አስጠነቀቃቸው (2ኛ ቆሮ. 13፡1-8)

ጳውሎስ ደብዳቤውን ለመዝጋት በሚቃረብበት ወቅት፥ ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረው ታላቅ ፍቅር አንድ የመጨረሻ ልመና እንዲያቀርብ ገፋፋው። በቤተ ክርስቲያናቸው የሚያደርገው ሦስተኛው ጉብኝቱ ለእርሱም ሆነ ለእነርሱ የሚያሳዝን ነገር እንዲሆን አልፈለገም ነበር። ለእነርሱ ልቡን ከፍቶላቸዋል፤ ስለ አገልግሉቱ ማብራርያ ሰጥቶአቸዋል፤ ለነቀፋዎቻቸው ምላሽ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቃል እንዲገዙና ጌታን እንዲታዘዙም ገፋፍቶአቸዋል። እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ሊያደርግ ወይስ ምን ሊል ይችል ነበር? 

በዚህ በደብዳቤው መዝጊያ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን ወደ መታዘዝና መገዛት ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት፥ በሦስት የአቀራረብ ዘዴዎች ተጠቅሟል። 

አሳፈራቸው (2ኛ ቆሮ. 12:11-21) ልጆች በነበርን ጊዜ፥ ከወላጅም ይሁን ከጎረቤት«ኀፍረት አይሰማህም!» የሚል ቃል ሲሰነዘርብን፥ ስንት ጊዜ ሰምተን ይሆን? ሰዎች ስለ ክፉ ነገራቸው ወይም አመለካከታቸው ማፈራቸው መልካም ነው። አንድ ጥፋተኛ ሰው የኀፍረት ስሜት የማይሰማው ከሆነ፥ ደንዳና ልብና የደነዘዘ ሕሊና እንዳለው ይታወቃል። «ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፤ እፍረትንም አላወቁም» (ኤር. 6፡15)። 

በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች ሊያመሰግኑት ባለመፈለጋቸው በመውቀስ ያሳፍራቸዋል (2ኛ ቆሮ. 12፡11-13)። እርሱን ለትምክህት ከመገፋፋት ይልቅ፥ ስለ እርሱ በትምክህት ሊናገሩ ይገባቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ግን፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ተወዳጅነትን አትርፈው ቤተ ክርስቲያናቸውን በመቆጣጠር ላይ ስለነበሩት «ምጡቅ-ሐዋርያት»፥ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በትምክህት ይናገሩ ነበር። 

ጳውሎስ ከእነዚህ ሰዎች ያንስ ነበር? በምንም ዓይነት! የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስን በተግባር አይተውታል፤ እንዲያውም፥ ነፍሳቸውን ጭምር ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የመራላቸው ባለውለታቸው ነበር። በመካከላቸውም ሐዋርያነቱን የሚያረጋግጡ ተአምራዊ ነገሮችን አድርጎ ነበር (ዕብ. 2፡1-4)። ውጫዊ ስደትንና ውስጣዊ ችግሮችን ተጋፍጦ፥ በቆሮንቶስ ውስጥ በአገልግሎቱ ጸንቶ ነበር። ከቤተ ክርስቲያኗ ምንም ነገር አልወሰደም ነበር። ጳውሎስ አሁንም «በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን ከመቅረቴ በቀር፥ ከሌሎች አብያተ-ክርስቲያናት እናንተን ያሳነስሁአችሁ በምንድነው? ይህም ጥፋት ሆኖ ከተቆጠረ ይቅር በሉኝ» (2ኛ ቆሮ. 12፡13 – አዲስ ትርጉም) በማለት በረቀቀ ቅኔአዊ አነጋገር ተጠቅሟል። 

ከክርስትና ሕይወት አደጋዎች አንዱ፥ በረከቶቻችንን እንደ ልማዳዊ ነገሮች አድርገን መውሰዳችን ነው። ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያደረበት መጋቢ ወይም የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ ብዙ ነገር ሊያደርግልን ይችላል፤ እኛ ግን እንደ ተራ ነገር እንቆጥረዋለን። (ላለማዳላት፥ አንዳንድ ጊዜ መጋቢዎች የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በረከቶችን እንደ ተራ ነገር ቆጥረው እንዲቀበሉ በማድረጉ በኩል ጥፋት እንዳለባቸው ለመግለጽ እወዳለሁ።) በዚህ ዝንባሌ በመመራት ካለፃመስገናቸው የተነሣ ጳውሎስ ሲያሳፍራቸው እናያለን (ቁ 14-18)። 

ይህን የመሳሰሉ ችግሮች ቢኖሩም ቅሉ፥ ጳውሎስ ግን የቆሮንቶስን ሰዎች በመጎብኘት ታማኝ ነበር፤ እናም አሁን ሦስተኛውን ጉብኝት ሊያደርግ ነበር (13፡1 ተመልከት)። በማመስገን ፈንታ፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስስ ዕቅዱን በመቀየሩ ወቀሱት። ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ምንም ድጋፍ አላገኘም ነበር፤ ይልቁንም፥ ለቤተ ክርስቲያን በመሥዋዕትነት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ እነርሱ ደግሞ ከሌሎች ጋር በመካፈል አመስጋኝነታቸውን ለማሳየት ፈቃደኞች አልነበሩም። ጳውሎስ ይበልጥ ሲወዳቸው፥ እነርሱ ደግሞ ባነሰ ሁኔታ የሚወዱት ይመስል ነበር። ለምን? ምክንያቱም ለክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር አልነበራቸውምና ነው (ቁ. 13)። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለመርዳት ያለውን ነገር ለማካፈል ይፈልግ ነበር። 

የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ቤተ ክርስቲያንን ለመበዝበዝ የማታለያ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር (4፡2 ተመልከት)፤ ዳሩ ግን ጳውሎስ ግልጽና ከአታላይነት የራቀ ነበር። ጳውሎስ የፈጸመው ብቸኛው «በደል» ከእነርሱ የገንዘብ ድጋፍ አለመቀበሉ ነበር። በዚህ ትጥቃቸውን ስላስፈታቸው፥ ገንዘብ ብቻ እንደሚፈልግ አድርገው ለሚያቀርቡት ክስ ምንም ምላሽ ሊሰጡ አይችሉም ነበር። ከእርሱ ጋር አብረው ከሚያገለግሉት ጳውሎስ የላካቸው ሰዎችም ቢሆኑ፥ አንዳቸውም በምንም መንገድ አልበዘበዙዋቸውም ወይም መጠቀሚያ አላደረጉዋቸውም ነበር። 

ልጆች ወላጆቻቸው ለሚያደርጉላቸው በጎ ነገር ሳያመሰግኑ ሲቀሩ እጅጉን ያሳዝናል። እንዲሁም ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች «መንፈሳዊ ወላጆቻቸው» ለሚያደርጉላቸው ነገሮች ባለውለታነታቸውን ሲዘነጉ አሳዛኝ ይሆናል። ለዚህ ለምስጋና እጦት መነሻው ምንድነው? ጳውሎስ በቀጣዩ አንቀጽ ውስጥ ገልጾታል – የቅድስና መታጣት (ቁ. 19-21)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የከፉ ኃጢአቶች ነበሩና ጳውሎስ ለጉብኝት ከመምጣቱ በፊት ፍርድ ተሰጥቶባቸው እንዲወገዱ ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን የአሁኑም ጉብኝቱ በሌላ አሳዛኝ ልምምድ ይቋጫል። 

ምናልባትም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት፥ «ጳውሎስ ዳግም ሊጎበኘን ከመጣ፥ ተጨማሪ ችግሮችን ይፈጥርብናል» ብለው እየተናገሩ ይሆናል። ጳውሎስ መሻቱ ችግሮችን መቅረፍና አብያተ ክርስቲያናትን ማጠናከር እንደ ሆነ በግልጽ ይናገራል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ኃጢአቶች ለማስወገድ በታማኝነት መጋፈጥንና ድፍረትን ይሻሉ። «አለባብሶ ማረሱ» ግን፥ የበለጠ ለክፋት ይዳርጋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ኃጢአት በሰው ሰውነት ውስጥ እንዳለ ካንሰር ነው .ተቆርጦ መውጣት አለበት። 

እስኪ ቤተ ክርስቲያኒቱ የወደቀችባቸውን ኃጢአቶች እናስብ – በመናዘዝና ንስሐ በመግባት ሊወገዱ የሚገባቸው ኃጢአቶች። እርስ በርሳቸው ስለሚመቀኛኙ ይጣሉ (ይከራከሩ) ነበር። ገንፍሎ የሚወጣ ቁጣም ነበረባቸው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥጋዊ ሤራዎችን፥ አድመኛነትንና ሐሜትን ያስፋፉ ነበር። ይህም ሁሉ ከትዕቢትና የራስን አስፈላጊነት ከፍ አድርጎ ከመመልከት የመነጨ ሲሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከትን አስከትሏል (2ኛ ቆሮ. 12፡20)። ይህንን የኃጢአቶች ዝርዝር ከ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ጋር ብናወዳድር፥ በማኅበረ-ምዕመናኑ መካከል የፍቅር መተሳሰብ እንዳልነበረ እንመለከታለን። 

ከእነዚህ «የመንፈስ ኃጢአቶች» ጎን (7፡1)፥ ታላላቅ የሥጋ ኃጢአቶችም ነበሩ- ዝሙትና ፍትወት። ጳውሎስ ስለ እነዚህ ኃጢአቶች በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5-6 ውስጥ ገልጾአል፤ ዳሩ ግን አንዳንድ ጥፋተኞች ባለመታዘዛቸው ጸንተው ነበር። ለአዲሱ ሕይወት ራሳቸውን ከመስጠት ይልቅ፥ አሮጌው ሕይወታቸው ዳግመኛ በላያቸው ላይ ግዛቱን እንዲያስፋፋ ይፈቅዱለት ነበር(1ኛ ቆሮ. 6፡9-10። 

ጳውሎስ ለዚህ ለሦስተኛው ጉብኝት ብዙም አልጓጓም ነበር። ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈልጋት ሳትሆን ቀርታ ላለማየት ከመሥጋቱም፥ እርሱም እንደሚፈልጉት ሆኖ ሳይገኝ እንዳይቀር ፈርቶ ነበር። ይሁን እንጂ፥ ምንም እንኳ በሁኔታው ማፈሩና ማዘኑ ባይቀርም (የቃሉ ትርጉም «ለሞተ ሰው ዘን»ን ያመለክታል)፥ ዳሩ ግን ነገሮችን የተቃና ለፃድረግ አሁንም በሥልጣኑ እንደሚጠቀም ቃል ይገባላቸዋል። ለእነርሱ የነበረው ፍቅር እጅግ ታላቅ በመሆኑ፥ እነዚህን ችግሮች ችላ በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዳከማቸውን እንዲቀጥሉ ሊፈቅድላቸው አይሻም ነበር። 

የቆሮንቶስ ሰዎች ማፈር ሲገባቸው ሳለ፥ እነርሱ ግን አላፈሩም ነበር። ጳውሎስ መልእክቱን በትክክል ማስተላለፉን ለማረጋገጥ ሲል፥ ቀጥሎ በምንመለከተው ሁለተኛው የአቀራረብ ዘዴ ይጠቀማል። 

አስጠነቀቃቸው (2ኛ ቆሮ. 13፡1-8) 

በዚህ ስፍራ ሁለት ማስጠንቀቂያዎች ቀርበዋል። 

«ራሳችሁን አዘጋጁ» (2ኛ ቆሮ. 13፡1-4)። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአትን ለማስወገድ በምንጣጣርበት ጊዜ፥ የምንመራው በሐሜቶች ሳይሆን በሐቆች መሆን አለበት። ጳውሎስ ዘዳግም 19፡15ን የጠቀሰ ሲሆን፥ ተመሳሳይ አሳብ ያላቸውን ምንባቦች ከዘኁልቁ 35፡30 እና ከማቴዎስ 18፡16፥ እንዲሁም ከ1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡19 ላይ እናገኛለን። በተለይ የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እርስ በርሳችው በማይስማሙበት ጊዜ የምስክሮች መኖር የነገሩን እውነትነት ለማረጋገጥ ይረዳል። 

የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ኢየሱስ በማቴዎስ 18፡15-20 የሰጣቸውን ትዕዛዛት ቢከተሉ ኖሮ፥ ራሳቸው ብዙዎቹን ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይችሉ ነበር። አማኞች የጌታችንን ትዕዛዛት ባለማክበራቸው ምክንያት ብቻ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አናሳ አለመግባባቶች ወደገዘፉና የተወሳሰቡ ችግሮች ሲሸጋገሩ ተመልክቻለሁ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦች በእውነተኛነት መፍትሔ እስካልፈለጉ ድረስ፥ መጋቢውና ማህበረ-ምዕመናኑ ጣልቃ መግባት የለባቸውም። 

የአይሁድ መምሕራን ጳውሎስን ደካማ ነው በማለት ከሰውታል (2ኛ ቆሮ. 10፡7-11 ተመልከት)። የጳውሎስ አገልግሉት የውሃትና ገርነት የሚታይበት ሲሆን (1፡24 ተመልከት)፥ የእነርሱ ግን ጠንካራና አምባገነናዊ ነበር። አሁን ግን ጳውሎስ እንዴት ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል እንደሚያሳያቸው ያረጋግጥላቸዋል – ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስፈልገው ይኸው ከሆነ። ማስጠንቀቂያውም፥ «አልራራላችሁም!» የሚል ነበር። የተጠቀመውም «በጦርነት ውስጥ መራራት» ን የሚያመለክት ቃል ነው። ባጭሩ፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣን በሚቃወም በማንኛውም ሰው ላይ ጦርነት እያወጀ ነበር። 

ባላንጣዎቹ፥ «እስኪ ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ መሆኑን ያረጋግጥ» ብለው ነበር። የጳውሎስም ምላሽ፥ «የደከምሁ በምመስልበት ወቅት፥ እኔም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርቱ ነኝ» የሚል ነበር። በመስቀል ላይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደካማነትን አሳይቷል፤ ይሁንና መስቀሉ አሁንም «የእግዚአብሔር ኃይል» ነው (1ኛ ቆሮ. 1፡18)። ጳውሎስ ቀደም ብሎ የመንፈሳዊ ውጊያውን ዘዴ የገለጸ ሲሆን (2ኛ ቆሮ. 10፡1-6)፥ አንባቢዎቹም ነገሮችን ላይ ላዩን በመመልከት ምትክ በጥልቀት እንዲያጤኑ አስጠንቅቋቸዋል። 

በዓለም መመዘኛ መሠረት፥ ጳውሎስና ኢየሱስ ሁለቱም ደካሞች ነበሩ፤ ዳሩ ግን በጌታ መመዘኛ መሠረት፥ ሁለቱም ብርቱዎች ነበሩ። ለምሳሌ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሥነ-ሥርዓት ጉዳዮችን ፈር በሚያስይዝበት ጊዜ፥ መቼ «መድከም» እና መቼ «መበርታት» እንዳለበት የሚያውቅ ሰው አዋቂና በሳል አገልጋይ ነው። 

አሁን በሞት ተለይቶ ወደ ጌታ የሄደ አንድ መጋቢ ወዳጄ፥ በምድረክ ላይ በሚቆምበት ጊዜ ዝግ ያለ ባሕርይ ነበረው፤ በግል አገልግሎቱም ቢሆን አቀራረቡ ይኸው ነበር። እናም አንዲት እንግዳ ሴት፥ ስብከቱን ሰምታ ስታበቃ፥ «ስብከቱን የሚጀምርበትን ጊዜ እየተጠባበቅሁ ነበር» እስከ ማለት ደርሳለች። ግን ለምን? ምክንያቱም እርሷ የተላመደችው ብርሃን ከሚያንጸባርቅ ይልቅ፥ ሙቀት ከሚፈጥር የጋለ የስብከት ድምፅ ጋር በመሆኑ ነው። ይሁንና ወዳጄ ለአገልግሎት እውነተኛዎቹ መመዘኛዎች የትኞቹ እንደ ነበሩ ስለሚያውቅ፥ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ችሏል። «በክርስቶስ» እንዴት «መድከም» እና «መበርታታ» እንደሚገባ ያውቅ ነበር። 

ዛሬ ሰዎች አገልግሎትን እንዴት ይለካሉ? በኃይለኛ የንግግር ችሎት ወይስ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት? በክርስቲያናዊ ባሕርይ ወይስ ሰዎችና ጋዜጦች በሚያናፍሱት ወሬ? እጅግ በርካታ ክርስቲያኖች አገልግሎቶችን በሚለኩበት ጊዜ የዓለምን መመዘኛዎች ይከተላሉ። ሆኖም ግን ለእግዚአብሔር መመዘኛዎች ብቻ ትኩረት ሊሰጡ በተገባ ነበር። 

«ራሳችሁን መርምሩ!» (2ኛ ቆሮ. 13፡5-8)። ይህ አንቀጽ ጳውሎስ በቁጥር 3 ላይ ማስረጃ ላለው ቃል በማብራሪያነት የሚያገለግል ነው። ጳውሎስ፥ «እኔን ስትመረምሩኝ ነበር፤ ዳሩ ግን ለምን ራሳችሁን ለመመርመር ጊዜ አትወስዱም?» በማለት ይጽፋል። እኔም ብሆን ከግል የአገልግሎት ልምዴ የተረዳሁት፥ ሌሎችን ለመመርመርና ላመኮነን የሚፈጥኑ ሰዎች፡ ራሳቸው በከፋ ኃጢአት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን ነው። በርግጥ፥ ራስን የተሻለ አድርጎ ለማቅረብ አንድኛው አማራጭ ሌላውን ሰው መኮነን ነው። 

በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ልባቸውን እንዲመረምሩና በርግጥ ዳግም ተወልደው፥ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ሆነው እንደ ሆነ ይመለከቱ ዘንድ ይነግራቸዋል፤ በልባችሁ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስክርነት አለ? (ሮሜ 8፡9፥ 16)። ወንድሞችን ትወዳላችሁ? (1ኛ ዮሐ 3፡14)። ጽድቅን ታደርጋላችሁ? (1ኛ ዮሐ. 2፡29፤ 3፡9)። ዓለምን አሸንፋችሁ፥ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለበትን የመለየት ሕይወት ትኖራላችሁ? (1ኛ ዮሐ 5፡14)። እዚህ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለማረጋገጥ፥ ከሕይወታችን ጋር ከምናዛምዳቸው በርካታ መመዘኛዎች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ 

በመጋቢነት ካገለገልኋቸው አብያተ ክርስቲያን በአንድኛው ውስጥ፥ በወጣቶች ቡድን የታቀፈና ችግር ጠንሳሽ የሆነ አንድ ልጅ 

ነበር። ስጦታ ያለው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችና የቤተ ክርስቲያን አባል ቢሆንም፥ ዳሩ ግን ችግር እየፈጠረ አስቸግሮን ነበር። በአንድ የክረምት ዕረፍት ወቅት፥ ይህ ልጅ ቤተ ክርስቲያናችን የወጣቶች ቡድን አባላት ጋር ሔዶ ስለ ነበረ በዚያኑ አጋጣሚ፥ የወጣቶች መሪዎች፥ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና እኔም ጭምር ለዚህ ልጅ በየቀኑ ለመጸለይ ተስማማን። ከዚያም በአንድ ስብሰባ ላይ ቆሞ፥ በዚያ ጸሎት ባደረግንለት ሳምንት ውስጥ ደኅንነትን እንዳገኘ መሰከረልን። እስከዚያን ጊዜ ድረስ የነበረው ክርስቲያናዊ ምስክርነት የማስመሰል ነበር። በሕይወቱ ግሩም ለውጥ ተፈጸመና ዛሬ ጌታን በታማኝነት እያገለገለ ይገኛል። 

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙዎቹ ችግሮች ድነናል በሚሉና ጻሩ ግን ከቶውንም ንስሐ ገብተው በኢየሱስ ክርስቶስ ባላመኑ ሰዎች መፈጠራቸው አይጠረጠርም። ዛሬ የእኛም አብያተ ክርስቲያናት በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች የተሞሉ ናቸው። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች የማይበቁ ይላቸዋል – ይህም «አስመሳዮች፥ ተፈትነው የማያልፉ» ማለት ነው። ጳውሎስ ለአንድ ሰው እንደ ዳነና ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደሚሄድ ልናረጋግጥለት እንደሚገባ በማጉላት፥ ይህንኑ ቃል በ2ኛ ቆሮንቶስ 13፡6-7 ውስጥ በድጋሚ ጠቅሷል (1ኛ ዮሐ 5፡11-13 ተመልከት)። 

በቁጥር 7 ውስጥ፥ ጳውሎስ የራሱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ብቻ ሲባል፥ የቆሮንቶስ ሰዎች በፈተናው እንዲወድቁ አለመፈለጉን ግልጽ አድርጓል። ስለ እነርሱ በትምክህት ለመናገር ይችል ዘንድ ብቻ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለበትን ሕይወት እንዲኖሩ አልፈለገም ነበር። ጌታን እስከታዘዙ ጊዜ ድረስ፥ ለእነረሱ ብሎ ስለ መናቁና ስለ መሰደቡ ግድ አልነበረውም። ጌታ ልቡን ስለሚያውቅ፥ እርሱ የተጨነቀው ስለ ራሱ የስም መጉደፍ ሳይሆን፥ ስለ እነርሱ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ነበር። 

ከሁሉም የሚበልጠው አስፈላጊ ነገር የወንጌሉ እውነታና የእግዚአብሔር ቃል ነው (ቁ. 8)። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ እውነትን መቃወም ወይም ማገድ እንደማይቻል አይገልጽም . ስለ ምን እነዚህ ነገሮች በጊዘው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተፈጸሙ ነበርና! እርሱና ተባባሪዎቹ ግን፥ የመጣው ቢመጣ እውነት እንዲያሸንፍ፥ እውነት እንዲስፋፋ ወስነው ነበር እንጂ፥ እውነትን ለማገድ አልፈለጉም ነበር። በመጨረሻው ጸንቶ የሚኖረው የእግዚአብሔር እውነት ሆኖ ሳለ፥ ሰዎች ግን ይህንን ለምን ለመቃወም ይሞክራሉ? «ጥበብ ወይም ማስተዋል ወይም ምክር በእግዚአብሔር ላይ የለም» (ምሳሌ 21፡30)።

Leave a Reply

%d