ታማኝነት- መጋቢው (1ኛ ቆሮ. 4፡1-6)

በምዕራፍ 3፥ ጳውሎስ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ሦስት ምስሎች አሳይቶአል። አሁን ደግሞ የአገልጋይን ሦስት ምስሎች ያቀርባል። እነርሱም መጋቢ (ቁ. 1-6)፥ መጫወቻ (ቁ. 7-13)። እና አባት (ቁ 14-21) ናቸው። አንባቢያኑ የአንድን ክርስቲያን አገልግሎት እግዚአብሔር እንዴት እንደሚመዝን ና እንደሚገመግም እንዲገባቸው ፈለገ። ቁጥር 6 የጳውሎስን ዓላማ ይገልጻል። «ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ።» 

ሰዎችን ና አገልግሎታቸውን በምንገመግበት ጊዜ ጽንፎችን ማስወገድ አለብን። በእንድ ወገን፥ ያጋጠመንን ማንኛውንም በመቀበል ግድየለሽ ልንሆን እንችላለን። ሌላው ጽንፍ ደግሞ ጳውሎስም እንኳ ምዘናውን እስከማያልፍ ከመጠን ያለፈ ሒሰኛ መሆኑ ነው። መናፍስትን መመርመራችን አስፈላጊ ነው (1ኛ ዮሐ 4፡1-6፤ 2ኛ ዮሐ ልብ በል)፥ ነገር ግን በምናደርግበት ጊዜ መንፈስን እንዳናሳዝን መጠንቀቅ አለብን። 

በእነዚህ ሦስት የአገልግሎት ምስሎች፥ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አገልጋይን ሦስት ባሕርያት ያቀርባል። 

ታማኝነት- መጋቢው (1ኛ ቆሮ. 4፡1-6) 

ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ለነበሩ ልዩ ልዩ አንጃ ዎች ለመሪዎች መልስ በሚሰጥበት ጊዜ ራሱን፥ ጴጥሮስን ና አጵሎስን የክርስቶስ አገልጋዮች» ብሎ ይጠራቸዋል። አገልጋይ የሚለው ቃል፥ ቃል በቃል ሲተረጎም «ቀዛፊዎች» ማለት ነው። ይህ የሚያመለክተው በነፋስ የሚነዱ ሰፋፊ ጥንታዊ የሮማውያን መርከቦችን የሚቀዝፉ ባሪያዎችን ነው። ጳውሎስ፥ «እኛ የመርከቡ ካፒቴን አይደለንም፥ ነገር ግን ከትእዛዝ በታች የሆንን የመርከብ ላይ ባሪያዎች ነን። እንግዲህ አንዱ ባሪያ ከሌላው ይልቃልን?» ይላል። 

ቀጥሎ ጳውሎስ የመጋቢን ምስል ይገልጻል። መጋቢ ለጌታው ሁሉንም ነገር ያከናውናል፤ ነገር ግን የራሱ ምንም የለውም። ዮሴፍ ለጶጢፋራ ቤተሰብ ዋና መጋቢ ነበር (ዘፍ 39)። ቤተ ክርስቲያን የእምነት ቤተሰብ ናት (ገላ. 6፡10)። እንደዚሁ አገልጋዮች የእግዚአብሔርን ብልጽግና ከቤተሰቡ ጋር የሚካፈሉ መጋቢዎች ናቸው (ማቴ. 13፡52)። ጳውሎስ ይህን መንፈሳዊ ብልጽግና «የእግዚአብሔር ምሥጢራት» ብሎ ይጠራዋል። ይህን ምሥጢር የሚለውን ተፈላጊ ቃል በ 2፡7 ተመልክተነው ነበር፤ ስለዚህ እንደገና ወደኋላ ተመልሰህ ልትመለከተው ትችላለህ። 

የመጋቢው ኃላፊነት ለጌታው ታማኝ መሆን ነው። መጋቢ የቤተሰቡን አባላት ላያስደስት ይችል ይሆናል። ምናልባት አብረውት የሚያገለግሉትን ሌሎች አገልጋዮችም ላያስደስት ይችላል። ነገር ግን፥ ጌታውን የሚያስደስት ከሆነ እርሱ መልካም መጋቢ ነው። ይኸው እሳብ ራሱ በሮሜ 14፡4 ተገልጾአል። 

ስለዚህ፥ ቁም ነገሩ «ጳ ውሎስ ተወዳጅ ነውን?» ወይም «አጵሎስ ከጳውሎስ የተሻለ ሰባኪ ነውን?» የሚለው አይደለም። ቁም ነገሩ «ጳውሎስ፥ አጵሎስ ና ጴጥሮስ እግዚአብሔር ላስቀመጣቸው ሥራ ታማኝ ነበሩን?» የሚል ነው። ኢየሱስም በሉቃስ 12፡48 የተመዘገበውን ምሳሌ በተናገረ ጊዜ በአእምሮው የነበረው ይኸው መመዘኛ ነበር። የእግዚአብሔር አገልጋይ በገዛ ሕይወቱ፥ በቤቱ እና በቃል አገልግሎቱ ታማኝ ከሆነ፥ መልካም መጋቢ ነውና ተገቢ ዋጋውን ይቀበላል። 

ነገር ግን አገልጋይ ያለ ማቋረጥ በፍርድ ውስጥ የሚያልፍ ነው። በሚያደርገው ነገር ላይ ሁልጊዜ ትችት የሚሰነዘርበት አለ። ጳውሎስ በመጋቢ ሕይወት ላይ የሚነጣጠሩ ሦስት ዓይነት ፍርዶች እንዳሉ እመልክቶአል። 

የሰው ፍርድ አለበት (4፡3)። ሰዎች በሚተቹት ጊዜ ጳውሎስ አልተበሳጨም። ምክንያቱም የጌታው ፍርድ የላቀ መሆኑን ስለሚያውቅ ነበር። የሰው ፍርድ የተሰኘው፥ ቃል በቃል «ያሳውቀን» ማለት ነው። ይህ ሊመጣ ካለው የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን (1፡8፤ 3፡13) የሚነጻጸር ነው። 

አገልጋዩ በራሱ ላይም የሚያስተላልፈው ፍርድ አለ (4፡3)። ጳ ውሎስ በሕይወቱ እና በአገልግሎቱ ምንም ስሕተት እንደሌለበት ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን ያም እንኳ ነፃ አላደረገውም። አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን በደንብ እናውቀውም። በንጹሕ ሕሊና ና በተመጻዳቂ አመለካካት መካከል ያለው መስመር በጣም ጠባብና የረቀቀ ስለሆነ መጠንቀቅ አለብን። 

በጣም ተፈላጊው ፍርድ የእግዚአብሔር ፍርድ ነው (4፡4)። በእርግጥ ዛሬ እግዚአብሔር በቃሉ (ዕብ 4፡12) እና በመንፈስ አገልግሎት አማካኝነት በእኛ ላይ ይፈርዳል። አንዳንድ ጊዜ ኃጢአትን ተጋፍጠን ንስሐ እንድንገባ ለመርዳት የምንወደውን ጓደኛችንን አገልግሎት ይጠቀማል (ማቴ. 18፡15-17)። ነገር ግን እዚህ ላይ የቀረበው ዋና ማጣቀሻ ክርስቲያን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት የሚቆምበትን የመጨረሻ ግምገማ የሚመለከት ነው (ሮሜ 14፡10፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡10)። በዚያን ጊዜ እውነተኛዎቹ ነገሮች ይገለጡና ታማኝ አገልጋዮች ይሸለማሉ። 

እነዚህ ቁጥሮች ለሰብአዊ ራስ አመጻዳቂ አርነት ማራመጃ መሣሪያዎች መደረግ የለባቸውም። አጥቢያ ቤተክርስቲያን ቤተሰብ ናት፤ የቤተሰቡ አባላት ደግሞ ለማደግ እርስ በርስ መተጋገዝ አለባቸው። ለትሕትናና በፍቅር ለተቀመመ ሒስ ምንጊዜም ስፍራ አለ። የሚተቸን ሰው ትክክል ከሆነ፥ እኛን ረዳን ማለት ነው። እርሱ ትክክል ካልሆነ ደግሞ እኛ ልንረዳው እንችላለን። በሁለት አቅጣጫም ቢሆን እውነት ይጎለብታል። 

ጳውሎስ በቁጥር 5 ላይ «ስለዚህ» ሲል ቀደም ብለው የተነገሩትን እውነቶች ወደ ግል ተዛምዶ ሊያመጣቸው መሆኑን እንድንጠባበቅ ያነሣሣል። ይህን ክፍል ግን በሦስት ጣምራ ግሣጼዎች ይደመድመዋል። 

በመጀመሪያ፥ «ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ» (4:5)። ሕይወታቸውንና አገልግሎታቸውን ጌታ የሚገመግመው በሚመለስበት ጊዜ ነው፤ ስለሆነም እስከዚያ ቀን ድረስ ጠብቁ። እንደ እውነቱ ከሆነማ፥ የሰዎችን ልብ ማየት አትችልም፤ ተነሥተህ አቋመ ልቡናቸውን ልትፈርድበት አትችልም። ያን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። «ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል» (1ኛ ሳሙ. 16፡7)። 

በጳውሎስ ላይ ፍርድን ያስተላልፉ የነበሩት ቆሮንቶሳውያን በመሠረቱ በእግዚአብሔር ቦታ ራሳቸውን ማስቀመጣቸው ና ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን መብት ለራሳቸው መናጠቃቸው ነበር። እኔም በራሴ አገልግሎት ይህን ስሕተት ስንት ጊዜ ፈጸምሁ! አንድን ሁኔታ ትክክል ባልሆነ መንገድ መገንዘብ ና ሰውንም ያለ አግባብ መፍረድ ምንኛ ቀላል ነው። 

ሁለተኛ፥ «የምትፈርዱት ትክክል ባልሆነ መለኪያ ነው» (4፡6)። ቆሮንቶሳውያን የተለያዩ ሰዎችን ይመዝኑ የነበሩት በገዛ ራሳቸው ምርጫ ግላዊ ጥላቻ ላይ ተመርኩዘው ነበር። አገልጋዮችንም እንኳ አንዱን ከሌላው ያበላልጡ ነበር። ለግምገማ ብቸኛው ትክክለኛ መሠረት የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ ከአገልጋዮች የሚጠበቀው ሕይወትና አገልግሎት ምን ዓይነት እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። አዲስ መለኪያዎችን ማበጀት ለእኛ አስፈላጊያችን አይደለም። መጋቢን ከሚያፈላልጉ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ጊዜ ደብዳቤ ይደርሰኛል። እነርሱም ዕጩ የሚሆኑትን ልጠቁምላቸው እችል እንደሆነ ይጠይቁኛል። አብዛኛውን ጊዜ መስፈርቶቻቸው እግዚአብሔር በቃሉ ካስቀመጠው የራቁ ናቸው። እንደገና፥ ይህ ጳውሎስ በምዕራፍ 1 እና 2 ያነሣው—በሰዎች ና በእግዚአብሔር ጥበብ መካከል ያለ ችግር ነው። 

ሦስተኛ፥ «የተሳሳተ አቋመ ልቡና ይዛችሁ ትፈርዳላችሁ» (4፡6)። በቤተ ክርስቲያን የነበሩ እያንዳንዱ ቡድን የወደዱትን ሰው ለማነጽ ሌሎች ሰባኪዎችን ይበጣጥቁአቸው ነበር። እቋመ ልቡናቸው ፍጹም መንፈሳዊ አልነበረም። ለአንድ ሰው ወገናዊ መሆን ና ሌሎችን መቃወም በቤተ ክርስቲያን ክፍፍልን ያፋፍም ነበር። ልባቸውን መመርመርና ቤተ ክርስቲያንን እያፈረሳት የነበረውን ትዕቢት መንግሎ መጣል ይገባቸው ነበር። 

የእግዚአብሔር አገልጋዮች የእርሱ እውነት መጋቢዎች ናቸው። ስለሆነም ቁልፍ መመዘኛቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝ እና ለማስተማር ምን ያህል ታማኝ ናቸው? የሚል ነው። እንዲያውም በታማኝነት ማስተማር ብቻ ሳይሆን በታማኝነት በተግባር ማሳየትም ነው። የሳሙኤል (1ኛ ሳሙ. 12፡1-5) እና የጳውሎስ (የሐዋ. 20፡17) ምስክርነት ለዚህ እውነት ማስረጃ ይሆናል።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: