ብንወድቅም – አልተጣልንም! (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡1-11 )

«እናንተ የምትገምቱት፥ በሕይወቴ ውስጥ አንዳችም ውጣ ውረድ እንዳልገጠመኝ፥ በምትኩ የሠመረ መንፈሣዊ ሕይወት እንደ መሪ በትፍስሕት የተሞላ ሰላማዊ ኑሮ እንደ ኖረኝ አድርጋችሁ ነው። ጨርሶ ያላጋጠመኝ ነገር ነው! እኔ ብዙውን ጊዜዬን በጉስቁልና ያሳለፍሁና ነገር ዓለሙ የጨለመብኝ ሰው ነኝ።» 

ከላይ የቀረበውን ጽሑፍ ያሰፈሩት በዘመናቸው «በእንግሊዝኛ ተናጋሪ ህብረተሰብ ውስጥ ከሁሉም የላቁ ሰባኪ» የሚል ቅጽል የተቸራቸው ዶክተር ጆን ሄንሪ ጆውት ነበሩ። እኚህ ሰው የአንጋፋ አብያተ-ክርስቲያናት መጋቢ፥ የታላላቅ መንፈሳዊ ስብሰባዎች ሰባኪና ከፍተኛ ተፈላጊነት የነበራቸውን መጻሕፍት የጻፉ ነበሩ። 

«እኔ የመንፈስ ጭንቀት ቁራኛና ስጋት የተጫነኝ ሰው በመሆኔ ማናችሁም የእኔ ዓይነቱ ሥቃይ እንዳይደርስባችሁ አጥብቄ እመኛለሁ።» 

እነዚህ ቃላት የፈለቁት በለንደን ከተማ ባበረከቱት አስደናቂ አገልግሎታቸው የተነሣ እንግሊዝ ካፈራቻቸው ሰባኪዎች ሁሉ የበላይ ተደርገው ከሚቆጠሩት ከቻርልስ ሂደን እስፐርጀን ስብከት ውስጥ ነበር። 

ተስፋ መቁረጥ የሰዎችን የኑሮ ደረጃ ተመልክቶ አክብሮት አይለግስም። እንዲያውም ተስፋ መቁረጥ በይበልጥ የሚያጠቃው የተሳካላቸውን ሰዎች ይመስላል – ይበልጥ ወደ ተራራው ጫፍ በቀረብን መጥን፥ አወዳደቃችንም ያንኑ ያህል የከፋ ሊሆን ይችላል። ስለ ሆነም ታላቁ ሐዋርያ ጳውሎስ «ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከአቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር» (2ኛ ቆሮ. 1፡8) በማለት የጻፈውን ነገር ስንመለከት በአድናቆት አንዋጥም። ጳውሎስ በባሕርይና በአገልግሎት ታላቅ እንደ ነበር ቢታወቅም፥ እንደ እኛው ሰው ነበር፡፡ 

ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥሪ ባይኖረውና (1፡1) ሌሎችን የመርዳት ፍላጎት ባይኖረው ኖሮ ከእነዚህ ሸክሞች ግና በዳነም ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሥርቶ በዚያው ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ 

አገልግሉ ነበር (የሐዋ. 18፡1-18)። ከእርሱ መለየት በኋላ ከባባድ ችግሮች ሲያቆጠቁጡ፥ ጢሞቴዎስ ሁኔታውን እንዲያስተካክል ከሰደደው በኋላ (1ኛ ቆሮ. 4፡17)። አንደኛ ቆሮንቶስ ብለን የምንጠራውን ደብዳቤ ጻፈላቸው። 

የሚያሳዝነው ሁኔታዎቹ እየተባባሱ ሄዱና ጳውሎስ ችግር ፈጣሪዎችን ለመጋፈጥ ወደ ቆሮንቶስ «አሳዛኝ ጉዞ» አደረገ (2ኛ ቆሮ. 2 ከቁ. 1 ጀምሮ)። አሁንም መፍትሔ አልተገኘም። ከዚያም የሥራ ተባባሪው ቲቶ የሚያደርስላቸውን «ከባድ ደብዳቤ» ይጽፋል (2፡4-9፤ 7፡8-12)። በጉዳዩ ብዙ ከተጨነቀበት በኋላ፥ ጳውሎስ በመጨረሻው ቲቶን አገኘውና ችግሩ እልባት እንዳገኘ የሚያመለክት መልካም ዜና ሰማ። ከዚያ በኋላ ነበር ሁለተኛ ቆሮንቶስ የምንለውን ደብዳቤ የጻፈላቸው። 

ደብዳቤውን የጻፈውም ለበርካታ ምክንያቶች ነው። በመጀመሪያ፥ ቤተ ክርስቲያኗ ያንን ሁሉ ችግር የፈጠረውን ምዕመን ይቅር ብላ እንድትመልሰው በመፈለጉ ነበር (2፡6-11)። እንዲሁም የዕቅዶቹን ለውጥ ለመግለጽና (1፡5-22) ሐዋርያ እንደ መሆኑ ሥልጣኑን ከሥራ ላይ ለማዋል ሲሆን (4፡ 1-2፤ ምዕ. 10-12)፥ በመጨረሻም በይሁዳ ለሚገኙ ድሆች በሚሰበሰበው የተለየ «የርዳታ አሰጣጥ» ላይ ቤተ ክርስቲያን ተካፋይ እንድትሆን ለማበረታታት በመፈለጉ ነበር (ምዕ. 8-9)። 

በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ካሚገኙ ቁልፍ ቃላት አንዱ መጽናናት ወይም መበረታታት ነው። ይህንን የሚገልጸው የግሪኩ ቃል «ይረዳው ዘንድ ከአንድ ሰው አጠገብ ተጠርቶ የቆመ» የሚል ትርጉም ይሰጣል። በዚህ ደብዳቤ ውስጥ አንቀጹ (ግሱ) 18 ጊዜ ያገለገለ ሲሆን፥ መጠሪያው (ስም) 11 ጊዜ አገልግሏል። ጳውሎስ ከመከራዎቹ ሁሉ ባሻገር፥ (በእግዚአብሔር ጸጋ) በመጽናናት የተሞላ ደብዳቤ ሊጽፍ በቅቷል። 

ይህን በመሰለ መከራን ጫናዎች መካከል ያለውን ጳውሎስ ድልን ለመቀዳጀት ያበቃው ምሥጢር ምንድን ነበር? ምሥጢሩ እግዚአብሔር ነበር። አንተም ተስፋ በቆረጥህና የጀመርኸውን ሥራ እርግፍ አድርገህ ለመተው በተቃረብህ ጊዜ፥ አትኩሮትህን ከራስህ ላይ አንሥተህ በእግዚአብሔር ላይ አስቀምጥ። ጳውሎስ ከራሱ አስቸጋሪ ልምምድ ውስጥ፥ እንዴት በእግዚአብሔር መጽናናትን እንደምናገኝ ይነግረናል። ሦስት ቀላል ማሳሰቢያዎችንም ይሰጠናል። 

እግዚአብሔር ለአንተ ማን እንደሆነ አስታውስ (2ኛ ቆሮ. 1፡3) 

ጳውሎስ ደብዳቤውን በምስጋና ይጀምራል። በርግጥ ስለ ነበረባቸው ሁኔታዎች የምስጋና መዝሙር ሊዘምር ባይችልም፥ ዳሩ ግን ሁኔታዎችን ሁሉ በመቆጣጠር ላይ ስለሚገኘው እግዚአብሔር ሊዘምር ይችል ነበር። ጳውሎስ ምስጋና ተስፋ በመቁረጥና በጭንቀት ላይ ድል ለማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ተረድቶ ነበር። «ጸሉት ነገሮችን እንደሚለውጥ» ሁሉ «ምስጋናም ነገሮችን ይለውጣል»። 

አምላክ ነውና አመስግኑት! «እግዚአብሔር ይባረክ» የሚለውን ይህንኑ ሐረግ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሌሉች ሁለት ሥፍራዎች ውስጥ ማለትም በኤፌሶን 1፡3 እና በ1 ጴጥሮስ 1፡3 ላይ እናገኛለን። በኤፌሶን 1፡3 ጳውሎስ እግዚአብሔርን የሚባርከው «በክርስቶስ በመረጠን» (ቁ. 4) እና «በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ» በባረከን ጊዜ አስቀድሞ ስላደረገው ነገር ነው። በ1ኛ ጴጥሮስ 1፡3 ላይ ደግሞ ጴጥሮስ ወደ ፊት ስለሚመጡ በረከቶችና ስለ «ሕያው ተስፋ» እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ዳሩ ግን በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ጳውሎስ በዚያን ጊዜ በዚያው ሥፍራው ስለ ነበሩት የወቅቱ በረከቶች እግዚአብሔርን እያመሰገን ነበር። 

በሠላሳ ዓመቱ ጦርነት ቀውጢ ወቅት፥ መጋቢ ጎርቲን ሪንካርት በኢላንበርግ ሳክሰኒ ሕዝቡን በታማኝነት አገልግለው ነበር። በየቀኑ ወደ 40 የሚጠጉ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ከመምራታቸውም፥ በጠቅላላው በአገልግሎታቸው ደግሞ ከ4000 የሚበዙ ቀብሮች አስፈጽመዋል። ይሁንና ከዚህ አሳዛኝ ልምምዳቸው ውስጥ ዛሬ የምስጋና መዝሙር አድርገን የምንጠቀምበትን «የጸጋ ማዕድ» ቡራኬ ለልጆቻቸው ጽፈዋል። 

ሁላችንም እናወድሰው – አምላካችንን ዛሬ፥ 

ከልባችን ተነሥተን – በጭብጨባ በዝማሬ፥ 

ድንቅ ነገሮችን በመሥራቱ፥ 

ፍጡራኑ በርሱ ይደሰቱ! 

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እባት ነውና አመስግኑት! እኛም እግዚአብሔርን «አባት»ብለን የምንጠራውና እንደ ልጆቹ ከፊቱ ልንቀርብ የምንችለው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ ነው። እግዚአብሔር እኛን በልጁ ውስጥ ስለሚያየን ልጁን እንደሚወደው አድርጎ ይወደናል (ዮሐ 17፡26)። «በውድ ልጁ» (ኤፌ. 1፡6) ተቀባይነትን ስላገኘን፥ «በእግዚአብሔር የተወደድን» (ሮሜ 1፡7) ነን። 

ኢየሱስ በምድር ላይ ሲያገለግል ሳለ ያደረገለትን ሁሉ፥ እግዚአብሔር ዛሬም ለኛ ሊያደርግልን ይችላል። ልጁ ለእርሱ ውድ ስለ ሆነና እኛም የ«ፍቅሩ ልጅ መንግሥት» (ቆላ 1፡13) ዜጎች ስለ ሆንን፥ ለአብ ውድ ነን። ለእርሱ ውድና ብርቅ በመሆናችን፥ የሕይወት ጫናዎች እንዳያጠፉን ይቆጣጠርልናል። 

የምህረት አባት ስለ ሆነ አመስግኑት! ለአይሁድ ሰዎች «አባት» የሚለው ቃል «ምንጭ» ማለት ነው። ውሸቶች የመነጩት ከሰይጣን ስለ ሆነ፥ ሰይጣን የውሸቶች አባት ነው (ዮሐ 8፡44)። በዘፍጥረት 4፡21 ላይ እንደተ ገለጸው፥ ዩባል በገናንና መለከትን ስለ ሠራ፥ የሙዝቃ መሣሪያዎች አባት ነበር። እንደዚሁም ምህረት ሁሉ የሚመነጨውና ሊገኝ የሚችለው ከእግዚአብሔር ብቻ ስለ ሆነ፥ እግዚአብሔር የምህረት አባት ነው። 

እግዚአብሔር በጸጋው የማይገባንን ነገር ይሰጠናል፤ እንዲሁም በምህረቱ ለጥፋተኛነታችን ተመጣጣኝ ቅጣት እንድናገኝ አያደርግም። «ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሣ ነው» (ሰቆቃ 3፡23)። የእግዚአብሔር ምህረት ብዙ (ነህ. 9፡ 19)፥ ፍቅር ያለበት [መዝ (25)፡6] እና ታላቅ (ዘኁ. 14፡9) ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ «የእግዚአብሔር ጸጋ ብዙ» እንደ ሆነና ከዚህም የተነሣ አቅርቦቱ ሊጎድል እንደማይችል ይናገራል [መዝ 5፡8፤ (51)፡1፤ (69)፡13፥16፤ (106)፡7፥ 45፤ ሰቆቃ. 3፡32]። 

የመጽናናት ሁሉ አምላክ ስለ ሆነ አመስግኑት! (በግሪክ ተመሳሳይ ሥርወ-ቃል ያላቸው) መጽናናት ወይም ዳረጎት የሚሉ ቃላት ከቁጥር 1-11 ውስጥ 10 ጊዜ ተደጋግመው ይገኛሉ። ስለ መጽናናት ስናስብ እንደ «ርኅራኄአድርገን ማሰብ የለብንም – ርኅራኄ ከማበርታቱ ይልቅ ሊያዝለን ወይም ሊያሳንፈን ይችላልና። እግዚአብሔር አእምሮአችንን ከተጨነቀበት ነገር ለማዘናጋት ጣፋጭ ከረሜላ ወይም አሻንጉሊት በመስጠት አይደልለንም። ይልቁንም መከራችንን ተጋፍጠን በድል እንወጣ ዘንድ በልባችን ውስጥ ብርታቱን ያኖራል። «መጽናናት» የሚለው ቃል «ብርታት ያለው» የሚል ትርጉም ካላቸው ሁለት የላቲን ቃላት የተገኘ ነው። የግሪኩ ቃል ትርጉም ወደ አንድ ሰው «ቀረብ ብሎ መርዳት» የሚል ነው። ይህንኑ ቃል በዮሐንስ 14-16 ስለ(«አጽናኑ») መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። 

እግዚአብሔር በቃሉና በመንፈሱ አማካኝነት ሊያጽናናን ይችላል፤ ዳሩ ግን አንዳንድ ጊዜ፥ የሚያስፈልገንን መጽናናት ለመስጠት በሌሎች አማኞች ይጠቀማል (2ኛ ቆሮ. 2፡7-8፤ 7፡6-7)። ለሁላችንም «በርናባስ – የመጽናናት ልጅ» የሚለው ቅጽል-ስም ቢኖረን ኖሮ ምንኛ ግሩም በሆነ ነበር! (የሐዋ. 4፡36)። 

ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሣ ተስፋ በቆረጥህ ጊዜ፥ ወደ ራስህና ወደ ስሜቶች መመልከት ወይም ዙሪያውን በከበቡህ ችግሮች ላይ ማተኮሩ ቀላል ነው። ዳሩ ግን ልንወስደው የሚገባን የመጀመሪያው እርምጃ በእምነት አቅንተን ጌታን ማየትና እግዚአብሔር ሊረዳን ከጎናችን መቆሙን መረዳት ነው። «ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው» [መዝ (121)፡1-2]። 

እግዚአብሔር ያደረገልህን ነገሮች አስታውስ (2ኛ ቆሮ. 1፡4፥ 8-11) 

ቀድሞ ነገር እግዚአብሔር መከራዎቹ እንዲመጡ ይፈቅዳል። በግሪክ ቋንቋ መከራን ለመግለጽ የሚያገለግሉ አሥር መሠረታዊ ቃላት ቢኖሩ፥ ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤው ውስጥ በአምስቶቹ ተጠቅሟል። ከሁሉም በላቀ ሁኔታ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ትሊፕሲስ የሚለው ሲሆን፥ ትርጉሙም «ጠባብ፥ የታሰረ፥ የተወጠረ» ማለት ነው፤ ይህ ቃል በዚህ ደብዳቤ ውስጥ መከራ (2፡4፤ 4፡17፤ 1፡4፥ 8) ተብሉ ተተርጉሞአል። ጳውሎስ ዙሪያውን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደተከበበ ስለ ተሰማው፥ ማየት የሚችለው ወደ ላይ ወደ አምላኩ ብቻ ነበር። 

ጳውሎስ በቁጥር 5 እና 6 የጌታችንን መከራ ለመግለጽ ባገለገለው «ፓቴማ» በሚለው ቃል ይጠቀማል (1 ጴጥ. 1፡11፤ 5፡1)። ሰብዓዊ ሰዎች በመሆናችንና ለችግር ስለ ተጋለጥን ብቻ የምንታገሣቸው አንዳንድ መከራዎች አሉ፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለ ሆንንንና እርሱን ለማገልገል ስለምንፈልግ የምንቀበላቸው ሌሎች መከራዎች ይኖራሉ። 

መከራ በድንገት የሚመጣ ነገር እንደ ሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። ለአማኝ፥ ሁሉም ነገር በመለኮታዊ ቀጠሮ የሚመጣ ነው። ወደ ሕይወታችን የሚመጡትን መከራዎች በተመለከተ አንድ ሰው ሊይዛቸው የሚችላቸው ሦስት አማራጭ አመለካከቶች ብቻ አሉ። መከራዎቻችን የ«ዕጣ-ፈንታ» ወይም የ«ዕድል» ውጤቶች ከሆኑ፥ ማድረግ የምንችለው ነገር ብቻ ይሆናል። ማንም ሰው ዕጣ-ፈንታን ወይም ዕድልን ሊቆጣጠር አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ያለብን እኛው ከሆንን፥ ሁኔታው በተመሳሳይ ደረጃ ተስፋ የሚጣልበት አይሆንም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሁኔታዎችን የሚቆጣጠር ከሆነና እኛም በእርሱ ከታመንን፥ በእርሱ እርዳታ ሁኔታዎችን ልናሽንፍ እንችላለን። 

እግዚአብሔር መከራዎቹ እንዲመጡ የሚፈቅደው እርሱ እንደ ሆነ ከቃሉ ውስጥ በማስተማር፥ በመከራችን ሁሉ እንዳንሸነፍ ያደፋፍረናል። የሚገጥሙንን መከራዎች በመቆጣጠር ላይ እንዳለ በማስታወስ ያጽናናናል (1፡8)። «ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር።» ጳውሎስ ከሚችለው በላይ ጭነት እንደ ተከመረበት የጋማ ከብት ሁኔታው ከብዶት ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔር የጳውሎስን ዓቅም ስለሚያውቅ፥ ሁኔታውን ተቆጣጥሮታል። 

የገጠመው «መከራ» በትክክል ምን እንደ ነበር ባናውቅም፥ ዳሩ ግን ጳውሎስ ለሞት እንደ ተቃረበ እስኪመስለው ድርስ ከባድ እንደ ነበር እንረዳለን። ከበርካታ ጠላቶቹ የተሰነዘረ አደጋ ይሁን (1ኛ ቆሮ. 15፡30-32፤ የሐዋ. 19፡ ከ21 ጀምሮ)፥ ወይም ብርቱ ሕመም ይሁን፥ ወይም የተለየ ሰይጣናዊ ጥቃት ይድረስበት ግልጽ የሆነልን ነገር የለም፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሁኔታዎቹን እንደ ተቆጣጠረና ባሪያውን እንደ ጠበቀው አሳምረን እናውቃለን። እግዚአብሔር ልጆቹን በመከራ እቶን ውስጥ ሲያስቀምጥ፥ እጁን በሙቀት መቆጣጠሪያው መሣሪያ ላይ፥ ዓይኑን ደግሞ በሙቀት መለኪያው ላይ ያኖራል (1ኛ ቆሮ. 10፡13፤ 1 ጴጥ. 1፡6-7)። ጳውሎስ እሞታለሁ ሲል ተስፋ ቆርጦ እንደ ሆነ እንጂ፥ እግዚአብሔር ግን ስለ ጳውሎስ አልተጨነቀም ነበር። 

እግዚአብሔር መከራችንን እንድንሸከም ይረዳናል (2ኛ ቆሮ. 1፡9)። በመጀምሪያ ደረጃ እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር በራሳችን ምን ያህል ደካሞች እንደ ሆንን ማሳየት ነው። ጳውሎስ በተለያዩ ዓይነት መከራዎች ውስጥ ያለፈ፥ ስጦታና ልምድ የነበረው የእግዚአብሔር አገልጋይ ነበር (4፡ 8-12፤ 11፡ ከቁ 23 ጀምሮ ይመልከቱ)። በመሠረቱ ይህ ሁሉ ልምምድ እነዚህን አዳዲስ ችግሮች ለመጋፈጥና ለማሸነፍ ባስቻለውም ነበር። 

እግዚአብሔር ግን በስጦታችን ወይም በችሎታችን ፥ በልምምዳችን ወይም «ባካበትነው መንፈሳዊ ብቃታችን» ሳይሆን፥ በእርሱ እንድንታመን ይፈልጋል። በራስ የመተማመን ስሜት ተሰምቶን ከጠላት ጋር ስንጋጠም በሚያሳዝን ሁኔታ ለሽንፈት እንዳረጋለን። «ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና» (12፡10)። 

አንተና እኔ የእኔነት ስሜታችንን ስናስወግደው (ስንገድለው)፥ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የትንሣኤው ኃይል በውስጣችን መሥራት ይጀምራል። የእግዚአብሔር የትንሣኤው ኃይል አብርሃምና ሣራን በሥጋቸው ልጅ እንዲያገኙ ያስቻላቸው እንደ ሙት በሆኑ ጊዜ ነበር (ሮሜ 4፡16-25)። ይሁንና «ለእኔነት መሞት» ማለት ምንም ነገር አለማድረግና ዝም ብሎ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንዲያደርግ በመጠበቅ በግድየለሽነት መመልከት አይደለም። ጳውሎስ እንደ ጸለየ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደ መረመረ፥ ከሥራ ተባባሪዎቹ ጋር እንደ ተማከረና እግዚአብሔር ሥራውን እንዲሠራ እንደ ታመነበት እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ሙታንን የሚያስነሣ አምላክ ለማንኛውም የሕይወት እንቆቅልሽ ብቁ ነው። እርሱ ሁሉንም የሚችል ብቁ አምላክ ነው፤ ዳሩ ግን እኛም እንዲጠቀምብን ፈቃደኞች መሆን ይገባል። 

ጳውሎስ የተሰማውን ስሜት ለማስተባበል ወይም ለመካድ አልሞከረም፤ እግዚአብሔር ስሜቶቻችንን እንድንክድ ወይም እንድንደብቅ አይፈልግም። «በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን … በውጭ ጠብ ነበረ፤ በውስጥ ፍርሃት ነበር» (2ኛ ቆሮ. 7፡5)። በ1፡9 ላይ የተጠቀሰው «የሞት ፍርድ» ምናልባት በጳውሎስ ላይ የተበየነውን የእስራትና ሞት ይፋዊ ውሳኔ የሚያመለክት ይሆናል። እዚህ ላይ ልብ ልትል የሚገባው የማያምኑ አይሁዶች የጳውሎስን ስደት እንዳባባሱና ሊያስወግዱትም እንደ ፈለጉ ነው (የሐዋ. 20፡19)። «በወገኔ በኩል ፍርሃት» (2ኛ ቆሮ. 11፡26) የሚለው ከአደጋዎች ዝርዝር ውስጥ አነስተኛ ሥፍራ ሊሰጠው አይገባም። 

እግዚአብሔር ከመከራችን ያድነናል (2ኛ ቆሮ.1፡10)። ጳውሎስ ወደ ኋላም ሆነ ወደፊት፥ ወይም ደግሞ ዙሪያ-ገባውን ቢያይም፥ የተመለከተው የእግዚአብሔርን የማዳን እጅ ነበር። ጳውሎስ የተጠቀመበት ቃል «በጭንቀት ውስጥ መርዳት፥ ማዳንና መጠበቅ» የሚል ትርጉም አለው። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከመቅጽበት አያድነንም፤ ልጆቹንም ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ አያድናቸውም። ሐዋርያው ያዕቆብ ራሱን ተቆርጦ ሲሞት፥ ጰጥሮስ ግን ከወኅኒው እስራት አምልጧል (የሐዋ. 12)። ሁለቱም ድነዋል – ዳሩ ግን በተለያየ መንገድ፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ከመከራዎች ይሰውረናል – ሌላ ጊዜ ደግሞ በመከራዎቻችን ያድነናል። 

እግዚአብሔር ማዳኑን የገለጸው ለጳውሎስ እምነት፥ እንዲሁም በቆሮንቶስ ከተማ ለሚጸልዩ ሰዎች እምነት ምላሽ በመስጠት ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡11)። «ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው» [መዝ (34)፡6]። 

በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር በመከራችን ይከብራል (2ኛ ቆሮ. 1፡1)። ጳውሎስ እግዚአብሔር ያደረገላትን በሚዘግብበት ጊዜ፥ ታላቅ የውዳሴና የምስጋና አዝማች ከቅዱሳኑ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን አርጓል። እኔም ሆንኩኝ አንተ በምድር ላይ ልንፈጽመው የምንችለው ከሁሉም የላቀው አገልግሉት ለእግዚአብሔር ክብርን ማምጣት ሲሆን፥ አንዳንድ ጊዜ ያ አገልግሉት መከራ መቀበልንም ይጨምራል። «የተሰጠን … ስጦታ» የሚለው ገለፃ የጳውሎስን ከሞት መዳን ያመለክታል – እውነትም ድንቅ ስጦታ ነበር! 

ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዲጸልዩላት ለመጠየቅ አላፈረም ነበር። ቢያንስ በሰባቱ ደብዳቤዎቹ ውስጥ፥ ጸሎት በጣም እንደሚያስፈልገው ጠቅሶአል (ሮሜ 15፡30-32፤ ኤፌ.6፡18-19፤ ፊልጵ. 1፡19፤ ቆላ. 4፡3፤ 1ኛ ተሰ 5፡25፤ 2ኛ ተሰ 3፡1፤ ፊል. 22)። ጳውሎስና የቆሮንቶስ አማኞች እርስ-በርሳቸው ይረዳዱ ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡11፥ 24)። 

በቅርቡ አንድ ሚስዮናዊ ወዳጄ ሐኪሞች ትሞታለች ያሉዋት በሽተኛ ልጁ በድንቅ ስለ ዳነችበት ሁኔታ አጫውቶኝ ነበር። ልጅቱ በጣም በታመመችበት ወቅት፥ በርካታ ወገኖች በዩናይትድ እስቴትስ እየጸለዩላት ነበርና እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ሰምቶ ልጅቱን ፈወሳት። ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ልንሰጥ የምንችለው ታላቁ እገዛ «በጸሎት መርዳት» ነው። 

«እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን» (ለ በጸሎት መረዳዳት) ተብሎ የተተረጎመው ሳኑፖርጂዎ በግሪክ አዲስ ኪዳን ውስጥ ያገለገለው በዚህ ሥፍራ ብቻ ሲሆን፥ ቃሉም፡- ከ-ጋር፥ ከ-ሥርና ሥራ ከሚሉት ሦስት ቃላት የተገነባ ነው። ይህም ከሸከም ሥር ሆነው፥ ሥራውን ለማጠናቀቅ በኅብረት የሚተጉትን ሠራተኞች ያመለክታል። እዚህ ላይ መንፈስ ቅዱስ በጸሉታችን እንደሚያግዘንና ሸክሙን ለመሸከም ትከሻችንን እንደሚያጠነክረው መረዳቱ የሚያጽናና ነገር ነው (ሮሜ 8፡26)። 

ራሳችንን ለርሱ ብንሰጥ ፥ ብንታመንበትና እንድናደርገው የሚሰጠንን ትዕዛዝ ሁሉ ብንፈጽም፥ እግዚአብሔር ዓላማዎቹን በመከራ በምንፈተንበት ጊዜ ይፈጽማል። ችግሮች እምነታችንን ሊጨምሩና የጸሎት ሕይወታችንን ሊያጠናክሩ ይችላሉ። የችግሮቻችንን ሸክሞች ከሌሉች ክርስቲያኖች ጋር በምንጋራበት ጊዜ ከእነርሱ ጋር የቀረበ ኅብረት እንዲኖረን ሊያደርጉን ይችላሉ። ችግሮች እግዚአብሔርን ለማስከበር ሊረዱ ይችላሉ። በመሆኑም፥ አንተም በመከራ ሕይወት ውስጥ ስትገኝ፥ እግዚአብሔር ለአንተ ምን እንደ ሆነና ምንስ እንደሚያደርግልህ አስታውስ። 

እግዚአብሔር በአንተ በኩል ያደረገውን ነገር አስታውስ (2ኛ ቆሮ. 1፡4-7) 

በመከራ ጊዜ፥ ብዙዎቻችን ስለ ራሳችን ብቻ ወደ ማሰብና ሌሎችን ወደ መዘንጋት እናዘነብላለን። ማስተላለፊያ ቧንቧዎች በመሆን ፈንታ ማጠራቀሚያ ጋኖች እንሆናለን። ይሁንና መከራዎች የሚመጡበት አንድኛው ምክንያት እኔና አንተ ሌሎችን ለማጽናናትና ለማበረታታት የበረከት ቧምቧዎች እንሆን ዘንድ ነው። እግዚአብሔር እኛን ስላጽናናን፥ ሌሉችን ለማጽናናት እንችላለን። 

ከምወዳቸው ሰባኪዎች አንዱ በዳላስ፥ ቴክሳስ የምትገኘውን የመጀመሪያ የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያንን ለ50 ዓመታት ያህል በመጋቢነት ያገለገሉት ዶክተር ጆርጅ ደብልዩ ትሩዩት ናቸው። ከስብከቶቻቸው በአንድኛው ወቅት፥ ሕፃናቸው ስለ ተባቸው የማያምኑ ባልና ሚስት ታሪክ ነገሩን። ሥነ-ሥርዓት ያስፈጸሙት ዶክተር ትሩዩት ከመሆናቸውም የኋላ ኋላ ባለትዳሮቹ በኢየሱስ ክርስቶስ ሲታመኑ በማየት ደስ ተሰኝተዋል። 

ከብዙ ወራት በኋላ፥ አንዲት ወጣት እናት ልጇ ሞተባትና አሁንም ዶክተር ትሩዬት እንዲያጽናኑዋትተጠየቁ።ይሁንናእርሳቸው ያካፈሉዋት የማጽናኛቃላትሁሉሐዘኗን የቀነሱላት አይመስልም ነበር። ዳሩ ግን የቀብሩ ሥነ-ሥርዓት በመፈጸም ላይ እንዳለ ያቺ ቀደም ሲል የተለወጠችው እናት ወደ አሁኗ ወጣት ሓዘንተኛ አጠገብ በመቅረብ፥ «እኔ በተመሳሳይ ሁኔታ ስላለፍሁ፥ አንቺም እያለፍሽ ያለሽበትን ነገር አውቃለሁ። እግዚአብሔር ጠርቶኛልና በዚያ በጨለማ አማካኝነት ወደ እርሱ መጣሁ። እርሱ አጽናንቶኛልና አንቺንም እንደ እኔ ያጽናናሳል!» አለች። 

ዶክተር ትሩዩትም እንዲህ አሉ፡- «የመጀመሪያዪቱ እናት ለሁለተኛዪቱ እናት እኔ ምናልባት በዕለታትና በወራት ውስጥ ላደርግ ከምችለው እጅግ የላቀ ነገር አድርጋለች፤ ይኸውም የመጀመሪያዪቱ እናት ራሷ በዚሁ ዓይነት የስቃይ መንገድ በመጓዟ ነው።» 

ይህም ሆኖ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ማጽናናት ለመጋራት በትክክል ተመሳሳይ መከራዎችን ማለፍ እንደማያስፈልገን ይናገራል። የእግዚአብሔርን መጽናናት ካገኘን። «በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን» (2ኛ ቆሮ. 1፡4)። በርግጥ ተመሳሳይ መከራዎችን አሳልፈን ከሆነ፥ በመከራ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ችግር በቀላሉ እንድንረጻና እንዴት እንደሚሰማቸውም በበለጠ እንድገነዘብ ያስችለናል። ዳሩ ግን ልምምዶቻችን የእግዚአብሔርን ማጽናናት ሊለውጡት አይችሉም። የእኛ ልምምድ ምንም ይሁን ምን፥ ያ የእግዚአብሔር ማጽናናት ለምንጊዜም በቂና ብቁ ሆኖ ይኖራል። 

ወደ በኋላ በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፥ እንደምንመለከተው ጳውሎስ የዚህን መመሪያ ምሳሌ ይሰጠናል። እንደ ሹል እሾክ ሆኖ ሥጋውን – ባለማቋረጥ በመቸክቸክ የሚያውከው አንድ የሆነ ሥጋዊ ሥቃይ ተሰጥቶት ነበር። ይህ «የሥጋ መውጊያ» ምን እንደ ሆነ አናውቅም . ማወቁም የሚሰጠን ፋይዳ የለውም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ግን፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንደ ተለማመደና ከዚያም ያንኑ መጽናናት ለእኛ እንዳጋራን ብቻ ነው። መከራህ ምንም ዓይነት ቢሆን፥ «ጸጋዩ ይበቃሃል» (12፡9) የሚለው አለኝታ ልትመካበት የምትችለው የተስፋ ቃል ነው። ጳውሎስ መከራ ባይቀበል ኖሮ፥ እኛም ይህንን የተስፋ ቃል ባልተቀበልንም ነበር። 

የሰብዓዊ መከራ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የምንረዳው አይደለም። ወደ መንግሥተ-ሰማይ እስክንደርስ ድረስ ስለ እግዚአብሔር አሠራር የማንረዳቸው ምሥጢራት ስላሉ፥ እንዲህ በዋዛ የምንገነዘበው አይሆንም። አንዳንድ ጊዜ እንደ ዮናስ በራሳችን ኃጢአትና ዓመፅ ምክንያት አንሰቃያለን። አንዳንድ ጊዜ እንደ ጳውሎስ፥ ከኃጢአት ለመራቅ እንሰቃያለን (2ኛ ቆሮ. 12፡7)። መከራ ባሕርያችንን በመቅረጽ (ሮሜ 5፡1-5)፥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ እንድንጋራ ይረዳናል (ዕብ. 12፡1-11)። 

ዳሩ ግን መከራ ሌሎችን እንድናገለግል ሊረዳንም ይችላል። በሁሉም ቤተ ክርስቲያን፥ መከራ የተቀበሉና የእግዚአብሔር ጸጋ የተለማመዱ በሳል ቅዱሳን አሉ፤ እነዚህም በማህበረ-ምዕመናኑ ውስጥ ታላቅ «አጽናኞች» ናቸው። ጳውሎስ መከራ የተቀበለው ለፈጸመው ጥፋት በአፀፋው ቅጣት ተወስኖበት ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ከፊቱ ለሚጠብቀው ሥራ እንዲዘጋጅ ነበር። ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ ውስጥ የምናገኘውን ታላቅ መጽናናት ለእኛ ለማስተላለፍ ይቻለው ዘንድ፥ እስቲ የቱን ያህል ከባድ መከራዎች በትዕግሥት እንዳሳለፈ አስብ። 

ከ2ኛ ቆሮንቶስ 1፡7 እንደምንረዳው ሁኔታው ምንጊዜም ሊቀለበስ እንደሚችል በግልጽ ሰፍሯል፡- የቆሮንቶስ አማኞች በመከራ ውስጥ ያልፉ ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ልክ እንደ ጳውሎስ ሌሎችን ለማጽናናት የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ይቀበላሉ። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብን ለተለየ መከራ የሚጠራው፥ በእነርሱ በኩል የተላየና የሚበዛ ጸጋውን ለማስተላለፍ ነው። 

መታገሥን የምንማር እስከ ሆነ፥ የእግዚአብሔር የቸርነት መጽናናት በእጅጉ ይረዳናል። «በትዕግሥት መጽናት» የእምነትን መኖር የሚያመለክት መረጃ ነው። ለእግዚአብሔር መራራ ወይም ግትር ብንሆን፥ ከመገዛት ይልቅ ብናምፅ፥ መከራዎቻችን ለመልካም ሳይሆን ለክፋት በላያችን ላይ ይሰለጥናሉ። ተስፋ ባለመቁረጥ፥ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በትዕግሥት መጽናት የመንፈሳዊ ብስለት ምልክት ነው (ዕብ 12፡1-7)። 

እግዚአብሔር በእኛ በኩል ሥራውን ከማከናወኑ በፊት፥ በውስጣችን መሥራት አለበት። ለእኛ ግን ከጸጋ ይልቅ በእውቀት ማደጉ ይቀለናል (2 ጴጥ. 3፡18)። የእግዚአብሔርን እውነት መማርና በጭንቅላታችን ውስጥ ማከማቸት አንድ ነገር ሲሆን፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር እውነት መኖርና ይህንኑም ከባሕርያችን ጋር ማዋሃድ ፍጹም የተለየ ነገር ነው። እግዚአብሔር ወጣቱን ዮሴፍ ሁለተኛው የግብፅ ባለሥልጣን አድርጎ ከመሾሙ በፊት በ13 ዓመታት መከራ ውስጥ አሳለፈው፤ ዮሴፍም ግሩም ሰው ሆኖ ተለወጠ። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ለእኛ ለሚያዘጋጀው ነገር እኛንም ያዘጋጀናል፤ ዮዝግጁቱም አንድኛው አካል በመከራ መፈተን ነው። 

በዚህ አንፃር እስካየነው ድረስ፥ 2 ቆሮንቶስ 1፡5 በጣም አስፈላጊ ነው፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ መከራ መቀበል ነበረበት! በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ሆነን በምንሰቃይበት ጊዜ፥ የአዳኛችንን መከራዎች እየተካፈልን ነው ማለት ነው። ይህ በመስቀል ላይ «በሌሎች ምትክ መሰቃየቱን» አያመለክትም . የመስቀሉን ሞት ኃጢአት ያልነካው ምትካችን ሆኖ ሊቀበል የሚችለው እርሱ ብቻ ስለ ሆነ (1 ጴጥ. 2:21-25) ነው። እዚህ ላይ ጳውሎስ መከራዎችን የምንታገሠው፥ እኛም እንደ ክርስቶስ የአብን ሥራ በታማኝነት ስለምንሠራ ነውና «በመከራው ወደ መካፈል» (ፊልጵ. 3፡10) እያመላከተ ነበር። ይህ «ስለ ጽድቅ» (ማቴ. 5፡10-12) መከራ መቀበል ነው። 

ዳሩ ግን የመከራው መጠን ሲጨምር፥ የእግዚአብሔርም የጸጋ አቅርቦት ይጨምራል። «የተትረፈረፈ» የሚለው ቃል ሞልቶ የሚፈሰውን የወንዝ ምስል ያሳስበናል። «ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል» (ያዕ. 4፡6)። ይህ ልንረዳው የሚገባን አስፈላጊ መመሪያ ነው፡- እግዚአብሔር ለሚያስፈልገን ነገር ሁሉ የሚበቃ ጸጋ አለው፤ ዳሩ ግን ጸጋውን ተገቢው ጊዜ ከመድረሱ በፊት አይሰጠንም። «እንግዲህ ምህረትን እንድንቀበል፥ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን ፊት በእምነት እንቅረብ» (ዕብ. 4፡16)። የግሪኩ ቃል «በሚያስፈልገን ጊዜ የምንቀበለው እርዳታ፥ ወቅታዊ እርዳታ» ይለዋል። 

ስለ አንድ በእምነቱ ምክንያት ከታሰረ በኋላ በመጨረሻም በአደባባይ ተቃጥሉ እንዲሞት ስለ ተፈረደበት ብሪቱ አማኝ አንድ ጊዜ አንብቤ ነበር። ሰውየው እንደነገ ሊቃጠል ሲል ማምሻውን ያንን የሚጠብቀውን ነዲድ እሳት ለመቋቋም የሚያበቃ ጸጋ ይኖረው እንደ ሆነ ያስብ ነበርና ለሙከራ ያህል ጣቱን በሻማ ነበልባል ውስጥ በመጨመር ብርታቱን ለካው። ሻማውም ስለ አቃጠለው እጁን በፍጥነት ስቦ መለሰው። ከዚያም ያንን ሰማዕትነትን ሞት በቆራጥነት ሊጋፈጥ ከቶውንም እንደማይችል እርግጠኛ ሆነ። ዳሩ ግን በቀጣዩ ዕለት፥ እግዚአብሔርና የሚያስፈልገውን ጸጋ ስለ ሰጠው፥ በጠላቶቹ ሁሉ ፊት በደስታ የተሞላና በድል ያሸበረቀ የሰማዕትነት ተግባር ፈጽሟል። 

አሁን 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡9ን በተሻለ ሁኔታ ልንረዳ እንችላለን፤ የእግዚአብሔርን ጸጋ በድንገተኛ ችግራችን ወቅት ልንጠቀምበት የምናከማች ከሆነ፥ በራሳችን እንጂ «በጸጋ ሁሉ አምላከ» (1ኛ ጴጥ. 5፡10) ወደ መታመን አላዘነበልንም ማለት ነው። ገንዘብ፥ ምግብ፥ እውቀትና የመሳሰሉትን እግዚአብሔር የሚሰጠን ሀብቶች በሙሉ ምናልባትም ለወደፊት ግልጋሉታችን ልናጠራቅማቸው እንችል ይሆናል። የእግዚአብሔር ጸጋ ግን ለወደፊት አይጠራቀምም። 

ይልቁንም፥ በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ጸጋ ስንለማመድ፥ በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰተው የፈሪሃ-እግዚአብሔር ባሕርይ እጅግ ትርፋማ እየሆነ ይሄዳል (ሮሜ 5፡1-5 ተመልከት)። በዚህም ባሕርያችን የመበልፀጋችን ጠቀሜታው የሚለካው፥ ለእግዚአብሔር ክብር ስንል ወደ ፊት የሚያጋጥሙንን አዳዲስ መከራዎች ለመቋቋም በሚኖረን የብቃት ደረጃ ነው። 

መከራ ወደ ክርስቶስና የእርሱ ወደ ሆነው ሕዝቡ ይበልጥ ስለሚያቀርበን፥ በመከራ ውስጥ «አንድነት» አለ። ዳሩ ግን በራስ-ወዳድነት ተይዘን ስለ ራሳችን ብቻ ማሰብ ብንጀምር መከራ ከኅብረት ይልቅ መለየትን ሊፈጥር ይችላል። በዚህ ጊዜ የሚያገናኙ ድልድዮችን ሳይሆን፥ የሚያለያዩ ግድግዳዎችን እንገነባለን። 

ስለዚህ አስፈላጊው ነገር አትኩሮትን በራስ ላይ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ላይ ማስቀመጡ ነው። እግዚአብሔር ለአንተ ምን እንደ ሆነ አስታውስ – «የርኅራኄ አባት፥ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት» (2ኛ ቆሮ. 1፡3) ነው። እግዚአብሔር ምን እንደሚያደርግልህ አሁንም አስታውስ – እርሱ መከራዎችህን ሊቆጣጠርና ለአንተ በጎነትና ለራሱም ክብር ሊለውጣቸው የሚችል ነው። በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር በአንተ በኩል የሚሠራውን ነገር በማስታወስ ለሌሎች መጽናኛ አድርጎ እንዲጠቀምብህ ፍቀድለት።

Leave a Reply

%d bloggers like this: