የዕርቅ ልመና (2ኛ ቆሮ.7፡2-16)

«ልባችሁን ክፈቱልን» (6፡13 – አዲስ ትርጉም)። «በልባችሁ ሥፍራ አስፉልን» (7፡2)። «በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ በአንድነት ይሄዳሉን?» (አሞ. 3፡3)። እግዚአብሔር የሚቀበላቸውና ደግሞ ከጳውሎስ ጋር ኅብረት ሊኖራቸው የሚችለው፥ የቆሮንቶስ አማኞች ሕይወታቸውንና የቤተ ክርስቲያን ኅብረታቸውን ሲያነጹ ብቻ ነበር። 

በዚህ ክፍል ውስጥ አጽንኦት የተሰጠው፥ እንዲህ ያሉ ታላላቅ መከራዎችን በእስያና በጢሮአዳ ከተቀበለ በኋላ፥ እግዚአብሔር ጳውሎስን ባጽናናበት ሁኔታ ላይ ነው (1፡8-10 2፡12-13 ተመልከት)። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ሦስት የመጽናናት ሁኔታዎች ይገኛሉ። 

1. ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ያጽናናል (2ኛ ቆሮ. 7፡2-4)። ቤተ ክርስቲያኗ ቲቶን ስለ ተቀበለች፥ አሁን ጳውሎስን መቀበል ነበረባት (ቁ 13)። ጳውሎስ እነርሱን ለመበደል ብሉ ያደረገው ምንም ነገር ስላልነበረ፥ እንዲተማመኑበት ይጠይቃቸዋል። ይህ በተለይም «ማጭበርበር» («መበዝበዝ» 11፡20 ተመልከት) በሚለው ቃል የሐሰት አስተማሪዎች እርሱን ለመወንጀል እንደ ተጠቀሙበት የሚያመለክት ነው። «ጳውሎስ ይህን የእርዳታ ስጦታ የሚሰበስበው፥ ራሱ ሊጠቀምበት ሲል ነው» ሲሉ ስሙን ያጠፉት ነበር። 

ሰዎችን እንደምንወዳቸው በመግለጽ ስለ ፍቅራችን ማረጋገጥ አቀበት የሚሆንብን ለምንድነው? ጳውሎስ እነርሱን ለማሳመን ከዚህ የበለጠ ምን ሊያደርግ ይችል ነበር? እነርሱ ከልቡ ውስጥ ሥፍራ ተሰጥቶአቸው ስለ ተቀመጡ፥ ካስፈለገ ሊሞትላቸው እንኳ ይፈቅድ ነበር (3 ከቁ 1 ጀምሮ፤ 6፡11-13 ተመልከት)። እርሱ ስለ እነርሱ መልካምነት በመመካት ለሌሎች «በልዩ አክብሮት» ይናገርላቸው እንጂ እነርሱ ግን የትችት ዶፍ እያወረዱበት ነበር። 

ዳሩ ግን ከእነዚህ ችግሮች ባሻገር፥ የቲቶ ጉብኝት ስኬታማ ስለ ነበር፥ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጽናናት አመቺ መንገድ አግኝቶ ነበር፤ በመሆኑም አሁን «ያዘመመውን ቅጥር ለመጠገንና» ኅብረትን ለማደስ በር ተከፍቶ ነበር። ይህም ወደ ሁለተኛው መጽናናት ያሸጋግረናል። 

2. ቲቶ ጳውሎስን ያጽናናዋል (2ኛ ቆሮ. 7፡5-10)። ጳውሎስ በመጀመሪያ የተጽናናው፥ ከረጅም ጊዜ መለያየት በኋላ ከቲቶ ጋር ግንኙነት ለማድረግ በመቻሉ ነበር። በዚያን ዘመን ራቅ ባለ አካባቢ ከሚኖር ሰው ጋር መገናኘት ወይም እንደ ልብ መጓጓዝ የዋዛ አልነበረምና፥ ጳውሎስ የቲቶን የቆሮንቶስ ጉብኝትም ሆነ የዕቅዶቹን ከዳር መድረስ በተመለከተ በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ መደገፍ ነበረበት። (ዘመናዊ መገናኛና መጓጓዣ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ቢሆንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ መደገፍ አለብን።) 

ዳሩ ግን ጳውሎስ ቲቶ በቆሮንቶስ የተደረገለትን አቀባበል ሲናገር ተጽናና። የጳውሎስን «አሳዛኝ ደብዳቤ» አንብበው ከኃጢአታቸው ንስሐ ገቡ፤ ችግሮቹን የቆሰቆሱትንም ምዕመናን ቀጡዋቸው። 

ጳውሎስ ጠንካራ ደብዳቤ ጽፎ ነበርና በዚያ ምክንያት ተጸጽቶ ነበር። ይሁንና ደብዳቤው ግቡን ስለ መታና የቆሮንቶስ ሰዎች ንስሐ ስለ ገቡ፥ ጳውሎስ ደስ ተሰኘ። ንስሐቸውም እንዲያው አላፊ «ጸጸት» ብቻ ሳይሆን፥ ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያደረበት ኃዘን ነበር። «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኃዘን ጸጸት የሌለበትን ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኃዘን ግን ሞትን ያመጣል» (7፡10)። የሐዘን የልዩነቱ ደረጃ በይሁዳና በጰጥሮስ ሕይወት ውስጥ ተስተውሏል። ይሁዳ በኃጢአቱ ተጸጸተና ራሱን ገደለ፤ ጴጥሮስ ግን ስለ ውድቀቱ አንብቶ ንስሐ ገባ (ማቴ. 26፡75-27፡5)። 

ክርስቲያኖች ንስሐ መግባት ያስፈልጋቸዋል ወይ? ኢየሱስ እንደሚያስፈልገን ይናገራል (ሉቃ. 17፡3-4)፤ ጳውሎስም ከእርሱ ጋር ይስማማል (2ኛ ቆሮ. 12፡21)። በራእይ ምዕራፍ 2-3 ውስጥ ከተዘረዘሩት የትንሹ እስያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አራቱ ንስሐ እንዲገቡ ታዘዋል። ንስሐ መግባት ማለት «አእምሮን መለወጥ» ማለት ሲሆን፥ ባለመታዘዝ የሚመላለሱ ክርስቲያኖች ይህንኑ ማድረግ አለባቸው . ደኅንነትን ለማግኘት ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያደርጉት የነበረውን የቅርብ ግንኙነት ለማደስ። 

3. የቆርንቶስ አማኞች ቲቶን አጽናንተዋል (2ኛ ቆሮ. 7፡11-16)። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ትልቅ እርምጃዎችን ወሰዱ። በመጀመሪያ፥ ቲቶን አገኙትና ከእርሱ ጋር ባደረጉት አንድነት አጽናኑት(ቁ 13)። ጳውሎስ ሲመካባቸው በነበረው ሁኔታ አሁንም በመገኘታቸው፥ በዚህም የቲቶ ልብ በፍስሐ ተሞልቶ ነበር። በተጨማሪም ከጳውሎስ የተጻፈውን መልእክት ስላመኑበት፥ በዚያው መሠረት መንቀሳቀስ ያዙ። 

በቁጥር 11፥ ጳውሎስ አሠራራቸውን ገልጾአል። «እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኃዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፡ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል፥ በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል።» ጳውሎስ ንስሐ የገቡበትንና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያሳዩትን አሳቢነትና ቅንዓት ከቲቶ ሲሰማ ልቡ ዐረፈ – ተጽናና። የጳውሎስ የደብዳቤው ዓላማ በደለኛውን ሰው ለመገሠጽና ለመርዳት ብቻ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ጭምር መሆኑን ያረጋግጣል። ጳውሎስ ከዚህ ነገር የተነሣ ብዙ ተሰቃይቷል፤ ዳሩ ግን አሁን ችግሩ ስለ ተቃለለ ስቃዩ ዋጋ አላጣም ነበር። 

እጅግ ከሚያዳግቱ ነገሮች አንዱ የሻከረን ግንኙነት መልሶ መገንባት ነው። ጳውሎስም በበኩሉ ይህንን ለማድረግ መሞከሩን በ2ኛ ቆሮንቶስ በተለይ በምዕራፍ 6 እና 7 ላይ እናያለን። ሆኖም የሚያሳዝነው ነገር፥ ዛሬም ቢሆን በርካታ ሻካራ ግንኙነቶች በቤት፥ በቤተ ክርስቲያን፥ ብሉም በአገልግሉት ውስጥ መታየታቸው ሲሆን ሊወገዱ የሚችሉት ደግሞ ሰዎች ችግሮችን በእውነተኛነት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በመመራትና በፍቅር ሲጋፈጡና ከእግዚአብሔር ጋር ለመስማማት ሲፈልጉ ነው። 

እኔና አንተ የግል ሕይወታችንን ስንመረምር፥ የመፍትሔው እንጂ የችግሩ አካል እንዳንሆን መወሰን አለብን። እግዚአብሔር በተቃቃሩ ወገኖች መካከል ስምምነትን ለማስገኘት በእኛ እንዲጠቀምብን እስከ ፈለግን፥ አክብሮት ያለበትን አመስጋኝነትን ማሳየት መለየትን መለማመድና ዕርቅን ማበረታታት አለብን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: