አጽናናቸው (2ኛ ቆሮ. 13፡9-14)

በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ለእነርሱ ባቀረበው ጸሎት የቆሮንቶስን ሰዎች ያጽናናል (ቁ 9)። «ኪንግ ጄምስ ቨዥን» በሚባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ «እንመኛለን» ተብሎ የተተረጎመው ቃል፥ በአማርኛ መጽሐፋችን ውስጥ «እንጸልያለን» ተብሉ ተጽፎአል። ጳውሎስ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ ጸልዮአል፤ ይህም ኃጢአት የሌለበት ፍጹምነት ሳይሆን፥ «መንፈሳዊ ብስለት» ነበር። ይህ ቃል በግሪኩ፥ «ብቁ መሆን፥ መታጠቅ» የሚሉት ቃላት ወገን ነው። የሕክምና ቃል እንደ መሆኑ፥ «የተሰበረ አጥንት መጠገን፥ ተጠምዝዞ የዞረውን እግር ወይም እጅ ማስተካከል» ማለት ነው። እንዲሁም ደግሞ፥ «አንድን መርከብ ለጉዞ ብቁ ማድረግ» እና «ሠራዊትን ለጦርነት ማስታጠቅ» የሚሉ ትርጉሞች ይኖሩታል። በማቴዎስ 4፡21 ላይ «መረብ ማበጀት» ተብሎ ተተርጉሞአል። 

ከሙታን ከተነሣው ከጌታችን አገልግሎቶች አንዱ ሕዝቡን ፍጹም በማድረግ ማዘጋጀት ነው (ዕብ 13፡10-21)። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ውስጥ (ኤፌ. 4፡11-16) ሕዝቡን ለሕይወትና ለአገልግሉት ለማስታጠቅ፥ በእግዚአብሔር ቃል ይጠቀማል (2ኛ ጢሞ. 3፡16-17)። እንዲሁም መከራን ለመቋቋም መዘጋጃ መሣርያ አድርጎ ይጠቀምበታል (1ኛ ጴጥ. 5፡10)። ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው በጸሉት ሲደጋገፉ (1ኛ ተሰ. 3፡10) እና በግልም ሲረዳዱ (ገላ.6፡1 «አቅኑት» የሚለው ከዚሁ ፍጹም ተብሉ ከተተረጎመው ቃል ጋር አንድ ዓይነት ነው)፥ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያደረገው ጌታ ቤተ ክርስቲያኑን ያገለግላታል – ለአገልግሉትም ብቁ ያደርጋታል። 

በመነጣጠል ሕይወት ውስጥ፥ ሚዛናዊነትን የጠበቀ ክርስቲያናዊ ዕድገትና አገልግሎት ተግባራዊ ይሆናል ብሎ ከቶውንም አይታሰብም። አንድ ሰው ሲናገር፥ «አንድን ክርስቲያን ከኅብረቱ ነጥሉ ማሳደግ ማለት፥ አንድን ንብ ከመንጋው ነጥሉ እንደማሳደግ ያህል የማይሞከር ነው» ብሏል። ክርስቲያኖች እርስ በርስ የሚኖሩና እርስ በርስ የሚፈላለጉ ናቸው። አንድ ሕፃን ልጅ ሚዛናዊነቱ ተጠብቆ በመልካም ሁኔታ እንዲያድግ ከተፈለገ፥ በሚያፈቅር ቤተሰብ ውስጥ ማደግ አለበት። ዛሬ አንድን ክርስቲያን በአጥቢያ ማኅበረ-ምዕመናን ውስጥ ካለው ስፍራ ነጥሎ «በግል የክርስትና» ልምምድ እንዲመላለስ የማድረጉ አትኩሮት፥ የተሳሳተና በጣም አደገኛ ነው። እኛ በጎች ስለ ሆንን፥ በአንድ ላይ ልንሰማራ ይገባል። የአንድ አካል ክፍሉችም ስለ ሆንን፥ አንዳችን ሌላችንን ልናገለግል ይገባል። 

በ2ኛ ቆሮንቶስ 13፡10፥ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሁለተኛውን መጽናኛ ሰጥቷል – የእግዚአብሔር ቃል። ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ የጻፈው የአንድን ማኅበረ-ምዕመናን ጉድለት ለመሸፈን ሲሆን፥ ዳሩ ግን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል አካል በመሆኑ ዛሬ እኛም እንጠቀምበታለን። ይህ ደብዳቤ የሐዋርያውን በመካከላቸው በአፀደ-ነፍስ የመገኘት ያህል ሥልጣን ተሸክሞአል። የጳውሎስ ትልቁ ፍላጎት ማኅበረ-ምዕመናኑ ለደብዳቤው የሚኖራቸው መታዘዝ ችግሩን እንዲፈታውና እርሱ በሚጎበኛቸው ጊዜ በሥልጣኑ ላለመጠቀም ነበር። 

አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል አገልጋይ ከማነጹ በፊት ለመናድና ለማፍረስ የሚገደድበት ጊዜ አለ። (ኤር. 1፡7-10 ተመልከት)። ገበሬው ዘር ከመዝራቱና መልካም ምርት ከመሰብሰቡ በፊት፡ አካባቢውን መመንጠር አለበት። ጳውሎስ እውነትን በልባቸውና በአእምሮአቸው ውስጥ ከማነጹ በፊት፥ ከክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ የተሳሳተውን አስተሳሰብ ማስወገድ ነበረበት (2ኛ ቆሮ. 10፡4-6)። ምንም እንኳ ትልቅ ፍላጎቱ ማነጽ ቢሆንም፥ የቆሮንቶስ ሰዎች አሉታዊ አመለካከት ግን ጳውሎስን ወደ ማፈራረሱ እንዲያመራ አስገደደው። 

በራሴ የአገልግሎት ዘመን ውስጥ፥ ሁለት የማነጽ ፕሮግራሞችንና ሁለት እንደ ገና መልሶ የማዋቀር ፕሮግራሞች አከናውኛለሁ። ምንም እንኳን የሚጠይቁዋቸው ልፋቶች ከፍተኛ ቢሆኑም፥ ለእኔ የማነጽ (የግንባታ) ፕሮግራሞች ይቀሉኛል። አንድን አሮጌ ሕንፃ አፍርሶ ከመሥራት ይልቅ፥ አንድን አዲስ መዋቅር በአዲስ መሬት ላይ ማነጹ ቀላልም፥ ጊዜ የማያባክንም ነው። እንደዚሁም፥ የቆየውን አማኝ የተሳሳተ አሳብ ለማስለወጥ ከመሞከር ይልቅ፥ አንድን አዲስ አማኝ ወስዶ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማሩ ቀላል ተግባር ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ በአእምሮአችን ውስጥ የተከማቸውን የተሳሳተ የአስተሳሰብ ግድግዳ እስኪንደው ድረስ፥ የተሳሳቱ አሳቦች ለረዥም ጊዜ እውነትን «ለመቋቋም፥ ለመከላከል» ይችላሉ። 

ጳውሎስ ቅዱሳኑ ጸጋን፥ ፍቅርንና ሰላምን እንዲከታተሉ ያበረታታቸዋል (ቁ. 11-12)። «ደኅና ሁኑ» ተብሎ የተተረጎመው ቃል «ጸጋ» የሚል ትርጉም ሲኖረው፥ በዚያን ዘመን የተለመደ የሰላምታ ዓይነት ነበር። «ተደሰቱ» ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ፍጹማን ሁኑ የሚለው ትዕዛዝ፥ በቁጥር 9 ላይ ጳውሎስ ካቀረበው ጸሎት ጋር የተያያዘ ሲሆን፥ «የበሰላችሁ፥ የጸናችሁና ለሕይወት የምትመቹ የሆኑ» የሚል አሳብ አለው። «በአንድ ልብ ሁኑ» የሚለው «ተጽናኑ» የሚል ትርጉም ይኖረዋል ። ከእነዚያ ሁሉ ኃጢአቶቻቸውና ችግሮቻቸው ባሻገር፥ ለመጽናናት የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች ነበሯቸው። 

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መከፋፈል ስለ ነበር፥ በሰላም ኑሩ የሚለው አስፈላጊ ምክር ነበር (12:20 ተመልከት)። በፍቅር ቢመላለሱና በአንድ ልብ ለመኖር ቢፈልጉ የእርስ በርስ ጦርነቶቹ አብቅተው፥ በኅብረታቸው ውስጥ ሰላም ይኖር ነበር። በአንድ ልብ መሆን ማለት ሁላችንም በሁሉም ነገር ላይ እንስማማለን ማለት ሳይሆን፥ ዳሩ ግን አላስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አለመግባባትን ለማስወገድ እንችላለን ማለት ነው። 

አምላካችን «የፍቅርና የሰላም አምላክ» ነው (13፡11)። ታዲያ ከውጭ ያለው ዓለም ከአኗኗራችንና የቤተ ክርስቲያንን ሥራ ከምናከናውንበት ሁኔታ በመንሣት የእኛን የፍቅርና የሰላም ሕይወት ለረዳው ይችል ይሆን? ከደኅንነት ርቆ የጠፋው ዓለም ስለ ቀደመችው ቤተ ክርስቲያን፥ «አቤት እንዴት ይዋደዳሉ!» ይል ነበር፤ እነሆ በዛሬው ጊዜ ግን ቤተ ክርስቲያን የዚህ ዓይነቱን ምስጋና ከተቀበለች ረዥም ጊዜ ሆኖአታል። 

ከጥንት ጀምሮ፥ መሳሳም የሰላምታ ዓይነትና እንደዚሁም የፍቅርና የኅብረት መግለጫ ነበር። ይሁንና ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው በተመሳሳይ ጾታዎች መካከል ነበር። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አማኞች እርስ በርስ የነበራቸውን ፍቅርና መተሳሰብ ለማመልከት፥ የሰላምንና የፍቅርን መሳሳም ያከናውኑ ነበር። ለኢየሱስ ክርስቶስ ከነበራቸው መሰጠት የተነሣ፥ ክንውኑ «የተቀደሰ አሳሳም» ነበር። ለቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አባላት፥ አዳዲስ አማኞችን የጥምቀት ሥርዓታቸውን ከፈጸሙ በኋላ፥ መሳምና ወደ ኅብረቱ መቀላቀል (አቀባበል ማድረግ) እንግዳ ነገር አልነበረም። 

የእግዚአብሔር ሕዝብ ዕለታዊ ኅብረት ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ነው። ስጉባዔው ኅብረት ውስጥም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች እርስ በርሳችን ሰላምታ ልንለዋወጥና አንዳችን ለሌላችን ያለንን አሳቢነት ልንገልጽ ይገባል። በቁጥር 12 ላይ ይህንን ምክር በመስጠት ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ ከባድ ችግሮች በአንዱ ላይ እያነጣጠረ ነበር – ይኸውም በመከፋፈላቸውና እርስ በርስ ሊተሳሰቡ ባለመቻላቸው ላይ ነበር። 

በቁጥር 14 ላይ የሚገኘው የማጠቃለያ ቡራኬ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ ተወዳጁና አዘውትሮም በአገልግሎት ላይ የሚውል ነው። ይህም በሥላሴ አንድነት ምሥጢር ላይ (ማቴ. 28፡19 ተመልከት) እና የእግዚአብሔር ንብረት በመሆናችን በምናገኛቸው በረከቶች ላይ ያተኩራል። የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ እኛን ሀብታም ለማድረግ እርሱ ድሀ በሆነበት ጊዜ የተፈጸመውን የልደት ታሪክ ያስታውሰናል (2ኛ ቆሮ. 8፡ 9 ተመልከት)። የእግዚአብሔር ፍቅር እግዚአብሔር ልጁን ለኃጢአታችን መሥዋዕት አድርጎ ወደሰጠበት ወደ ጎልጎታ ይወስደናል ( ዮሐ 3፡16)። የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለ ወረደበትና ቤተ ክርስቲያንን ስለ መሠረተበት ሁኔታ ያስታውሰናል (የሐዋ. 2)። 

በዚያን ጊዜ የቆሮንቶስ ለአማኞች፥ በዛሬው ጊዜ ደግሞ ለሁሉም አማኞች፥ የጸጋ፡ የፍቅርና የኅብረት በረከቶች በጥብቅ ያስፈልጉአቸዋል። ይሁንና፥ በዚያን ዘመን የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች፡ ዛሬ ደግሞ መናፍቃን፥ ከጸጋ ይልቅ በሕግ ከፍቅር ይልቅ በመለየት፥ እንዲሁም ከኅብረት ይልቅ በመነጣጠል ላይ ያተኩራሉ። መከፋፈልን ያስከተለው የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውድድር ሊቀረፍ የሚችለው ሕዝቡ በእግዚአብሔር ጸጋና ፍቅር ሲመላለስ ብቻ ነበር። 

ቤተ ክርስቲያን ተአምር ስለ ሆነች፥ ልትቆም የምትችለውም በእግዚአብሔር የተአምር አገልግሎት ብቻ ነው። ምንም ያህል ሰብዓዊ ጥበብ፥ ብቃት፥ ወይም ዕቅድ ቤተ ክርስቲያን መሆን የሚገባትን እንድትሆን አያደርግም። ይህንን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እያንዳንዱ አማኝ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የሚደገፍ፥ በእግዚአብሔር ፍቅር የሚመላለስ፥ በሥጋ ከመመላለስ ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ፥ መፍትሔ ሰጪ እንጂ ችግር ፈጣሪ አይሆንም። ይህም ሲሆን ሕይወቱ የተባረከ ይሆናል። በረከቱም ለሌሎች ይተርፋል! 

እግዚአብሔር ይህን ዓይነት ክርስቲያን እንዲያደርግህ በጸሎት ጠይቀው። 

ተጽናና – ሌሎችንም አጽናና። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: