስታ የሞላበት ግብዣ ዓይነት (ቁ 8) መሆኑ እውነት ቢሆንም፥ ኃዘን የሚሆንበትም አንዳንድ ጊዜያት አሉ። ክርስቲያን ወንድም ወይም እኅት ኃጢአት በሚያደርጉበት ጊዜ፥ ወቅቱ ቤተሰቡ የሚያዝንበትና ለወደቀው አማኝ እርዳታን የሚሻ በት ነው (ገላ. 6፡1-2)። የጌታን ነገር በተመለከተ በቆሮንቶስ የነበረው ወንድም «ሞቶአል»። ከጌታ እና በቤተ ክርስቲያን የተቀደሰ ሕይወት ከሚኖሩት ሰዎች ኅብረት ተለይቶአል። 

በኃጢአት ላይ ፍረዱ (5፡3-5)። ክርስቲያኖች አንዳችን የሌላችንን አቋመ ልቡና (ማቴ. 7፡1-5)፥ ወይም አገልግሎት (1ኛ ቆሮ. 4፡5) እንድንፈርድበት የሚገባ ባይሆንም፥ ስለ እርስ በርሳችን ጠባይና ተግባር እውነተኞች እንድንሆን ይጠበቅብናል። በራሴ የመጋቢነት አገልግሎት፥ በቤተክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ እንዲደረግ ማነሣሣት ያስደሰተኝ ጊዜ ፈጽሞ የለም፤ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የታዘዘ ስለሆነ፥ እግዚአብሔርን መታዘዝ እና ግላዊ ስሜቶችን ወደ ጎን ማድረግ ይገባናል። 

ጳውሎስ እዚህ ላይ የገለጸው ጥፋተኛው በመለኮታዊ ሕግ መሠረት የተዳኘበትን ኦፊሴላዊ የቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ነው። ግልጽ ኃጢአት በግልጽ ሊዳኝ እና ሊወገዝ ይገባዋል። (ጌታችን ስለ ቅጣት- የሥነ ሥርዓት እርምጃ የሰጠውን መመሪያ፥ ከማቴዎስ 18፡15-20 እጥና።) ኃጢአቱ ከጉያ ውስጥ ተሸጉጦ የሚታለፍ አልነበረም፤ አገር ያወቀው እና ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በነበሩት ባልዳኑ ሰዎች መካከል እንኳ የተገኘ ነበር። 

ቤተ ክርስቲያን በአንድ ላይ ተሰብስባ ጥፋተኛውን ማስወገድ ነበረባት። ጳውሎስ ሲያዝዛቸው የተጠቀመውን ጠንካራ ቃል ልብ በል። «የአባቱን ሚስት ያገባ» (ቁ. 2)፥ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት «ለሰይጣን እንዲሰጥ» (ቁ 5)፥ «አስወግዱ» (ቁ.7)፥ «ከመካከላችሁ አውጡት» (ቁ.13)። ጳውሎስ ጥፋተኛውን በልስላሴ እንዲያስተናግዱት አላሳሰባቸውም። በእርግጥ አስቀድሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪዎች ሰውየውን ለመመለስ በግል የጣሩ ይመስለናል። 

ይህ መደረግ የነበረበት በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን – በስሙ እንጂ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን አልነበረም። የቤተ ክርስቲያን አባልነት ከባድ ነገር ስለሆነ በቀላል ወይም በግድ የለሽነት የሚያዝ ጉዳይ አይደለም። 

ክርስቲያንን «ለሰይጣን» መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? ደኅንነቱን ማሳጣት ማለት አይደለም፤ ቀድሞ ነገር ደኅንነትን የምታድል ቤተ ክርስቲያን እይደለችም። አንድ ክርስቲያን ከጌታ እና ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ኅብረት ሲኖረው፥ ልዩ በሆነ ጥበቃ ከሰይጣን ይጋረዳል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ኅብረቱን ካቋረጠ እና ከቤተ ክርስቲያን ከተወገደ፥ የጠላት «መቀለጃ » ይሆናል። በኃጢአት የወደቀው አማኝ ንስሓ ገብቶ ወደ ጌታ እንዲመለስ፥ እግዚአብሔር የጥፋተኛውን ሰውነት ሰይጣን እንዲያጠቃ ሊፈቅድለት ይችላል። 

ኃጢአትን (አሮጌውን እርሾ) አስወግዱ 6፡6-13)። እዚህ ላይ የቀረበው የፋሲካ እራት ምሳሌ ነው (ዘፀአ 12)። እኛን ከኃጢአታችን አርነት ለማውጣት ደሙን ያፈሰሰው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ነው (ዮሐ 1፡29፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡18-25)። በግብጽ የነበሩት አይሁድ ከሞት ያመለጡት የጠቦቱን በግ ደም በመቀባት ነበር። ደሙን ከቀቡት በኋላ፥ የአይሁድ ቤተሰቦች የፋሲካውን እራት ተመገቡ። ከመስፈርቶቹ አንዱ በመኖሪያቸው ምንም ዓይነት እርሾ እንዳይገኝ የሚል ነበር። በበዓሉ ላይ የሚቀርበው ቂጣም እንኳ ያልቦካ ነበር። 

እርሾ የኃጢአት ምሳሌ ነው። ትንሽ ሆኖ ነገር ግን ኃይለኛ ነው፤ የሚሠራው በስውር ነው፤ ከዚያም ሊጡን ይነፋዋል»፤ ከዚያም ይሰራጫል። ኃጢአት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ያደርግ የነበረው እንደ ትንሽ እርሾ ነበር። መላውን እንጀራ (ጉባኤውን) ያረክስ ነበር። በቀዶ ሕክምና መወገድ እንደሚገባው በሰውነት ውስጥ እንዳለ አደገኛ ካንሰር ነበር። 

ቤተ ክርስቲያን ከ«አሮጌው እርሾ» – ክርስቶስን ከማመናችን በፊት ከነበሩ የሕይወት ግሳንግሶች – ራሷን ማጽዳት አለባት። ምቀኝነትና ክፋትን (በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል ብዙ ቅሬታዎች ነበሩ) አስወግደን በእነዚህ ቦታ ትሕትናን እና እውነትን መተካት አለብን። እንደ እንጀራ (1ኛ ቆሮ 10፡17)፥ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በተቻለ መጠን ንጹሕ መሆን አለባት። 

ይሁንና ቤተ ክርስቲያን በውጭ ባሉት መፍረድና መኮነን የለባትም። የዚህ ዓይነቱ ፍርድ ወደፊት የሚሆን ሲሆን ኃላፊነትን የሚወስደውም እግዚአብሔር ነው። በቁጥር 9-13 ከዓለም የመለየትን አስፈላጊነት ጳውሎስ እንደገና አጽንኦት ይሰጥበታል። ክርስቲያኖች ብቸኛ መሆን ሳይሆን መለየት ነው ያለባቸው። ከኃጢአተኞች ጋር ከመገናኘት ልንወገድ አንችልም፣ ነገር ግን በእነርሱ ኃጢአት መበከልን ልናስወግድ እንችላለን። 

በዚህ ስፍራ በተጠቀሱት ዓይነት ኃጢአቶች ክርስቲያን ተብዬው ሰው ከተወነጀለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን ከእርሱ ጋር ማስተካከል አለባት። እያንዳንዱ ምእመን ከእርሱ ጋር «መተባበር» የለባቸውም (ቁ. 9- «አትቀላቀሉ»፥ «በጥልቅ አትቀራረቡ»)። ከዚህ ሰው ጋር አብሮ መብላት አልነበረባቸውም፤ ይህም በግል የሚደረገውን ወይም በማኅበር የሚደረገውን የጌታን እራት የሚመለከት ሊሆን ይችላል (11፡23-34ን ተመልከት)። 

የቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ቀላል ወይም ተወዳጅ አይደለም፤ ነገር ግን አስፈላጊ ነው። በአግባቡ ከተሠራበት እግዚአብሔር የባዘነውን አማኝ ለመውቀስ እና ለመመለስ ይጠቀምበታል። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 2፡1-11 እንደሚያሳየው ይህ ሰው ንስሐ ገብቶ ወደ ኅብረቱ ተመልሶአል።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: