ወደ ኅብረት የተጠራችሁ (1ኛ ቆሮ. 1፡10–25)

ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን የርኩሰት ችግር ከጠቀሰ በኋላ ወደ ክፍፍሉ ጉዳይ ተመለሰ። ክፍፍል በእግዚአብሔር ሰዎች መካከል ሁልጊዜ የነበረ ችግር ነው። ስለሆነም ሁሉም የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ማለት ይቻላል ይህን ርእስ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ይነኩታል ወይም ይጠቅሱታል። አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትም እንኳ እርስ በርስ ሁልጊዜ የተስማሙበት ወቅት አልነበረም። 

ከምንወዳቸው ቅዱሳን በከፍታ መኖር፥ 

ይህ በእርግጥም ነው ክብር! 

በዝቅታ መኖር ከምናውቃቸው ቅዱሳን፥ 

ያ ደግሞ ሌላ ታሪክ ነው የሚከነክን! 

በቁጥር 13፥ ጳውሎስ አንባቢዎቹን ሦስት አስፈላጊ ጥያቄዎችን ጠየቃቸው፥ ታዲያ እነዚህ ጥያቄዎች ለዚህ ረጅም አንቀጽ ቁልፍ ናቸው። 

ክርስቶስ ተከፋፍሎአልን? (1፡10-13) የግሡ ትርጉም፥ «ክርስቶስ ተከፋፍሎ የተለያዩ ክፍሎቹ ለተለያዩ ሰዎች ታድለዋልን?» የሚል ነው። ይህ አሳብ ራሱ አስጠሊታ ስለሆነ መጣል የሚገባው ነው። ጳውሎስ አንድ ክርስቶስን፥ አጵሎስ ደግሞ የተለየ ክርስቶስን፥ ጴጥሮስም እንዲሁ ሌላ ክርስቶስን አልሰበኩም። ያለው አንድ ወንጌል እና አንድ አዳኝ ብቻ ነው (ገላ. 1፡6-9)። ታዲያ ቆሮንቶሳውያን ይህን የአራት አቅጣጫ ክፍፍል እንዴት ፈጠሩት? በመካከላቸው ለምን ጠብ (“ውድድር ) ሆነ? 

አንደኛው መልስ ወንጌልን ይመለከቱት የነበረው ከፍልስፍና እቅጣጫ ስለሆነ ነው። ቆሮንቶስ «ጥበባቸውን» በማሰራጨት በሚሽቀዳደሙ አስተማሪዎች እና ፈላስፋዎች የተሞላች ነበረች። 

ሌላኛው መልስ ሰብአዊ ተፈጥሮ ሰብአዊ መሪዎችን በመከተል የመርካቱ ጉዳይ ነው። ከሚረዱን፤ አገልግሎታቸው ከሚገባን እና ከሚያስደስተን መንፈሳውያን መሪዎች ራሳችንን የበለጠ ወደ ማዛመዱ እናዘነብላለን። እነርሱ አጽንኦት የሰጡት ከቃሉ መልእክት ይልቅ ለመልእክተኛው ነበር፤ ዓይኖቻቸውን ከጌታ ላይ እንሥተው በጌታ ባሪያ ላይ አደረጉ፤ ይህ ደግሞ ወደ ውድድር መራቸው። 

ጳውሎስ በምዕራፍ 3 ላይ በእውነተኛ የእግዚአብሔር ባሪያዎች መካከል ውድድር ወይም እሽቅድምድም ሊኖር እንደማይችል ያመለክታል። ለቤተ ክርስቲያን አባላት መጋቢያንን ማወዳደር ኃጢአት ነው፥ ወይም አማኞች እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው ቀርቶ እንደ ሰዎች ደቀ መዛሙርት በመሆን ሰብአዊ መሪዎችን ከተከተሉአቸው ይህም ኃጢአት ነው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ «ሰው አድናቂ ክፍሎች» ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ግንባር ለግንባር በሚጋጭ ዓመፅ ላይ ናቸው። ከፍተኛውን ስፍራ መያዝ ያለበት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ቆላ. 1፡18)። 

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱሳን በክርስቶስ ስላላቸው አንድነት አጽንኦት ለመስጠት በርካታ ቁልፍ ቃላትን ተጠቅሞአል። የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ለአንባቢዎቹ ለማሳሰብ ወንድሞች ብሎ ጠራቸው። «የተባበራችሁ» የሚለው ቃል የተሳሰረውን የሰው አካል የሚገልጽ የሕክምና ቃል ነው። ስለዚህ፥ የአካሉ ብልቶች እንደመሆናቸው የፍቅር አንድነት ነበራቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም የታወቁ ነበሩ። ይህ ምናልባት ጥምቀታቸውን የሚያመለክት ነበር። 

«የቀሎዔ ቤተሰቦች» አባላት እነማን እንደነበሩ አናውቅም፥ ሆኖም ግን ለጽናታቸውና ለመሰጠታቸው እናደንቃቸዋለን። ችግሮችን ለመሽሽግ አልሞከሩም። ተጨንቀውባቸው ስለነበር ከችግሮቻቸው ጋር ወደ ትክክለኛው ሰው ቀረቡ፤ እንዲሁም ጳውሎስ ስለ እነርሱ መጥቀሱ አላሸማቀቃቸውም። ይህ በእነርሱ ዘንድ ብዙ ጊዜ በየቤተክርስቲያኑ እንደምናያቸው -ችግሩን የባሰ እንጂ ምንም የተሻለ እንደማያደርጉ ድርጊቶች «ምሥጢራዊ ጉዳይ» አልነበረም። 

ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመሠረተ አገልጋይ ነበር፤ በመሆኑም አብዛኛዎቹ ምእመናን በእርሱ እገልግሎት የተለወጡ ሊሆኑ ይችላሉ። አጵሎስ ጳውሎስን የተከተለ ሲሆን (የሐዋ. 18፡24-28)፥ ውጤታማ  አገልግሎትም ነበረው። ጴጥሮስ (ኬፋ) 1ኛ ቆሮ. 9፡5 ከሚዘግበው በቀር ቆሮንቶስን ስለመጎብኘቱ ምንም መረጃ የለንም። እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው የተለያዩ ባሕርያት እና ቃሉን የሚያገለግሉበትም የተለያዩ እቀራረቦች ነበሩአቸው፤ እንዲሁም ሆኖ ግን አንድ ነበሩ (3፡3-8፤ 4፡6)። 

ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? (1፡13-17) በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ጥምቀት አስፈላጊ ነገር እንደነበር ልብ በል። አንድ ኃጢአተኛ ክርስቶስን አምኖ በሚጠመቅበት ጊዜ፥ ራሱን ከቀድሞ ሕይወቱ ስለሚለይ ብዙ ጊዜ በቤተሰቡ እና በጓደኞቹ ዘንድ ተቀባይነት ያጣ ነበር። በዚያን ዘመን መጠመቅ አንድን ነገር (ዋጋ) ያስከፍል ነበር። 

ኢየሱስ ሰዎችን እንዳላጠመቀ ሁሉ (ዮሐ. 4፡1-2)፥ ጴጥሮስ (የሐዋ. 10፡48) እና ጳውሎስም እንዲሁ አዳዲስ አማኞችን እንዲያጠምቁ ለሥራ ተባባሪዎቻቸው ተዉላቸው። በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን እስከምታድግ ድረስ፥ ጳውሎስ ጥቂት የማጥመቅ ሥራ ሠርቶ ነበር፤ ሆኖም ያ የእርሱ ዋነኛ አገልግሎት አልነበረም። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚታየው ጳውሎስ ጥምቀትን ማሳነሱ ሳይሆን፥ ይልቁንም በተገቢ ስፍራው ማስቀመጡ ነበር። ምክንያቱም ቆሮንቶሳውያን የጥምቀትን ተግባር በጣም ያዋድዱት ስለነበር ነው። «እኔ በአጵሎስ ተጠምቄአለሁ!» በማለት አንዱ ሲመጻደቅ፥ ሌላው ደግሞ «የለም እኔስ በጳውሎስ ነው የተጠመቅሁት!» ይል ነበር። 

ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር የማንንም ስም ከጥምቀትህ ጋር ማዛመዱ አግባብ አይደለም። ይህን ማድረግ ክፍፍልን መፍጠር ነው። ድርጊቱ ሁሉ በጣም አስፈላጊ ይመስል፥ ለጥምቀታቸው የተለየ ሰባኪ፥ የተለየ ውኃ (ብዙውን ጊዜ ከዮርዳኖስ ወንዝ የመጣህ፥ የተለየ ቀን የሚጠቀሙ ሰዎች ስለመኖራቸው የተጻፈ ነገር አንብቤአለሁ! ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማክበርና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማዳበር ፈንታ፥ እነዚህ ሰዎች ግለሰቦችን ከፍ ከፍ በማድረግ ክፍፍልን ይፈጥራሉ። 

ቀርስጶስ በቆሮንቶስ ለነበረው ምኵራብ አለቃ ነበር (የሐዋ. 18፡8)፤ ጋይዮስ ደግሞ ምናልባት ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ አብሮት የኖረ ሰው ሳይሆን አይቀርም (ሮሜ 16፡23)። ስለ «የእስጢፋኖስ ቤተሰዎች» (1ኛ ቆሮ. 1፡16) ምናልባት በ 1ኛ ቆሮ. 16፡15-18 በከፊል ተገልጾአል። በእግዚአብሔር መጽሐፍ መጻፋቸው በቂ ስለነበር፥ ጳውሎስ ያጠመቃቸውን ሰዎች ስም ሁሉ ስመዝገብ የያዘ አይመስልም። 

ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? (1፡18-25) በቁጥር 7 የተጠቀሰው መስቀል ከሰው ጥበብ ደካማነት አንፃር የወንጌል ኃይል የተገለጸበትን ይህን ረጅም ክፍል እስተዋወቀ። በቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ይህን የክፍፍል ችግር ጳውሎስ እንዴት እንዳስተናገደው ማየቱ በጣም አጓጊ ነው። በመጀመሪያ፥ እንድ እዳኝና አንድ አካል በማለት ወደ ክርስቶስ አንድነት አመለከተ። ቀጥሎ ስለ ጥምቀታቸው አሳሰባቸው፣ ይህም በክርስቶስ አካል የመጠመቃቸው አምሳል ነበረ (12፡13)። እንዲህ አድርጎ፥ ወደ መስቀል አደረሳቸው። 

ስቅለት ዘግናኝ ሞት ብቻ አልነበረም፤ የውርደት ሞትም እንጂ። ሮማዊ ዜጋን መስቀል ሕገወጥ ነበር። እኛ ዛሬ እራት እየበላን፥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመኑ ሂትለር አይሁዳውያንን ስለፈጀበት ስለ መርዝ ጋዝ ክፍል ወይም በአሜሪካን የሞት ቅጣት ስለሚፈጸምበት ስለ ኤሌክትሪክ ወንበር እንደማንነጋገር ሁሉ፥ በጨዋ ማኅበረሰብ ውስጥ ስቅለት ተጠቅሶ አይታወቅም። 

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ቁልፍ ቃል ጥበብ ሲሆን፤ ስምንት ጊዜ ተጠቅሶአል። ጳ ውሎስ የሚናገረው ቁልፍ አሳብ ሰብአዊውን ጥበብ ከተገለጠው የእግዚአብሔር መልእክት ጋር ለመቀየጥ እንዳንዳፈር ነው። ስለ ጥበብ የሚናገረው መላው ክፍል (1፡17-2፡16) በተገለጠው የእግዚአብሔር ቃልና በሰዎች ጥበብ መካከል በርከት ያሉ ንጽጽሮችን ይሰጣል። 

የእግዚአብሔር ጥበብ በመጀመሪያ የተገለጠው በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው፤ ይሁንና ይህን ሁሉም ሰው እያየውም። ጳውሎስ መስቀልን በተመለከተ ሦስት የተለያዩ አመለካከቶች እንዳሉ አመልክቶአል። 

እንዳንዶች በመስቀል ይሰናከላሉ። ይህ የአይሁዶች አመለካከት ነበር፤ ምክንያቱም አጽንኦታቸው በተአምራታዊ ምልክቶች ላይ ስለሆነ መስቀል ደግሞ ደካማነት ሆነባቸው። ከግብፅ መውጣታቸው አንሥቶ እስከ ኤልያስና ኤልሳዕ ዘመን ድረስ የአይሁድ ታሪክ በተአምራት የተሞላ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሚያገለግልበት ወቅት፥ የአይሁድ መሪዎች በተደጋጋሚ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠይቀውት ነበር፤ እርሱ ግን እምቢ አለ። 

የአይሁድ ሕዝብ የራሳቸውን የተቀደሱ መጻሕፍት አላስተዋሉአቸውም ነበር። ጽኑ ኃይል ተላብሶ የሚመጣ እና ጠላቶቻቸውን በሞላ ድባቅ የሚመታ መሢሕ ይጠባበቁ ነበር። ይህ ሰው መንግሥትን አቋቁሞ ለእስራኤል ክብርን የሚመልስ መሆን ነበረበት። በሐዋርያት ሥራ 1፡6 ላይ የተነሣው የሐዋርያት ጥያቄ ይህ ተስፋ በአይሁድ መካከል ምን ያክል ጠንካራ እንደነበረ ያሳያል። 

በተመሳሳይ ጊዜ፥ ጸሐፊዎቻቸው መሢሑ እንደሚሠቃይ እና እንደሚሞትም ከብሉይ ኪዳን ያውቁ ነበር። እንደ መዝሙረ ዳዊት 22 እና ኢሳይያስ 53 ያሉ ምንባቦች ያመለከቱት ወደተለየ ዓይነት መሢሕ ነበር፥ ጠበብቱም እነዚህን ሁለት ተጻራሪ መሰል ገጽታዎች ሊያስታርቁ አልቻሉም። መሢሓቸው ወደ ክብሩ ከመግባቱ በፊት መሠቃየት እና መሞት እንደነበረበት (ሉቃ. 24፡13-35ን ተመልከት)፥ እንዲሁም የሚመጣውን የመሢሑ መንግሥት የቤተ ክርስቲያን ዘመን እንደሚቀድመው አልተረዱም ነበር። 

አይሁዶች ኃይልን እና ታላቅ ከብርን ይፈልጉ ስለነበር የመስቀል ደካማነት ዕንቅፋት ሆነባቸው። የተራ ወንጀለኛን የውርደት ሞት በሞተ የናዝሬቱ ሥራአጥ አናጢ ላይ ሰው እንዴት እምነቱን መጣል ይቻል? ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል «የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው» (ሮሜ 1፡16)። መስቀል የድካም ምስክርነት ከመሆን ይልቅ ከፍተኛ የኃይል መሣሪያ ነው! ለነገሩ፥ «የእግዚአብሔር ድካም [በመስቀል] ከሰው ይልቅ ይበረታልና» (1ኛ ቆሮ. 1፡25)። 

እንዳንዶች በመስቀል ይስቃሉ። ይህ የግሪኮች ምላሽ ነበር። ለእነርሱ መስቀሉ ሞኝነት ነበር። ግሪኮች ጥበብን ያጠብቃሉ፤ ዛሬም እንኳ የግሪክ ፈላስፋዎችን ጥልቅ ጽሑፎች እናጠናለን። ሆኖም ግን እነርሱ በመስቀል ውስጥ ምንም ጥበብ አላዩበትም፥ ምክንያቱም መስቀልን የተመለከቱት በሥጋዊ ዓይን ነበር። ከእግዚአብሔር አቅጣጫ ተመልክተውት ቢሆን ኖሮ፥ ታላቅ የእግዚአብሔር የደኅንነት ዕቅድ የተገለጠበትን ጥበብ ባወቁት ነበር። 

ጳውሎስ ሦስት ሰዎች ምስክርነት እንዲሰጡ ጠየቀ። ጠቢቡ (ሊቁ)፥ ጸሐፊው (ተርጓሚው እና ዘጋቢው)፥ እና ተቀናቃኙ (ፈላስፋው እና ተከራካሪው)። ሁላቸውንም አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው፥ በሰብአዊ ጥበብ ባካሄዳችሁት ጥናት እግዚአብሔርን በግል ወደ ማወቅ ደርሳችኋልን? ሁላቸውም አይደለም ብለው መመለስ አለባቸው! መስቀሉን እንደ ሞኝነት መቁጠራቸው እና በእርሱም ላይ መሳቃቸው ራሱ እየጠፉ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው። 

እግዚአብሔር ለሰዎች ጥበብ ትልቅ «ዜሮ_ክስረት» መስጠቱን ለማረጋገጥ ጳውሎስ በቁጥር 19 ላይ ኢሳይያስ 29፡14 ን ይጠቅሳል። በማርስ ኮረብታ (አርዮስፋጎስ) ንግግሩ ጳውሎስ የግሪክ እና የሮማውያን ታሪክ ያለማወቅ ዘመን» እንደነበር ለፈላስፋዎች ለመንገር ደፍሮአል (የሐዋ. 17፡30)። ምንም አያውቁም ማለቱ አልነበረም፤ ምክንያቱም የግሪክ ተመራማሪዎች አንዳንድ ውጤቶችን ማስመዘገባቸውን በሚገባ ያውቅ ነበርና። ይሁንና ጥበባቸው እግዚአብሔርን እንዲያገኙት እና ደኅንነትንም እንዲለማመዱ እላስቻላቸውም። 

አንዳንዶች የመስቀሉን ኃይል እና ጥበብ የሚያምኑ እና የሚለማመዱ ናቸው። ጳውሎስ ከአይሁድ አድማጭ ወደ ግሪክ አድማጭ በሚመለስበት ጊዜ መልእክቱን አልቀየረም። የተሰቀለውን ክርስቶስን ሰበከ እንጂ። «የስብከት ሞኝነት» (1ኛ ቆሮ. 1፡21) ማለት የስብከት ተግባር ሞኝነት ነው ማለት አይደለም፤ ይልቅ የመልእክቱ ይዘት ማለት እንጂ። አዲሱ ዓለም አቀፍ እትም (NIV) «በተሰበከው ነገር ሞኝነት ምክንያት» በማለት ያስቀምጠዋል፤ ይህ ደግሞ እውነት ነው። 

በእግዚአብሔር ጸጋ የተጠሩ፥ እና በእምነት ምላሽ የሰጡ (2ኛ ተሰ. 2፡13-14ን ተመልከት) ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑን ያውቁታል። ይህ የከብቶች በረቱ፥ ወይም የቤተ መቅደሱ፥ ወይም የገበያ ስፍራው ክርስቶስ ሳይሆን ነገር ግን የመስቀሉ ክርስቶስ ነው። እግዚአብሔር የሰውን ጥበብ ሞኝነት እና የሰውን ኃይል ደካማነት የገለጠው በክርስቶስ ሞት ነው። 

ወደ ኅብረቱ የተጠራነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት ነው። እርሱ ለእኛ ሞተ፤ በስሙ ተጠመቅን፤ ከእርሱ መስቀል ጋር ራሳችንን እንድ አደረግን። ይህ ለመንፈሳዊ ኅብረት እንዴት ያለ ድንቅ መሠረት ነው!

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d