እውነተኛ ነገር በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ፥ ሰዎች የማስመሰል ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል። ሌላው ቀርቶ የኪነ-ጥበብ ሃያሲያን እንኳ «ምርጥ ሥራዎች» ተብለው በቀረቡ አስመሳይ የሥዕላ ሥዕል ቅቦች ተሞኝተዋል፤ እንደዚሁም እውነተኛ አሳታሚዎችም «ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መዛግብት» እንደ ሆኑ በመቁጠር የገዙዋቸው ንብረቶች በማስመሰል የተሠሩ መሆናቸውን ዘግይተው ይረዳሉ። ይህን የመሳሰለውን ማጭበርበር ስንመለከት፥ ሄነሪ ዎርድ ቢቸር የተባሉት ሰው «ለውሸት ምንጊዜም ምርኩዙ እውነት ነው» በማለት የተናገሩትን ነገር ሐቀኝነት ያስታውሰናል።
የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል በአሕዛብ መካከል መሠራት ከጀመረ ብዙም ሳይሰነብት፥ የጸጋና የሕግ ቅልቅል የሆነው የማስመሰል « ወንጌል» ብቅ ማለት ጀመረ። ይህም ተግባር የተከናወነው «አይሁዳውያን ወግ አጥባቂዎች» ብለን በምንጠራቸው ቀናተኛ ቡድኖች ነበር። ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች እምነታቸውን ውድቅ እንዲያደርጉባቸው የጻፈላቸው ሲሆን፥ በ2ኛ ቆሮንቶስም ውስጥ ስለ እነዚህ ወገኖች ብዙ ጊዜ ይጠቅሳል።
የእነዚህ ቡድኖች ዓቢይ መልእክት ያተኮረው ደኅንነት የሚገኘው በክርስቶስ በማመንና ሕግን በመጠበቅ እንደ ሆነ በማስገንዘብ ላይ ነበር (የሐዋ. 15 ከቁ. 1 ጀምሮ)። እንደዚሁም አማኙ በእምነቱ ፍጹም የሚሆነው የሙሴን ሕግ በመጠበቅ እንደ ሆነያስተምሩ ነበር። እንዲሁም ደካማው ሰብዓዊ ተፈጥሮ ክርስቶስን ከመታመንና መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ ከመፍቀድ ይልቅ፥ ቀደምትነቱን ሃይማኖታዊ ግቦችን ለመጨበጥ በመስጠቱ፥ «የሕጋዊነት ወንጌላቸው» ከፍተኛ ተወዳጅነትን ሊያተርፍ ችሉ ነበር። ለሰብዓዊው ሚዛን፥ ከእውነተኛ ጽድቅ ይልቅ «ሃይማኖት»ን መለካት በጣም ቀላል ነው።
ጳውሎስ እነዚህን የሐሰት አስተማሪዎች የእግዚአብሔር ቃል «ሸቃሎች» አድርጎ ይመለከታቸዋል (2ኛ ቆሮ. 2፡17 ተመልከት) – አላዋቂዎችን የሚበዘብዙ «ሃይማኖታዊ ቀማኞች» ማታለል የተሞላበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሪያ ዘዴዎቻቸውን ከመነሻው አውግዟል (4፡2)፤ ነፍሳትን እንደ ማረኩ በመግለጽ ለመመካት የቃጡበትንም ሁኔታ አናንቋል (10:12-18)። የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ ያሳሰባቸውን ልዩ እርዳታ በመሰብሰብ በኩል ወደ ኋላ ከቀሩባቸው ምክንያቶች አንዱ እነዚህ ቀናተኛ አይሁዳውያን ቤተ ክርስቲያንን ስለ ዘረፉ ነበር (11፡7-12፥ 20፤ 12-14)።
ለመሆኑ ጳውሎስ የነዚህን ሕጋውያን የሐሰት አስተማሪዎች የእምነት ትምህርቶችና ልምምዶች እርባና-ቢስነት ያረጋገጠው እንዴት ነበር? የእግዚአብሔርን የጸጋ አገልግሎት የላቀ ክብር በማሳየት ነበር። በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 ጳውሎስ የአሮጌውን ቃል ኪዳን አገልግሎት (ሕግ) ከአዲሱ ኪዳን አገልግሎት (ጸጋ) ጋር በማነጻጸር፥ የአዲሱን ኪዳን አገልግሎት የበላይነት አረጋግጧል። እነሆ ያቀረባቸውን ማነጻጸሪያዎች ተመልከት፡-
የድንጋይ ጽላት – የሰው ልብ ጽላት (2ኛ ቆሮ. 3፡1-3)
እነዚህ አይሁዳዊነትን ለማስፋፋት የሚታገሉ ወገኖች፥ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ «ታላላቅ ሰዎች» «የምስጋና ደብዳቤ» (ቁ. 1 አዲስ ትርጉም) እንደ ተቀበሉና ጳውሎስ ግን ይህን ያህል አስፈላጊ ከበሬታዎች እንዳልነበሩት በትምክህት ይናገራሉ። አንድ ሰው የግል ከበሬታውን እግዚአብሔር ስለ እርሱ በሚያውቀው ሳይሆን፥ ሰዎች ስለ እርሱ በሚናገሩት ነገር መለካቱ የሚያሳዝን ነው። ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያሞካሽ ደብዳቤ አላስፈለገውም፡- አስፈላጊዎቹ ምስጋናዎቹ ሕይወቱና አገልግሎቱ ብቻ ነበሩ።
እግዚአብሔር ሕግን ሲሰጥ፥ በድንጋይ ጽላቶች ላይ የቀረጻቸው ሲሆን፥ እነዚያም ጽላቶች በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ምንም እንኳ እስራኤላውያን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ለማንበብ ቢችሉም፥ ሆኖም ግን ይኸው ልምምድ በራሱ ሕይወታቸውን ሊለውጥ አይችልም ነበር። ሕግ ውጫዊ ነገር ሲሆን፥ የሰዎች ሕይወት እንዲለወጥ ከተፈለገ፡ ውስጣዊ ኃይል ያስፈልጋቸዋል። አንድ የሕግ ሰው «ይህን አድርግ! » ወይም «ይህን አታድርግ! » የሚል ትዕዛዝ ይሰጠናል እንጂ፥ የምንታዘዝበትን ኃይል አያጎናጽፈንም። ብንታዘዝ እንኳ፥ ከልብ የመነጨ ስለማይሆን፥ ማብቂያችን ከቀድሞው ሁኔታችን የከፋ ይሆናል!
የጸጋ አገልግሎት ግን ልብን ይለውጣል። የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔርን ቃል በመጠቀም ከልብ ውስጥ ይጽፋል። የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዘ የከፉ ኃጢአተኞች ነበሩ፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር የጸጋ አገልግሎት ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለወጠው (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11 ተመልከት)። ይህም የእግዚአብሔር የጸጋ ልምምዳቸው የሐሰት አስተማሪዎች ተሸክመው ከሚዞሩዋቸው የምስጋና ደብዳቤ የላቀ ትርጉም ይሰጣቸው ነበር። የቆሮንቶስ አማኞች በጳውሎስ ልብ ውስጥ በፍቅር የተጻፉ ሲሆን፥ በዚያው መጠን ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ «የክርስቶስ ሕያው መልእክተኞች» አድርጎ፥ እውነትን በእነርሱም ልብ ላይ ጽፎት ነበር።
የአገልግሎት መፈተኛው የተለወጠ ሕይወት እንጂ፥ ይህን ያህል ሠርቻለሁ በማለት የሚቀርብ የመረጃ ጋጋታ አይደለም። ለሕግ አጥባቂው ሰው ግን አገልግሉቱን «በውጫዊ» መመዘኛዎች ስለሚለካ፥ ራሱን ለማወደስ ይቀለዋል። በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ ተደግፎ የሚያገለግል አማኝ ውጤቶቹን ለጌታ መልቀቅ አለበት። እንግዲህ የቆሮንቶስ ሰዎች ትምክህተኞቹን የአይሁዳዊነት አስተማሪዎች ተከትለው፥ ከፍርድ ያዳናቸውን ሰው ልብ በሐዘን መስበራቸው እንደ ምን የሚያሳዝን ነገር ነው!