ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያኗ በጳውሎስ ላይ የተለያዩ ችግሮችና ልብን የሚሰብሩ ሐዘኖች ብታደርስበትም፥ እርሱ ግን በቆሮንቶስ ውስጥ የሚገኙትን አማኞች በጣም ይወዳቸው ነበር። አስቀድሞ በታማኝነትና በፍቅር ተናግሮአቸው ነበር፤ አሁን ደግሞ ልባቸውን ይከፍቱለት ዘንድ በፍቅር ይጠይቃቸዋል። ጳውሎስ የወለዳቸው ልጆቹ የሚገባውን ፍቅር እንደ ነፈጉት አባት ያህል ሐዘኔታ ተሰምቶት ነበር (1ኛ ቆሮ. 4፡15 ተመልከት)።
ፍቅራቸውን የሚነፍጉት ለምን ነበር? ምክንያቱም የተከፋፈለ ልብ ስለ ነበራቸው ነው። የሐሰት አስተማሪዎች ልባቸውን ስለሰረቁባቸው፥ ለጳውሎስ የነበራቸው ፍቅር ቀዝቅዞ ነበር። ልክ ለጋብቻ የታጨችና ጻሩ ግን በሌላ ሰው ማባበል የተማረከችን ልጃገረድ ይመስሉ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡1-3)። የቆሮንቶስ ሰዎች ከዓለም ጋር ለመስማማት ይከጅሉ ነበርና፥ ጳውሎስ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲለዩ ይለምናቸዋል፥ ታማኝ ሚስት ራስዋን ለባልዋ እንደምትለይ ዓይነት።
የመለየት ትምህርት አስፈላጊ እውነት መሆኑ ጉልቶ እየታየ፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠቀሜታው እየተዘነጋና እየተናቀ መምጣቱ አሳዛኝ ነው። አንዳንድ ቀናዒና ሐቀኛ ክርስቲያኖች፥ ከራሳቸው ጋር እንኳ ለማበር እስኪሳናቸው ድረስ ኅብረታቸውን አጥብበው፥ መለየትን ወደ መገንጠል ለውጠውት ይታያሉ። ከዚህ እጅግ ከተስፈነጠረ አቋም በተቃራኒ ያሉ ሌሎች አማኞች ደግሞ ስለሚያምኑበት ወይም ስለሚኖሩበት የሕይወት ዘይቤ ግድ ሳይኖራቸው የመለያየት ግድግዳዎችን ሁሉ አፍርሰው፥ ካገኙት ከማንኛውም ሰው ጋር ኅብረት ያደርጋሉ። ምንም እንኳ የእነዚህን ወገኖች ክርስቲያናዊ ፍቅርን የመለማመድ መሻት በአንድ በኩል ብንደግፈውም፥ ዳሩ ግን በክርስቲያናዊ ፍቅርም ውስጥ ቢሆን መቼ መለየት ወይም አለመለየት እንደሚያስፈልግ ማስተዋል እንዳለባቸው ለማሳሰብ እንወዳለን (ፊልጵ. 1፡9-11)።
ጳውሎስ እንዚህ አማኞች ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ከሚቃረን ነገር እንዲለዩ ሦስት የማሳመኛ አሳቦችን ያቀርባል።
1. የአማኙ ባሕርይ (2ኛ ቆሮ. 6፡14-16)። ኅብረትን የሚወስነው ባሕርይ ነው። አሣማ የአሣማ ባሕርይ (ተፈጥሮ) ስላለው፥ ከሌሎች አሣማዎች ጋር በጭቃ ውስጥ ኅብረት ያደርጋል። በግ የበግ ባሕርይ ስላለው፥ ከሌሎች በጎች ጋር በመስከ ሣር ያመነዥካል። ክርስቲያን መለኮታዊ ባሕርይ ስላለው (2ኛ ጴጥ. 1፡3-4)፡ ጌታን ከሚያስደስት ነገር ጋር ብቻ መተባበር አለበት።
«በማይመች አካሄድ አትጠመዱ» የሚለው አሳብ ከዘዳግም 22:10 የተወሰደ ነው፤ «በሬንና አህያን በአንድ ቀንበር ጠምደህ አትረስ» (አዲስ ትርጉም)። ለአይሁዶች በሬ ንጹሕ እንስሳ ሲሆን፥ ዳሩ ግን አህያ ንጹሕ አልነበረም (ዘዳ 14፡1-8)። ስለ ሆነም ሁለቱን በአንድ ላይ ማጣመዱ ትክክል አልነበረም። በተጨማሪም፥ ሁለቱም ሁለት የተለያዩ ባሕርያት ስላሉዋቸው፥ ለሥራውም ቢሆን የማይመች ነበር። ሁለቱን ማጣመድ የጭካኔ ተግባር ይሆን ነበር። እንደዚሁም፥ የአማኞች ከማያምኑ ሰዎች ጋር መጠመድ ትክክል አይደለም።
እስቲ ጳውሎስ የተጠቀማቸውን ስያሜዎች ልብ ብለህ ተመልከት፡- ተካፋይነት፥ ኅብረት፥ መስማማት፥ ክፍል፥ መጋጠም። እነዚህ ቃላት ሁሉ የጋርዮሽን አሳብ ያንጸባርቃሉ። ስምምነት የሚለው ቃል የ«ዝማሬ»ን አሳብ ያዘለ ሲሆን፥ መመዘምራን አንድን የዜማ ጽሑፍ እያነበቡና በአንድ መሪ እየተመሩ የሚያሰሙትን የግሩም ዝማሬ መዋጣት ያመለክታል። ዳሩ ግን እያንዳንዱ የመሣሪያ ተጫዋች የራሱን ዜማ በራሱ የአጨዋወት ዘይቤ ቢያቀርብ ምን ዓይነት ሁከት በተፈጠረ ነበር!
በእነዚህ ቃላት ውስጥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያሉት መሻቶች ታይተዋል። እርስ በርሳችን ያለንን እንድንከፋፈል (ኅብረት) እና የክርስትናን ሕይወት በረከቶች በጋርዮሽ እንድንቋደስ ይፈልጋል። አብረን ስንሠራና ስንኖር ሳለ በአንድነትና በመስማማት ደስ እንድንሰኝ ይሻል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን በአንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር እና ከዓለም ጋር ለመራመድ ከሞከርን፥ የተገኘውን መንፈሳዊ ኅብረት በማፍረስ መለያየትን እናመጣለን።
ጳውሎስ አማኞችና የማያምኑ ሰዎች በግልጽ እንደሚቃረኑ ይመለከታል፡- ጽድቅ -፥ ብርሃን – ጨለማ፥ ክርስቶስ – ቤልሆር (ሰይጣን)፥ እምነት – ክህደት፥ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ – የጣዖት መስገጃዎች። እነዚህን ተቃራኒ ነገሮች እንዴት ወደ አንድነት ለማምጣት ይቻላል? ክርስቲያን ካልተቀደሰው ነገር ይለይ ዘንድ ባሕርዩ ያስገድደዋል። አንድ በክርስቶስ አምኖ የዳነ ሰው (ሴት) በዚህ ልምምድ ውስጥ ያላለፈ የትዳር ጓደኛ በሚመርጥበት ጊዜ፥ የማይዘለቅ አቀበት ይፈጠራል፤ በንግድ ሽርኮችና በሃይማኖታዊ «አንድነቶች» መካከል የሚፈጠረውም አለመግባባት ከዚህ ያልተለየ ይሆናል።
በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፡16 ውስጥ «እናንተ» የሚለው ቃል ብዙኃንን እንደሚወክል ልብ ማለት ያሻል። በዚህ ሥፍራ ጳውሎስ አጥቢያዪቱን ቤተ ክርስቲያን በጥቅል እያመለከተ እንጂ፥ እንደ 1ኛ ቆሮንቶስ 6:19-21 አማኞችን በግል እየጠቀሰ አልነበረም። አማኞች የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለ ሆኑ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር የመኖሪያ ሥፍራ ነች (ሕዝ. 37፡26-27፤ ዘሌ. 26፡12፤ ዘፀ.6፡7፤ 25፡8)። ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምስክርነቷን መበረዝ ማለት ቅዱስ ቤተ መቅደስን ማርከስ እንደ ማለት ነው።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ (2ኛ ቆሮ. 6፡17)። የዚህ ጥቅስ አቢይ ክፍል የተወሰደው ከኢሳይያስ 52:11 ሲሆን፥ ዳሩ ግን የሕዝቅኤል 20:34፥ 41 ጥቅሶችም እንደ ገደል ማሚቴዎች በላዩ ላይ ያስገመግሙበታል። በኢሳይያስ ውስጥ የሚገኘው ማጣቀሻ የሚያመለክተው ፥ ባቢሎንን ለቀው ወደ ገዛ አገራቸው የሚመለሱትን ምርኮኞች ሲሆን፥ ዳሩ ግን በመንፈሳዊ ተዛምዶነቱ የሚያመለክተው፥ ዛሬም ቢሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ ከዓለም መለየት እንዳለበት ነው።
እግዚአብሔር ሕዝቡን «ውጡ» እያለ ያዛል፤ ይህም በበኩላቸው ሊወስዱት የሚገባቸውን ግልጽ እርምጃ ያመለክታል። «የተለያችሁ ሁኑ» የሚለው ለተለየ ዓላማ ለእግዚአብሔር መሰጠትን ያሳያል። መለየት አሉታዊ የመገንጠል ተግባር ብቻ ሳይሆን፡ አዎንታዊ ለእግዚአብሔር የመሰጠት ተግባርም ነው። ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር መለየት አለብን። «ርኩስንም አትንኩ» የሚለው ከርኩሰት እንድንርቅ የተሰጠን ማስጠንቀቂያ ነው። አንድ የብሉይ ኪዳን አይiዳዊ አስክሬን ወይም የከፋ ቁስል ከነካ ይረክስ ነበር። በርግጥ ዛሬ በንኪኪ ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ርኩሰት የለም፤ ዳሩ ግን መመሪያው ያው ነው፡- ምስክርነታችንን ሊያበላሽ ወይም ወዳለመታዘዝ ከሚመራን ነገር ጋር መተባበር የለብንም።
እግዚአብሔር እንድንለይለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ያዘናል። እስራኤላውያን በከነዓን ምድር ከጣዖት አምላኪዎች ጋር እንዳይተባበሩ አስጠንቅቆአቸዋል (ዘኁል 33፡50-56)፤ ዳሩ ግን በተደጋጋሚ ቃሉን ተላልፈው ለቅጣት ተዳርገዋል። ነቢያት ሕዝቡ ጣዖት ማምለካቸውን ትተው፥ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ይማጸኑዋቸው ነበር። በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር እስራኤልን ለአሦራውያን፥ ይሁዳን ደግሞ ለባቢሎናውያን ምርኮ አሳልፎ መስጠት ግድ ሆኖበት ነበር። ጌታችን የፈሪሳውያንን የውሸት «መለየት» የተቃወመ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ (ሐሰተኛ ትምህርት) እንዲጠበቁ አስጠንቅቆአቸዋል። እንዲሁም ከዓለም ርኩሰት እንዲጠበቁም ጸልዮላቸዋል (ማቴ. 16፡6፥ 11፤ ዮሐ 17፡14-17)።
ሐዋርያትም ለአብያተ ክርስቲያናት በጻፍአቸው ደብዳቤዎች ውስጥ የእምነት ትምህርትና በግል ሕይወት ንጽሕና ላይ ትኩረት አድርገዋል። አማኙ በዓለም ውስጥ ቢኖርም፥ ዳሩ ግን ዓለምን ላለመምሰል መጠንቀቅ አለበት። እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስና በሐዋርያት የተሰጠውን ትምህርት ከሚገፉ ሰዎች መለየት አለባት (ሮሜ 12፡1-2፤ 16፡17-20፤ ቆላ. 3፡1-2፤ 1ኛ ጢሞ. 6፡10-11፤ ቲቶ 2፡14፤ 1ኛ ጴጥ. 4፡3-6፤ 1ኛ ዮሐ 4፡6)። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ እንኳ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሐሰተኛና የረከሰ ሕይወት ከሚመሩ ወገኖች ስለ መለየታቸው አስፈላጊነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል (ራእ 2፡14-16፥ 20-24፤ 18 ከቁ. 4 ጀምሮ)።
እንዲህም ስለ ተባለ ደግሞ ለእምነት ትምህርትና ለግል ሕይወታችን ንጽሕና በሚኖረን መሻት ምክንያት፥ በዙርያችን የሚገኘውን ምስኪን ዓለም እስክንዘነጋ ድረስ ራስ-ወዳዶች መሆን የለብንም። ጌታችን «ቅዱስና ያለ ተንኮል፥ ነውርም የሌለበት፥ ከኃጢአተኞችም የተለየ» (ዕብ 7፡26) ሲሆን፥ ዳሩ ግን «የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ» ነበር (ሉቃ. 7፡34)። እንደ ጥበበኛ ሐኪም፥ «በሽታው ሳይተላለፍብን መገናኘትን» መለማመድ አለብን። ይህማ ካልሆነ፥ አገልግሎታችን እጅግ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ራሳችንን መነጠላችን ነው።
3. የእግዚአብሔር የበረከት ተስፋ (2ኛ ቆሮ. 6፡17-7፡1)። ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን በምንቀበልበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር አባታችን ይሆናል፤ ዳሩ ግን እስካልታዘዝነውና ከእርሱ ጋር ኅብረት እስካላደረግን ጊዜ ድረስ አባታችን ሊሆን አይችልም። እርሱ በፍቅር ሊቀበለንና እንደ ውድ ልጆቹ አድርጎ ሊንከባከበን ይናፍቃል። ደኅንነት ማለት የአብን ሕይወት መጋራታችን ሲሆን፥ ዳሩ ግን መለየት ማለት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ አብ ፍቅር ውስጥ ዘልቀን ገብተናል ማለት ነው። ኢየሱስ ይህን «የጠለቀ ፍቅር» እንደሚሰጠን በዮሐንስ 14፡21-23 ውስጥ ተስፋ ሰጥቶናል።
እግዚአብሔር ራሳቸውን ከኃጢአት ለእርሱ የሚለዩትን ሰዎች ይባርካቸዋል። አብርሃም ራሱን ከከለዳውያን ዑር ለየና እግዚአብሔርም ባረከው። ሆኖም አብርሃም የመለየቱን ነገር ችላ ብሉ ወደ ግብፅ በመሔዱ፥ እግዚአብሔር ጥፋቱን ማሳየት ነበረበት (ዘፍ 11፡31-12፡20)። እስራኤላውያን በከነዓን ከሚገኙ ኃጢአተኛ ሕዝቦች እስከ ተለዩ ድረስ እግዚአብሔር ይባርካቸው ነበር፤ ዳሩ ግን ከጣዖታት ጋር መዳራት በሚጀምሩበት ጊዜ፥ የቅጣት አለንጋውን ማውረድ ነበረበት። ዕዝራና ነህምያ ሁለቱም የመለየትን ትርጉም ደግሞ ማስተማር አስፈልጎአቸው ነበር (ዕዝ 9-10፤ ነህ. 9፡2፤ 10፡28፤ 13፡1-9፥ 23-31)።
ከእግዚአብሔር የቸርነት የተስፋ ቃሎች የተነሣ፥ እኛም በበኩላችን ልናሟላቸው የሚገባ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች አሉን (2ኛ ቆሮ. 7፡0። ራሳችንን ከሚያረክሰን ከማንኛውም ነገር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማንጻት አለብን። እግዚአብሔር እንዲያነጻን መጠየቅ ብቻ በቂ አይደለም፤ ዳሩ ግን የራሳችንን ሕይወት ልናነጻና በቀላሉ ከኃጢአት አዘቅት ውስጥ እንድንወድቅ ከሚያደርጉን ነገሮች መለየት አለብን። ማንኛውም አማኝ ለሌላው አማኝ ውሳኔ ሊያስተላልፍ አይችልም፤ እያንዳንዱ የልቡንና የሕይወቱን ችግር ያውቃል።
ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የሚታገሉት ከተፈጠረው ችግር ምልክቶቹ ጋር እንጂ ከመነሻ ምክንያቶቹ ጋር አይደለም። የችግሩን ሥር ስላላገኘንና «ሕይወታችንን ስላላነጻን»፥ አንዱን ኃጢአት ደጋግመን ስንናዘዝ እንኖራለን። ምናልባት አሮጌውን ባሕርይ «የሚቀልብ» አንድ ተወዳጅ ኃጢአት ይኖርና «የሥጋችን እድፈት» ሊቀጥል ይችላል (ሮሜ 13፡14)፤ ወይም ደግሞ የኃጢአትን አመለካከት የተላበሰ፥ «መንፈሳዊ እድፈት» ሊኖርብን ይችላል። የጠፋው ልጅ የሥጋ ኃጢአቶች ቁራኛ ሲሆን፥ «ሥነ-ምግባራዊ» ብቃት የነበረው ታላቅ ወንድሙ ግን ለመንፈሳዊ ኃጢአቶች ሰለባ ነበር። ከአባቱ ጋር እንኳ ሊስማማ አልቻለም ነበር (ሉቃ 15፡11-21 ተመልከት)።
ዳሩ ግን ራሳችንን ማንጻት የኃላፊነቱን ግማሽ አካል ከመወጣት የሚልቅ አይደለም – በተጨማሪም «በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም» ማድረግ አለብን (2ኛ ቆሮ. 7፡1)። በጸጋና በእውቀት እያደግን ስንሄድ፥ ይህ የማያቋርጥ ሂደት ይሆናል (2ኛ ጴጥ. 3፡18)። ሚዛናዊነትን መጠበቅ መልካም ነው። ፈሪሳውያን ኃጢአትን ለማስወገድ ቢጓጉም፥ ዳሩ ግን ቅድስናን ፍጹም ለማድረግ አልተጉም ነበር። ይሁንና የታወቀ ኃጢአት በሕይወታችን ውስጥ ተቀምጦ እያለ፥ ቅድስናን ፍጹም ለማድረግ መጣር ሞኝነት ነው።
ጳውሎስ ለምስጋናና ለመለየት ልመና አቅርቧል። በተጨማሪም የቆሮንቶስን አማኞች ፍቅርና መሰጠት መልሶ ለማምጣት አንድ የመጨረሻ ልመናም አክሏል።