እግዚአብሔርን ለማክበር የተጠራችሁ (1ኛ ቆሮ. 1፡26-31)

ቆሮንቶሳውያን በትዕቢት «የመነፋት» አዝማሚያ ነበራቸው (4፡6፥18-19፤ 5፡2)። ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል ራስን በትምክህት ለመሙላት ምንም ስፍራ አይሰጥም። መልካችን፥ ማኅበራዊ አቋማችን፥ ደረጃችን፥ የተፈጥሮ ቅርሳችን፥ ወይም የገንዘብ ዓቅማችን የእግዚአብሔርን አድናቆት ወይም አክብሮት አያተርፍልንም። ጳውሎስ ለማንም ሳይሆን ለብዙዎች እንደ ጻፈ ልብ በል። በአዲስ ኪዳን «ከፍተኛ ማኅበራዊ አቋም» ያላቸውን ጥቂት አማኞች እናገኛለን፤ ሆኖም ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ብዙ አይደሉም። ለአዲስ አማኞች ጳውሎስ የሰጠው አገላለጽ በእርግጥ የበለጠ አልነበረም (6፡9-11)። 

ጳውሎስ ምን እንደነበሩ አስታወሳቸው (1፡26)። ጥበበኞች፥ ኃያል፥ ወይም የተከበሩ አልነበሩም። እግዚአብሔር የጠራቸው የነበራቸውን መነሻ ምክንያት አድርጎ ሳይሆን ያንን ካቁጥር ሳያስገባ ነበር! የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በመሠረቱ የተውጣጣችው በጣም የከፉ ኃጢአተኞች ከነበሩ ተራ ሰዎች ነበር። ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት በጣም ተመጻዳቂ ሰው ነበር፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሃይማኖቱን መተው ግድ ሆነበት! ቆሮንቶሳውያን በሌላኛው ጽንፍ ነበሩ፤ ቢሆንም ቅሉ እግዚአብሔር ደርሶ ማዳን እስከሚያዳግተው ድረስ በጣም ኃጢአተኞች አልነበሩም። 

ሮበርት ሙሬይ ማክቼይን የተባለ ብፁዕ የእስኮቲሽ መጋቢ አንድ ቀን ለአንዲት ሴት የወንጌል ትራክት በሰጣት ጊዜ ሴቲቱ በጣም ተቀየመችው። በዚሁ ስሜት ሆና «ማን እንደሆንሁ አላወቅህም!» አለችው። ማክቼይንም መለሰና፥ «እሜቴ፥ የፍርድ ቀን እየመጣ ነው፥ በዚያ ቀን የእርስዎ ማንነት የሚፈይድ አይሆንም» አላት። 

ጳውሎስ ቆሮንቶሳውያንን እግዚአብሔር ለምን እንደጠራቸው አስታወሳቸው (1፡27-29)። እግዚአብሔር ለሚታበየው ዓለም ጉድለታቸውን እና የእርሱን ጸጋ ያሳይ ዘንድ ሞኙን፥ ደካማውን፥ ምናምንቴውን («ከዝቅተኛ የተወለደውን») እና የተናቀውን መረጠ። ጠፊዋ ዓለም የዘር ሐረግን፥ ማኅበራዊ አቋምን፥ ጥሪታዊ ስኬትን፥ ኃይልን እና እውቅናን ታደንቃለች። ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ የትኛውም ለዘላለም ሕይወት ዋስትናን አይሰጥም። 

መልእክቱ እና በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው የእግዚአብሔር የጸጋ ተአምር የዚህችን ዓለም ታላላቅ እና ኃያል ሰዎች ያጣጥላቸዋል (ያሳፍራቸዋል)። የዚህች ዓለም ጥበበኞች እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንዴት ቅዱሳን አድርጎ እንደሚለውጣቸው ሊገባቸው አይችልም። የዚህች ዓለም ኃያላንም ቢሆኑ ይህን ተአምሩን የመድገም ዓቅም የላቸውም። የእግዚአብሔር «ሞኝነት» ጥበበኛውን ያሳፍረዋል፤ የእግዚአብሔር «ድካም» ኃያሉን ያሳፍረዋል! 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መዛግብት ሕይወታቸው በወንጌል ኃይል በተለወጠ ታላላቅ ኃጢአተኞች ዝክረ-ነገር የተሞላ ነው። እንደ አብዛኛዎቹ መጋቢያን እና ሰባኪዎች አገልግሎት ሁሉ፥ በእኔ አገልግሎትም የሕግ እና የሥነ ልቡና ጠበብት መረዳት ያልቻሉት አስደናቂ ነገሮች ሲከሰቱ አይቻለሁ። ወጣት አጥፊዎች የተዋጣላቸው ተማሪዎች እና ጠቃሚ ዜጋዎች ሲሆኑ አይተናል። ፍርድ ቤቶች አፋቸውን እስኪይዙ ድረስ ትዳሮች ሕይወት ሲዘሩ እና ወና የቀሩ ቤቶችም ዳግም ሲሟሟቁ ተመልክተናል። 

እግዚአብሔር የዚህን የዛሬውን ዓለም ሥርዓት፥ የፍልስፍናውን እና የሃይማኖቱንም ሞኝነት እና ደካማነት የሚገልጠው ለምንድን ነው? «ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ» (ቁ 29) ነው። ደኅንነት ሙሉ ለሙሉ በጸጋ መሆን አለበት፤ አለበለዚያ እግዚአብሔር ክብሩን አይቀዳጅም። 

ጳውሎስ ለቆሮንቶሳውያን ለማስተላለፍ የሚሻው ይህን እውነት ነው፤ ምክንያቱም ጥፋታቸው በሰው የመመካት ነበር (3፡2)። በሰዎች፥ እንደ ጴጥሮስ፥ ጳውሎስ እና እጵሎስ ባሱ የእግዚአብሔር ሰዎችም እንኳ የምንመካ ከሆነ- እግዚአብሔር ብቻውን ሊቀዳጅ የሚገባውን ክብር እየተናጠቅን ነን ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርግ የነበረው ይህ ኃጢአታዊ የትምክህት አመለካከት ነው። 

በመጨረሻም፥ ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ የነበራቸውን ሁሉ አስታወሳቸው (1፡30-31)። እያንዳንዱ አማኝ «በክርስቶስ» ስለሆነ እና የሚያስፈልገው ሁሉ ስላለው እርስ በርስ መወዳደር ወይም ራስን ከሌላው ማነጻጸር ለምን ያስፈልጋል? ሁሉንም ያደረገው ጌታ ነው! «የሚመካ በጌታ ይመካ» (ቁጥር 31 ከኤርምያስ 9፡24 የተወሰደ ሲሆን እንደገና በ 2ኛ ቆሮ. 10፡17 ተጠቅሶአል)። 

የሚያስፈልጉን መንፈሳዊ በረከቶች ከእጃችን የሚያፈተልኩ ረቂቅ ነገሮች አይደሉም፤ ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እርሱ ጥበባችን ነው (ቆላ. 2፡3)፥ ጽድቃችን ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡2)። ቅድስናችን ነው (ዮሐ 17፡19)፥ እና ቤዛችን ነው (ሮሜ 3፡24)። በእርግጥ እዚህ ላይ እግዚአብሔር በክርስቶስ ባለን ጽድቅ፥ ቅድስና እና ቤዛነት ጥበቡን እንደሚያሳይ አጽንኦት ተደርጎበታል። እነዚህ ሥነ መለኮታዊ ቃላት እያንዳንዳቸው ለክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም አላቸው። ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ያለንን አቋም የሚመለከት ነው። ጸድቀናል። በኢየሱስ ክርስቶስ እንደጻደቅን እግዚአብሔር ይናገራል። ደግሞም ተቀድሰናል፥ የእግዚአብሔር ገንዘብ በመሆን እና እርሱን ለማገልገል ተለይተናል። ቤዛነት በአጽንኦት የሚያሳየው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ዋጋን በመክፈሉ አርነት መውጣታችንን ነው። ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ወደሚጠናቀቀው ፍጹም ቤዛነት ይመራናል። 

ስለዚህ በአንድ መልኩ፥ እዚህ ላይ ሦስት የደኅንነት ጊዜያት አሉን ከኃጢአት ቅጣት ድነናል (ጽድቅ)፤ ከኃጢአት ኃይል እየዳንን ነው (ቅድስና)፤ ከኃጢአት ህልውና እንድናለን (ቤዛነት)። በመሆኑም እያንዳንዱ አማኝ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እነዚህ ሁሉ በረከቶች አሉት! 

እንግዲህ፥ ለምን በሰው እንመካለን? አንተ የሌለህ ጳውሎስ ያለው ምንድን ነው? ጴጥሮስ ከአንተ ይልቅ ክርስቶስን በብዙ ለራሱ ያደርጋልን? (ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን በብዙ የራሱ አደረገ ማለት ከሆነ የሚመስል ነገር ነው፤ ያ ግን ሌላ ጉዳይ ነው!) መመካት የሚገባን በጌታ እንጂ በራሳችን ወይም በመንፈሳዊ መሪዎቻችን አይደለም። 

ይህን ምዕራፍ በምትከልስበት ጊዜ፥ ቆሮንቶሳውያን ይፈጽሙአቸው የነበሩትን ስሕተቶች ማየት ትችላለህ፤ እነዚህ ስሕተቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች እንዲፈጠሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የተቀደሰውን ጥሪያቸውን የሚመጥን አኗኗር አልነበራቸውም፤ ይልቁኑ ይከተሉት የነበረው የዓለምን ልኬቶች ነበር። ወደሚደነቀው የጌታ እና የእርስ በርስ መንፈሳዊ ኅብረት የመጠራታቸውን እውነታ ችላ አሉት። በዚህ ፈንታ ከሰብአዊ መሪዎች ጋር ያብሩና በዚህም ተግባራቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን ይፈጥሩ ነበር። እግዚአብሔርን ጸጋውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ይልቅ እንደፈለጋቸው ያደርጉና ሰዎችን ያሞካሹ ነበር። 

እነርሱ የረከሰች፥ የተከፋፈለችና ጸጋዋን የተገፈፈች ቤተ ክርስቲያን ነበሩ! 

ሆኖም ግን፥ በእነርሱ ላይ ፍርድን ከማሳለፋችን በፊት የራሳችንን ቤተ ክርስቲያንና የግል ሕይወታችንን መመርመር ይገባናል። እኛም እንደ እነርሱ ቅዱስ ለመሆን፥ ወደ ኅብረቱና እግዚአብሔርን ለማክበር ተጠርተናል። 

ለዚህ ጥሪ ብቁ ሆነን እየኖርን ነው ወይ?

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d