ዕድሎች (1ኛ ቆሮ. 16፡5-9)

«እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ» (ኤፌ. 5፡15-16)። ጳውሎስ እንደ ገንዘብ አጠቃቀሙ ሁሉ በጊዜ አጠቃቀሙም ጥበበኛ ነበር። አንድ ሰው የዘመኑ ኅብረተሰብ ዋና ሥራው ጊዜን መግደል ነው ብሏል፥ ነገር ግን ማንም ክርስቲያን ጊዜን መግደልና ዕድሎችን ማባከን አይችልም። 

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ላሉት ወዳጆቹ ስለ ወደ ፊት ጉዞውና አገልግሎቱ ነገራቸው። አባባሎች እርግጠኞች አለመሆናቸውን ልብ ማለቱ ይጠቅማል። «የሚገባኝ ቢሆን. . . ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ . . ምናልባት. . . ተስፋ አደርጋለሁ. . .።» በእርግጥ አጠቃላይ ዕቅዱ በእግዚአብሔር የቸርነት ምሪት ላይ የቆመ ነው። «ጌታ ቢፈቅደው» ሲል መጻኢ ዕቅዶቹ ጳውሎስ የነበረው አቋም በያዕቆብ 4፡13-17 ካለው ትእዛዝ ጋር ይስማማል። 

ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በሚጽፍበት ጊዜ በኤፌሶን ነበር። የእርሱ ዕቅድ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት ወደ መቄዶንያ መሄድ (በቁጥር 5 ሳልፍ የሚለው «ለታቀደ አገልግሎት መጓዝ» ማለት ነው)፥ ክረምቱን በቆሮንቶስ ማሳለፍ፥ ከዚያም መዋጮውን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ነበር። ከኅዳር እስከ የካቲት በመርከብ መጓዝ የማይቻልበት ጊዜ ነበር፤ ስለዚህ በቆሮንቶስ መቆየትና ከወዳጆቹ ጋር መሆን ለጳውሎስ የሚመች ሆነ። በቤተ ክርስቲያን መፈታት የነበረባቸው አንዳንድ ችግሮች ነበሩና ጳውሎስ መጥቶ መሪዎችን እንደሚረዳ ቃል ገብቶ ነበር (11፡34)። 

ይሁንና፥ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ጳውሎስ ዕቅዱን ሁለቴ እንዲከልስ ግድ ብለውታል። ሁለተኛው ዕቅዱ» ቆሮንቶስን መጎብኘት፥ ከዚያም ወደ ይሁዳ እየተጓዘ እግረ መንገዱን ለሁለተኛ ጊዜ በቆሮንቶስ በማለፍ ወደ መቄዶንያ መጓዝ ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡15-16)። ከአንድ ረጅም ጉብኝት ይልቅ ሁለት አጫጭር ጉብኝቶችን በቀደ፤ ነገር ግን እንዲህም ሆኖ እንኳ ዕቅዱ ተግባራዊ አልነበረም። «ሦስተኛው ዕቅዱ አስቸኳይና አስቸጋሪ የቆሮንቶስ ጉብኝት ነበር፥ ከዚያ በኋላ ወደ ኤፌሶን ተመለሰ። ከዚያም በኋላ ቲቶን (ወደ ቆሮንቶስ ተልኮ የነበረውን፥ 2ኛ ቆሮ. 2፡12-13፤ 15) ለመጠባበቅ ወደ ጢሮአዳ ሄደ፥ መቄዶንያንም ጎበኘና ወደ ይሁዳ አመራ። በቆሮንቶስ እርሱ እንዳሰበውና እነርሱም የጠበቁትን ያክል ብዙ ጊዜ አላሳለፈም። 

ከዚህ ከጳውሎስ አስቸጋሪ ልምምድ ምን እንማራለን? አንደኛው ነገር፥ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመወሰን አእምሮውን፥ ጸሎቱን፥ የሁኔታዎችን ጥናት መጠቀምና ከዚህም ይበልጥ የሚቻለውን ሁሉ መፈለግ እንዳለበት ነው። በምሳሌ 3፡5-6 («በራስህም ማስተዋል አትደገፍ») የሚለው «እእምሮህን ባዶ አድርገህ ማሰብ አቁም!» ተብሎ መተርጎም የለበትም። አእምሮን የሰጠ እግዚአብሔር ነው፥ እንድናስብም ይጠብቅብናል፥ ነገር ግን በራሳችን ማስተዋል ብቻ እንድንደገፍ አይፈልግም። መጸለይ፥ በቃሉ ላይ ጥሞና ማድረግ እናም የበሰሉ ክርስቲያን ወዳጆችን ምክርም እንኳ መሻት አለብን። 

ሁለተኛ፥ ውሳኔዎቻችን ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ላይሆኑ ይችላሉ። የማናደርጋቸውን ቃል ኪዳኖች፥ የማንፈጽማቸውን ዕቅዶች ልንወጥን እንችላለን። ይህ ማለት ዋሾዎች ወይም ተረቺዎች ነን ማለት ነውን? (በቆሮንቶስ ከነበሩት አንዳንድ አማኞች ጳውሎስ አታላይ ስለሆነ መታመን የለበትም ብለው ያስቡ ነበር። 2ኛ ቆሮ. 1፡12-2፡13ን ተመልከት።) በገዛ አገልግሎቴ፥ ከቁጥጥሬ በላይ በሆኑ ሁኔታዎች የተነሣ ዕቅዶቼን መቀየርና መርሐ ግብሬንም መለወጥ ግድ የሆኑብኝ ጊዜያት ነበሩ። ዕቅዶቼን በማወጣበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ነበርሁ ማለት ነውን? ሙሉ በሙሉ አይመስልም። ሐዋርያው እንኳ (ወደ ሰማይ ደርሶ የተመለሰው) አንዳንዴ ቀጠሮውን ማሻሻ ል ነበረበት። 

በዚህ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመሻት አስፈላጊ ጉዳይ ላይ ሁለት ጽንፎችን ማስወገድ አለብን። እንደው ምንም ውሳኔ እስከማናደርግ ስሕተትን እጅግ መፍራት ነው። ሁለተኛው፥ ጌታን ለመጠበቅ ጊዜ ሳይወስዱ የዱብዕዳ ውሳኔዎችን ማድረግና ወደፊት መቸኮል ነው። የጌታን ምሪት ለማወቅ የተቻለንን ሁሉ ካደረግን በኋላ የቀረውን ነገር ለጌታ በመተው መወሰንና ማድረግ አለብን። በሆነ መንገድ ከፈቃዱ ከወጣን፥ በመጨረሻ እርሱ ምሪቱን እንድናገኝ በሆነ መንገድ ይሠራዋል። ቁም ነገሩ ፈቃዱን ለማድረግ በቅንነት መፈለጋችን ነው (ዮሐ 7፡17)። ለነገሩማ፥ እርሱ «ስለ ስሙ ሲል» ይመራናል [መዝ (23)፡3]። እንድንባዝን ከፈቀደ የሚጎዳው የእርሱ ክብር ነው። 

ጳውሎስ በኤፌሶን ለአገልግሎት የተከፈተ በር ነበረው። ይህ ደግሞ ለእርሱ ጠቃሚ ጉዳይ ነበር። በቆሮንቶስ የዳኑትን ከማባበል በኤፌሶን የጠፉትን ለመመለስ ፈለገ። («የተከፈተ በር» ስለሚለው የሐዋ. 14፡27፤ 2ኛ ቆሮ. 2፡12፤ ቆላ. 4፡3፤ ራእይ 3:8ን ተመልከት።) ጳውሎስ ደግ አላሚ ወይም ክፉ አላሚ አልነበረም፤ እርሱ እውነታን ፈላጊ ነበር እንጂ። ዕድሎችንና መሰናክሎችን ሁለቱንም አይቶአቸዋል። እግዚአብሔር «ለውጤታማ ሥራ ታላቅ በር ከፍቶ ስለነበር» ጳውሎስ ዕድሎች ሳያመልጡ ለመጨበጥ ፈለገ። 

ጥንታዊ የሮማውያን ምሳሌ፥ «ማሰብ ካቆምን ዕድል ያመልጠናል» ይላል። ማድረግ የሚገባንን አንዴ ካወቅን ወዲያው ማድረግ እንጂ መዘግየት የለብንም። ላለማድረግ ብዙ ምክንያቶችን ልናስብ እንችላለን። ምንም እንኳ ጳውሎስ በኤፌሶን በአደጋ ውስጥ ቢሆንም (15፡32)፥ በሩ ክፍት እያለ በዚያው መቆየትን ዐቀደ። እንደ ብልህ ነጋዴ፥ ጭራሽ ሳይመለስ ከመጥፋቱ በፊት «ዕድሉን መግዛት» ነበረበት። 

ዕድልን መዋጀት በጣም ጠቃሚ ነው። ግለሰብ አማኝም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ፥ ዛሬ እግዚአብሔር የሚሰጠን ምን ዕድሎች አሉን? ብሎ ሳያቋርጥ መጠየቅ አለበት። ስለ መሰናክሎቹ ከማማረር ይልቅ፥ ዕድሎቹን መጠቀምና ውጤቱን ለጌታ መተው ይገባናል። 

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: