Site icon

የከበረ አገልግሎት አለን (2ኛ ቆሮ. 4፡1-6)

የዚህ ክፍል ዋናው መልእክት በቁጥር 1 እና 16 ውስጥ የተደጋገመ ሲሆን፥ ይኸውም «አንታክትም!» ወይም ጳውሎስ በቀጥታ እንዳሰፈረው፥ «ተስፋ አንቆርጥም» የሚል ነው። እርግጥ በጳውሎስ ሁኔታ ውስጥ ተስፋ ለመቁረጥ የሚያበቁ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፥ ዳሩ ግን ታላቁ ሐዋርያ ከተልዕኮው አላፈገፈገም ነበር። ይህን በመሰለው የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ዝሎ እንዳይወድቅ ያበረታው ምን ነበር? ጳውሎስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንዳገኘ ያውቅ ነበር! በመሆኑም ጳውሎስ በሌለው ነገር ከማጉረምረም ይልቅ፥ ባለው ነገር ተደሳች ነበር፤ እኔና አንተም እንደ እርሱ ልናደርግ እንችላለን። 

የከበረ አገልግሎት አለን (2ኛ ቆሮ. 4፡1-6) 

ጳውሎስ የጻፈው ቃል በቃል ሲተረጎም «ስለዚህ፥ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ስላለን» የሚል ነው። ለመሆኑ ይህ አገልግሎት ምን ዓይነት አገልግሎት ይሆን? በቀደመው ምዕራፍ ውስጥ የተገለጸው ዓይነት አገልግሎት ነው፡- ለሰዎች ሕይወትን፥ ደኅነትንና ጽድቅን የሚያመጣ የከበረ አገልግሉት፤ የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ የሚችል አገልግሎት። ይህ አገልግሎት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚለገስና እኛም ከእርሱ የተቀበልነው ስጦታ ነው። የተሰጠንም ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሣ እንጂ፥ ከእኛነታችን ወይም ካደረግነው አንዳች ነገር የተነሣ አይደለም (1ኛ ጢሞ. 1፡12-17 ተመልከት)። 

አገልግሉትህ የምትመለከትበት መንገድ እንዴት እንደምትፈጽመው ለመወሰን ይረዳሃል። ለክርስቶስ ማገልገል እንደ መታደል ሳይሆን እንደ ሸክም የምትቆጥር ከሆነ፥ ፍላጎት ታጣና የሚጠበቅብህን ተግባር ብቻ ታከናውናለህ፤ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች አገልግሎትን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ወረደ ቅጣት ይቆጥሩታል። ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ የመሆኑን እውነታ ሲያስብ፥ የእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት ከአእምሮው በላይ ሆነበት። ይህም በአገልግሎቱ ላይ የነበረው አዎንታዊ አመለካከት በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ውጤቶችን አስከትሉ ነበር። 

በመጀመሪያ፤ ተስፋ ቆርጦ አገልግሎቱን ከማቋረጥ ጠብቆታል (2ኛ ቆሮ. 4፡1)። በእስያ የተጋፈጣቸው መከራዎች እንዳስጨነቁት ለቆሮንቶስ ሰዎች ተናዞአል (1፡8)። ጳውሎስ ከታላላቅ ስጦታዎቹና ሰፋፊ ልምዶቹ ባሻገር፥ ሰው እንደ መሆኑ ለሰብዓዊ ድክመቶችም ተጋልጦ ነበር። ዳሩ ግን እንዲህ ባለው አስደናቂ አገልግሎት ውስጥ እያለ እንደ ምን ተስፋ መቁረጥ ይችላል? እግዚአብሔርን ይህን አገልግሉት በኃላፊነት የሰጠው እንዲወድቅ ነውን? በርግጥ አይደለም! ከመለኮታዊው ጥሪ ጋር መለኮታዊ ብቃትም ተሰጥቶታል፤ እግዚአብሔር እስከ መጨረሻው እንደሚረዳው ያውቅ ነበር። 

ተስፋ የቆረጠ አንድ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ምክር አስፈልጎት ኖሮ፥ የእስኮትላንድ ታላቁ ሰባኪ ለነበሩት አለክሳንደር ዋይት ደብዳቤ ጻፈ። አገልግሎቱን ትቶ መኮብለል ይሻለው ይሆን? ዋይት የመልስ ደብዳቤ ሲጽፉ፥ «ስብከትን ስለ መተው ከቶውንም እንዳታስብ! በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ ያሉት መላእክት እንኳን በዚህ ታላቅ አገልግሉትህ እየቀኑብህ ነው» በማለት አጽናንተውታል። ጳውሎስም ቢሆን የሚሰጠው የዚህ ዓይነቱን ምላሽ ነበር፤ ሁላችንም ሥራችን ከንቱ እንደ ሆነ በሚሰማን ጊዜ ሁሉ ልናስብበት የሚገባን አሳብ ይህ ነው። 

ሁለተኛ፥ አታላይ ከመሆን ጠብቆታል (2ኛ ቆሮ. 4፡2-4)። «ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን» (ቁ.2) ጳውሎስ እነዚህ ቃላት በሚጽፍበት ጊዜ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ስለ አይሁድ ሃይማኖት አጥባቂዎች እየተናገረ ነበር። ዛሬ ማንኛውም የሐሰት አስተማሪ ትምህርቱን በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንደሚመሠርት ይናገራል፤ ዳሩ ግን ሐሰተኛ አስተማሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል በማታለል መንገድ ይጠቀሙበታል። አንተም ብትሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከዓውድ ውጭ በመጠምዘዝና የራስህን የሕሊና ምስክርነት በማግለል የማንኛውንም ነገር እውነትነት ወይም ውሸትነት በመጽሐፍ ቅዱስ ለማረጋገጥ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ-ጽሑፍ መጽሐፍ ስለ ሆነ፥ መሠረታዊ የአተረጓጎም ሕግጋትን በመከተል ሊተረጎም ይገባል። ሰዎች ሌሎች መጻሕፍትን መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያነቡት አድርገው ቢያነቡ፥ ምንም እውቀት ሊገበዩበት አይችሉም። 

ጳውሎስ በግል ሕይወቱም ሆነ በስብከት ውስጥ የሚሸሽገው ነገር አልነበረውም። ሁሉም ነገር ግልጽና ታማኝነት ያለበት ነበር፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለማታለል ወይም ለመጠምዘዝ የሞከረበት ጊዜ የለም። የአይሁድን ሃይማኖት የሚያጠብቁ ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ከራሳቸው የቀድሞ ግንዛቤ ጋር ለማስማማት የሚጠመዝዙ ሲሆኑ፥ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ይከተሉዋቸው ነበር። 

እንግዲህ ጳውሎስ ለቃሉ ይህን ያህል ታማኝ አስተማሪ ከሆነ ዘንዳ፥ ብዙ ሰዎች መልእክቱን ያልተቀበሉት ለምንድን ነበር? ለሐሰተኛ አስተማሪዎች ነፍሳትን በቀላሉ የመማረኩ ተግባር የሚሳካላቸው በምን ምክንያት ነበር? ምክንያቱ፥ ደኅንነትን ያላገኘ ኃጢአተኛ ሰው አእምሮው በሰይጣን ስለሚታወርና ለእንደዚህ ዓይነቱም የተሰናከለ ሰው ከእውነት ይልቅ ውሸትን ማመን ስለሚቀለው ነው። «ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ» (ቁ 3-4)። 

ጳውሎስ አስቀድሞ የአይሁዶች አእምሮ ከልባቸው ዕውርነት የተነሣ «እንደ ተጋረደ» ገልጾአል (3፡14-16፤ ሮሜ 11፡25)። የአሕዛቦች አእምሮም ጨልሞአል! ደኅንነትን ያላገኙ ሰዎች («የሚጠፉ») የወንጌሉን መልእክት ለመረዳት አይችሉም። የከበረው የደኅንነት ብርሃን በሕይወታቸው ውስጥ እንዲያበራ ሰይጣን ጨርሶ አይፈልግም። ሰይጣን የዚህ ዓለም አምላክና አለቃ በመሆኑ (ዮሓ 12:31)፥ ከደኅንነት የራቁትን ኃጢአተኞች በጨለማ ውስጥ ያቆያቸዋል። የሚያሳዝነው ደግሞ ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል (የአይሁድን ትምህርት ያስፋፉ የነበሩትን ዓይነት) በሃይማኖት መሪዎች መጠቀሙ ነው። ዛሬ ላኑፋቄ ከተጋለጡት ሰዎች ብዙዎቹ በመጀመሪያ የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት አባላት ነበሩ።  

ጳውሎስ ይህንን አገልግሎት ከክርስቶስ የመቀበሉ የሚያስገርም እውነት ግን ከክህደትና ከማታለል ጠብቆታል፤ እንዲሁም ደግሞ ስለ ራሱ ብዙ ከመናገርም ጠብቆታል (2ኛ ቆሮ. 4፡5-6)። «ራሳችንን አንሰብክምና!» (ቁ. 5)። የአይሁድን ትምህርት የሚያስፋፉ መምህራን ስለ ራሳቸው መስበክንና በፈጸሙዋቸው ተግባራት መከበርን ይወዱ ነበር (10፡12-18)። ሕዝቡን ለመርዳት የሚጥሩ አገልጋዮች ሳይሆኑ፥ ሕዝቡን የሚበዘብዙ አምባገነኖች ነበሩ። 

ጳውሎስ ያለ አንዳች ጥርጥር ትሑትና ራስን ዝቅ የማድረግ ሕይወት የሚመራ ሰው ነበር። በራሱ ማንነት የማይታመን (1፡9)። ወይም ራሱን የማያመሰግን (3፡1-5)፥ ወይም ስለ ራሱ የማይሰብክ (4፡5) ሰው ነበር። የሚፈልገው ነገር ቢኖር ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መምራትና በእምነት ማነጽ ብቻ ነበር። ለነገሩማ ለጳውሎስ «የአድናቂዎች ክበብ» በማቋቋም ከታላላቅ ሰዎች ጋር ለመጎዳኘት ጉጉት ከነበራቸው ደካማ ሰዎች ጥቅም ማግኘቱ በቀለለውም ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የሚሠሩት በዚህ መልኩ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ጳውሎስ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሉት አምሮቱም፥ ፍላጎቱም አልነበረውም። 

አንተስ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ላላወቁት ሰዎች በምታካፍልበት ጊዜ የሚከሰተው ነገር ምንድን ይመስልሃል? ብርሃኑ ማብራት ይጀምራል! ጳውሎስ ደኅንነትን በዘፍጥረት 1፡3 ላይ ከተገለጸው ከፍጥረት ታሪክ ጋር አወዳድሮታል። ልክ በዘፍጥረት 1፡2 ላይ እንደምንመለከታት ምድር፥ ደኅንነትን ያላገኘ ኃጢአተኛ ቅርጽ የሌለውና ባዶ ነው፤ ይሁንና በክርስቶስ በሚታመንበት ጊዜ፥ አዲስ ፍጥረት ይሆናል (2ኛ ቆሮ. 5፡17)። ከዚያም እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚታመነው ሰው ሕይወት ቅርጽ በመስጠት ባዶነቱን መሙላት ይጀምራል፤ ሰውየውም ለጌታ ፍሬያማ መሆን ይጀምራል። «ብርሃን ይሁን!» ያለው የእግዚአብሔር ቃል ሁሉንም ነገር አዲስ ያደርገዋል። 

Exit mobile version