አስተውሎት (1ኛ ቆሮ. 14፡6-25)

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ማስተዋል የሚለውን ቃል ስምንት ጊዜ ተጠቅሞአል። አንድ አገልጋይ ለሕዝቡ መረጃን ማስፈሩ ብቻ በቂ አይሆንም፤ እንዲጠቅማቸው ካስፈለገ መቀበል አለባቸው። ፍሬን የሚያፈራው ዘር በመልካም አፈር ተቀባይነትን ያገኘው ነው። ይህ ማለት ለእግዚአብሔር ቃል እስተውሎት ሊኖር ይገባል ማለት ነው (ማቴ. 13፡23)። አንዱ አማኝ መታነጽ ከፈለኝ ቃሉን ለመቀበል ልቡን ማዘጋጀት አለበት (1ኛ ተሰ. 2፡13)። የሚያደምጥ ሁሉ ይሰማል ማለት አይደለም። 

ታዋቂው የጉባኤ አገልጋይ፥ ዶክተር ዮሴፍ ፓርከር፥ በአንድ ታላቅ ስብሰባ ሰብከው ካበቁ በኋላ፥ አንድ ሰው ቀርቦ በስብከቱ ውስጥ ስላነሡት አነስተኛ ነጥብ ሂስ አቀረበባቸው። ፓርከር በትዕግሥት የሰውየውን ሂስ ሰምተው ሲጨርሱ፥ «ከመልእክቱ ሌላ ያገኘኸውስ፥ የለም?» አሉና ጠየቁት። ይህ አባባል ሂሰኛውን ሰው ቅስሙን ስለሰበረው ምንም ሳይናገር ወደ ጉባኤው ተመልሶ ሄደ። ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል እኛን እንዲፈርደን ከመፍቀድ ይልቅ ስብከቱን ለመፍረድ እንቸኩላለን። 

ምሳሌ (14፡6-11)። የሚያንጽ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲኖር ከተፈለገ አስተውሎት መኖር እንዳለበት ለማመልከት ጳውሎስ ሦስት ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቀመ። እነዚህም የሙዚቃ መሣሪያዎች፥ ለጦርነት የሚነፋ የመለከት ጥሪ እና ዕለታዊ የእርስ በርስ ንግግር ናቸው። 

የሙዚቃ መሣሪያ ግልጽ እና የተለየ ድምፅ ካልሰጠ፥ ሙዚቃውን ማንም ሊያውቅ አይችልም። አንድ መሣሪያ ተጫዋች መሣሪያው በመበላሸቱ ወይም በደንብ ባለመቃኘቱ ትክክለኛውን የዜማ ለዛ ማሰማት ሲሳነው ምን እንደሚሰማው ሁሉም ሰው ያውቀዋል። ትልልቅ የቧንቧ ኦርጋኖች ዘወትር ሰርቪስ መደረግ አለባቸው፤ አለበለዚያ መቃው በትክክል መሥራት ይሳነዋል። እንድ ምሽት በአንድ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን አገልግሎት ተካፍዬ ነበር። በአካባቢው አየር ለውጥ የተነሣ የኦርጋኑ ቃና ቀስ በቀስ እየተለወጠ ሲሄድ አስተዋልሁ። አገልግሎቱ ሊያበቃ አካባቢ ለውጡ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ እርጋኑ እና ፒያኖው ከነጭራሹ መጣጣም አቃታቸው። 

መለከተኛው (መለከት ነፊው) «አፈግፍግ» ወይም «ገሥግሥ!» የሚሉ ጥሪዎችን ስለማስተላለፉ እርግጠኛ ካልሆነና ወታደሮችም እርግጠኞች ካልሆኑ በስተቀር የሚያደርጉትን አያውቁም። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ግማሾቹ ወደ ፊት ግማሾቹ ወደ ኋላ ነው የሚሮጡት። የሚስተዋል መሆን እንዲችል ጥሪው ግልጽ መሆን አለበት። 

ይህ ነጥብ በዕለታዊ ንግግር ውስጥም የሚሠራ እውነት ነው። ባለቤቴና እኔ ታላቋን ብሪታኒያን የጎበኘንበት የመጀመሪያ ጊዜ ትዝ ይለኛል። በወቅቱ ብዙ የተለያዩ ቀበሌኛ ቋንቋዎች ገጥመውን ነበር። በሎንዶን አንድ በጣም ተግባቢ የሆነ ሰው አግኝተን አቅጣጫ ጠየቅነው። እውነቱን ለመናገር ምን እንዳለ የሰማነው በጣም ጥቂቱን ነበር። (ምናልባት እርሱም እኛን ለመረዳት ሳይቸገር አልቀረም!) 

ጳውሎስ ስለ ልሳኖች በጻፈ ጊዜ፥ ስለታወቁ ቋንቋዎች እንጂ ስለ «ሰማያዊ» ቋንቋዎች ላለማመልከቱ ቁጥር 10 ጥሩ ማሳመኛ ምክንያት ይሰጠናል። እያንዳንዱ ቋንቋ ልዩ እና የራሱ ትርጉም ያለው ነው። አንዱ ተናጋሪ የቱንም ያህል ትሑት ይሁን ቋንቋውን ካልተረዳሁለት፥ ከእኔ ጋር ልንግባባ አንችልም። ለግሪኮች ባርቤሪያን (ጨካኝ መሐይም ሰው) ማለት በማኅበራዊ ወይም በብሔራዊ ደረጃ ዝቅተኛው ሰው ማለት ነበር። እንዲያውም፥ ግሪክ ያልነበሩ ሁሉ ባርቤሪያን ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። 

ሙዚቀኛው፥ መለከተኛው፥ እና የዕለት ተዕለት ተናጋሪው መልእክቶቻቸው ለሰሚው ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ካልተላለፉ አስተውሎትን ሊያገኙ አይችሉም። የአስተውሎትን መርህ በምሳሌ ካሳየ በኋላ፥ ጳውሎስ ከሦስት የተለያዩ ሰዎች ጋር ያዛምደዋል። 

ተዛምዶ (14፡12-25)። ጳውሎስ በመጀመሪያ የአስተውሎትን መርህ ለተናጋሪው ለራሱ አዛመደው (ቁ. 12-15)። የሆነ ዓይነት ግላዊ «መንፈሳዊ ደስታን» ከመለማመድ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን በረከት መሆን እንደሚሻል ጳውሎስ ቆሮንቶሳውያንን እንደገና አሳሰባቸው። እማኝ በልሳን ሲናገር፥ መንፈሱ (ውስጣዊ ሰውነቱ) የልምምዱ ተካፋይ ቢሆንም፥ አእምሮው ግን የልምምዱ ተካፋይ አይደለም። «በመንፈስ» መጸለይ ወይም መዘመር ስሕተት አይደለም፤ ነገር ግን እእምሮንም በመጨመር የምትጸልየውንም ሆነ የምትዘምረውን ማስተዋሉ ይሻላል። (ከቁጥር 14-15 ባለው ክፍል መንፈስ ተብሎ የተጠቀሰው ቃል መንፈስ ቅዱስ ማለት ሳይሆን በ 2፡11 ላይ እንዳለው ውስጣዊው ሰው ማለት መሆኑን ልብ በል። ተናጋሪው እንዲታነጽበት ከተፈለገ፥ የሚናገረውን ማስተዋል አለበት። 

ታዲያ ተናጋሪው ምን ማድረግ ይገባዋል? መልእክቱ እንዲተረጎምለት እግዚአብሔርን መጠየቅ አለበት። ጳውሎስ እዚህ ላይ እውነት እድርጎ የወሰደው ተርጓሚ እንደሚገኝ (ቁ 27-28) ወይም ተናጋሪው ራሱ የመተርጎም ስጦታ እንደሚኖረው ነው። በእርግጥ ይህ ሁሉ ሐተታ እንደገና አጽንኦት የሚሰጠው ትንቢት ከልሳኖች በላይ መሆኑን ነው። ትንቢት ትርጉም ስለማያስፈልገው ለሁሉም ሰው በረከት ነው። 

ጳውሎስ ከዚያ በኋላ መርሁን በጉባኤው ላሉ ሌሎች አማኞች አዛመደ (16–20)። መልእክቱን ሰምተው ምላሽ እንደሚሰጡም አሰበ። ነገር ግን መልእክቱን ካላስተዋሉት፥ እንዴት ምላሽ ይስጡ? (በዚያን ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሜን! ማለት ስሕተት ተደርጎ አይቆጠርም ነበር።) «ያልተማረው» ሰው ምናልባት አዲስ ክርስቲያን፥ ወይም ጉጉት ያደረበት «ፈላጊ» ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የሚነገረውን ካላስተዋለ በቀር ሊታነጽበት የሚችል አልነበረም። 

እንደገና ጉዳዩ የቅደም ተከተል ነበር። ጳውሎስ የልሳኖችን አገልግሎት ባይቃወምም፥ ትክክለኛ እይታ እንዲያገኝ ጥረት አደረገ። ተፈላጊው ጉዳይ የቃላት ብዛት ሳይሆን፥ ነገር ግን የንግግር ጥራት ነበር። ቆሮንቶሳውያን በአሻንጉሊት እንደሚጫወቱ ልጆች ነበሩ። ጳውሎስ ኃጢአት በማወቅ ጉዳይ «ሕፃናት»፥ መንፈሳዊ አስተውሎትን በተመለከተ በሳል ሰዎች እንዲሆኑ ፈለገ (3፡1-4፤ 13፡11-13)። 

አንዳንድ ሰዎች በልሳኖች መናገር የመንፈሳዊ ብስለት ማረጋገጫ ነው የሚል አሳብ አላቸው። ነገር ግን ጳውሎስ ይህን ስጦታ መንፈሳዊ ባልሆነ ና ብስለት በጎደለው ሁኔታ መለማመድ እንደሚቻልም አስተማረ። 

የጳውሎስ የመጨረሻው ተዛምዶ በአምልኮ ጊዜ ወደ ጉባኤ ከመጣ ያልዳነ ሰው ጋር ነበር (ቁ. 21-25)። ጳውሎስ እዚህም ላይ ከልሳኖች ይልቅ የትንቢትን የበላይነት የሚገልጽ ሌላ ነጥብ ሰጠ። በልሳኖች የተነገረ መልእክት (ካልተተረጎመ) ለጠፋ ኃጢአተኛ ሰው ልብ ፈጽሞ ወቀሳን ሊያመጣ የሚችል አለመሆኑ ነበር። እንዲያውም፥ ያልዳነው ሰው መላው ጉባኤ አብዲል በማለት የልሳኖች ትርጉም ከመሰጠቱ አስቀድሞ ስብሰባውን አቋርጦ እንዲወጣ የሚያስችል ነበር። በጴንጤቆስጤ ቀንም ሆነ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ልሳኖች ለወንጌል አገልግሎት ጥቅም ላይ አልዋሉም። 

ይሁንና፥ ልሳኖች በተለይ ለጠፉት አይሁዶች መልእክት ነበራቸው። ይኸውም ልሳኖች የእግዚአብሔር ፍርድ ምልክት ነበሩ። ጳውሎስ ኢሳይያስ 28፡11-12ን በመጥቀስ አይሁድ በማይገባቸው ባዕድ አፍ የሚናገሩ ወራሪ አዎ ርያውያን እንደሚመጡ የተነገረውን አመለከተ። የዚህ ልሳን በመካከላቸው መገኘት በሕዝቡ ላይ ለሰፈነው የእግዚአብሔር ፍርድ ማረጋገጫ ነበር። እግዚአብሔር በሚገባቸው ግልጽ ቋንቋ ለሕዝቡ መናገር ፈቃዱ ነበር፤ ነገር ግን የተደጋገመው ኃጢአታቸው ይህ እንዳይሆን አገደው። በመልእክተኞቹ አማካኝነት በገዛ ቋንቋቸው ተናግሮ ነበር፤ ሆኖም ግን ሕዝቡ ንስሐ አልገቡም። በዚህ ጊዜ በባዕድ ልሳን መናገር ግድ ሆነበት፤ ያ ደግሞ ፍርድ ነበር። 

የአይሁድ ሕዝብ ሁልጊዜ ምልክትን ይሹ ነበር (ማቴ. 12፡38፤ 1ኛ ቆሮ. 1፡22)። በጴንጠቆስጤ ቀን፥ ሐዋርያት በልሳኖች መናገራቸው በዚያ በዓላቸውን ያከብሩ ለነበሩ የማያምኑ አይሁዶች ምልክት ነበር። የልሳኖች ተአምር ፍላጎቶቻቸውን ቢቀሰቅስም፥ ነገር ግን ልቦቻቸውን አልወቀሰም። ለወቀሳ እና ለመለወጥ ደረጃ ለማድረስ የጴጥሮስን ስብከት (ሁሉም ሰው በሚገባው አረማይክ ቋንቋ) ጠይቋል። 

የማነጽ መርህ ቤተ ክርስቲያን ትጠነክር እና ታድግ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ማካፈሉ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። የአስተውሎት መርህ የምናካፍለው መልእክት ጥቅም ያስገኝ ዘንድ ግልጽ መሆን እንዳለበት ያሳስበናል። የመንፈስ ስጦታዎችን በግል መጠቀሙ ተጠቃሚውን ቢያንጽም፥ ቤተ ክርስቲያንን እያንጽም፤ በመሆኑም ጳውሎስ «ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ» በማለት ይመክረናል (14፡12)። 

ሆኖም ግን ሦስተኛው መርህ፥ የሥርዓት መርህ በተግባር ላይ መዋል አለበት።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: