አርነት ከኃላፊነት ጋር መጣጣም አለበት (1ኛ ቆሮ. 10፡23-33)

በክርስቶስ ያለውን ልዩ መብትና ጥቅም እንዳይደሰትበት ጳውሎስ የበሳሉን ክርስቲያን አርነት የካደበት ጊዜ የለም። «ሁሉ ተፈቅዶልኛል» – ነገር ግን ሁሉም የሚጠቅም አይደለም፥ ደግሞም አንዳንዶቹ ነገሮች ወደ ባርነት የሚወስዱ ናቸው (6፡12)። ሁሉም ነገር ይጠቅማል»- ነገር ግን አንዳንዶቹ ድርጊቶች ደካማው ወንድምህ እንዲሰናከል ያደርጉታል (8፡11-13)። በሌላ አነጋገር እርነታችንን ከኃላፊነት ጋር ስናጣጥም የብስለት ምልክት ነው፤ አለበለዚያ አርነት መሆኑ ይቀርና ሥርዓተ አልበኝነትና ሕገወጥነት ይሰፍናል። 

ቀድሞ ነገር፥ በቤተ ክርስቲያን ላሉት ወገኖቻችን እኮ ኃላፊነት አለብን (ቁ 23-30)። ሌሎችን በእምነት የመገንባት ና ጥቅማቸውንም የመፈለግ ኃላፊነት አለብን። ፊልጵስዩስ 2፡1-4 አንድ ዓይነት ማስጠንቀቂያ-አዘል ምክር ይሰጠናል። በክርስቶስ አርነት ያለን ቢሆንም ሌላውን አማኝ ለመጉዳት ነፃ አይደለንም። 

ጳውሎስ ይህን እውነት ሊመጣ ካለው ለጣዖት የተሰጠ ሥጋ ጥያቄ ጋር እዛመደው። እማኝ በገሃድ በጣዖት አምላኪዎች ማዕድ እንዳይሳተፍ ቀደም ሲል አስጠንቅቆአል (8፡9-13)፥ በመሆኑም በዚህ ደረጃ የግል ማዕድን አስመልክቶ ተናገረ። ከቁጥር 25-26 ባለው፥ ለገዛ ቤታቸው አገልግሎት ከገበያ ስለተገዛ ሥጋ ጥያቄ እንዳያነሡ እማኞችን አዝዞእል። ቀድሞ ነገር፥ ሁሉም ነገር የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው [መዝ. (24)፡1ን ጠቀሰ ደግሞም ሁሉም ምግብ ለአማኙ የተፈቀደ ነው (ማር. 7፡14-23፤ የሐዋ. 10፡ 9-16፥ 28፤ 1ኛ ጢሞ. 4፡3-5ን ተመልከት)። ብርቱው አማኝ ለጣዖት የታረደውን ሥጋ እንኳ በገዛ ቤቱ ሊበላው ይችላል። በመደበኛው ገበያ የተገዛው ሥጋ መጀመሪያ የተገኘበት ምንጭ ከቤተ መቅደስ ቢሆንም (ብዙውን ጊዜ ነው) እንኳ፥ አይጎዳበትም። 

ነገር ግን አማኙ በማያምኑት ሰዎች ቤት እንግዳ በሚሆንባቸው ጊዜያትስ? ጳውሎስ ይህን ችግር ከቁጥር 27-30 አስተናግዶታል። ክርስቲያኑ የፈለገውን ማድረግ ከተሰማው (ጳውሎስ ይህን ውሳኔ እንደ ትልቅ ነገር አልቆጠረውም) ከፊቱ የቀረበውን ማንኛውንም ነገር ጥያቄ ሳያነሣ መብላት አለበት። (ሉቃ. 10፡8፤ 1ኛ ጢሞ. 6፡17ን ተመልከት።) ይሁን እንጂ፥ በግብዣው ላይ ለጣዖት የታረደ ሥጋ ለመብላት የማይፈልግና ሥጋውም ከዚህ ውጭ አለመሆኑን የደረሰበት፥ ከደካማ ወንድሞች ወይም እኅቶች አንዱ ተገኝቶ ይሆናል። ይህ ደካማ ቅዱስ ሰው ብርቱውን ክርስቲያን ይህ ሥጋ ለጣዖት የቀረበ ነው ቢለው፥ ያኔ ብርቱው ቅዱስ ሰው መብላት የለበትም። ከበላው፥ ደካማው አማኝ እንዲሰናከልና ምናልባትም ኃጢአት እንዲሠራ ሰበብ ይሆናል። 

ጳውሎስ የሚከተለው ዓይነት ተቃውሞ እንደሚነሣ ከወዲሁ እይቶአል። «የማመሰግንበትን ምግብ የማልበላው ለምንድን ነው?» በሌላ ሰው ደካማ ሕሊና የተነሣ የእኔ አርነት የሚገደበው ለምንድን ነው?» ለእነዚህ የሚሰጠው ምላሽ በሁለተኛ ደረጃ የሚኖረንን ኃላፊነት ያስተዋውቃል። ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር ለማድረግ ኃላፊነት አለብን (ቁ 3)። ሌላው ክርስቲያን እንዲሰናከል ሰበብ እየሆንን እግዚአብሔርን ልናከብር እንችልም። በአንዳንድ ተግባራት ሳንጎዳባቸው ተካፋይ እስከምንሆን ድረስ ሕሊናችን ብርቱ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኞች ነን። ነገር ግን በክርስቶስ ያገኘነውን አርነት ክርስቲያን ወገናችንን ሊጎዳ ስሚችል በምንም ዓይነት መንገድ መጠቀም የለብንም። 

ይሁንና፥ ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ጋር የሚተሳሰር ሦስተኛ ኃላፊነት አለ። የጠፋውን ለመመለስ የመፈለግ ኃላፊነት አለብን (ቁ 32-33)። አይሁድ ወይም አሕዛብ ጌታን እንዳያምኑ ወይም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት ለጌታ እንዳይመሰክሩ ችግር መፍጠር የለብንም። የገዛ ጥቅማችንን ብቻ ለመፈለግ ሳይሆን፥ ነገር ግን ይድኑ ዘንድ የሌሎችንም ጥቅም መሻት አለብን። 

ጳውሎስ፥ «በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ» ብሎ ሲጽፍ (ቁ. 33)፥ አቋሙን የሚያደራድር አድር ባይ ወይም ሰውን ለማስደሰት የቆመ መሆኑን ማመልከቱ እልነበረም (ገላ. 1፡10ን ተመልከት)። ሕይወቱ እና አገልግሎቱ ራሱን እና ፍላጎቶቹን ለማራመድ ሳይሆን ሌሎችን ለመርዳት የቆሙ የመሆናቸውን እውነት እያጸና ነበር። 

ይህን ጠቃሚ ክፍል ከመሰናበታችን በፊት፥ ጳውሎስ ክርስቲያናዊ የአኗኗር መርሁን ላልተገነዘቡት ምናልባት ተለዋዋጭ መስሎ ሳይታይ እንዳልቀረ ልብ ልንል ይገባል። አንዳንድ ጊዜ አሕዛብ የሚበሉትን ይበላ ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ፥ ከአይሁድ ጋር «ኮሽር» ምግብ ይመገብ ነበር። ተለዋዋጭ ከመሆን ይልቅ፥ በእነዚህ ምዕራፎች ባስቀመጣቸው መርሆች መሠረት በአንድ አቋም ይኖር ነበር። የአየር ሁኔታ አመልካች ቀስት አንዴ በአንድ አቅጣጫ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ሲያመለክት የሚለዋወጥ ይመስላል። ሆኖም የአየር ሁኔታ መቆጣጠሪያው ቀስት ሁልጊዜ ጽኑ ነው። ሁልጊዜ የሚያመለክተው ነፋስ ወደሚነፍስበት አቅጣጫ ነው። ጠቃሚ መሣሪያ የሚያደርገውም ይኸው ነው። 

ብርቱው ክርስቲያን በአደባባይ የማያደርገው ሆኖ በቤቱ ውስጥ በግሉ የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ ወይ? አዎን፥ እርሱን የማይጎዳና እርሱም ጌታውን የማይፈታተንበት እስከሆነ ድረስ። ልጆቻቸው ትንንሾች ሳሉ፥ ካርታ የመሳሰሉ መጫዎቻዎችን ከቤታቸው ያራቁ ባልና ሚስትን አውቃለሁ። በኋላ ልጆቻቸው ወደ እውቀት ዕድሜ ሲደርሱ፥ እነዚያኑ መጫዎቻዎች እንዲጫወቱባቸው ፈቀዱላቸው። 

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አርነት አለን። ይህ አርነት ለእኛ የተገዛው በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ በጣም ውድ ነው። አርነት የሚመጣው ከእውቀት ነው «እውነትን ታውቃላችሁ፥ እውነትም አርነት ያወጣችኋል» (ዮሐ 8፡32)። ለምሳሌ ስለ እቶም ባወቅን መጠን በብልሃት ለመጠቀም የበለጠ አርነት ይኖረናል። ሆኖም ግን፥ እውቀት ከፍቅር ጋር መጣጣም አለበት፤ አለበለዚያ ያፈራርሳል እንጂ አይገነባም። 

ብርቱው ክርስቲያን እውቀት ብቻ ሳይሆን ልምድም አለው። ወደኋላው፥ ወዳለፉት ዓመታት ዘወር ብሎ እግዚአብሔር እንዴት ከእርሱ ጋር እንደተገናኘ ማየት ይችላል። ነገር ግን ልምድ ከጥንቃቄ ጋር መጣጣም ስላለበት መጠንቀቅ አለበት። ተጠንቀቅ አለበለዚያ ትወድቃለህ! 

ብርቱው ክርስቲያን ይህ አርነት እንዳለው ያውቃል፤ ነገር ግን አርነት ኃላፊነትንም እንደሚያካትት ይገነዘባል። ለምሳሌ፥ መኪናዬን ከጋራዤ አውጥቼ በአውራ ጎዳናው ላይ የመንዳት ነጻነት አለኝ፤ ነገር ግን ኃላፊነት በተሞላው መንገድ መንዳት አለብኝ። በተፈቀደልኝ መስመር በፈለግሁት ፍጥነት መንዳት አልችልም፤ በመንገዱ ያሉትንም የትራፊክ ምልክቶች ችላ ልላቸው አልችልም። 

ከእነዚህ ምዕራፎች ለግል ውሳኔዎቻችንና ተግባሮቻችን የሚሆኑ በርካታ መመዘኛዎች ይመነጫሉ። 

«ሁሉም ነገሮች የተፈቀዱ ናቸው፥» ነገር ግን፡- 

1. የሚመሩት ወደ አርነት ወይስ ባርነት? (6፡12) 

2. የሚሆኑልኝ የመሰናከያ ድንጋይ ነው ወይስ የመረማመጃ ደረጃ ? (8፡13) 

3. ያንጹኛል ወይስ ያፈራርሱኛል? (10፡23) 

4. እኔን ብቻ የሚያስደስቱኝ ናቸው ወይስ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ናቸው? (10፡31) 

5. ያልዳኑት ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱ ይረዳሉ ወይስ ያርቁአቸዋል? (10፡33) 

የአርነት አጠቃቀማችንና ለሌሎችም የምናዛምድበት አካሄዳችን በክርስቶስ ያደግን ወይም ያላደግን መሆናችንን ያሳያል። ብርቱ ና ደካማ ክርስቲያኖች አንዱ ሌላውን ለማነጽና ኢየሱስ ክርስቶስን ለማስከበር በፍቅር በአንድነት መሥራት አለባቸው።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: