የሚጸልዩ ና ትንቢት የሚናገሩ ሴቶች (1ኛ ቆሮ. 11፡3-16)

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ወደ ኋላ የሚላቸው አሉታዊ ነገሮች ስለነበሩት፥ ቤተ ክርስቲያንን በማወደስ በአዎንታዊ ቃል ጀመረ። ውዳሴ የሚገባቸው በተለይ ሁለት ነገሮች ነበሩ። ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስን አስታውሳዋለች፥ አድንቃውማለች። በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን ትምህርት ለመጠበቅ ታማኝ ነበረች። ሕጎች የሚለው ቃል «ትውፊቶች»፥ ከአንድ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፉ ትምህርቶች (2ኛ ጢሞ. 2፡2) ማለት ነው። የሰዎች ትውፊቶች መወገድ አለባቸው (ማቴ. 15፡2-3፤ ቆላ. 2፡8)፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተሰጡት ትውፊቶች መጠበቅ ይገባቸዋል። 

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩ ችግሮች አንዱ በጉባኤዎች መካከል የሚታይ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ነበር። አንዳንዶቹ ሴቶች ገደብ-ዘለል አርነት ተጸናውቶአቸው ነበር፤ በጌታ እራት ወቅት የሥርዓት ጉድለት ይታይ ነበር፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመጠቀም ረገድም ውዥንብር ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈሳዊ ስጦታዎች እጅጉን የበለጸገች ብትሆንም መንፈሳዊ ጸጋ ይጎድላቸው ነበር። 

ጳውሎስ እነዚህን ችግሮች ሐዋርያዊ ቀላጤ በማውጣት ለመፍታት በሞከረ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ፈንታ ለቤተ ክርስቲያን አስተምሮ የነበሩትን ትምህርቶች የሚደግፍ መርሆችን አቅርቦ በትዕግሥት እብራራቸው። መከራከሪያዎቹን የመሠረተው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ነበር። 

ጳውሎስ የጉባኤ አምልኮአቸውን ሦስት የውዥንብር አቅጣጫዎች አጤነ። 

የሚጸልዩ ና ትንቢት የሚናገሩ ሴቶች (1ኛ ቆሮ. 11፡3-16) 

የክርስትና እምነት ለሴቶች፥ ለልጆችና ለባሪያዎች አርነትን እና ተስፋን አመጣሁሉም ሰዎች፥ ከዘር ወይም ከፆታ ባሻገር በፈጣሪያቸው ፊት እኩል መሆናቸውንና ሁሉም እማኞች በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ መሆናቸውን (ገላ 3፡28) አስተማረ። ቀደም ብለን እንደገለጽነው፥ በሮማ መንግሥት ሁሉንም ሰዎች፥ ከብሔራቸው፥ ከማኅበራዊ አቋማቸው፥ ከፆታቸው፥ ወይም ከኢኮኖሚ ይዞታቸው ውጭ የምታስተናግድ ኅብረት ብትኖር ምናልባት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። 

ይህን አዲስ የተገኘውን አርነት ከልክ አልፈው የሚሄዱ አንዳንድ ሰዎች እንደሚኖሩ የተጠበቀ ነበር። አዲስ ንቅናቄ ምንጊዜም ከጠላቶቹ ይልቅ በተከታዮቹ ምክንያት የበለጠ ይሠቃያል፤ በቆሮንቶስም የነበረው እውነት ይህ ነው። ከሴቶች አንዳንዶቹ በጉባኤ በሚሳተፉበት ወቅት ራሳቸውን ባለመሸፈን «አርነታቸውን» መመጻደቂያ አደረጉት። 

ጳውሎስ እነዚህ ሴቶች እንዳይጸልዩ ወይም ትንቢት እንዳይናገሩ አልከለከለም። (ትንቢት መናገር ከእኛው «ስብከት» ወይም «የቃል ገለጣ» ጋር አንድ አይደለም። የትንቢት ስጦታ የነበረው ሰው የእግዚአብሔርን መልእክት እንደተሰጠው ወዲያው በመንፈስ ይናገራል። ዘመናዊው ሰባኪ ቃሉን በማጥናት መልእክቱን ያዘጋጃል።) አዲስ ኪዳን የሴት ሽማግሌዎችን የሚፈቅድ ባይመስልም (1ኛ ጢሞ. 3፡2)፥ በቀደሞዪቷ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ሴቶች የትንቢት ስጦታዎቻቸውን ይለማመዱ ነበር። በጉባኤ ላይም እንዲጸልዩ ይፈቀድላቸው ነበር። ሆኖም ግን፥ የወንዶችን ሥልጣን መንጠቅ (1ኛ ጢሞ. 2፡11-15) ወይም የሌሎችን ነቢያት መልእክት መፍረድ (1ኛ ቆሮ. 14፡27-35) አልነበረባቸውም። ጥያቄዎች ከነበሩአቸው፥ ባሎቻቸውን (ወይም ሌሎች ወንዶችን) ከቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ውጭ መጠየቅ ይችሉ ነበር። 

ምሥራቃዊ ማኅበረሰብ በዚያ ዘመን በሴቶቹ በጣም ይቀና ነበር። የቤተ መቅደስ ዘማውያን ካልሆኑ በቀር ሴቶች ፀጉራቸውን በረጅሙ ያሳድጉና በአደባባይም ራሶቻቸውን ይሸፋፈኑ ነበር። (ጳውሎስ እዚህ ላይ ዓይነ ርግብ ማለቱ አልነበረም፤ ይህ በፊት ላይ የሚደረግ ሽፋን ነው። ሴቶች ተለምዶአዊውን ሽፋን በራሳቸው ላይ ያደርጉ ነበር፤ ይህ ሽፋን የመገዛታቸው እና የንጽሕናቸው መለያ ነበር።) በሕዝብ ፊት ፀጉርን ሳይሸፈኑ መጸለይ ና ቃሉን ማንበብ ቀርቶ እንዲህ ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መታየቱ ድፍረት ና ጸያፍ ነበር። 

ጳውሎስ ለቆሮንቶሳውያን እግዚአብሔር በወንዶችና በሴቶች መካከል ልዩነትን እንደ ፈጠረ፥ በእርሱ ምጣኔ እያንዳንዱ የራሱ ስፍራ እንዳለው በማሳሰብ ሥርዓት እንዲመለስ ፈለገ። እነዚህን ግንኙነቶች የሚያንጸባርቁ እና በመለኮታዊ አወቃቀር ውስጥ ሁለቱም ወንዶች ና ሴቶች ያሉአቸውን ትክክለኛ ስፍራ የሚያሳስቡ አግባብ ያላቸው ባሕሎችም ነበሩ። ጳውሎስ ልዩነት እኩል አለመሆን ወይም ዝቅተኝነት ነው ብሎ ማሰብ ቀርቶ አዝማሚያውንም አላሳየም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላም (15፡33) እንዲኖር ከተፈለገ፥ የሆነ ዓይነት ሥርዓት መኖር አለበት፤ ሥርዓት ደግሞ የተዋረድን ቀዳሚነት ይፈልጋል። ቢሆንም፥ ተዋረድ እና ብቃት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ካፒቴን ከተራ ወታደር የላቀ ማዕረግ ነው፤ ነገር ግን ተራው ወታደር የተሻለ ሰው ሊሆን ይችላል። 

በቤተ ክርስቲያን የሚገኝ የእግዚአብሔር ሥርዓት በሦስት ፍሬ እሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው። ጳውሎስ እነዚህ ፍሬ አሳቦች ራስ ገለጽ ናቸው ይላል። 

ቤዛነት (11፡3-7)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተወሰነ «ራስነት» አለ። አብ የክርስቶስ ራስ ነው፥ ክርስቶስ የወንድ ራስ ነው፥ ወንድም ደግሞ የሴት ራስ ነው። አንዳንዶች ራስ የሚለውን «መነሻ » ወይም ∫«ምንጭ» ብለው ይተረጉሙታል፤ ነገር ግን ይህ አብ ክርስቶስን እንዳመነጨ ይመስላል- ይህ ደግሞ የማንቀበለው ነው። ምንም እንኳ ከአብ ጋር እኩል ቢሆንም (ዮሐ 10፡30፤ 14፡28) በመቤዥት እገልግሎት፥ ወልድ ለአብ ተገዢ ነበር። ምንም እንኳ ሴት በክርስቶስ ከወንድ እኩል ብትሆንም ለወንድ ትገዛለች (1ኛ ቆሮ. 3፡21-23፤ ገላ. 3፡28፤ ኤፌ. 5፡21-33)። 

ጳውሎስ ይጽፍ የነበረው በአጥቢያ ጉባኤ ውስጥ ያለውን ግንኙነት እንጂ በመላው ዓለም ያለውን እንዳልሆነ ልብ በል። በቤት ውስጥ እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፥ ወንዶች በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ሥር ሆነው የራስነት ስፍራ እንዲለማመዱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። 

አስፈላጊው ነጥብ ይህ ነው። ሁለቱም ወንዶች እና ሴቶች እነዚህን የራስነት ምልክቶች የሆኑትን-ፀጉር እና የራስ ሽፋንን አክብሮ በመያዝ ጌታን ከፍ ከፍ ማድረግ አለባቸው። አንዲት ሴት በጉባኤ በምትጸልይበት ወይም ትንቢት በምትናገርበት ማንኛውም ጊዜ ፀጉሯን ለቅቃ እና ራሷን ተሸፍና መሆን አለበት። ወንድ ፀጉሩ አጭር ሆኖ በራሱ ላይ ምንም ሽፋን ማድረግ የለበትም። (ይህ ለጳውሎስ መለወጥ ነው፤ ምክንያቱም አክራሪ የአይሁድ ወንዶች በሚጸልዩበት ጊዜ በራሳቸው ላይ ኮፍያ ያደርጉ ነበር።) ወንድ ራሱን ባለመሸፈን የእርሱን ራስ (ክርስቶስን) ያከብራል፤ ሴት ግን ራሷን በመሸፈን የእርሷን ራስ (ወንድን) ታከብራለች። ለእግዚአብሔርም ሆነ ለወንድ መገዛቷን ማሳየቷ ነው። 

ራሳቸውን ሳይሸፍኑ በጉባኤ ላይ ይገኙ የነበሩ የቆሮንቶስ ሴቶች እንደ እውነቱ ከሆነ ያደርጉት የነበረው ራሳቸውን ወደ ቤተ መቅደስ ዘማዊነት ደረጃ ቁልቁል ማውረድ ነበር። ዘማዊ ሴቶች ፀጉራቸውን ይቆረጡ፥ በአደባባይም በራሳቸው ላይ ምንም ሽፋን አያደርጉም ነበር። የፀጉር አሠራራቸው እና ሁኔታቸው ማን እንደሆኑ እና ምን እያቀረቡ እንዳሉ ለሌሎች አዋጅ የሚናገር ነበር። ጳውሎስ ሲጽፍ፥ «ራሳችሁን የማትሸፍኑ ከሆነ ለምን እስከነጭራሹ አትቆረጡትም?» አላቸው። 

በአይሁድ ባሕል በዝሙት የተወነጀለች ሴት ፀጉራን ትቆረጥ ነበር (ዘኁ. 5፡11-31)። ጳውሎስ ከቁጥር 5-6 ባለው ሁለት የተለያዩ ቃላትን ተጠቅሞአል። መላጨት ማለት ፀጉርን ሙሉ በሙሉ ጠርጎ ማስወገድ ሲሆን፥ መቆረጥ ማለት «መከምከም» ነው። የትኛውም ቢሆን ለሴት አሳፋሪ ነበር። 

ሁለቱም ወንድ ና ሴት የተፈጠሩት በእግዚአብሔር አምሳል እና ለእግዚአብሔር ክብር ነው፤ ነገር ግን ሴት ከወንድ ስለተሠራች (ዘፍ 2፡18-25)፥ እርሷ «የወንድ ክብርም» ናት። ለእግዚአብሔር ትእዛዝ በመገዛት እና በጉባኤ አምልኮ ወቅት ራሷን ስመሽፈን እግዚአብሔርን ታከብራለች፤ ለወንድም ክብርን ታመጣለች። እንግዲህ፥ ጳውሎስ አካባቢአዊ ባሕልን ና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን አንዱ ወደ ሌላው እንዲያመለክት እድርጎ ሁለቱንም አስተሳሰራቸው። 

ፍጥረት (11፡8-12)። ይህን እውነት ቀደም ብለን በአጭሩ ነካክተነዋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ወንድ አስቀድሞ መፈጠሩ (1ኛ ጢሞ 2፡13)፥ እና ሴቲቱ የተፈጠረችው ለወንድ በመሆኑ እውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። እንደገና፥ ቅደም ተከተል ዝቅተኛነትን አያመለክትም፤ ምክንያቱም ጳውሎስ ከ11–12 ላይ በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ጉድኝነት እና ራስነት እንዳሉ ግልጽ አድርጓል። ወንድም ሆነ ሴት በመንፈሳዊው ረገድ በጌታ አንድ ሲሆኑ (ገላ. 3፡28) አንዱ ያለ ሌላው ሊሆን አይችልም። በተጨማሪ፥ ከመነሻው ሴት ከወንድ የተገኘች ቢሆንም፥ ነገር ግን ዛሬ ከሴት የሚወለደው ወንድ ነው። ወንድ እና ሴት አንዱ የሌለው እና እርስ በርስ ተፈላላጊ ናቸው። 

ጳውሎስ በቁጥር 10 መላእክትን ያመጣው ለምንድን ነው? ይከራከር የነበረው ከፍጥረት አኳያ ስለሆነ እና መላእክቱም የዚያ ፍጥረት አካል ስለነበሩ ነው። መላእክት ስፍራቸውን የሚያውቁ ስለሆነ በሚያመልኩበት ጊዜ ፊታቸውን በመሸፈን ክብርን ይሰጣሉ (ኢሳ. 6፡2)። በመጨረሻ ም፥ በሆነ ልዩ መንገድ፥ መላእክት በቤተ ክርስቲያን የጉባኤ አምልኮ ይካፈላሉ፤ ከቤተ ክርስቲያንም ይማራሉ (ኤፌ. 3፡10፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡12)። የጉባኤ አምልኮ፥ መላእክትም ስለሚገኙበት ከባድ ነገር ነው፤ በመሆኑም በመንግሥተ ሰማይ እንዳለን አድርገን ሥርዓት መያዝ ይገባናል። 

ተፈጥሮ (11፡13-15)። በጥቅሉ ሲታይ ተፈጥሮ ለሴቶች ረጅም ፀጉር፥ ለወንዶች አጭር ፀጉር ማደሉ እውነት ነው። ሮማውያን፥ ግሪኮች እና አይሁዶች (ናዝራውያን ካልሆነ በቀር) ይህንኑ ባሕል ይከተሉ ነበር። ፀጉራችን ምን ያህል ረጅም መሆን እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ የትም ስፍራ ላይ አይነግረንም። የፆታ ግራ መጋባት እንዳይኖር በወንዶች ፀጉር እና በሴቶች ፀጉር ርዝማኔ መካከል የሚታይ ልዩነት መኖር አለበት። (ይህ መርህ «አንድ ፆታ» የሚባለውን ዘይቤ ያስወግዳል።) ለወንድ ሴትን መምሰል፥ ወይም ለሴት ወንድን መምሰል አስነዋሪ ነው። 

የሴት ረጅም ፀጉር ክብሯ ነው፥ «በሽፋኑ ፈንታም» የተሰጣት ነው (ቀጥታ ትርጉም)። በሌላ አነጋገር የአካባቢው ባሕል የራስን መሸፈን የሚያስገድድ ካልሆነ በቀር፥ ረጅሙ ፀጉሯ ሽፋን ሊሆንላት ይችላል። ጳውሎስ በሁሉም ባሕል ሥር ያሉ ሴቶች ራሳቸውን ይሸፋፍኑ ማለቱ አይመስለኝም፤ ነገር ግን ረጁሙን ፀጉሯቸውን እንደ ሽፋን ና ለእግዚአብሔር ሥርዓት የመገዛታቸው ምልክት እንዲያደርጉት ይጠብቅባቸው ነበር። ይህም ማንም ሴት ልታደርገው የምትችለው ነው። 

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በነበረኝ አገልግሎት የራስነት መርህ በሁሉም መሥራቱን አይቻለሁ፤ ነገር ግን የሚገለጽባቸው መንገዶች ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። ዋናው ነገር ልብን ለጌታ ማስገዛት ና ለእግዚአብሔር ሥርዓት በገሃድ ታዛዥነትን መግለጽ ነው፡፡

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: