እውቀት ከፍቅር ጋር መጣጣም አለበት (1ኛ ቆሮ. 8፡1-13)

ስለ ጋብቻ ያነሷቸውን ጥያቄዎቻቸውን ከመለሰ በኋላ፥ ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን በተላከው ደብዳቤ ውስጥ ከሚገኙት አንዱ ወደሆነው ጉዳይ፥ «ክርስቲያኖች ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ሊበሉ ይችላሉ?» ወደሚለው ፊቱን አዞረ። ያን ዓይነት ችግር ስለማናይ ይህ ጥያቄ በቀጥታ ለዛሬው አማኞች ብዙም ቁም ነገር ያለው አይመስልም። ነገር ግን ሰፋ ያለው «ክርስቲያናዊ አርነት» እኛንም ይመለከተናል፤ ምክንያቱም ጳውሎስ አይቶአቸው የማያውቃቸውን ጥያቄዎች እኛ ዛሬ እየተፋጠጥን ነው። ለክርስቲያን ቴአትር ማየት ትክክል ነውን? እማኝ በቤቱ ቴሌቪዥን ሊኖረው ይገባልን? ክርስቲያን በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፈው እስከ ምን ደረጃ ነው? 

በምዕራፍ 8-10፥ ጳውሎስ በክርስቲያናዊ ሕይወት ዙሪያ «ጥያቄ ስለሚያስነሡ» ጉዳዮች ውሳኔ አወሳሰዱን በተመለከተ እማኞችን የሚመሩ አራት መሠረታዊ መርሆችን በሚገባ አብራርቶአል። እነዚህ አራት መርሆች የሚከተሉት ናቸው። 

እውቀት ከፍቅር ጋር መጣጣም አለበት (ምዕ. 8)። 

ሥልጣን ከሥነ ሥርዓት እርምጃ ጋር መጣጣም አለበት (ምዕ. 9)። 

ልምምድ ከጥንቃቄ ጋር መጣጣም አለበት (ምዕ. 10፡1-22)። 

አርነት ከኃላፊነት ጋር መጣጣም አለበት (ምዕ. 10፡23-33)። 

ጳውሎስ በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን ለሚገኙ ብርቱ ክርስቲያኖች፥ መንፈሳዊ እውቀትና ልምምድ ወደነበራቸውና በክርስቶስ ያላቸውን ሥልጣንና አርነት ወዳወቁት ፊቱን ሲመልስ መመልከት ትችላለህ። ለደካማው መጠንቀቅ ያለበት ብርቱው ነው (ሮሜ 14-15)። 

ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ የሚነሣው ጥያቄ የተስተናገደው በምዕራፍ 8 እና 10 ስለሆነ፥ እኛም በዚሁ ምዕራፍ ላይ እንመረምረዋለን። በ 1ኛ ቆሮ. 9 ጳውሎስ ይህን ትክክለኛ የሥልጣን አጠቃቀምን መርህ የገዛ ራሱን የገንዘብ አጠቃቀም መመሪያ አስደግፎ ይገልጸዋል፤ በመሆኑም በሚቀጥለው ጥናታችን ያንኑ እናጤናለን። 

እውቀት ከፍቅር ጋር መጣጣም አለበት (1ኛ ቆሮ. 8፡1-13) 

በጥንቱ ዓለም የሥጋ ምንጮች ሁለት ነበሩ። ተለምዶአዊ ገበያ (ባለ ከፍተኛ ዋጋ) እና የአካባቢው ቤተ መቅደስ (የመሥዋዕት ሥጋ ሁልጊዜ የሚገኝበት)። የቤተ ክርስቲያኒቱ ብርቱ አባላት ጣዖታት ምግብን ለማርከስ እንደማይችሉ ያውቁ ስለነበር በቤተ መቅደስ የነበረውን ሥጋ በመሸመት ገንዘባቸውን ይቆጥቡ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፥ ያላመኑ ወዳጆቻቸው የመሥዋዕት ሥጋ ወደሚቀርብበት በሚጋብዙአቸው ጊዜ በቤተ መቅደስም ይሁን በቤት ውስጥ ይበሉት ነበር። 

ይህ ሁሉ ደካሞቹን ክርስቲያኖች አሳዘናቸው። ብዙዎቻቸው ድነው የወጡት ከሃይማኖት-የለሽ ሥርዓተ ጣዖት ስለነበር እማኝ ወዳጆቻቸው ለጣዖት ከተሠዋ ሥጋ ጋር ንክኪ እንዲኖራቸው ለምን እንደፈለጉ ሊገባቸው አልቻለም ነበር። (በሮሜ 14–15 ደካማ ክርስቲያኖች ሥጋንና የበዓላት ቀናትን በተመለከተ ችግር ነበረባቸው። ይሁንና ይህም ቢሆን ሥረ መሠረቱ ያው ነው።) በቤተ ክርስቲያን ክፍፍል አንዣብቦ ስለነበር መሪዎች ጳውሎስን ጠሩት። 

ጳውሎስ ሦስት ዐበይት ነጥቦችን ወደ አትኩሮታቸው ስቦአል። 

እውቀት (8፡1-6)። ቆሮንቶሳውያን በመንፈሳዊ እውቀት የበለጸጉ (1፡5) እና ይልቁንም በድሎቻቸው የሚመኩ ነበሩ። ጣዖት፥ በሚያመልኩት ሰዎች የጨለመ አእምሮ ውስጥ የሚገኝ የውሸት አምላክ አምሳል እንጂ ምንም እንዳልሆነ ያውቁ ነበር። በቤተ መቅደስ ውስጥ የጣዖቱ መገኘት አምላኩ ለመኖሩ በቂ ማረጋገጫ አይደለም። (በኋላ ጳውሎስ አምልኮተ ጣዖት አምልኮተ አጋንንት መሆኑን አመልክቶአል።) የሌለ አምላክ ለእርሱ በተዘጋጀው መሠዊያ የቀረበውን ምግብ ሊያረክስ ” አይችልም የሚለው ምክንያታዊ አቀራረባቸው ትክክል ነበር። 

እስከዚህ ድረስ ሲታሰብ ብርቱዎች ክርስቲያኖች የግንባር ቀደምትነት ስፍራ አላቸው። አቋማቸው የሚያስኬድ ሆኖ ሳለ፥ ለምንድን ነው ደካሞች ክርስቲያኖች የተበሳጩባቸው? ለዚህ መልሱ ማንኛውም ችግር ሁልጊዜ በምክንያታዊ አቀራረብ መፈታት አለመቻሉ ነው። ጨለማውን የፈራ ሕፃን ልጅ ምክንያት ሲደረድሩለት ሊረጋጋ አይችልም፤ በተለይ አዋቂው (ታላቅ ወንድሙ) ለትላልቆች እንደሚደረግ ያለ አመለካከት ሲያንጸባርቅ የማያስኬድ ነገር ነው። እውቀት አጠቃቀምን መሠረት አድርጎ የጠብ ወይም የግንባታ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። «የሚያስታብይ» ከሆነ «ሊያንጽ» አይችልም። 

ሁሉን አውቃለሁ የሚል አመለካከት ያለማወቅ ማረጋገጫ ነው። በትክክል እውነትን የሚያውቅ ሰው ምን ያህል እንደማያውቅ በጥልቀት ወደ መረዳት ብቻ ነው የሚደርሰው። ከዚህም በተጨማሪ፥ ዶክትሪን (አስተምህሮን) ማወቅ አንድ ነገር ሲሆን እግዚአብሔርን ማወቅ ግን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያደጉ ሆኖ፥ በጸጋ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር በግል ግንኙነት አለማደግ ይቻላል። መመዘኛው ጳውሎስ በሁለተኛ ደረጃ ያወሳው ፍቅር ነው። 

ፍቅር (8፡1-3)። ፍቅር እና እውቀት በአንድነት መሄድ አለባቸው፤ «እውነትን በፍቅር እየያዝን» (ኤፌ. 4፡15)። «እውቀት ያለ ፍቅር ጭካኔ፥ ነገር ግን ፍቅር ያለ እውቀት ግብዝነት» መሆኑ በትክክል የተነገረ አባባል ነው። እውቀት ኃይል ስለሆነ በፍቅር መገራት አለበት። ነገር ግን ፍቅር ሁልጊዜ በእውቀት ቁጥጥር ሊደረግበት ያስፈልጋል (የጳውሎስን ጸሎት ከፊልጵ. 1፡9-11 ተመልከት)። በቤተ ክርስቲያን የነበሩ ብርቱ ክርስቲያኖች እውቀት ነበራቸው፤ ነገር ግን እውቀታቸውን በፍቅር አይጠቀሙትም ነበር። ደካማ ቅዱሳንን በማነጽ ፈንታ፥ ራሳቸውን በትዕቢት ይወጥሩ ነበር። 

የጳውሎስ ጭንቀት ደካማዎቹ ቅዱሳን ከደካማነታቸው ወጥተው ማደግ እንዲችሉ ብርቱዎቹ ቅዱሳን እንዲረዱአቸው ነበር። አንዳንድ ሰዎች ብርቱ ክርስቲያኖች በሕግጋትና በደንቦች የሚኖሩና ሌሎች በክርስቶስ ያላቸውን አርነት ሲጠቀሙ የሚጎዱበት ናቸው የሚል አሳብ አላቸው፤ ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም። የሕግን ጥበቃ የሚፈልጉትና በክርስቶስ ያላቸውን አርነት ለመጠቀም የሚፈሩት ናቸው ደካማ ክርስቲያኖች። በብርቱ ክርስቲያኖች ላይ የሚፈርዱ ና የሚተቹ በሚያደርጉትም የሚደናቀፉት ደካማ ክርስቲያኖች ናቸው። በእርግጥ ብርቱዎች ቅዱሳን ለደካማዎቹ ወንድሞችና እኅቶች እንዳያገለግሉ ችግር የሚፈጥረው ይህ ነው። 

እዚህ ላይ ነው ፍቅር መምጣት ያለበት፥ ምክንያቱም «ፍቅር ያንጻል»፥ ሌሎችንም ያስቀድማል። መንፈሳዊ እውቀት በፍቅር ሲጠቀሙት፥ ብርቱው ክርስቲያን ደካማው ክርስቲያን በክርስቶስ ያለውን አርነት እንዲደሰትበት እጁን ይዞ እንዲቆምና እንዲራመድ ለመርዳት ያስችለዋል። ጨቅላ ክርስቲያኖችን በግድ በመመገብ ወደ ግዙፍነት ልንለውጣቸው አንችልም። እውቀት ከፍቅር ጋር መቀየጥ አለበት፤ አለበለዚያ ቅዱሳኑ የሰፉ ልቦች ከመሆን ይልቅ «ትልልቅ ጭንቅላት» ሆነው ይቀራሉ። አንድ ታዋቂ ሰባኪ፥ «አንዳንድ ክርስቲያኖች ያድጋሉ፤ ሌሎች ዝም ብለው ያብጣሉ» የሚል አነጋገር ነበረው። 

እውቀትና ፍቅር ሁለት ጠቃሚ ነጥቦች ናቸው፤ ምክንያቱም ክርስቲያናዊ አርነታችንን በትክክለኛው መንገድ መጠቀም ካለብን እውቀት ከፍቅር ጋር መጣጣም አለበት። ይሁን እንጂ ሦስተኛም ነጥብ አለ። 

ሕሊና (8፡7-13)። ሕሊና የሚለው ቃል በቀላል አነጋገር «ማወቂያ» ማለት ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ 32 ጊዜ በአገልግሎት ላይ ውሎአል። ሕሊና ድርጊቶቻችን ተመርምረው ትክክለኝነታቸው የሚጸናበት ወይም የሚኮነንበት የውስጥ ችሎት ነው (ሮሜ 2፡14-15)። ሕሊና ሕግ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር የሥነ ምግባር ሕግ ምስክርነት የሚሰጥ እንጂ። ነገር ግን አስፈላጊው ነገር ይህ ነው። ሕሊና የሚደገፈው በእውቀት ላይ ነው። ብዙ መንፈሳዊ እውቀት ሲኖረንና ስንተገብረው ሕሊናችን ይጠነክራል። 

እንዳንድ ክርስቲያኖች በቅርቡ የዳኑ ስለሆነና ለማደግም ዕድል ስላልነበራቸው ደካማ ሕሊና አላቸው። በቤት ውስጥ እንዳሉ ሕፃናት በጥንቃቄ መጠበቅ አለባቸው። ሌሎች ቅዱሳን ደካማ ሕሊና ያላቸው ስለማያድጉ ነው። መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውንና ክርስቲያናዊ ኅብረትን ስለሚተዉ ስሕፃንነት ደረጃ ላይ ይቀራሉ (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4፤ ዕብ. 5፡11-14)። ይሁንና ሌሎች አማኞች ደካማ የሚሆኑት አርነትን ስለሚፈሩ ነው። ዕድሜው ለትምህርት ደርሶ ሳለ ቤቱን ትቶ መሄድ እንደፈራና በየቀኑ እናቱ ትምህርት ቤት እንደምታደርሰው ልጅ ናቸው። 

የደካማ ክርስቲያን አእምሮ በቀላሉ ይረክሳል (ቁ 7)፥ ይቆስላል (ቁ 12)፥ ደግሞም ይጎዳል (ቁ 13)። በዚህ ምክንያት፥ ብርቱዎቹ ቅዱሳን ለደካማዎቹ ቅዱሳን ተሸንፈው የሚጎዳቸውን ምንም ነገር ከማድረግ መታቀብ አለባቸው። ጣዖት በሚመለክበት ቤተ መቅደስ ማዕድ መካፈል ለብርቱው ክርስቲያን የሚጎዳው ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ደካማውን ወንድሙን ሊጎዳው ይችላል። ቁጥር 10 ጨቅላው እማኝ ብርቱውን ወንድሙን ለመኮረጅ ይወስንና ወደ ኃጢአት ሊገባ ይችላል በማለት ያስጠነቅቃል። 

ብርቱው አማኝ ለደካማው አማኝ በፍቅር የሚሽነፍለት እንዲጸና ለመርዳት ብቻ መሆኑን ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። ሊያንጸው፥ እንዲያድግ ሊረዳው ይፈልጋል እንጂ «እሽሩሩ እይለውም»። አለበለዚያ ሁለቱም ደካሞች ይሆናሉ። 

በክርስቶስ ነፃ ነን፤ ነገር ግን መንፈሳዊ እውቀታችን በፍቅር የለዘበ እንዲሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፥ ደግሞም ደካማው ክርስቲያን ከሕሊና ውጭ እንዲወጣ ልንፈትነው አይገባም። እውቀት ከፍቅር ጋር በሚጣጣምበት ቦታ፥ ብርቱው ክርስቲያን ለደካማው ክርስቲያን አገልግሎት ይኖረዋል፥ እናም ደካማው ክርስቲያን እድጎ ብርቱ ይሆናል። 

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: