ደኅንነታችን በመለኮት የተጠቃለሉትን ሦስቱንም አካላት ይመለከታል (1ኛ ጴጥ. 1፡2፤ ኤፌ 1፡3-14)። የአብ የጸጋ ምርጫ፥ የወልድ የፍቅር መሥዋዕት፥ እና የመንፈስ ቅዱስ የመውቀስ እና የማደስ አገልግሎት ሳይኖር ልትድን አትችልም። «በእግዚአብሔር አምናለሁ» ማለቱ በቂ አይደለም። ምን ዓይነት እግዚአብሔር ነው? የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ «አምላክ እና አባት» (ኤፌ. 18) ካልሆነ በቀር ደኅንነት ሊኖር አይችልም።
ይህ የደኅንነታችን አሀዱ ሥሉሳዊ ገጽታ የደኅንነታችንን እንዳንድ ምሥጢራት የበለጠ እንድንረዳ ያደርገናል። ስለ መለኮታዊ ምርጫ እና ቅድሚያ ውሳኔን በተመለከተ ሲሰሙ ብዙ ሰዎች ግራ ይገባቸዋል (ወይም ይደነግጣሉ)። አብን በተመለከተ ዓለም ከመመሥረቱ እስቀድሞ በክርስቶስ ሲመርጠ ድቼአለሁ (ኤፌ. 1፡4)፤ ነገር ግን በዳንኩበት ምሽት ስለዚህ የማውቀው ምንም ነገር አልነበረም! ይህ የእግዚአብሔር ድንቅ ዘላለማዊ ዕቅድ ስውሩ ክፍል ነበር።
እግዚአብሔር ወልድን በተመለከተ ደግሞ፥ ስለ እኔ በመስቀል ላይ ሲሞት ድኜአለሁ። እርሱ የሞተው ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ነው፤ ሆኖም ግን ዓለም በሙሉ አልዳነም። መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው። መንፈስን በተመለከተ እኔ የዳንኩት ግንቦት 12 ቀን 1945 ዓ.ም. በወጣት ለክርስቶስ ጉባኤ ላይ ቢል ግሬሃም (ያኔ ወጣት ወንጌላዊ ነበሩ) ወንጌልን ሲሰብኩ በሰማሁ ጊዜ ነበር። ያኔ ነበር መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ከልቤ ውስጥ ሲያዋህደው፥ ያመንሁትና እግዚአብሔርም ያዳነኝ።
ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ አራት ዐበይት አገልግሎቶች አመልክቶአል።
መንፈስ በአማኞች ውስጥ ይኖራል (2፡12)። ኢየሱስ ክርስቶስን ባመንህበት በዚያች ቅጽበት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ አካልህ ውስጥ በመግባት ቤተ መቅደሱ አድርጎታል (1ኛ ቆሮ. 6፡19-20)። እርሱም ወደ ክርስቶስ አካል ውስጥ አጠመቀህ (እንድ አደረገህ) (1ኛ ቆሮ. 12፡13)። አትሞሃል (ኤፌ. 1፡13-14) ደግሞም ከአንተ ጋር ይኖራል (ዮሐ 14፡16)። እርሱ ለአንተ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።
መንፈስ ቅዱስ የአርነት መንፈስ ነው (2ኛ ቆሮ. 3፡17)። ከዚህ ዓለም ተጠርተን ስለተለየን እና የዓለም ንብረት መሆናችን ስላከተመ (ዮሐ 17፡14፥16) የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። ከሰይጣን ሥልጣን እና ከእርሱ ሥርዓተ ዓለም ሥር መሆናችን እብቅቷል።
«እንደገና ለፍርሃት የባርነት መንፈስን አልተቀበልንም» (ሮሜ 8፡15)። መንፈስ ቅዱስ በፍቅር ያገለግለናል እናም አብን ለእኛ እውን ያደርግልናል። ይህ ከ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡7 ጋር ይያያዛል «እግዚአብሔር የኃይል እና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና» (2ኛ ጢሞ 1፡7)። መንፈስ በውስጣችን ስለሚኖር ምን ዓይነት መንፈሳዊ ሀብት ነው የያዝነው!
መንፈስ ይመረምራል (2፡10-11)። በአንተ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ እኔ ላውቅ አልችልም፤ ነገር ግን በአንተ ውስጥ ያለው የሰው (ሰብአዊ) መንፈስ ያውቃል። በሆነ ሁኔታ ወደ እግዚአብሔር ማንነት ውስጥ እስካልገባሁ ድረስ «የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች» ማወቅ አልችልም። ይህን እኔ ማድረግ አልችልም እግዚአብሔር ግን በመንፈሱ ወደ ስብዕናዬ ገብቷል። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እያንዳንዱ አማኝ የእግዚአብሔር ሕይወት ተካፋይ ይሆናል።
መንፈስ ቅዱስ «የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች» ያውቃል፤ ደግሞም ለእኛ ይገልጽልናል። ቁጥር 10 ላይ «የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገሮች» የሚለው «እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ያዘጋጀው» (ቁ 9) በሚል የተገለጸ ሌላኛው አባባል ነው። እግዚአብሔር በእኛ ያቀደውን የጸጋውን በረከት ሁሉ ዛሬውኑ እንድናውቅ ይፈልጋል።
መንፈስ ያስተምራል (2፡13)። ኢየሱስ መንፈስ እንደሚያስተምረን (ዮሐ 14፡26) እና ወደ እውነት እንደሚመራን (16፡13) ተስፋ ሰጥቶአል። ነገር ግን እዚህ ላይ ያለውን ቅደም ተከተል በጥንቃቄ ልብ ልንል ይገባል። መንፈስ ጳውሎስን ከቃሉ አስተማረው፤ ከዚያም ጳውሎስ አማኞችን አስተማራቸው። የእግዚአብሔር እውነት የሚገኘው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ነው። እነዚህ መንፈሳዊ እውነቶች ደግሞ ልዩ በሆኑ ቃላት ውስጥ እንደተሰጡ ማስተዋሉ በጣም ተፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ካረፈባቸው አሳቦች በላይም የእግዚአብሔር መንፈስ ያረፈባቸውን ቃላትም እናገኛለን። «የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና» (ዮሐ 17፡8)።
አራቱ ልጆቻችን እያንዳንዳቸው የተለያዩ ሙያዎች አሉአቸው። መጋቢ፥ ነርስ፥ ኤሌክትሮኒክ ዲዛይነር እና በአንድ የንግድ ድርጅት ውስጥ ጸሐፊ። እያንዳንዳቸው ስኬታማ ለመሆን የተለዩ ቃላትን መማር ነበረባቸው። በደንብ የምረዳው መጋቢውን ብቻ ነው።
ስኬታማ ክርስቲያን የመንፈስን ቃላት በመማር ይጠቀምባቸዋል። መጽደቅን፥ መቀደስን፥ ልጅ መሆንን፥ ሞገስ ማግኘትን፥ መመረጥን፥ በኃይል መሞላትን እና የመሳሰሉትን ትርጓሜአቸውን ያውቃል። የእግዚአብሔርን ቃላት በማወቅ የእግዚአብሔርን ቃል እና ለሕይወታችን ያለውን ፈቃዱን ወደ ማወቅ እንሸጋገራለን። የምሕንድስና ተማሪ የኬሚስትሪ፥ የፊዚክስ ወይም የኤሌክትሮኒክስ ቴክኒካዊ ቃላትን የሚያውቅ ከሆነ፥ በመንፈስ የተማሩ ክርስቲያኖች የክርስቲያናዊ እውነትን ቃላት ለመያዝ ለምን ይከብዳቸዋል?
እንዲህም ሆኖ የቤተ ክርስቲያን አባላት፥ «ዶክትሪን አታስተምር። የሚያበረታቱንን ልብ አሟሟቂ ስብከቶችን ብቻ ስጠን!» ሲሉ እሰማለሁ። በምን ላይ የተመሠረቱ ስብከቶችን? በዶክትሪን ላይ ካልተመሠረቱ ምንም ፋይዳ አይሰጡም! «ዶክትሪን እኮ ድንዛዜ ነው» በማለት ሰዎች ያማርራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ አቀራረብ ሆኖ ከቀረበ ይህ አይከሰትም። ለእኔ ዶክትሪን አስደሳች ነው! መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት መቻል እና «የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች» (1ኛ ቆሮ. 2፡10) መንፈስ እንዲያስተምረን መፍቀድ ምንኛ አርኪ ነው!
መንፈስ አማኙን የሚያስተምረው እንዴት ነው? «መንፈሳዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊው ጋር» ያነጻጽራል። ምን እንዳስተማረን ያስታውሰናል (ዮሐ. 14፡26)፥ ያንን እውነት ከአዲስ ነገር ጋር ያነጻጽራል፤ ከዚያም ወደ አዲስ እውነት እና የአሮጌው እውነት አዲስ አጠቃቀም ይመራናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ፊት ቁጭ ብሎ መንፈስ የእግዚአብሔርን እውነት እንዲገልጥ ማድረግ ምንኛ ደስ ይላል? ችግሩ ብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ፀጥተኛ ጥሞና ለማድረግ በጣም ሥራ ይበዛባቸዋል። እንዴት ያለ ብልጽግና ነው የሚያጡት!
መንፈስ ቅዱስ «ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል» (ማቴ. 13፡52)። አዲሱ ሁልጊዜ የሚወጣው ከአሮጌው ሲሆን አሮጌውን የበለጠ እንድንረዳ ያግዘናል። አንደኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሌላው ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ እግዚአብሔር አሮጌዎቹን ጠልቀን የምንገባበትን አዲስ ብልጭታ ይሰጠናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቱን የመሠረተው በብሉይ ኪዳን ላይ ነበር፤ ሆኖም ግን ያስተማረው ነገር በጣም ወቅታዊና አስደሳች በመሆኑ ሕዝቡ በትምህርቱ በጣም ተደነቁ።
በየዕለቱ ቃል ለማንበብና ጥሞና ለማድረግ ጊዜ እንድትመድብ ላሳስብህ እወዳለሁ። በንባብህ የማይዛባ መርሐ ግብርን በመከተል ለመጸለይ፥ ለማሰብ እና ጥሞና ለማድረግ ጊዜ ውሰድ። የእግዚአብሔር መንፈስ ቃሉን እንዲመረምርና እንዲያስተምርህ ፍቀድለት። መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ዶክትሪን ጥናትና ተዛምዶ ሕይወትህን ሊለውጥ ይችላል።
መንፈስ እማኙን ያጎለምሰዋል (2፡14-16)። እዚህ ላይ የቀረበው ንጽጽር በዳነ ሰው («መንፈሳዊ» በተባለው ምክንያቱም መንፈስ በውስጡ ስለሚኖር) ና ባልዳነ ሰው («ተፈጥሮአዊ» በተባለው ምክንያቱም መንፈስ በውስጠጡ ስለሌለ) መካከል ነው። ሰ 3፡1-4 ላይ፥ ጳውሎስ ሦስተኛ ዓይነት ሰውን ያስተዋውቃል፤ «ሥጋዊ ሰው»። ይህ ያላደገ ክርስቲያን ነው፤ ይህ ሰው በሕፃንነት ደረጃ የሚኖር ነው ምክንያቱም ቃሉን ስለማይመገብ አያድግም።
በአንድ ወቅት፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን የተፈጥሮ ነገሮችን ብቻ የሚያደርግ «ተፈጥሮአዊ ሰው» ነበር። አዳኝን ባመንን ጊዜ፥ መንፈስ ሲገባብን ወደ መንፈሳዊነት ተሸጋገርን። ከዚህም የተነሣ በመንፈስ ዓለም መኖርን ቻልን። ከዚያ በኋላ ማደግ ነበረብን! ያልዳነ ሰው ስለማያምናቸው ና ስለማይረዳቸው የመንፈስን ነገሮች ሊቀበል አይችልም። ነገር ግን ክርስቲያን ዕለት ተዕለት የመንፈስን ነገሮች ስለሚቀበል፥ ያድጋል ይጎለምሳልም።
ከብስለት ምልክቶች አንዱ የመመርመር ብቃት ነው- ይህም ከገጻዊው ሕይወት ወደ ውስጥ በመዝለቅ ነገሮችን ባሉበት ደረጃ በትክክል የማየት ችሉታ ነው። ያልዳኑ ሰዎች የሚጓዙት በማየት ስለሆነ ምንም የሚታይ ነገር ያጣሉ። በመንፈሳዊ ነገር የታወሩ ናቸው። በሳሉ ክርስቲያን በመንፈሳዊ እውቀቱ ያድጋል እናም (በመንፈስ እርዳታ) የእግዚአብሔርን ፈቃድ ና አሳብ በበለጠ የማወቅን ችሎታ ያዳብራል። ቆሮንቶሳውያን ይህ እውቀት ይጎድላቸው ነበር። በመንፈሳዊ ነገር ምንም እውቀት አልነበራቸውም።
«የክርስቶስ ልብ አለን» ማለት የማንሳሳት ና በሌሎች ሰዎች ሕይወት የእግዚአብሔርን ቦታ እንተካለን ማለት አይደለም። ማንም እግዚአብሔርን አያዝዝም! (ጳውሎስ ኢሳይያስ 40፡13ን ጠቅሷል። ሮሜ 11፡33-36 በተጨማሪ ተመልከት።) «የክርስቶስ ልብ አለን» ማለት ሕይወትን ከአዳኙ እይታ አቅጣጫ መመልከት፥ የእርሱን ፍላጎቶችና እሴቶች በልብ ማኖር ማለት ነው። እንደ ዓለም ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚያስብ ማሰብ ማለት ነው።
ያልዳነው ሰው ክርስቲያኑን ሊረዳ አይችልም፤ የሚኖሩት በሁለት በተለያዩ ዓለማት ነው። ነገር ግን ክርስቲያኑ ያልዳነውን ሰው ይረዳዋል። ቁጥር 15 ያልዳኑ ሰዎች በአማኙ ሕይወት ውስጥ ነቀፋን አያዩም ማለትን አያመለክትም (ብዙ ጊዜ ያዩታል)። ነገር ግን ያልዳነው ሰው የክርስቲያኑ ሕይወት ምን እንደሆነ ወደ ሙሉ መረዳት ሊዘልቅ አይችልም ማለት ነው። እኔ አዲሱን የአሜሪካን ስታንዳርድ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እወዳለሁ፡- «ነገር ግን መንፈሳዊ የሆነ ሰው የሁሉንም ነገር ዋጋ ይተምናል፥ እርሱ ራሱ ግን በማንም እይታመንም»። «በማንም» የሚለው ቃል ሌሎች ክርስቲያኖችንም የሚጠቀልል ነው። በእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት ላይ መንፈሳዊ አምባገነን እንዳንሆን በጣም መጠንቀቅ አለብን (2ኛ ቆሮ. 1፡24)።
የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ ተአምራዊ ስጦታዎች ስለተሸፈኑ መሠረታዊውን የመንፈስ አገልግሎት ችላ ይሉት ነበር። በመንፈስ ላይ በነበራቸው አጽንኦት ምክንያትም አብን ና ወልድን ችላ ይሉአቸው ነበር።
ሁሉንም መጥነው የሚይዙ የተባረኩ ናቸው! ደግሞም «የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ» የሚረዱ ና የሚያካፍሉት የተባረኩ ናቸው (የሐዋ 20፡27)።
ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው