ጳውሎስ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ከቤተሰብ ጋር ማነጻጸሩ የሚታወስ ነው (3፡1-4)። አሁን ግን የአጽንኦቱ ማዕከል አገልጋዩ እንደ «መንፈሳዊ አባት» መሆኑ ላይ ነው። በየትኛዎቹም መልእክቶቹ ጳውሎስ ራሱን «አባት» ብሎ አልጠራም። ጌታ በማቴ 23፡8-12 ላለው ክፍል የሰጠውን ትምህርት ያውቅ ስለነበር ነው። ነገር ግን ራሱን ከአንድ «መንፈሳዊ አባት» ጋር በማነጻጸር፥ ጳውሎስ ስለ እነርሱ ሆኖ ስለፈጸማቸው ጠቃሚ አገልግሎቶች ቤተ ክርስቲያንን አስታወሳት።
በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ቤተሰብን መሥርቷል (4፡14-15)። ቆሮንቶሳውያን በእምነት የጳውሎስ ተወዳጅ ልጆች ነበሩ። ወንጌልን ለአንድ ሰው ስናካፍል ና በክርስቶስ ወደሚገኝ እምነት በደስታ ስንመራው ለሕይወቱ «መንፈሳዊ ወላጅ» እንሆናለን። ይህ በግለሰቡ እምነት ላይ ምንም ዓይነት የተለየ ሥልጣን አያጎናጽፈንም (2ኛ ቆሮ. 1፡24)፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእድገቱ እንዲረዳው የሚጠቀምበትን ልዩ ግንኙነት ይፈጥራል። የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አዲስ የተወለዱ ክርስቲያኖች እንዲያድጉ የምትረዳ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ናት።
በመለወጣቸው ጳውሎስ የወሰደው «ክብር» አለመኖሩን ልብ ማለት ጠቃሚ ነው። መንፈሳዊ ልደታቸው በክርስቶስና በወንጌሉ አማካኝነት ነው። ኃጢአተኞች ዳግም የሚወለዱት በእግዚአብሔር መንፈስ ና በእግዚአብሔር ቃል (1ኛ ጴጥ. 1፡23-25፤ ዮሐ 3፡6) ነው። ጳውሎስ በልደታቸው ወቅት ከአጠገባቸው የቆመና የረዳቸው «አባት» ነው።
አንድ ሕፃን ልጅ ብዙ ሞግዚቶች እና አስተማሪዎች ሊኖሩት ይችላል። ነገር ግን ሊኖረው የሚችለው አንድ አባት ብቻ ነው። በማንም ሊታገድ የማይገባ ልዩ ግንኙነት ከአባቱ ጋር አለው። ጳውሎስ ከመምጣቱ በፊት በቆሮንቶስ ምንም ቤተ ክርስቲያን አልነበረም፤ በመሆኑም ሁለተኛ ትውልድ እማኞች ቢሆኑም እንኳ የጳውሎስ ውጤታማ አገልግሎት ፍሬ ነበሩ።
ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲመሠርት አጵሎስ ተከተለውና ሕዝቡን አስተማረ። ጴጥሮስም በቆሮንቶስ አገልግሎ ነበር፤ ይህ ግን በቅዱሳት መጻሕፍት በአንዳንድ በኩል ግልጽ አልተደረገም። (ምናልባት ራሱ በግንባር የተገኘ ሳይሆን፥ ነገር ግን ሌሎች አገልጋዮች ከኢየሩሳሌም የጴጥሮስ «ወኪል» ሆነው በቆሮንቶስ ሳያገለግሉ አልቀሩም።) የእግዚአብሔር ልጆች የተለያዩ አስተማሪዎች አገልግሎቶች ያስፈልጉአቸዋል። ነገር ግን ወደ ክርስቶስ ያመጣቸውን «መንፈሳዊ አባት» መዘንጋት የለባቸውም።
ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ለቤተሰቡ ምሳሌ ነበር (4፡16-17)። ልጆች ወላጆቻቸውን ለበጎ ይሁን ለክፉ፥ የመኮረጅ ነገር አላቸው። ተመራማሪዎች እንደሚሉን ከሆነ ወጣቶች መጠጥን የሚለምዱት ከጓደኞቻቸው ላይሆን ከቤት ነው። የእኔ ግምት ሌሎችም መጥፎ ልማዶች በዚሁ መንገድ እንደሚለመዱ ነው።
ተከታዮች የሚለው ቃል፥ በቀጥታ ሲተረጎም «ኮራጆች» ይሆናል። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፡17 ራሱን እንደሚያመጻድቅ አድርገው እንዳያስቡት ይህን ተግሣጽ ሰጠ። ትንንሽ ልጆች በመጀመሪያ የሚማሩት በምሳሌ፥ ከዚያም በገለጻ ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን በመጋቢነት ባገለገለበት ጊዜ በፍቅር፥ ለክርስቶስ በመሰጠት፥ በመሥዋዕትነት እና በአገልግሎት በፊታቸው ራሱን ምሳሌ አድርጎ ተከለ። «እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ» (1ኛ ቆሮ. 11፡1)። ጳውሎስ ጥሩ ምሳሌ ነበር፤ ምክንያቱም ይከተል የነበረው ከሁሉም ምሳሌዎች ታላቁን፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለነበር ነው።
ደግሞም ጳውሎስ ጥሩ አስተማሪ ነበር። አንድን ልጅ ወደ ብስለት የሚያደርሱት፥ ምሳሌም መመሪያም ሁለቱም ናቸው። ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ያስተማረውን ዶክትሪን እና ተግባራት ለማስታወስ ከመንፈሳዊ ልጆቹ አንዱ የሆነውን ጢሞቴዎስን ላከው። ጢሞቴዎስ ደብዳቤውን ለቤተ ክርስቲያን ሳያደርስ – (16፡10) ለደብዳቤው መንገድ ለመጥረግ ራሱ በቀጥታ ወደዚያው ሄደ።
እግዚአብሔር ለአንድ ቤተ ክርስቲያን አንድ መለኪያ፥ ለሌላ ቤተክርስቲያን ደግሞ የተለየ መለኪያ አያደርግም። ፈቃዱን በተለያዩ መንገዶች ያደርግ ይሆናል (ፊልጵ 2፡12-13)፥ ነገር ግን መሠረታዊ ዶክትሪኖች እና መርሆዎች አንድ ናቸው። ሰዎች ከእግዚአብሔር ጥበብ ስለራቁና የሰውን ጥበብ ስለተኩ፥ በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ጽኑ የሆኑ የዶክትሪን ልዩነቶች አሉን። ሰዎች «ከተጻፈው) (4:6) ርቀው ስለሄዱ ይህ በቤተ ክርስቲያን ክፍፍልን አምጥቷል፡፡
ሦስተኛ፣ ጳውሎስ ቤተሰቡን ለመግራት የታመነ ነበር (4፡18-20)፡፡ የሕጻን ፈቃድ መገራት እንጂ መደምሰስ የለበትም። ድንጉላ ፈረስ እስኪገራ ድረስ አደገኛ እና ጥቅመ ቢስ ነው፤ ነገር ግን አንዴ መታዘዝን ከለመደ ገራም እና ጠቃሚ ይሆናል። ትዕቢት በክርስቲያን ሕይወት እና በቤተ ክርስቲያን በጣም አደገኛ ነው። የኃጢአት እርሾ (5፡6-8) ቆርንቶሳውያን ጳውሎስ አይምጣብን ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው!» (2ኛ ቆሮ. 10፡8-11) እስኪሉ ድረስ “በትዕቢት እንዲነፉ” አደረጋቸው።
ጳውሎስ አለመታዘዛቸውን ታግሶት ነበር፥ ነገር ግን ሥነ ሥርዓት ለመያዝ ጊዜው እንደደረሰ ያስጠነቅቃቸዋል። ጳውሎስ «ይህ ለመጨረሻ ጊዜ ነው የምነግርህ፥ ለመጨረሻ ጊዜ!» እያለች በባለጌ ልጇ ላይ እንደምታምባርቅ ሆደ ሰፊዋ ዘመናዊ እናት አይደለም።
ታማኝ ወላጅ ልጁን መግራት አለበት። ማስተማርና በፊታቸው ምሳሌ ሆኖ መገኘት ብቻ አይበቃም፤ ሲያምፁ እና ለመታዘዝ እምቢ ሲሉ መቅጣት አለበት። ጳውሎስ በገርነት በመምጣት ኃጢአታቸውን በተለሳለሰ ሁኔታ መያዝን በመረጠ ነበር። ነገር ግን የእነርሱ የራሳቸው አመላካከት እንዲህ እንዳይሆን አስቸገረው። በትዕቢት በጣም የተወጣጠሩ ነበሩ-እንዲያውም አለመታዘዛቸውንም እንኳ ይኮሩበት ነበር! (5፡1-2)።
በዚህ አንቀጽ ንጽጽሩ የሚካሄደው በንግግር እና በኃይል፥ በቃላት እና በተግባር መካከል ነው። አይበገሬዎቹ ቆሮንቶሳውያን «ትልቅ ነገር ሲናገሩ» ችግር አልነበራቸውም፤ ብዙ ጊዜ ልጆች እንደሚያደርጉት ማለት ነው፤ ነገር ግን ንግግራቸውን «በአካሄዳቸው» እያጸኑትም ነበር። ሃይማኖታቸው በቃላት ብቻ ነበር። ጳውሎስ ኃጢአታቸውን እና የእግዚአብሔርን ቅድስና በሚገልጥ መንገድ የራሱን «ንግግር» በኃይል፥ በድርጊት ለማጠናከር ዝግጁ ነበር።
ይህ ክፍል በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስለሚኖረው ሥርዓት ለሚያወሱ ቀጣይ ሁለት ምዕራፎች መንገዱን ጠርጓል። በቆሮንቶሳውያን ጉባኤ ብዙ ኃጢአት ነበርና ጳውሎስ ይህን ለማስተካከል ተዘጋጀ፡፡ ስለ ጉዳዩ ቀደም አድርጎ ደብዳቤ ጽፎ ነበር (5፡9)፤ ነገር ግን ጉባኤው ሊታዘዘው አልፈቀደም። ይኼኔ ነበር ከመንፈሳውያን ምእመናን መካከል አንዳንዶቹ ጳውሎስን በመገናኘት (1፡11፤ 16–17) ችግሩን ያካፈሉት። ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንዳንዶቹ እንዲያማክራቸው ለጳውሎስ ደብዳቤ ጽፈው ነበር (7፡1)፥ ከዚያም የጻፈላቸውን ምክር እንዲታዘዙት ጳውሎስ ጸልዮአል።
ራሳቸውን መግዛት የማይችሉ በሥርዓት እንዲገዙ ማድረግ የሕይወት መርህ ነው። የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና የሕክምና ባለሥልጣናት አሽከሪካሪዎች በሚነዱበት ጊዜ የደኅንነት መጠበቂያ ቀበቶ እንዲያስሩ ይገፋፋሉ፤ ነገር ግን ብዙ አሽከርካሪዎች ይህን አይቀበሉትም። በመሆኑም መንግሥት አሽከርካሪዎች በሚነዱበት ጊዜ የደኅንነት መጠበቂያ ቀበቶ እንዲያስሩ ሕግ ማውጣት ግድ ይሆንበታል። ይህን የማትታዘዝ ከሆነ፥ ትቀጣለህ።
ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ቤታቸውን እንዲያስተካክሉ ዕድል ሰጥቶአቸዋል። በሚከተሉት ምዕራፎች፥ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዴት በእግዚአብሔር ፈቃድ ሥር መተዳደር እንዳለባት ጳውሎስ ይገልጻል። ምን ያደርጋል፥ ቤተ ክርስቲያን ወዲያው አልታዘዘችውም። ጳውሎስ አስቸኳይ ጉብኝት ወደ ቆሮንቶስ ማድረግ ነበረበት፤ በጉብኝት ወቅት ያለፈበት ሁኔታ በጣም የሚቆጠቁጥ ነበር (2ኛ ቆሮ. 2፡1፤ 12፡14፤)። ከዚያ በኋላ በጣም ጠንከር ያለ መልእክት እንዲጽፍላቸው ተገደደ (7፡8–12)፤ ይህ መልእክት የተወሰደው በቲቶ ሳይሆን አልቀረም።
በእግዚአብሔር ክብር እንደሚሆን ጉዳዮቹ በአብዛኛው ተስተካክለው ነበር። ጥቂት «የማጽዳት ሥራ» ይቀር ነበር (2ኛ ቆሮ. 12፡20-13፡5)። ይሁንና በዚህ ጊዜ ቀውሱ ተገባድዶ ነበር።
የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ መሆን ቀላል ነገር አይደለም። ሰዎች የፈለጉትን ቢናገሩህ ወይም ቢያደርጉህ፥ እንደ መጋቢነትህ ለጌታህ ባለህ ታማኝነት መጽናት አለብህ። በዓለም ሰዎች ተቀባይነት እንዳላገኘህ እንዲሁ በዚህም ተቀባይነት ታጣ ይሆናል።
የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች የእኛ ፍቅር፥ ክብር፥ ታዛዥነት ና የጸሎት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።