ምን ጊዜም ቢሆን እምነታችንና አካሄዳችን ጎን ለጎን ሊሄዱ ይገባል። እግዚአብሔር ያደረገልንን በጎ ነገር ለእርሱም በአፀፋው መልካምን እንድናደርግ ሊያነቃቃን ስለሚገባ፥ ጳውሎስ ተግባርንና የእምነት ትምህርትን አይነጣጥላቸውም ነበር። ፊልፕስ ብሩክስ፥ «ክርስትና የፍቅር ልጅና የተግባር ወላጅ ያልሆነውን እውነት አይቀበልም» ብለዋል።
አንዲት ሴት ለሰባኪው፥ «በስብከትህ መጨረሻ ላይ «ስለዚህ በሚለው ቃል ደጋግመህ ባትጠቀም ኖሮ ግሩም ሰባኪ በወጣህ ነበር» ስትል ተናግራዋለች።
ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ አዘውትሮ «ስለዚህ» እና «ሰመሆኑም» በሚሉት ቃላት እየደጋገመ ይጠቀምባቸው ስለ ነበር፥ ከመጋቢው አሳብ ጋር የሚስማማ እውነት ነው። እንዳውም በዚሁ የሁለተኛ ቆሮንቶስ ክፍል ውስጥ እንኳን እነዚሁ ቃላት በቁ. 9፡ 11፥ 16 ና 17 ውስጥ ተደጋግመው ተጠቅሰው ይገኛሉ። ይህም ጳውሎስ ከገለጻ ወደ ተግባራዊነት መሸጋገሩን የሚያመለክት ነው። የመልእክቱም ጭብጥ ለአገልግሎት የሚገፋፉትን መንስዔዎች በግልፅ በማሳወቅ ላይ ያተኰረ ነው። የጳውሎስ ጠላቶች የወንጌል አገልግሎቱን የራስ-ወዳድነት ዓላማዎቹን ለማራመድ በግሉ እንደ ተጠቀመበት አድርገው ከሰውት ነበር፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የወንጌሉን እውነት «በውሸት የሚቀላቅሉት» (4፡2፤ 2:17) ራሳቸው ነበሩ።
የክርስቲያን አገልግሎት ምንድነው? ኃጢአተኞችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ማሳመን ነው (5፡11፥ 20)። ሆኖም ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ ማስገደድ ወይም በማታለያ ዘዴዎች ጨርሶ መጠቀም የለብንም። « እኛ የመከርናችሁ በስህተት ወይም በርኩስ ዓላማ ተመርተን አይደለም፤ እናንተን ለማታለል ያደረግነው ምንም ነገር የለም» (1ኛ ተሰ 2፡3 – አዲሱ ትርጉም)። ክርስቲያን አገልጋይ፡ ለአገልግሎቱ ትክክለኛ ዓላማና ትክክለኛ መልእክት ሊኖረው ይገባል።
ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ፥ ለአገልግሉት የሚጠቅሙ ሦስት ዓላማዎች አስቀምጧል።
የጌታ ፍርሃት (2ኛ ቆሮ. 5፡9-13) «የጌታን ፍርሃት አውቀን» (ቁ. 11)። የዚህ ዓይነቱ አመለካከት ብዙውን ጊዜ በአገልግሎት ውስጥ አይታይም። የታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር፥ ቢ.ኤፍ ዌስትኮት፥ አንድ ጊዜ፥ «ሰዎች በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ደፍረው የሚናገሩበትን ሁኔታ ሳጤነው፥ እያንዳንዱን ዓመት በበለጠ እንድፈራው ያደርገኛል» በማለት ጽፈዋል። እንዲሁም ፊልፕስ ብሩክስ የተባሉት ሰው፥ እንዴት አንዳንድ «ቀልደኛ ሰባኪዎች» በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመቀለድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈውን ቃል ኃይልና ክብር እንደሚያሳጡት አስጠንቅቀው ነበር። ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ይፋዊ ጉባዔዎች ውስጥ ፈሪሃ-እግዚአብሔር መታጣቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ከመሆኑም፥ ወጣቱም ትውልድ ለእግዚአብሔር ቃል ክብደት አለመስጠቱ ከዚሁ የመነጨ ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።
ጳውሎስ በሦስት ጠንካራ ዓረፍተ ነገሮች የራሱን ምስክርነት ከማቅረቡም፥ መንስዔውንም ገልጾልናል።
እንቀናለን (2ኛ ቆሮ. 5፡9) የሚለው «እንሻለን» ማለት ነው። ራስ-ወዳድነትና ዓለማዊነት የነገሠበት መሻት ቢኖርም፥ ዳሩ ግን ጌታን የሚያስከብር ቅዱስ መሻትም አለ። የጳውሎስ ትልቅ መሻት ለኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ – ደስ የሚያሰኝ ሆኖ መገኘትን ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ሰዎችን ለማስደሰት ብለው ያገለገሉና ተከታይ ያበጁ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ለማስደሰት አገልግሏል (ገላ. 1፡10)። ሰውን ለማስደሰት የሚደረግ አገልግሎት ሥጋዊና ታማኝነት የጐደለው አገልግሎት በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ሊባርከው አይችልም።
ተቀባይነት ያለው («ደስ የሚያሰኝ») ተብሎ የተተረጎመው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በበርካታ ሥፍራዎች ስለ ተጠቀሰ፥ እነዚህ ማጣቀሻዎች ጌታን ደስ የሚያሰኘው ምን እንደ ሆነ የበለጠ ለመረዳት ይረዱናል። ሰውነታችንን ሕያው መሥዋዕት አድርገን ስናቀርብ፥ ይኼ ጌታን ደስ ያሰኘዋል (ሮሜ 12፡1)፤ ሌሎችን ስንረጻና የማሰናከያ ዓለት ከመሆን ስንታቀብ ደስ ይለዋል (ሮሜ 14፡18)። እግዚአብሔር ልጆቹ በዙርያቸው ካለው ክፉ ነገር ራሳቸውን ሲለዩ (ኤፌ 5፡10)። እንዲሁም ስጦታዎቻቸውን ሲያቀርቡለት (ፊልጵ. 4፡18) ደስ ይለዋል። እርሱ ለወላጆቻቸው በሚታዘዙ ልጆችና(ቆላ 3፡20) ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹምነት ያለበት ፈቃዱን በሕይወታቸው ውስጥ እንዲፈጽም በሚፈቅዱ ቅዱሳን ደስ ይለዋል።
ፈሪሃ-እግዚአብሔር የሚንጸባረቅበት መሻት ክፉ አይደለም። በሮሜ 15፡20 ላይ ጳውሎስ፥ «ወንጌልን ለመስበክ ተጣጣርሁ [ፈለግሁ]» በማለት ምስክርነቱን ይሰጣል። መልእክቱን ተሰብኮ ወደማያውቅበት ሥፍራ ለማዳረስ ያስገደደው ይኸው ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለበት መሻት ነበር። ጳውሎስ የተሰሎንቄን አማኞች «በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ (ልትፈልጉ) . (1ኛ ተሲ 4፡11) አዝዘናችኋል» ይላል። አማኞች በመንፈስ ተመርተው፥ ለስፖርት ውድድር ወይም ለሥራ የሚያደርጉትን ያህል ጥረት በክርስትና ሕይወታቸውና አገልግሎታቸው ላይ ቢያክሉ ኖሮ፥ ወንጌል በጠፋው ዓለም ላይ የላቀ አዎንታዊ ተጽዕኖ ባስከተለም ነበር። አንድ በቅርብ ጊዜ ወደ ጌታ የተመለሰ ክርስቲያን፥ «ለዲያብሎስ የቀናሁትን ያህል፥ ለእግዚአብሔር ለመቅናት እፈልጋለሁ» ብሎኝ ነበር፤ በርግጥም እግዚአብሔር በዚህ ወንድም ሕይወት በሚገባ ተጠቅሞበታል።
ሁላችንም መቅረብ አለብን (2ኛ ቆሮ. 5፡10)። ሁሉም አማኝ ለጌታ ሥራ ጉጉ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሁሉም አማኝ በጌታ ፊት ይቀርባል፤ በመሆኑም የዝግጅቱ ጊዜ አሁን ነው። የክርስቶስ የፍርድ ወንበር፥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደየሥራቸው መጠን ሽልማትን ለጎግኘት፥ በአዳኙ ፊት የሚቀርቡበት የወደፊት ክስተት ነው (ሮሜ 14፡8-10 ተመልከት)። ጳውሎስ ጌታን በድፍረት እንጂ በኀፍረት ሊገናኝ ባለመፈለጉ፥ ለሥራው ፍፁም ታማኝነት ነበረው (1ኛ ዮሐ 2፡28)።
የፍርድ ወንበር የሚለው ቃል በግሪክ «ቤማ» የሚል ሲሆን፥ ይህም በግሪክ ከተማ ውስጥ ዲስኩር የሚደረግበት ወይም ገዢዎች ውሳኔ የሚያስተላልፉበት መድረክ ነው (ማቴ. 27፡19፤ የሐዋ. 12፡21፤ 18፡12 ተመልከት)። ይህ ስፍራ በዓመታዊ የኦሉምፒክ ውድድር ወቅት ላሸነፉ ተወዳዳሪዎች ሽልማት የሚሰጥበትም ነበር። ይህ «የፍርድ ወንበር» ክርስቶስ በኃጢአተኞች ላይ ከሚፈርድበት ከታላቁ የነጭ ዙፋን ፍርድ ጋር መምታታት የለበትም(ራእ. 20፡11-15)። በመስቀል ላይ ከተፈጸመው የክርስቶስ የቸርነት ሥራ የተነሣ፥ አማኞች ኃጢአታችን ቢሰረዝልንም። (ሮሜ 8፡1፤ ዮሐ 5፡24)፥ ዳሩ ግን የሥራችንንና የአገልግሎታችንን ምላሽ ለጌታ መስጠት አለብን።
የክርስቶስ የፍርድ ወንበር የመገለጫ ሥፍራ ይሆናል፤ «መቅረብ» የሚለው ቃል የሚያመለክተው መገለጥን ነው። በዚህች ምድር ላይ እስከ ኖርንና እስከ ሠራን ድረስ፥ ነገሮችን መሸሸግና ማስመሰል በአንጻሩ ቀላል ነው፤ ዳሩ ግን በአዳኙ መርማሪ ዓይኖች ፊት የሥራዎቻችን እውነተኛ ባሕርይ ይጋለጣል። እርሱ ሥራዎቻችን መልካም ወይም ክፉ እንደ ነበሩ ይገልጣል። የአገልግሎት ባሕርያችን (1ኛ ቆሮ. 3፡13)። እንዲሁም ደግሞ የገፋፉን ውስጣዊ መንስዔዎችም (ዓላማዎች) ይገለጣሉ (1ኛ ቆሮ. 4፡5)።
እንዲሁም ደግሞ የአገልግሎት ዘገባችንን በምናቀርብበት ጊዜ ስለ ድርጊታችን ሁሉ መልስ የምንሰጥበት ስፍራ ይሆናል (ሮሜ 14፡10-12)። ታማኞች ከነበርን፥ ይህ ሥፍራ በሽልማትና በእውቂያ የምናሸበርቅበት ይሆናል (1ኛ ቆሮ.3፡10-15፤ 4፡1-6)። በታማኝነት ላገለገልን ሰዎች፥ ያ ጊዜ ሽልማቶቻችንን በአምልኮአችንና በውዳሴአችን አማካይነት ለጌታ መልሰን የምንሰጥበት በመሆኑ፥ በደስታ የምንፍለቀለቅበት ወቅት ይሆናል።
ሽልማትን መሻት፥ አገልግሎት ለማበርከት ወሳኙ መንስዔ ነውን? ምንም እንኳ ይህ እጅግ የላቀው አነሳሹ ምክንያት ባይሆንም፥ እግዚአብሔር ሽልማቶችን እንደሚሰጥ የተስፋ ቃል በመግባቱ ሽልማትን መሻት ኃጢአት እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። ልክ ወላጆች ልጆቻቸው እውቂያን ሲያተርፉ እንደሚደሰቱ ሁሉ፥ ጌታችንም ሕዝቡ ለእውቂያና ለሽልማት ሲበቁ በማየት ደስ ይሰኛል። አስፈላጊው ነገር ሽልማቱ ራሱ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ክርስቶስን ከማስደሰትና ከማስከበር ሐሴት ነው።
ለሰዎች እናስረዳለን (2ኛ ቆሮ. 5፡11)። እግዚአብሔር በገዛ ሕዝቡ ላይ የሚፈርድ ከሆነ፥ ደኅንነትን ያላገኙ ኃጢአተኞች ምን ይሆናሉ? «ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?» (1ኛ ጴጥ. 4፡18)። ፍርሃት የሚለው ቃል መንቀጥቀጥ ወይም መሥጋት ወይም ድንጋጤ ማለት አይደለም። አዳኛችንን ልናየው ወደዚያው መጓዛችን የማይቀር ነው – እርሱም ይወደናል። እርግጥ ጳውሎስ ይህን ሁኔታ ጨርሶ እንደማያስፈራ አድርጎ አልቆጠረውም። በክርስቶስ ፊት ልንቆም ይገባናል፤ «ለሰው ፊትም አድልዎ የለም» (ቆላ 3፡23-25)። ክርስቶስ ወንጌሉን ለሕዝቦች ሁሉ እንድናዳርስ አዞናል – እናም መታዘዝ አለብን። አንድ ሰው የዌሊንግተንን ዱክ (መስፍን) ስለ ውጭ አገር የሚሲዮን አገልግሎቶች ምን እንደሚያስቡ ጠይቆአቸው ነበር። እርሳቸውም «የዘመቻችሁ ትእዛዞች በቅድሚያ ምንድን ናቸው?» በማለት መልሰውለታል።
ክርስቲያን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ለመቅረብ እንዴት ሊዘጋጅ ይችላል? በመጀመሪያ ደረጃ፥ ንጹሕ ሕሊና ሊኖረው ይገባል (2ኛ ቆሮ. 5፡1)። በቆሮንቶስ ከተማ ከሚገኙ የጳውሎስ ጠላቶች አንዳንዶቹ፥ «ጳውሎስ በጌታ ፊት እስኪቆም ድረስ ብቻ ጠብቁ» ይሉ እንደ ነበር አይጠረጠርም። ዳሩ ግን ጳውሎስ ሕሊናው ንጹሕ እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር (1፡ 12 ተመልከት)፥ አልፈራም ነበር። ስለ እያንዳንዳችን እውነቱ ስለሚገለጽ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም ስለነዚያ እርሱን ደስ ስላሰኙት ነገሮች ያመሰግነናል።
ሁለተኛ፥ በሰዎች ምስጋና ላይ እንዳንደገፍ መጠንቀቅ አለብን (5፡12)። ይህ ቁጥር ጳውሉስ የአይሁድ መምህራን በከፍተኛ ደረጃ የሚመለከቱዋቸውን «የምስጋና ደብዳቤዎች» ከሚጠቅሱበት ከ3፡1 ጋር ይዛመዳል። የሰዎችን ምስጋና ለማግኘት ብለን ብቻ የምንኖር ከሆነ፥ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት የእግዚአብሔርን ምስጋና ልናተርፍ አንችልም። ከሰው ምስጋና ለማግኘት ብሉ መኖሩ ከባሕርይ ይልቅ ዝናን ለማትረፍ የሚደረግ ጥረት ከመሆኑም፥ በክርስቶስ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ዋጋ የሚሰጠው ለባሕርይ መሆኑን አለመረዳት ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስን ማመስገን በተገባቸውም ነበር፤ ዳሩ ግን ከልባቸው መንፈሳውያን ያልሆኑትንና፥ በሥጋቸው ከብረው የሚታዩትን የአይሁድ መምህራን ለማሞገስ መረጡ (11፡18 ተመልከት)።
በመጨረሻም፥ የሰዎችን ትችት ማግለል አለብን (5፡13)። የጳውሎስ ባላንጣዎች ማስተዋል የሌለው ሰው እንደ ሆነ ይናገሩ ነበር። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን በሚያሳድድበት ወቅት፥ «እብድ» እንደ ነበር ይናገራል፤ ዳሩ ግን ጠላቶቹ እንዳውም አማኝ ከሆነ በኋላ «እንዳበደ» ይናገራሉ (የሐዋ. 26፡24)። ይሁንና ሰዎች ጌታችንን እንኳን «አብደሃል» ብለውት ስለ ነበረ፥ ጳውሎስ ለእብደቱ ብቸኛ ሳይሆን መልካም ደባልም ነበረው ማለት ነው (ማር. 3፡21 ተመልከት)። ጳውሎስም፥ «እኔ እብድ ከሆንሁ፥ ለናንተ ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር ነው – ይህም የእብደቴን ጠቃሚነት ያጎላዋል ! » ይል ነበር።
ድዋይት ኤል ሙዲ በሺካጎ ውስጥ በሚገኘው ሰፊ የሰንበት ትምህርት ቤትና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያገለግሉበት ጊዜ፥ ብዙውን ጊዜ ሰዎች «ጅሉ ሙዲ» እያሉ ይጠሩዋቸው ነበር። ሙዲ የሰንበት ትምህርት ቤት ሠራተኛና ወንጌላዊ ለመሆን የተዋጣለትን የንግድ ሥራቸውን በመተዋቸው፥ ደኅንነትን ባላገኘው ዓለም ፊት «ጅል» ነበሩ። ይሁንና ያደረጉት ውሳኔ የአዋቂነት እንደ ነበር በጊዜ ማረጋገጫነት ታውቋል። ዛሬ፥ በእኚህ ሰው ላይ የተሳለቁትን ሰዎች ስም አናውቅም፤ ዳሩ ግን የዲ. ኤል ሙዲን ስም አሳምረን እናውቃለን – በአክብሮትም እናስታውሳቸዋለን።
ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ለክርስቶስ የፍርድ ወንበር መዘጋጀቱን ለመረዳት፥ ዘወትር ሕይወቱን መመርመሩ አስፈላጊ ነው። በክርስቶስ ፊት መልካም ዘገባ ለማቅረብ መሻቱ፥ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ተገቢ
መንስዔ ነው።
የክርስቶስ ፍቅር (2ኛ ቆሮ.2፡14-17)
ፍርሃትና ፍቅርን የመሳሰሉ የሚቃረኑ ስሜቶች በአንድ ልብ ውስጥ እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? በመሠረቱ እነዚህ ስሜቶች ወላጆቻቸውን በሚወዱና ዳሩ ግን ወላጆቻቸውን በወላጅነታቸው በሚያከብሩና ለሥልጣናቸውም በሚዙ ሕፃናት ልጆቻቸው ሕይወት የሚታዩ ናቸው። «ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፤ በረዓድም (በመንቀጥቀጥ) ደስ ይበላችሁ» (መዝ 2፡11)።
«የክርስቶስ ፍቅር» የሚለው ሐረግ፥ በመሥዋዕትነት ሕይወቱን ለእኛ ብሉ በሰጠ ጊዜ የታየው ለእኛ ያለው ፍቅሩ ማለት ነው። «እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና፥ እኛ እንወደዋለን» (1ዮሐ 4፡19)። እርሱ የማንወደድ ሳለን ወደደን፤ እንዲያውም ፈሪሃ-እግዚአብሔር የራቀን፥ ኃጢአተኞችና ጠላቶቹ ሳለን ነበር የወደደን (ሮሜ 5፡6-10 ተመልከት)። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ ለዓለም (ዮሐ 3፡16)። ለቤተ ክርስቲያን (ኤፌ 5፡25)፥ ብሉም በኃጢአት ለጠፉ ግለሰቦች (ገላ.2፡20) ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ክርስቶስ የሞተባቸውን ምክንያቶች በትክክል በምትረዳበት ጊዜ፥ እርሱን ከመውደድ በቀር ሌላ አማራጭ አይኖርህም።
እኛ እንድንሞት ሞተልን (2ኛ ቆሮ. 5፡14 – «እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ»)። ይህ የአግኙ ከክርስቶስ ጋር የመተባበር እውነት በሮሜ 6 ውስጥ በዝርዝር ተገልጾአል። ክርስተስ በሞተ ጊዜ በእርሱና ከእርሱ ጋር ሞትን። ስለ ሆነም አሮጌው ሕይወት ዛሬ በእኛ ላይ ሊሰለጥን አይገባም። «ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ» (ገላ 2፡20)።
በሕይወት እንድንኖር ሞተልን (2ኛ ቆሮ. 5፡15)። ይህ ከክርስቶስ ጋር የመተባበራችን አዎንታዊ ገጽታ ነው . ከርሱ ጋር መሞት ብቻ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን «በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ» (ሮሜ. 6፡4)። ከርሱ ጋር ተነሥተናል። ከክርስቶስ ጋር ስለ ሞትን፥ ኃጢአትን ልናሸንፍ እንችላለን፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር በሕይወት ስለምንኖር፥ ለእግዚአብሔር ክብር ፍሬ ልናፈራ እንችላለን (ሮሜ 7፡4)።
በእርሱ አማካኝነት በሕይወት እንድንኖር ሞተልን፡- «በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና» (1ኛ ዮሐ 4፡9)። ይህ የደኅንነት ልምምዳችን ነው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘላለምን ሕይወት ማግኘት። ዳሩ ግን ለእርሱ እንጂ፥ ለራሳችን እንዳንኖርም ሞቷል (2ኛ ቆሮ. 5፡15)። ይህም የአገልግሎት ልምምዳችን ነው። «ሕይወቱን ለእርሱ እንድንኖርለት ክርስቶስ ሞታችንን ሞተልን» የሚለው አባባል እውነትነት ያለው ነው። አንድ ከደኅንነት የራቀ ኃጢአተኛ ወደ መስቀሉ ከመጣና ከዳነ በኋላ፥ ቀሪ ሕይወቱን እንደ ምን በራስ-ወዳድነት ሊያሳልፍ ይችላል?
በ1858 ዓ.ም. ፍራንሲዝ ሪድሊ ሐቬርጌል የተባለችው ወጣት የተጎዳ ዓይናቸውን በመታከም ላይ ከሚገኙ አባቷ ጋር ጀርመንን ጎብኝታ ነበር። በአንድ መጋቢ ቤት ውስጥ ሳለችም፥ «እኔ ላንተ ይህን አደረግሁ። አንተስ ምን አድርገህልኛል?» የሚሉ ቃላት የሰፈሩበትን የስቅለት ሥዕል ከግድግዳው ላይ ትመለከታለች። ወዲያውም ቁራጭ ወረቀት ወስዳ፥ በዚያ መልእክት ላይ የተመሠረተ ግጥም ጻፈች፤ ዳሩ ግን የጻፈችው ግጥም ስላላረካት፡ ወረቀቱን ጨምድዳ እሳት ውስጥ ከተተችው። ይሁንና ወረቀቱ ሳይቃጠል ቀረ። በኋላም አባቷ ያንን ግጥም እንድታሳትመው ገፋፏትና ዛሬ በፊሊፕ ፒ ብሊስ ዜማ ወጥቶለት በመላው ዓለም በሚገኙ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ በመዘመር ላይ ይገኛል።
ሕይወቴን ለወጥሁልህ ልገዛ ነፍስህን፥ ሰማይን ልከፍትልህ ልሰጥህ ርስትህን። ትድን ዘንድ ደሜ ፈሶአል፤ ምን መልሰህልኛል?
ክርስቶስ የሞተው በእርሱ አማካኝነትና ለእርሱ፥ እንዲሁም ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው። «የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ስለ እኛ ሞተ» (1ኛ ተሰ 5፡10)። በጎልጎታ ላይ ከተፈጸመው ነገር የተነሣ፥ አማኞች ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር ለመኖር ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።
እኛ እንድንሞትና በሕይወት እንድንኖር ሞተልን። ዳሩ ግን የሞተው የአዲሱ ፍጥረት ተካፋይ እንድንሆንም ጭምር ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡16-17)። ከክርስቶስ ጋር ያለን አዲስ ግንኙነት ከዓለምና በዙሪያችን ከሚገኙ ሰዎች ጋር አዲስ ግንኙነት እንዲኖረን አድርጓል። ከእንግዲህ ሕይወትን እንደ ቀድሞው አንመለከትም። ክርስቶስን «በሥጋ ማወቅ» ማለት፥ እርሱን በሰብዓዊ እይታ መገመት ማለት ነው። ዳሩ ግን ወደ ሰማይ ስላረገና አሁን በአብ ቀኝ በክብር ስለሚኖር፥ «የሥጋው ወራት» አብቅተዋል (ዕብ. 5፡7)።
አዳም የአሮጌው ፍጥረት ራስ ሲሆን፥ ክርስቶስ የኋለኛው አዳም – 1ኛ ቆሮ. 15፡45) ደግሞ የአዲሱ ፍጥረት ራስ ነው። ከአዳም አለመታዘዝ የተነሣ፥ አሮጌው ፍጥረት ለኃጢአትና ለኩነኔ ተገዝቶአል። ከኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝ የተነሣ፥ አዲሱ ፍጥረት ግን ጽድቅና ደኅንነት ነው። (ስለ «ሁለቱ አዳሞች» ማብራሪያ ሮሜ 5፡12-21 ተመልከት።) እኛ የአዲሱ ፍጥረት አካል ስለ ሆንን፥ ሁሉም ነገር አዲስ ሆኗል።
ክርስቶስን በተመለከተ አንድ አዲስ አስተሳሰብ (አመለካከት) አለን። ዕለት በዕለት እንደምናየው፥ በተለይ በመዝሙሮችና በሥዕሎች አማካይነት ለክርስቶስ «ሥጋዊ ሕይወት» የሚሰጠው ልዩ ትኩረት በመሠረቱ አሳዛኝ ነው። እርግጥ የክርስቲያን መልእክት በታሪክ መሠረት ላይ የተደገፈ ስለ ሆነ፥ የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት እውነታዎች ማወቅ አስፈላጊ ነው። ዳሩ ግን ግርግሙን (የቤተልሔሙን በረት) በዙፋን መተርጎም አለብን። ዛሬ የምናመልከው በግርግም የሚተኛውን ሕፃን ሳይሆን፥ በዙፋን ላይ ከብሮ የተቀመጠውን አዳኝ ነው።
«ሁሉም ነገር ስለ ታደሰ»፥ በዙርያችን ለሚኖሩ ሰዎች የተለየ አመለካከት አለን። ክርስቶስ እንደ ሞተላቸው ኃጢአተኞች አድርገን እንመለከታቸዋለን። ከእንግዲህ እንደ ወዳጆች ወይም ጠላቶች፥ እንደ ገዢዎች ወይም አጋዥ-ሠራተኞች አድርገን አንመለከታቸውም። ልክ ክርስቶስ እረኛ እንደሚያስፈልጋቸው ተቅበዝባዥ በጎች አድርጎ እንደሚመለከታቸው ሁሉ እኛም በዚያው ዓይን እናያቸዋለን። የክርስቶስ ፍቅር ግድ የሚለን እስከሆንን፥ እኛም የእርሱን ፍቅር ለሌሎች ከማጋራት ወደ ኋላ አንልም።
የተለየ ውዝግብ ባስከተለ በአንድ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ወቅት፥ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከተወዳዳሪዎቹ አንዱን የሚደግፍ የደረት ምልክት አድርጎ ወደ ሰንበት ትምህርት ክፍል ገባ። መጋቢውም አስቆመውና ከቤተ ክርስቲያን ግቢ እስኪወጣ ድረስ ምልክቱን ከደረት ኪሱ ላይ እንዲያወርድ ጠየቀው።
ሰውየውም፥ «ለምን አወርዳለሁ? ሰውየው እኮ በጣም ጥሩ ተወዳዳሪ ነው! » በማለት ሙግት ገጠመ።
መጋቢውም፥ «ይሁን እሺ፥ ግን አንድ ደኅንነትን ያላገኘ የሌላ ፓርቲ አባል ምልክቱን አድርገህ ቢያይህና ከብስጭት ላይ ቢወድቅ፥ ቃሉን ሰምቶ ከመዳን የማያግደው አይመስልህም?» በማለት መለሰለት።
ሰውየውም በዝግታ ምልክቱን ካወለቀ በኋላ፥ ፈገግ ብሉ፥ «ሰዎች ሪፖብሊካን ወይም ዲሞክራቶች ሳይሆኑ፥ አዳኝ የሚያስፈልጋቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን ማስታወስ በተገባኝ ነበር፤ ይህም ምርጫውን ከማሸነፍ የላቀ ነገር ነው» አለ።
እንደዚሁ ሁሉ እኛም ሌሉች ክርስቲያኖችን የአዲሱ ፍጥረት አካላት እንደ ሆኑ አድርገን መመልከት እንጂ፥ ባላቸው ትምህርት፥ ዘር፥ ሀብት፥ ወይም ማህበራዊ እሴት ላይ ተመርኩዘን ማናናቅ ወይም ማንገሥ የለብንም። «አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፤ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፤ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና» (ገላ 3፡28)።
የክርስቶስ ተልዕኮ (2ኛ ቆሮ.5፡18-21):: በዚህ አንቀጽ ውስጥ ቁልፉ አሳብ ዕርቅ ነው። ሰው ከዓመፁ የተነሣ፥ የእግዚአብሔር ጠላትና ከእርሱ ጋር ከሚኖረው ኅብረት የራቀ ነበር። ከመስቀሉ ሥራ የተነሣ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ሰውንና እግዚአብሔርን ወደ አንድነት አመጣ። እግዚአብሔርም ከሰው ጋር በመታረቅ፥ ፊቱን በፍቅር ወደ ጠፋው ዓለም መለሰ። የዕርቅ መሠረታዊ ትርጉም «ሙሉ ለሙሉ መለወጥ» የሚል ሲሆን፥ በእግዚአብሔርና በጠፋው ዓለም መካከል የተደረገውን የግንኙነት ለውጥ ያመለክታል።
የዕርቅ ሥራ በመስቀል ላይ ስለ ተፈጸመ፥ ለእግዚአብሔር ከሰው ጋር ዕርቅን ማድረግ አያሻውም። ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ያለበት ኃጢአተኛው ሰው ነው። «ሃይማኖት» ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ የፈጠረው ደካማ ዘዴና ከንቱም ልፋት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀን አካል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፥ የመታረቂያ ቦታውም ከመስቀሉ ሥር ነው።
በዚህ ክፍል ውስጥ ሌላው ቁልፍ አሳብ መቁጠር የሚለው ሲሆን (ለምሳሌ የእኛ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ ተቆጠረ)፥ አሳቡ በባንክ ቤት ውስጥ ገንዘብ ከማከማቸት ጋር የሚዛመድ ነው። «በአንድ ሰው የሂሳብ ደብተር ውስጥ ገንዘብ ማስቀመጥን» ያመለክታል። ገንዘብ በባንክ ቤት ውስጥ ስታስቀምጥ፥ ኮምፒውተሩ (ወይም ሠራተኛው) ያንኑ የገንዘብ መጠን በሂሳብ ደብተርህ ውስጥ ይመዘግባል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ ኃጢአታችን በሙሉ ወደ እርሱ ተላለፈ – በርሱ ደብተር ላይ ተመዘገበ። እግዚአብሔርም እነዚያን ሁሉ ኃጢአቶች ክርስቶስ ራሱ እንደ ፈጸማቸው አድርጎ ቆጠረ።
ውጤቱስ? ክርስቶስን እንደ አዳኛችን አድርገን ስላመንን፥ እግዚአብሔር የእነዚያ ሁሉ ኃጢአቶች ዋጋ እንደ ተከፈለ በመቁጠር፥ ከእንግዲህ በእኛ ላይ ኃጢአቶችን አይዝም። ከዚህም በላይ፥ እግዚአብሔር በእኛ መዝገብ ውስጥ የክርስቶስን ጽድቅ አስቀምጦታል! «እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን [ክርስቶስን] ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» (ቁ 21)።
ዕርቅ [ኃጢአትን በመሸከም ላይ የተመሠረተ ነው፡- ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ መጠይቆች በመስቀሉ ላይ ሙሉ ለሙሉ ስለ ተፈጸሙ፥ እግዚአብሔር ከኃጢአተኞች ጋር ሊታረቅ ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛቸው አድርገው የሚያምኑ ሰዎች፥ ኃጢአታቸውን ዳግም አይቆጥርባቸውም [ሮሜ. 4፡1-8፤ መዝ. (32):1-2]፡ መዝገባቸውንም በተመለከተ፥ የኢየሱስ ክርስቶስን ጽድቅ ለመጋራታቸው ተረጋግጦላቸዋል።
ጳውሎስ ለወዳጁ ለፊልሞና በጻፈው አነስተኛ መልእክት ውስጥ ይህንኑ እውነታ የሚያብራራ ግሩም መግለጫ አለ። የፊልሞና ባሪያ የነበረው አናሲሞስ ከጌታው ዘንድ ገንዘብ ሰርቆ ወደ ሮም ሸሽቶ ነበር። በዚህ ወንጀሉም ሊገደል ይችል ነበር። ይሁንና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፥ አናሲሞስ ከጳውሎስ ጋር ተገናንና ደኅንነትን ተቀበለ። ከዚያም ጳውሎስ አናሲሞስን ይቅር ብሎ ወደ ቤት ያስገባው ዘንድ ለማበረታታት ለወዳጁ ለፊልሞና ደብዳቤ ይጽፍለታል። ጳውሎስ፥ «እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው …ብድር ያለበት እንደ ሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቁጠር» (ፊልቁ 17 ና 18) ይለዋል። ጳውሎስ አናሲሞስና ፊልሞና እንዲታረቁ ዕዳውን ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር።
ይህ አስደናቂ የዕርቅ ትምህርት ክርስቶስን እንድናገለግል እንዴት ያነሣሣናል? እኛ መልእክት ያለን አምባሳደሮች ነን። እግዚአብሔር የዕርቅን አገልግሎት (2ኛ ቆሮ. 5፡18) እና የዕርቅን ቃል (ቁ. 19) ሰጥተናል።
በሮም መንግሥት ውስጥ ሴናተሪያልና ኢምፔሪያል የሚባሉ ሁለት የግዛት ዓይነቶች ነበሩ። ሴናተሪያል የሚባሉት ከሮም ጋር መዋጋትን አቁመው በሰላም የሚኖሩቱ ናቸው – እጃቸውን በመስጠት ተገዝተው የሚኖሩ ጻሩ ግን ኢምፔሪያሎቹ አቅሙ ከፈቀደላቸው በሮም ላይ ለማመፅ ይፈልጉ ስለ ነበር፥ አደገኞች ነበሩ። በመሆኑም ዓመፁ እንዳይነግሣ ሮም ወደ ኤምፔሪያል ግዛቶች አምባሳደሮችን መላክ ያስፈልጋት ነበር።
በዚህ ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች የክርስቶስ አምባሳደሮች ስለ ሆኑ፥ ዓለም በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ላይ ነች ማለት ነው። ይህች ዓለም ለእግዚአብሔር «የኢምፔሪያል ግዛት» ነች። እርሱም አምባሳደሮቹን ወደ ዓለም የላከው ጦርነትን ሳይሆን፥ ሰላምን እንዲያውጁ ነው። «ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ! » ብለን ኢየሱስ ክርስቶስን እንወክላለን (2ኛ ቆሮ. 4፡5፤ የሒ20፡21)። ኃጢአተኞች እኛንና መልእክታችንን ቢገፉ፥ በመሠረቱ የተገፋው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለዚህ ዓለም ዕመፀኛ ኃጢአተኞች የሰማይ አማባሳደር ሆኖ መሾም ምንኛ ታላቅ ዕድል ነው!
ገና ወጣት መጋቢ በነበርሁበት ጊዜ፥ ሰዎችን ለመጎብኘትና ስለ ክርስቶስ አዳኝነት ለመመስከር ኃፍረት ይሰማኝ ነበር። በኋላ ግን የነገሥታት ንጉሥ አማባሳደሩ ሆኘበመሾም፥ ዕድለኛ መሆኔን ተረዳሁ። ምንም የሚያሳፍረኝ ነገር አልነበረም። እንዲያውም፥ የምጎበኛቸው ሰዎች፥ ከክርስቶስ አምባሳደሮች አንዱ ሊጠይቃቸው በመምጣቱ መደሰት ነበረባቸው።
እግዚአብሔር በዓለም ላይ ጦርነትን አላወጀም፤ ይልቁንም በመስቀሉ ላይ ሰላምን አውጇል። ይሁንና አንድ ቀን ጦርነትን ያውጃል፤ በዚያን ጊዜም አዳኙን ለገፉት ሰዎች ጊዘው ይመሽባቸዋል (2ኛ ተሰ. 1፡3-10)። ሰይጣን በዓለም ውስጥ ነገሮችን ሁሉ ለመበታተን እየጣረ ነው፤ ዳሩ ግን ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያኑ ነገሮችን ወደ አንድነት በማምጣቱና ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በመመለሱ የዕርቅ አገልግሎት ላይ ተሰማርተዋል።
አገልግሉት ቀላል አይደለም። በአገልግሎታችን ስኬታማ ለመሆን ከፈለግን፥ አነሣሽ ምክንያታችን ፈሪሃ-እግዚአብሔር፥ አፍቅሮተ-ክርስቶስና እንዲሁም እርሱ የሰጠን ተልዕኮ መሆን አለበት። እርሱን ማገልገል ምንኛ መታደል ነው!