ክርስቲያን ካልሆኑት የተጋቡ ክርስቲያኖች (1ኛ ቆሮ. 7፡12-24)

አንዳንድ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ከጋብቻ በኋላ የዳኑ ነበሩ፤ ነገር ግን የትዳር ጓደኞቻቸው ገና ያልተለወጡ ነበሩ፤ አንዳንዶቹ በቤት ውስጥ ችግር እንደነበረባቸው የሚያጠራጥር አይደለም፤ በመሆኑም ጳውሎስን፥ «ካልዳኑ የትዳር ጓደኞቻችን ጋር በትዳር መቀጠል አለብንን? የእኛ መለወጥ ነገሮችን አይቀይርምን?» በማለት ጠየቁ። 

ጳውሎስም ሲመልስላቸው የትዳር ጓደኞቻቸው እብረው ለመኖር እስከፈቀዱ ድረስ ካልዳኑ የትዳር ጓደኞቻቸው ጋር በትዳር መቀጠል እንዳለባቸው አሳሰበ። ደኅንነት የጋብቻን አቋም አይቀይርም፤ ሊያደርገው የተገባ ነገር ቢኖር፥ የጋብቻን ግንኙነት ማሻሻል ነው። (ጴጥሮስ በ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡1-6 ያልዳኑ ባሎች ለነበሩአቸው ሚስቶች የሰጠውን ምክር ልብ በል)። ጋብቻ በመሠረቱ ሥጋዊ ግንኙነት ስለሆነ («አንድ ሥጋ ይሆናሉ» – ዘፍ. 2፡24)፥ ሊቋረጥ የሚችለውም በሥጋዊ ምክንያት ነው። ዝሙት እና ሞት እንዲህ ያሉ ሁለቱ ምክንያቶች ናቸው (ቁ. 39)። 

እያወቁ ያልዳነን ሰው ማግባቱ ለክርስቲያን ሰው አለመታዘዝ ነው። (በቁ. 39 «በጌታ ይሁን እንጂ» የሚለውን እና 2ኛ ቆሮ. 6፡14 ላይ ያለውን ልብ በል)። ነገር ግን አንድ ሰው ከጋብቻው በኋላ ክርስቲያን ከሆነ፥ ችግሮችን ለማስወገድ ሲል ብቻ ጋብቻውን ማቋረጥ የለበትም። እንዲያውም፥ ጳውሎስ ክርስቲያን የሆነው ወገን ባልዳነው ላይ መንፈሳዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አጽንኦት ሰጥቶበታል። እያንዳንዱ ሰው ለክርስቶስ የግሉን ውሳኔ ማድረግ ስላለበት ቁጥር 14 ያልዳነው ወገን በአማኙ ወገን አማካኝነት ይድናል ብሎ አያስተምርም። ይልቅ፥ አማኙ በቤት ውስጥ የሚያሳድረው መንፈሳዊ ተጽዕኖ ያልዳነውን ወገን ወደ ደኅንነት ሊመራ ይችላል ነው። 

የልጆችስ ሁኔታ እንዴት ነው? እንደገና ትኩረቱ የተሰጠው መንፈሳዊ ሰው በሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ ነው። አማኝ የሆኑት ባል ወይም ሚስት ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ራሳቸውን የሰጡ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ በመኖራቸው ምክንያት ከጊዜ በኋላ ፍቅረኞቻቸው አዳኝን ሲያምኑ ለማየት መብቃታቸውን በግል አገልግሎቴ ተመልክቼአለሁ። 

ደኅንነት የጋብቻን አቋም አይቀይርም። የሚስት ክርስቲያን መሆን ጋብቻውን ተቀባይነት የሚያሳጣው ከሆነ፥ በቤት ያሉ ልጆች ሕጋዊነትን ያጣሉ «ርኩሳን» በቁጥር 14)። በሌላ መልኩ ክርስቲያኑ ወገን ለጌታ ታማኝ ከሆነ፥ እነዚህ ልጆች አንድ ቀን ሊጸኑ ይችላሉ። 

በክርስቲያናዊ እምነት ውስጥ «ለኖርን» ይህ አዲስ ዶክትሪን በሮማውያን ዓለም ላይ የነበረውን ጫና ለመገንዘብ ያዳግተናል። ይህ የዘር እና የማኅበራዊ አቋምን ሳይለይ፥ ለሁሉም ሰው ሊሆን የሚችል ትምህርት ነው። በሮማ ግዛት ባሪያዎችና ጨዋዎች፥ ወንዶችና ሴቶች፥ ሀብታምና ድሀ በእኩልነት የሚያመልኩበት ጉባኤ ቢኖር ምናልባት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነበረች (ገላ. 3፡28)። ይሁንና ይህ አዲስ እኩልነት ከራሱ ጋር አንዳንድ ግራ መጋባቶችንና ችግሮችን አመጣ፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹን ጳውሎስ ከቁጥር 17-24 ባለው ክፍል መፍትሔ ሰጥቶባቸዋል። 

ጳውሎስ ያስቀመጠው መርህ ይህ ነው፡ ምንም እንኳ ሁሉም ክርስቲያኖች በክርስቶዕ አንድ ቢሆኑም፥ እያንዳንዱ ጌታ ሲያድነው በነበረው ጥሪ መቆም ወይም መቀጠል አለበት። አይሁድ አማኞች አሕዛብ ለመሆን ጥረት ማድረግ የለባቸውም (የቃል ኪዳኑን ሥጋዊ ምልክት በመፋቅ)፤ አሕዛብ ደግሞ አይሁድ ለመሆን መጣር አልነበረባቸውም (በመገረዝ)። ባሪያዎች በክርስቶስ ካገኙት እኩልነት የተነሣ ብቻ ከክርስቲያን አሳዳሪዎቻቸው አርነትን መጠየቅ ተገቢያቸው አልነበረም። ይሁንና ክርስቲያን ባሪያዎች ከተቻላቸው አርነታቸውን ለማግኘት እንዲጥሩ መክሮአቸዋል። ምናልባት ይህ በግዢ የሚገኝ ሳይሆን አልቀረም። ይህ መርህ ራሱ ካልዳኑ ወገኖች ጋር ለተጋቡ ክርስቲያኖችም ተግባራዊ ነው። 

ነገር ግን ያላመነው ወገን ለቅቆ ቢሄድስ? ቁጥር 15 መልስ አለው። ክርስቲያኑ ወገን በአንድ ለመሆን አይገደድም። የተጠራነው ለሰላም ነው፤ በሰላም ለመኖር የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን (ሮሜ 12፡18)፤ ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታ ሰላም የማይቻልበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል። ያልዳነው ወገን ቢለይ ወይም ብትለይ፥ ክርስቲያን ከመጸለይ ና ላጌታ ባለው ታማኝነት ከመጽናት ያለፈ የሚያደርገው ብዙ ነገር የለውም። 

መለየቱ ለክርስቲያኑ ወገን የመፋታትን እና እንደገና የማግባትን መብት ይሰጠዋልን? ጳውሎስ አላለም። ያላመነው ወገን ከሌላ የትዳር ጓደኛ ጋር መኖር ከጀመረስ? ያ ዝሙት ስለሆነ ለፍቺ ምክንያት ይሰጣል። ነገር ግን በዚህ ጊዜም እንኳ፥ ከቁጥር 10–11 የተጻፈው የሚያበረታታው ይቅርታንና የትዳርን ተመልሶ ማቆም ነው። ጳውሎስ ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሙሉ አላነሣም። ያስቀመጠው መንፈሳዊ መርህን እንጂ ዝርዝር ትእዛዛትን አይደለም። 

የሁኔታዎች መለዋወጥ ሁልጊዜም ለችግሩ መልስ ነው ብለን ወደ ማሰቡ እናዘነብላለን። ነገር ግን የሁሉም ችግር ሥር፥ በልብ ውስጥ ያለ ችግር ነው። ብዙ ጊዜ ችግሩ በውስጣችን እንጂ በዙሪያችን አይደለም። የትዳር ጓደኛሞች በፍቺ አልፈው ስአዲስ ሁኔታዎች ደስታን ሲሹ፥ ዳሩ ግን በመጨረሻ ችግራቸውን ተሸክመው የሚዞሩ መሆናቸውን ወደ መገንዘቡ ብቻ ሲደርሱ መታዘብ ችዬአለሁ። እንድ ክርስቲያን ጠበቃ እንድ ጊዜ እንዲህ አለኝ፥ «ከፍቺ የሚጠቀሙ ሰዎች ቢኖሩ ጠበቆች ብቻ ናቸው!»

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d