ደኅንነት የተገዛው በልጁ ሲሆን የታቀደው ግን በአብ ነው። ስለ «ቀላል ወንጌል» የሚናገሩ ሰዎች ትክክልም ስሕተትም ናቸው። አዎን፥ የወንጌል መልእክት ያልተማረ ሃይማኖት የለሽ ሰው እውቆት፥ አምኖ እስከሚድን ቀላል ነው። ነገር ግን በጣም የመጠቀ የሥነ መለኮት አዋቂ እንኳ እስከማይዘልቅበት ድረስ በጣም የጠለቀ ነው።
በጣም የረቀቀውን አእምሮ እንኳ የሚቋቋም «የእግዚአብሔር ጥበብ» በወንጌል ውስጥ ይገኛል። ይሁንና፥ ይህ ጥበብ ለጠፉ ብዙኃን ኃጢአተኞች ወይም ላልበሰሉ አማኞች አይደለም። በእግዚአብሔር ቃል እውቀታቸው እያደጉ ላሉ በሳል አማኞች ነው። (በቁጥር 6 «ሰበሰሉት» የሚለውን ከ 3፡1–4 ጋር አነጻጸር።) ምናልባት ጳውሎስ እዚህ ላይ ምላሽ የሚሰጠው ማራኪ ንግግርና በጥልቀት የማስተማር ክህሎት የነበረውን አጵሎስን (የሐዋ. 18፡24-28) ለሚደግፉ የቤተክርስቲያን ሰዎች ሳይሆን አይቀርም።
እስኪ የዚህን ጥበብ ባሕርያት እንወቅ።
ይህ ጥበብ የሚመጣው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው (2፡7)። ይህ ጥበብ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለፍጥረቱ ስላለው ሰፊ ዘላለማዊ ዕቅድ ለበሳሉ ቅዱስ ሰው ይናገራል። «ከዚች ዓለም (የዘመኑ) ገዢዎች የላቁ ጠበብት የተባሉትም ይህን ጳ ውሎስ ከእግዚአብሔር የተካፈለውን አስደናቂ ጥበብ ሊፈላሰፉት ወይም ሊደርሱበት አልቻሉም።
ይህ ጥበብ የተሰወረ ነበር (2፡7)። ስለዚህ ነው ምሥጢር የተባለው። በአዲስ ኪዳን ምሥጢር ማለት «የተቀደሰ ሕቡዕ ነገር» ማለት ነው። ይህ ባለፉት ዘመናት የተደበቀና አሁን በእግዚአብሔር ሕዝብ የተገለጠ እውነት ነው። ከወንጌል ጋር የሚዛመዱትን ልዩ ልዩ ምሥጢራት ለማካፈል እግዚአብሔር በልዩ መንገድ የተጠቀመው ጳውሎስን ነበር (ኤፌ. 3 ተመልከት)፤ ነገር ግን «እኛ» የሚለውን የተውላጠ ስም ድግግሞሽ አስተውል። ጳውሎስ ሌሎችን ሐዋርያት ከዚህ ሁኔታ አላገለላቸውም።
ይህ ጥበብ የእግዚአብሔርን ቅድሚያ ውሳኔ ያካትታል (2፡7)። ይህ ማለት እግዚአብሔር ዕቅዱን ሠራው፤ በእንቅስቃሴ ላይ አደረገው፤ ከዚያም ፍጻሜ ማግኘቱን ይከታተለዋል ማለት ነው። ታላቁ የቤዛነት ዕቅድ እግዚአብሔር ሰው ያደረገውን ከተመለከተ በኋላ ያመጣው የችኮላ ረፋድ አሳብ አይደለም። ምንም እንኳ ይህ አእምሮአችንን ቢያሸብረውም፥ የመለኮታዊ ምርጫንና የቅድሚያ ውሳኔን (የሚሆነው ሁሉ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነና ሰውም የማይቀይረው መሆኑ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ መቀበል አለብን። ምንም እንኳ ለክፋት ድርጊታቸው ሰዎች በኃላፊነት ቢጠየቁበትም፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትም አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነ ነበር (የሐዋ. 2፡22-23፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡18-20)። የውጤታማ የጸሎት ሕይወት ምሥጢራት አንዱ የእግዚአብሔርን ዓላማዎች በእምነት መጨበጥ ነው (የሐዋ. 4፡23-31)።
ይህ ጥበብ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መክበር ያስከትላል (2፡7)። የዚህ «የዘመናት ዕቅድ» ከፍተኛ ገለጣዎች አንዱ በኤፌሶን 1 የሚገኘው ነው። በዚያ ምንባብ ውስጥ ጳ ውሎስ ሦስት ጊዜ፥ ይህ ሁሉ የተደረገው ለእግዚአብሔር ክብር ነው ይላል (ቁ. 6፥12፥ 14)። ይህንኑ የእግዚአብሔር ክብር እኛም አንድ ቀን የምንካፈል መሆኑ በጣም የሚያስደንቅ አሳብ ነው! (ዮሐ 17፡22-24፤ ሮሜ 8፡28-30ን ተመልከት።)
ይህ ጥበብ ካልዳነው ዓለም የተሰወረ ነው (2፡8)። የዚህ ዓለም [የዘመኑ] ገዢዎች ብሎ ጳውሎስ የሚጠቅሳቸው እነማን ናቸው? ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በመንግሥት ሥልጣን የነበሩት ያለጥርጥር እርሱ ማን እንደነበር አላወቁትም (የሐዋ. 3፡17፤ 4፡25 28)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» (ሉቃ. 23፡34) ብሎ ሲጸልይ ይህን እውነት እያስተጋባ ነበር። በእርግጥ አለማወቃቸው ለኃጢአታቸው ይቅርታን ሊያስገኝላቸው አልቻለም፤ ምክንያቱም ተፈላጊውን ማረጋገጫ ጌታ ሰጥቶአቸው ስለነበር ማመን ነበረባቸው።
ነገር ግን ሌላም አማራጭ ነበር። ጳውሎስ ያጣቅስ የነበረው የዚህን የአሁን ዘመን መንፈሳውያንና አጋንንታዊ ገዢዎችን ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 8፡38፤ ቆላ. 2፡15፤ ኤፌ. 6፡12)። ይህ በተለይ በቁጥር 6 ላይ የበለጠ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም በእርግጥ ጲላጦስ፥ ሄሮድስ እና ሌሎች የዘመኑ ገዢዎች የሚታወቁበት ምንም የተለየ ጥበብ አልነበራቸውም። የዘመኑ ጥበብ ምንጩ ከሰይጣን አለቅነት ሥር የነበሩ የዘመኑ ገዢዎች ናቸው (ዮሐ 12፡31፤ 14፡30፤ 16፡11)። እርግጥ ነው፥ መንፈሳውያን ገዢዎች የሚሠሩት በሰብአዊ ገዢዎች ውስጥ እና አማካኝነት ነው። በመሆኑም ልዩነቱን እጅግም ልናጠብቀው አያስፈልግ ይሆናል (ዮሐ 13፡2፥27)።
ነገር ግን ይህ ትርጉም እውነት ከሆነ፥ ጠጣር የእሳቤ አቅጣጫዎችን ይከፍታል። ሰይጣናዊ ኃይላት፥ ሰይጣን ራሱን ጨምሮ የእግዚአብሔርን ታላቅ ዘላለማዊ ዕቅድ እላወቁትም ነበር! የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚወለድና እንደሚሞት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሊያውቁት ችለዋል። የመስቀልን አስፈላጊነት ግን ሊረዱት አልቻሉም ነበር። ምክንያቱም እነዚህ እውነቶች በእግዚአብሔር የተሰወሩ ነበሩ። እንዲያውም እነዚህ እውነቶች አሁን ለአለቆች እና ሥልጣናት እየተገለጠ ያለው በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው (ኤፌ. 3፡10)።
ሰይጣን ቀራኒዮ የእግዚአብሔር ታላቅ ሽንፈት መስሎት ነበር፤ ነገር ግን በተገላቢጦሽ ለእግዚአብሔር ታላቅ ድል ለሰይጣን ደግሞ ሽንፈት ሆነ! (ቆላ. 2፡15)። ጌታችን ተወልዶ ወደዚህ ዓለም ከመጣ ጊዜ ጀምሮ፥ ሰይጣን ሊገድለው ጥረት አድርጓል። ምክንያቱም ሰይጣን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ሰፊ ውጤት አልተረዳም ነበር። አጋንንታዊ አለቆች አውቀውት ቢሆን ኖሮ የክርስቶስን ሞት አያቀነባብሩትም ነበር። (በእርግጥ፥ ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ አካል ነበር። የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን አልነበረም።)
በመጨረሻም፥ ይህ ጥበብ ዛሬም በአማኙ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን ነው (2፡9)። ይህ ቁጥር ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው በቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት እና መንግሥተ ሰማያትን በተመለከተ ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ተዛምዶው ለዛሬው ክርስቲያን ሕይወት ነው። የሚቀጥለው ቁጥር እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች የሚገልጠው እዚሁ እና አሁኑኑ መሆኑን ግልጽ ያደርጋል።
ይህ ቁጥር በኢሳይያስ 64፡4 በማዛመድ) የተወሰደ ጥቅስ ነው። ዓውዱ በቀጥታ በምርኮ ከነበረችውና የእግዚአብሔርን ነፃ ማውጣት ከምትጠባበቀው ከእስራኤል ጋር ያዛምደዋል። የእስራኤል ሕዝብ ስለበደለ ለቅጣት ወደ ምድረ ባቢሎን ተሰድዶ ነበር። እግዚአብሔር ወርዶ ነፃ እንዲያወጣቸው ጮኹ፤ እርሱም ከ 70 ዓመታት የስደት ዘመናቸው በኋላ ጸሎታቸውን መለሰ። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕቅድ ስለነበረው መፍራት አልነበረባቸውም (ኤር. 29፡11)።
ጳውሎስ ይህን መርህ ለቤተክርስቲያን ተጠቅሟል። ያለንበት ሁኔታ የፈለገውን ይሁን የወደፊታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠበቀ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ገንዘቡ ላደረጋቸው ያሉት ዕቅዶች ፍጹም ድንቅ ስለሆኑ አእምሮአችን ሊያስበው ወይም ሊያስተውለው ይሳነዋል! እግዚአብሔር ይህንን አስቀድሞ ለክብራችን እንዲሆን ወስኖታል (ቁ 7)። ከምድር እስከ መንግሥተ ሰማይ ድረስ መንገዱ ሁሉ ክብር ነው!
እግዚአብሔርን ለሚወዱት እያንዳንዱ ቀን መልካም ቀን ነው (ሮሜ 8፡28)። መልካም ቀን መስሎ ላይታይ ወይም ላይሰማ ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ዕቅዱን በሚሠራበት ጊዜ የላቀ እንደሚሆንልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እርሱን ከመተማመን ስንጓደል፥ ወይም ሳንታዘዘው ስንቀር፥ ለእርሱ ያለን ፍቅር ሲቀዘቅዝ ያኔ ሕይወት የጽልመት ጭጋግ ትላበሳለች። በእግዚአብሔር ጥበብ ከተመላለስን፥ የእርሱን በረከቶች እናጣጥማለን።
ሁለት የወንጌል እውነቶችን እይተናል። እነዚህም ይህ መልእክት የክርስቶስን ሞት ማዕከል ማድረጉን እና የአብ ሰፊ ዕቅድ አካል መሆኑ ናቸው። በቆሮንቶስ የነበሩ እማኞች የደኅንነታቸውን ዋጋ ዘንግተው ነበር፤ ዓይኖቻቸውን ከመስቀሉ ላይ እንሥተው ነበር። በተጨማሪ በጥቃቅን ነገሮች– (የሕፃናት አሻንጉሊት በሚመስሉ) ተይዘው ነበር- ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ለነበረው ዕቅድ ታላቅነት እድናቆት አጥተው ነው። ወደ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት መመለስ አስፈላጊያቸው ነበር። በመሆኑም የጳውሎስ ቀጣዩ ነጥብ ይህን የሚመለከት ይሆናል።
ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው