አስተማማኝ እምነት አለን (2ኛ ቆሮ. 4፡13-18)

የእምነት መንፈስ የሚለው ሐረግ «የእምነት እይታ ወይም አመለካከት» ማለት ነው። ጳውሎስ ወደ ልዩ የእምነት ስጦታ ሳይሆን (1ኛ ቆሮ. 12፡9)፥ ዳሩ ግን አማኝ ሁሉ ሊኖረው ወደሚገባ የእምነት አመለካከት እያመለከተ ነበር። ጳውሎስ ራሱን፥ «አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ» የሚለውን የመዝሙር (116)፡10 መልእክት ከጻፈው ሰው ጋር ይመሳሰላል። ለእግዚአብሔር የሚሰጠው እውነተኛ ምስክርነት በእግዚአብሔር በማመን ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ ይህም እምነት የሚመጣው ከእግዚአብሔር ቃል ነው (ሮሜ 10፡17)። አለማመንን ያህል የአንድን አማኝ አፍ የሚለጉም ነገር የለም (ሉቃ 1፡20 ተመልከት)። 

ጳውሎስ የተማመነው በምን ነበር? ለሞት ወይም ለሕይወት የሚያሰጋው ምንም ነገር ባለመኖሩ ነው! የሕይወቱና የአገልግሎቱ አካል የነበሩትን መከራዎች ቀደም ብሎ ስለ ዘረዘረ፥ አሁን ደግሞ እምነቱ በእነዚህ ሁሉ ላይ ድልን እንዳቀዳጀው ያረጋግጣል። ከእምነቱ የተነሣ የሚተማመንባቸው ነገሮች ቀጥለን እንመልከት፡-

1. በመጨረሻ ላይ ድልን እንደሚቀዳጅ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 4፡14)። ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻውን ጠላት ሞትን ካሸነፈ፥ ሌላውን ነገር መፍራት ለምን ያስፈልጋል? ሰዎች የሞትን ትርጉም ለማግኘትና በዚያውም አንጻር ለመዘጋጀት የሚችሉትን ጥረት ሁሉ ቢያደርጉም፥ ዓለም ግን ለዚህ ጥያቄ ምንም ምላሽ አላገኘችም። አንድ ሰው ለመሞት እስካልተዘጋጀ ድረስ፥ በርግጥም ለመኖር አልተዘጋጀም። የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን አስደሳች መልእክት ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ላይ ስለ ተቀዳጀው ድል ሲሆን፥ እኛም ወደዚያው በድል ወጻሸበረቀ ምዕራፍ መመለስ ያስፈልገናል። እንዲሁም ደግሞ፥ ጳውሎስ «ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን» ሲል፥ ወደ ፊት የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚኖረውን አንድነት እንደ ተመለከተ መገንዘብ ያሻል። ሞት ታላቁ አከፋፋይ ሲሆን፥ ዳሩ ግን እርሱ ራሱ ባለበት ስፍራ ሕዝቡ ዳግም እንደሚሰባሰብ በኢየሱስ ክርስቶስ ዋስትና አለን (1ኛ ተሰ 4፡13-18)። 

2. እግዚአብሔር እንደሚከብር እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ.4፡15)። ይህ ምንባብ ከሮሜ 8፡28 ጋር የሚዛመድ ሲሆን፥ መከራዎቻችን እንበለ ከንቱ እንደማይቀሩ ያረጋግጥልናል፡- እግዚአብሔር ለሌሎች ለማገልገልና ላስሙ ክብር ለማምጣት ይጠቀምባቸዋል። እግዚአብሔር በመከራችን የሚከበረው እንዴት ነው? ጉዞው አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ፥ በደስታና በብርታት የምንቸገርበትን «የተትረፈረፈ ጸጋ» በመስጠቱ ነው። በጸጋ የሚጀመር ማንኛውም ነገር፥ ወደ ክብር ይመራል [መዝ. (84)፡11፤ 1ጴጥ. 5፡10 ተመልከት። 

3. መከራዎቹ የሚፈጸሙት ለእርሱ ጥቅም እንጂ ሊጎዱት እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 4፡16-17)። «አንታክትም» (ቁ 1 ተመልከት) የሚለው የጳውሎስ አስተማማኝ ምስክርነት ነበር። የአንድ ሰው «የውስጥ ሰውነቱ» ዕለት በዕለት መንፈሳዊ ተሐድሶ እስካገኘ ድረስ፥ «የውጭው ሰውነቱ» ቢጠፋ ምን ችግር ያስከትልበታል? ጳውሎስ ይህንን በመናገሩ ሰውነት አስፈላጊ አይደለም ለማለት፥ ወይም የሰውነትን ማስጠንቀቂያዎችና መሻቶች · ማግለል እንዳለብን ማመልከቱ አልነበረም። ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቤተ-መቅደስ ስለ ሆነ፥ እንክብካቤ ልናደርግለት ይገባል፤ ዳሩ ግን የሰብዓዊ ተፈጥሮ ተፈጥሮአዊ ድክመት የሆኑትን አንዳንድ ባሕርያት ተቆጣጥረን ልናስወግዳቸው አንችልም። ጳውሎስ የዳነባቸውን ሥጋዊ መከራዎች ሁሉ ስንመለከት፥ እንደዚህ ብሉ መጻፉ አያስገርመንም። 

ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን፥ በአንድ ጊዜ አንድን ቀን መኖር አለብን። ምንም ያህል ስጦታ ወይም ሀብት ቢኖረው፥ ማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜ ሁለት ቀናትን አይኖርም። እግዚአብሔር ወደ እርሱ ስንጸልይ (ሉቃ. 11፡3)። «ዕለት-በዕለት» የሚያስፈልገንን ይሰጠናል። እርሱ ለየዕለቱ የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል (ዘዳ 33፡25)። እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ጸጋ የሚሰጠን በተፈለገው ጊዜ ስለ ሆነ (ዕብ 4፡16)፥ ምናልባት በወደፊት ለሚያጋጥመን ችግር ያገለግለናል በማለት «ጸጋውን ለማከማቸት» የመሞከር ስንፍናን ልንፈጽም አይገባም። በአንድ ጊዜ አንድን ቀን ብቻ መኖርን እስከ ተለማመድን በእግዚአብሔር እንክብካቤ ላይ የሚኖረን እርግጠኛነት፥ የሕይወታችንን ውጥረት ባመዛኙ ያስግደዋል። 

አንተም በክርስቶስ በማመን እስከ ተመላለስህ፥ መከራን በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት ይኖርሃል። እስቲ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17 ላይ ያቀረባቸውን ንጽጽሮች እንመልከት፡- ቀላል መከራ . ብዙ ክብር፤ ጊዜያዊ . ዘላለማዊ፤ ያደርግብናል – ያደርግልናል። ጳውሎስ በዘላለማዊ እሴቶች ላይ ተመርኩዞ ይጽፋል። ያሁኑን መከራ ከሚመጣው ክብር ጋር በማመዛዘን፥ መከራዎቹ ለጥቅሙ እንደ ሆኑ ይገነዘባል (ሮሜ 8፡ 18 ተመልከት)። 

የዚህን መመሪያ አሳብ በመሳት፥ ክርስቲያን ደስ እንዳለው ሊኖርና በመጨረሻው ሁሉም ነገር ወደ ክብር እንደሚለወጥለት ተስፋ ሊያደርግ ይችላል ብለን ማሰብ የለብንም። ጳውሎስ የሚጽፈው የእግዚአብሔርን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሚመጡ መከራዎች ነበር። እግዚአብሔር መከራን ወደ ክብር ሊለውጥ ይችላል – ይለውጣልም፤ ዳሩ ግን ኃጢአትን ወደ ክብር ሊለውጥ አይችልም። በኃጢአት ውስጥ ክብር ስለሌለ፥ ኃጢአት ፍርድን መቀበል አለበት። 

ሁለቱም ቁጥሮች ስለ እግዚአብሔር ልጅ መንፈሳዊ ተሐድሶ ስለሚናገሩ፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16 እና 3፡18 ሊዛመዱ ይገባል። መከራ በራሱ የተቀደስን ወንዶችና ሴቶች አያደርገንም። እንዲያውም ራሳችንን ለጌታ እስካልሰጠን፥ ወደ ቃሉ እስካልተመለከትንና እንደሚሠራ እስካልተማመን ድረስ፥ መከራችን የበለጠ የከፋን ክርስቲያኖች ሊያደርገን ይችላል። በራሴ የመጋቢነት አገልግሎት ውስጥ፥ አንዳንድ የእግዚአብሔር ሰዎች ግትርና መራራ በመሆን፥ «ከክብር – ወደ – ክብር» በመሻገር ፈንታ፥ «ከማጡ – ወደ – ድጡ» የወደቁበትን ሁኔታ ተመልክቻለሁ። በመሆኑም ጳውሎስ በቁጥር 13 ላይ የጠቀሰው «የእምነት መንፈስ» ያሻናል። 

4. የማይታየው ዓለም እውነተኛ ስለ መሆኑ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 4፡18)። ዶክተር ኤ. ደብልዩ. ቶዘር የተባሉት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው የማይታይ ዓለም ብቸኛው «እውነተኛ ዓለም» እንደ ሆነ ተናግረዋል። በዙርያችን የሚገኘውን ገሀዱን ዓለም እግዚአብሔር እንድንመለከተው በሚፈልገው ዓይነት ሁኔታ ብቻ እስከ ተመለከትነው፥ በውስጡ በሚገኘው በማንኛውም ነገር አንማረክም (1 ዮሐ.2፡15-17)። በዕብራውያን 11 ውስጥ የተጠቀሱት ታላላቅ የእምነት ሰዎች፥ ከዚያ ደረጃ የደረሱት «የማይታየውን እንደሚታይ አድርገው ስለ ተመለከቱ» ነው (ዕብ 11፡10፥ 13-14፥ 2)። 

የዚህን ዓለም ነገሮች ልናያቸውና ልንዳስሳቸው ስለምንችል፥ በጣም እውነተኛ ይመስላሉ። ዳሩ ግን ሁላቸውም ጊዜያዊና ለሕልፈት የተወሰኑ ናቸው። ለዘለቄታው የሚኖሩት የመንፈሳዊ ሕይወት ዘላለማዊ ነገሮች ብቻ ናቸው። እዚህ ላይ ማጤን ያለብን ይህን እውነት እጅግ በማስፋት፥ «ቁሳዊ» እና «መንፈሳዊ» ነገሮች እንደሚቃረኑ አድርገን ማሰብ እንደማይገባን ነው። ቁሳዊውን ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ ስንጠቀምበት ወደ መንፈሳዊነት ይለወጥና በሰማይ ያለው መዝገባችን አካል ይሆናል። (በምዕራፍ 8-9 በዚህ ጉዳይ ላይ በይበልጥ እናተኩራለን።) ለቁሳዊ ነገሮች ስፍራ የምንሰጠው፥ መንፈሳዊውን ነገር ለማሳደግ ሊረዳን ስለሚችል እንጂ፥ በራሱ ስለሚሰጠን ጥቅም አይደለም። 

ለመሆኑ የማይታዩትን ነገሮች እንዴት ልታያቸው ትችላለህ? የእግዚአብሔርን ቃል ስታነብ ሳለ በእምነት ልትመለከታቸው ትችላለህ። ክርስቶስን ወይም መንግሥተ-ሰማይን አይተን አናውቅም፤ ይሁንና የእግዚአብሔር ቃል ስለሚነግረን በእውነት እንዳሉ እናውቃለን። እምነት «የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው» (ዕብ 11፡1)። አብርሃም ሰማያዊቷን ከተማ ስለ ተመለከተ፥ ከሰዶም ተለየ፤ ዳሩ ግን ሉጥ በእምነት ሳይሆን በማየት ስለ ተመላለሰ፥ ሰዶምን መረጠ (ዕብ. 11፡10፤ ዘፍ. 13)። 

በርግጥ፥ ደኅንነትን ያላገኘው ዓለም እኛን የተለየንና የማንረባ ሰዎች እንደ ሆንን አድርጎ ይቆጥረናል፤ ምናልባትም እብዶች እንደ ሆንንም ጭምር ሊያስብ ይችላል – ይኸውም በማይታየው ዓለም መንፈሳዊ በረከት እውነታ ስለምናምን ነው። ይሁንና የክርስቲያኖች እርካታ ሕይወታቸውን በዘላለማዊ እሴቶች መምራት እንጂ፥ ጊዜያዊ ነገሮችን መከተል አይደለም። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: