ትሕትና-መጫወቻ (1ኛ ቆሮ. 4፡7-13)

ጳውሎስ ራሱን ና ሌሎች ሐዋርያትን «ለዓለም መጫወቻ ሆነናል» (ቁ.) ሲል፥ በሮማውያን ግዛት የነበሩ ሰዎች አበክረው የሚያውቁትን ምሳሌ መጠቀሙ ነበር። የሮማ መንግሥት በተለያዩ ከተሞች መዝናኛዎችን በማዘጋጀት ሕዝቡን ዝም ያሰኙ ነበር። በጨዋታ የሚወዳደሩ ወንዶችን እና ከአራዊት ጋር የሚታገሉ እስረኞችን ለማየት በጓጉ ዜጎች የቲያትር ቤቶቻቸው ይጨናነቁ ነበር። (እንዲያውም መጫወቻ የሚለው የግሪክ ቃል ሲተረጎም «ቴአትር» የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ይሰጣል።) በሮም የሚገኘው ኮሎሲየም የእነዚህ «መዝናኛዎች» ማዕከል ሆኖ ነበር። 

ዋነኞቹ «ጨዋታዎች» ሲጠናቀቁ፥ ከዚያ ቀጥሎ ድሆች ና ደካሞች የሆኑ እስረኞች ከአራዊት ጋር እንዲታገሉ ይገባሉ። ከእነርሱ ብዙ የሚጠብቅ አልነበረም። 

ይህ እንዴት ያለ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ትክክለኛ ሥዕል ነው! ይሁንና ጳውሎስ ቆሮንቶሳውያንን ትሑት በማድረጉ ዓላማ ለሚያካሄዳቸው ጥረቶች ለሚያገለግሉ ተከታታይ ንጽጽሮች ይህ መነሻ ነው። 

ነገሥታት-እስረኞች (4፡7-9)። በቁጥር 7 ላይ ያሉት ጥያቄዎች ቆም ብለን እንድናስብ ሊያደርጉን ይገባል። እኔ፥ ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ መጽሐፍ ቅዱስ (NASB) ለመጀመሪያው ጥያቄ የሰጠው ትርጓሜ ያስደስተኛል። «ማን ነው እንደ የበላይ የሚቆጥርህ?» አንድ ወጣት ሰባኪ ለጓደኛዩ፥ «ትሑት እንድሆን ጸልይልኝ» አለው። ጓደኛዬም መለሰና፥ «እስኪ ንገረኝ፥ ልትታበይበት የሚገባ ምን አለ?» አለው። ለምንድን ነው ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚያየው? ምናልባት እኮ ተፈላጊ ሰዎች እንደሆንን እንዲሰማን የሚያደርገው የተዛባው አስተያየታችን ሊሆን ይችላል። ለቁጥር 7 ከሁሉም የሚልቀው መግለጫ የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ነው፥ «ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው አንዳች ሊቀበል አይችልም. . . እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል» (ዮሐ 3፡27-30)። 

ጳውሎስ በቁጥር 8 ላይ ቆሮንቶሳውያንን ነገሥታት ብሎ በሚገልጽበት ጊዜ መጠነኛ የተቀደሰ ምፀት ተጠቅሞአል። «እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር!» በማለት ጻፈ። «ነገር ግን በዚህ ፈንታ፥ ወደ መጫወቻው መውጣት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ መሠቃየት አለብን። በሰው ፊት እናንተ ቀዳሚዎች ናችሁ፤ እኛ ሐዋርያት ግን መጨረሻዎች ነን» በእግዚአብሔር ፊት ሐዋርያት ቀዳሚዎች ነበሩ (12፡28)፥ ነገር ግን በሰዎች ዓይን መጨረሻ ነበሩ። 

በአገልግሎት ውስጥ ለትዕቢት ስፍራ የለም። እንደ ጳውሎስ ያለ ታላቅ መሪ ራሱን «በማሳያው ቦታ በፕሮግራሙ መጨረሻ » ካደረገ፥ ይህ የተቀረነውን የት ይከትተናል? እግዚአብሔር ከሰጠው መለኪያ በተለየ አገልጋዮችን የሚመዝኑ ከሆነ፥ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተሳሳቱ ናቸው። ተወዳጅ ሰባኪዎቻቸውንም ማሞካሽታቸው ስሕተተኞች ያደርጋቸዋል። ይህ ማለት ታማኝ አገልጋዮች ሊታወቁ አይችሉም ወይም አይከበሩም ማለት አይደለም። ነገር ግን፥ በነገር ሁሉ እግዚአብሔር መክበር ይገባዋል (1ኛ ተሰ. 5፡12-13)። 

ልባሞች-ሞኞች (4፡10)። ጳውሎስ በሰዎች መለኪያ አኳያ ሞኝ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪ በመሆኑ ጸንቶ ቢቀጥል ኖሮ በሃይማኖቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰ ነበር (ገላ. 1፡14)። ወይም በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከነበሩ የሕግ ሊቃውንት ወግኖ ለአሕዛብ ቢያገለግል ኖሮ፥ አብዛኛው ስደት በቀረለት ነበር (የሐዋ. 15፡21፥17)። ነገር ግን ጳውሎስ «ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወድዳለህ?» (የሐዋ. 9፡6) በማለት ጌታን በጠየቀበት ጊዜ፥ ክልቡ ማለቱ ነበር። 

ቆሮንቶሳውያን በገዛ ዓይኖቻቸው ፊት ልባሞች ነበሩ፥ ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ በእግዚአብሔር ዓይን ሞኞች ነበሩ። በዓለም ጥበብ ና መለኪያ ላይ መመካታቸው፥ እንደ ሞኞች ማድረጋቸው ነበር። በመንፈሳዊ ረገድ ልባም ወይም ጥበበኛ መሆን በዓለም ፊት ሞኝ መሆን ነው (1ኛ ቆሮ. 3፡18)። ራሴን ሁልጊዜ የሰማእቱን የጂም ኤሊዮትን ቃላት ስጠቅስ አገኘዋለሁ። «ሊያጣው የማይችለውን ለማግኘት ሲል ሊያቆየው የማይችለውን የሚሰጥ እርሱ ሞኝ እይደለም።» 

ኃይለኞች- ደካሞች (4፡10)። ጳውሎስ በኃይሉ የተመካባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲገናኝ ገንዘቤ ናቸው ብሎ ያሰባቸው ዕዳ መሆናቸውን ደረሰበት (ፊልጵ. 3)። የእርሱ መንፈሳዊ ብርታት የደካማነቱ ውጤት መሆኑን ጳውሎስ የደረሰበት ራሱ ከገጠመው ሥቃይ ተነሥቶ ነበር (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። ብርቱ ነኝ ብሎ የሚያስብ ብርቱ፥ ደካማ ነው፤ ነገር ግን ደካማ መሆኑን የሚያውቅ ደካማ ብርቱ ይሆናል። 

ቆሮንቶሳውያን በመንፈሳዊ ነገር ስለደረሱበት ደረጃ ይመኩ ነበር። በቤተ ክርስቲያን የነበሩ አንጃዎች በሰብአዊ መሪዎቻቸው እና በተወዳጅ ሰባኪዎቻቸው ይኮሩ ነበር። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ደካማነት ነበር። ብርታት የሚመጣው እግዚአብሔር ክብርን ሲቀዳጅ ብቻ ነው። «ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና [ፍጹም ይሆናል] » (2ኛ ቆሮ. 12፡9)።

የተከበራችሁ- የተዋረድን (4፡10-13):: የነገሩ ሁሉ እምብርት ይህ ነው። በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰው የሚመጣውን ክብር ፈለጉ። ራሳቸውን «ከታላላቅ ሰዎች» ጋር አንድ በማድረግ ክብርን «ለመዋስ» ይሞክሩ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መልሶአል፥ «ከእኛ ጋር ከሆናችሁ፥ ለመከራ ብትዘጋጁ ይሻላል፡፡ እኛ ሐዋርያት የተከበርን አይደለንም–የተናቅን ነን!» 

ከዚህ ቀጠለና ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር አገልጋይነቱ መታገሥ ያለበትን እጦት ና መከራ ገለጸ። ድንኳን ሰፊ ሆኖ በገዛ እጆቹ መሥራቱ በብዙዎች ዓይን ሳያስንቀው አልቀረም፤ ምክንያቱም ግሪኮች ዕደ ጥበብን ይንቁ ነበርና። 

በተጨማሪም ጳውሎስ ሰዎች በእርሱ ላይ ለሚፈጽሙት ነገር እንዴት ምላሽ እንደሰጠም ገልጾአል፤ ይህ በራሱ ጳውሎስን ታላቅ በማድረጉ በኩል አስተዋጽኦ አበርክቶአል። ሕይወት ለእኛ የሚያደርገው፥ ሕይወት በእኛ ውስጥ በሚያገኘው ይወሰናል። ጳውሎስ ሲረግሙት፥ መረቀ፥ ልክ ኢየሱስ እንዳዘዘው (ማቴ. 5፡44)። ሲሰደድ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ታገሠ፥ አጸፋውንም አልመለሰም። ክፉ ሲናገሩት፥ ጳውሎስ ለመማለድ ሞከረ። በሁሉም ነገሮች፥ በፍቅር ለመመለስ ተጣጣረ። 

ውጤቱስ ምን ነበር? «ሰዎች እንደ ዓለም ጥራጊ. . . የሁሉም ነገር ጉድፍ» (1ኛ ቆሮ. 4፡13) አድርገው ቆጠሩት። እንደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው! በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና (የሐዋ 22:22) ጳውሎስና ሌሎች ሐዋርያት ልክ በጌታቸው ላይ እንደተደረገበት ነው የተደረገባቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ነቀፋቸውን ገፍፎ ለስሙ ክብርን አመጣ። 

የአገልግሎት ታማኝነትና የልብ ትሕትና እነዚህ ሁለቱ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ናቸው። ለመሥራት ፈቃደኛ ለመሠቃየትም ፈቃደኛ መሆን ይገባዋል። ታማኝ መሆን አንድ ነገር ነው፥ ዝነኛ መሆን ደግሞ በጣም የተለየ ነገር ነው። ለሌሎቹ ሚዛን ለመስጠት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሦስተኛ ባሕርይ አለ።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: