ብስለት፡- የመንፈስ ጸጋዎች (1ኛ ቆሮ. 13፡1-13)

የጋሊቨር ጉዞዎች በተሰኘው መጽሐፍ፥ «እንድንጣላ የሚያደርገን በቂ ሃይማኖት አለን፥ ነገር ግን እርስ በርስ እንድንዋደድ የሚያደርገን ሃይማኖት ይጎድለናል» ያለው አሽሟጣጭ ደራሲ ዮናታን ስዊፍት ነበር። መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ የቱን ያህል የሚያስደስቱና አስደናቂ ቢሆኑም በፍቅር አገልግሎት ላይ እስካልዋሉ ድረስ ፋይዳ-ቢስ፥ እንዲያውም አጥፊ ናቸው። በሦስቱም የጳውሎስ «የአካል» ምንባቦች፥ ትኩረት የተሰጠው ለፍቅር ነው። በክርስቲያን ሕይወት የብስለት ዐቢይ ማረጋገጫ ለእግዚአብሔር፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እና ለጠፉት ነፍሳት እየጎለበተ የሚሄድ ፍቅር መኖር ነው። ፍቅር የክርስቶስ አካል «ሥርዓተ ዑደት» ነው መባሉ ትክክለኛ አነጋገር ነው። 

እንደ 1ኛ ቆሮንቶስ 13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተሳሳተ ትርጉም እና ተዛምዶ ይበልጥ የተዳረጉ ምዕራፎች ቢኖሩ ጥቂት ናቸው። ይህ ክፍል ከዐውዱ ከተፋታ፥ «የፍቅር ዜማ» ወይም ስለ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት የቀረበ ስሜት ቀስቃሽ ስብከት ነው የሚሆነው። ጳ ውሎስ ስለ ልሳኖች ስጦታ ተገቢ ያልሆነ አጠቃቀም፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል፥ ስለ ሌሎች ስጦታ መቅናት፥ ስለ ራስ ወዳድነት (ክሱን አስታወስህ?)፥ በማኅበር ስብሰባዎች የእርስ በርስ ትዕግሥት ስለመጥፋት እና ጌታን ስለሚያዋርድ ባሕርይ የጻፈው የቆሮንቶሳውያንን ችግር ለማስተካከል መሆኑን ብዙዎች ማየት ይሳናቸዋል። 

መንፈሳዊ ስጦታዎችን በጥበብ መጠቀም የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ክርስቲያኖች ከውስጣቸው በፍቅር ሲነሣሡ ነው። ጳውሎስ ፍቅር በአገልግሎት ለምን ተፈላጊ እንደሆነ የሚያሳዩ ሦስት የክርስቲያናዊ ፍቅር ባሕርያትን ገለጸ። 

ፍቅር አበልጻጊ ነው (13፡1-3)። ጳውሎስ አምስት መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይጠራል። ልሳኖች፥ ትንቢት፥ እውቀት፥ እምነት እና መስጠት (መሥዋዕት) ናቸው። ያለ ፍቅር እነዚህን ነገሮች መለማመድ ከንቱ መሆኑን አመለከተ። ፍቅር የሌለበት ልሳን የጦፈ ጩኸት ብቻ ነው! አንድን ስጦታ የሚያበለጽገው እና ዋጋ የሚያሰጠው ፍቅር ነው። ፍቅር የሌለበት እገልግሎት አገልጋዩንም ሆነ በአገልግሎቱ የተሳቡትን ያራክላል፤ ነገር ግን ፍቅር ያለበት አገልግሎት መላውን ቤተ ክርስቲያን ያለማል። «እውነትን በፍቅር እየያዝን” (ኤፌ 4፡15)። 

ክርስቲያኖች «እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ ከእግዚአብሔር ተምራችኋልና» (1ኛ ተሰ. 4፡9) የተባለላቸው ናቸው። እግዚአብሔር አብ ልጁን በመላክ ማፍቀርን አስተማረን (1ኛ ዮሐ 4፡19)። እግዚአብሔር ወልድ ደግሞ ሕይወቱን በመስጠት እና እርስ በርስ እንድንዋደድ በማዘዝ ማፍቀርን አስተማረን (ዮሐ 13፡34-35)። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፍቅር በውስጣችን በማፍሰስ (ሮሜ 5፡5) እርስ በርስ እንድንዋደድ ያስተምረናል። በእምነት ትምህርት ቤት ከሁሉም በላቀ ሁኔታ ተፈላጊው ትምህርት እርስ በርስ መዋደድ ነው። ፍቅር የሚነካውን ሁሉ ያበለጽጋል። 

ፍቅር ያንጻል (13፡4-7)። «እውቀት ያስታብያል፥ ፍቅርን ግን ያንጻል ይገነባል» (8፡1)። የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ ነው (12፡7፤ 14፡5፥12፥7፥26)። ይህ ማለት ስለ ራሳችን ሳይሆን፥ ነገር ግን ስለ ሌሎች ማሰብ አለብን ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ፍቅርን ይጠይቃል። 

ቆሮንቶሳውያን በማኅበር ስብሰባዎች ላይ ትዕግሥት አልነበራቸውም (14፡29-32)፤ ነገር ግን ፍቅር ቢኖራቸው በታገው ነበር። በእርስ በርሳቸው ስጦታዎች ይቀናኑ ነበር፤ ፍቅር ቢኖራቸውማ ኖሮ ቅናትን ባስወገደላቸው ነበር። በትዕቢት «የተነፉ» ነበሩ (4፡6፥18-19፤ 5፡2)፥ ፍቅር ግን ትዕቢትን እና በራስ መመጻደቅን አስወግዶ የሌሎችን እድገት መፈለግን ይተካበታል። «በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ» (ሮሜ 12፡10)። 

ቆሮንቶላውያን በ«ፍቅር ግብዣ» እና በጌታ ማዕድ ላይ የሚያሳዩት ጠባይ በጣም ተገቢ ያልሆነ ነበር። የእውነተኛ ፍቅርን ትርጉም አውቀውት ቢሆን ኖሮ ጌታን በሚያስደስት መንገድ ራሳችውን ባስከፉ ነበር። እርስ በርስ በፍርድ ቤት ይካሰሱ ነበር! ፍቅር ግን «የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም» (ቁ 5)። በደልን አይቆጥርም የሚለው ሐረግ «የጥፋትን መዝገብ አያስቀምጥም» ማለት ነው። ሌሎች ፈጽመውብኛል ያላቸውን ጥፋቶች በማስታወሻ ደብተሩ ላይ በዝርዝር ያሰፈረ አንድ ክርስቲያን ተዬ ሰው ካጋጠሙኝ ምስኪን ሰዎች አንዱ ነው። ይቅርታ ማለት መዝገብን ንጹሕ ማድረግና በሰዎች ላይ ፈጽሞ ነገርን አለመያዝ ነው (ኤፌ 4፡26፥32)። 

ፍቅር በዓመፅ ደስ አይለውም፤ እንዲህም ሆኖ ቆሮንቶሳውያን በቤተ ክርስቲያናቸው ስላለው ኃጢአት ገና ይመጻደቁ ነበር (ምዕ. 5)። «ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና» (1ኛ ጴጥ. 4፡8)። እንደ ኖኅ ልጆች የሌሎችን ኃጢአት ለመሽፈን መፈለግ እና ከዚያም ነገሮችን እንዲያስተካክሉ መርዳት አለብን (ዘፍ 9፡20-23)። 

ከቁጥር 4-7 ያለውን በጥንቃቄ አንብብና በገላትያ 5፡22-23 ከተዘረዘረው ጋር አነጻጽር። በዚያ ፍሬ ውስጥ ሁሉም የፍቅር ባሕርያት እንደሚታዩ ትመለከታለህ። ለዚህ ነው ፍቅር የሚያንጸው፤ የመንፈስን ኃይል በሕይወታችንና በየቤተ ክርስቲያናችን የሚያፈስሰው። 

ፍቅር ይጸናል (13፡8-13)። ትንቢት፥ እውቀት እና ልሳኖች ዘላቂ ስጦታዎች አልነበሩም። (እውቀት «ትምህርት» ማለት ሳይሆን ለአእምሮ ቅጽበታዊ የመንፈሳዊ እውነት መሰጠት ነው።) እነዚህ ሦስቱ ስጦታዎች አንድ ላይ የሚሄዱ ነበሩ። እግዚአብሔር ለነቢዩ እውቀትን ይሰጣል፤ እርሱም መልእክቱን በልሳን ያቀርባል። ከዚያም ተርጓሚ (አንዳንዴ ነቢዩ ራሱ) መልእክቱን ይገልጽ ነበር። ቆሮንቶሳውያን ያከብሩአቸው የነበሩት ስጦታዎች እነዚህ፥ በተለይም ልሳን ነበሩ። 

እነዚህ ስጦታዎች ይጠፋሉ ደግሞም ያቆማሉ፤ ነገር ግን «እግዚአብሔር ፍቅር» ስለሆነ ፍቅር ለዘላለም ይኖራል (1ኛ ዮሐ 4፡8፥16)። ቆሮንቶሳውያን አንድ ቀን በሚጠፉ አሻንጉሊት እንደሚጫወቱ ልጆች ነበሩ። ልጅን እንደ ልጅ እንዲያስብ፥ እንዲገነዘብ እና እንዲናገር ትጠብቀዋለህ፤ ደግሞም በተጨማሪ እንዲያድግ እና እንደ አዋቂ ማሰብና መናገር እንዲጀምርም ትጠብቀዋለህ። «የልጅነት ነገሮችን የሚጥልበት ቀን ይመጣል» (ቁ 1)። 

በአዲስ ኪዳን (በዚያን ጊዜ ባልተጠናቀቀው) ሙሉ የሆነ መገለጥ አለ፤ ነገር ግን ስለ እርሱ ያለን ግንዛቤ ከፊል ነው። (ከዚህ በተለየ የምታስብ ከሆነ 8፡1-3 ከልስ።) ለመላው ቤተ ክርስቲያን (ኤፌ. 4፡11-16) እና ለግለሰብ አማኝ (14፡20፤ 2ኛ ጴጥ. 3፡18) የእድገት ሂደት አለ። ኢየሱስ እስኪመለስ ሙሉ ለሙሉ ፍጹም አንሆንም፤ ነገር ግን አሁን እያደግንና እየበሰልን ልንገኝ ይገባል። ልጆች ለጊዜያዊው ነገር ሲኖሩ አዋቂዎች ግን ለዘላቂው ነገር ይኖራሉ። ፍቅር ጽኑ ነው፥ የሚያፈራው ፍሬም ይጸናል። 

ምንም እንኳ «እምነት የሚታይ ተስፋም የሚፈጸም ቢሆኑም» እነዚህ ሦስቱ የክርስቲያን ጸጋዎች እንደሚጸኑ ልብ በል። ከእነዚህ ጸጋዎች የሚበልጠው ፍቅር ነው፤ ምክንያቱም አንድን ሰው በምትወድድበት ጊዜ፥ ታምነዋለህ ደግሞም ሁልጊዜ አዳዲስ ተስፋዎችን ትጠባበቃለህ። እምነት፥ ተስፋ እና ፍቅር አብረው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እምነትን እና ተስፋን በኃይል የሚሞላው ፍቅር ነው። 

የሚያሳዝነው፥ ዛሬ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ከሚደረጉት አጽንኦቶች አንዳንዱ የተቀደሰ አይደለም (ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ቶል ስላለህ፤ ደግሞም መንፈሳዊም አይደለም (ምክንያቱም ቀስቃሽነቱ ለሥጋዊ ተፈጥሮ ስለሆነ። ለሌሎች እማኛች ምን ዓይነት ስጦታዎችን ማግኘት እንዳለባቸው ወይም እንዴት እንደሚያገኙ መንገር የለብንም። ይህ በሉዓላዊው አምላክ እጅ ያለ ጉዳይ ነው። ስጦታዎችን መናቅ የለብንም፤ በሌላ በኩል የመንፈስ ጸጋዎችንም ቸል ማለት አይገባንም። በዝውውር አገልግሎቴ፥ ለስጦታዎች ከፍተኛ ጉጉት ለነበራቸው፥ ነገር ግን ለጸጋዎች ደንታ በማይሰጡ ሰዎች የተፈጠሩ እያሌ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ገጥመውኛል። 

አንድነት–ልዩነት–ብስለት፤ ብስለት ደግሞ በፍቅር የሚገኝ ነው።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: