ድል-ነሺ እምነት (2ኛ ቆሮ. 2፡12-17)

በእስያ የተዘረጉት የጳውሎስ ዕቅዶች ሙሉ ለሙሉ የከሸፉ ይመስል ነበር። ቲቶ የት ነበር? በቆሮንቶስ ያለውስ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ጳውሎስ በጢሮአዳ ለአገልግሉት የተከፈቱ በሮች ቢኖሩም፥ በእነዚያ በሮች ውስጥ እንደምኞቱ ለመመላለስ የልብ ሰላም አልነበረውም። በሰብዓዊ አባባል፥ ጦርነቱ በሰይጣን ድል-አድራጊነት የተፈጸመ ይመስል ነበር። 

የቀረው ነገር ቢኖር የጳውሎስ ድል-አድራጊ እምነት ብቻ ነበር! በእርግጥም የነበረበትን ሁኔታ ተቋቁሞ፥ «ለአምላክ ምስጋና ይሁን!» (ቁ 14) ለማለት ቻለ። ይህ የምስጋና መዝሙር የፈለቀው ጳውሎስ ጌታን በመተማመን ካገኘው ዋስትና ውስጥ ነው። 

እግዚአብሔር እየመራው እንዳለ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 2:14) ሁኔታዎቹ አመቺ ባለመሆናቸው፥ ጳውሎስ ማብቂያ ያልነበራቸውን ችግሮችና ኃዘኖች ለመግለጽ አይችልም ነበር፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሁኔታዎቹን እየተቆጣጠረ እንዳለ እርግጠኛ ነበር። አንድ አማኝ እግዚአብሔርን እስከ ወደደውና ፈቃዱን ለማድረግ እስከ ፈለገበት ጊዜ ድረስ፥ እግዚአብሔር ነገርን ሁሉ ለበጎ እንደሚያደርግለት ሁልጊዜም እርግጠኛ ሊሆን ይችላል (ሮሜ 8፡28)። ይህም ለግድየለሽነት የተሰጠ የማመካኛ የተስፋ ቃል ሳይሆን፥ ለመተማመኛ የሚረዳ ማበረታቻ ነው። 

አንድ ወዳጄ በሶሻሊስት አገር ውስጥ ከሚገኝ ከአንድ ክርስቲያን መሪ ጋር ሊገናኝና ስለ አንድ መጽሐፍ ሕትመት ሊወያይ ፈልጎ ነበር። ይሁንና ከሰውየው ጋር ለመገናኘት የነበረው ዕቅድ ሳይሳካለት ቀረ። ወዳጄም በአደገኛ ሥፍራ ብቻውን ተቀምጦ የሚያደርገው ጠፍቶት ግራ ተጋብቶ ሳለ፥ አንድ የማያውቀው እንግዳ ሰው አጋጠመው። ይሁንና ያ እንግዳው ሰው ወደሚፈልገው መሪ ሊያደርሰው ቻለ! ይህም የእግዚአብሔር ፈቃድ በሥራ ላይ እንደ ነበር የሚያመለክትና ለሮሜ 8፡28 ተፈፃሚነት ማረጋገጫ ነበር። 

እንዲሁም ጳውሉስ እግዚአብሔር በድል እየመራው ለመሆኑ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ. 2:14)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የምናገኘው ሥዕል፥ ሮም ከጦር ሜዳ በአሸናፊነት ለሚመለሱ ጀነራሎችዋ የምታዘጋጀውን ዓይነት «የድል አቀባበል» የሚያመለክት ነበር። 

አንድ ሮማዊ ጠቅላይ አዛዥ በባዕድ ምድር ላይ ሙሉ ለሙሉ ድል ከተቀዳጀ፣ ቢያንስ 5000 የጠላት ወታደሮችን ከገደለና ለንጉሠ ነገሥቱ ተጨማሪ ግዛት ካስገኘ፥ ያ ጠቅላይ አዛዥ ለሮማዊ ድል አድራጊ የሚሰጥ የክብር ሥርዓት ይደረግለታል። ከሚደረጉት የአቀባበል ሥርዓቶችም ውስጥ አንዱ ጠቅላይ አዛዥ በባልደረቦቹ ታጅቦና በወርቅ ሰረገላ ላይ ተቀምጦ የሚያልፍበት ትርዒት ነበር። በተጨማሪም የማረካቸው የጠላት ወታደሮችና የበዘበዛቸው ንብረቶች ለዕይታ ይቀርቡ ነበር። የሮም ካህናትም ድል ለነሣው ሠራዊት ባለውለተኛነታቸውን ለመግለጽ ዕጣን እያጤሱ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በድምቀት ይካፈሉ ነበር። 

ሰልፉም በከተማዪቱ ውስጥ የተለየ መንገድ ይዞ በመጓዝ፥ ምስኪኖቹ ምርኮኞች ከአራዊት ጋር በመታገል ሕዝቡን ወደሚያዝናኑበት የትርዒት ማሳያ መድረክ (ሰርከስ ማክሲመስ) ሲደርስ ያቆማል። ያም ዜጎቹ በሙሉ ሮማዊውን ድል አድራጊ በክብር የሚቀበሉበት ዕለት በሮም ታሪክ ውስጥ አንደ ልዩ ዕለት የሚቆጠር ነበር። 

ይህ የታሪክ ምዕራፍ ዛሬ ሸክም ከተጫነው አማኝ ሕይወት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ታላቁ ጠቅላይ አዛዦችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ባዕድ ምድር (ወደዚህች ዓለም) መጥቶ፥ ጠላትን (ሰይጣንን) ሙሉ ለሙሉ ድል አድርጓል። 5000 ሰዎችን በመግደል ፈንታ፥ ከ5000 ለሚልቁ ሰዎች ሕይወትን ሰጠ – በዕለተ-ጰንጠቆስጤ የዳኑትን 3000 እና ብዙም ሳይቆይ ወደ መዳን የመጡትን 2000 ሰዎች ጨምሮ (የሐዋ. 2:41፤ 4፡4)። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣንና የኃጢአት ባሪያዎች የነበሩትን የጠፉ ነፍሳት ማርኮ ወደ መዳን አምጥቷል (ሉቃ 11፡14-22፤ ቆላ 2፡15፤ ኤፌ 4፡8)። ምንኛ የሰመረ ድል ነው! 

የድል-ነሺ ጄነራል ልጆች የድሉ ተካፋይ በመሆን፥ ከአባታቸው ሰረገላ ኋላ ኋላ ይከተሉ ነበር፤ ዛሬም የአማኞች ሕይወት እንዲሁ ነው፤ የክርስቶስን ድል መከተል። እኛ ገና ለገና ለድል አንዋጋም፤ ዳሩ ግን ድልን ተላብሰን እንዋጋለን። ለጳውሎስ በእስያም ሆነ በቆሮንቶስ የነበረው ሁኔታው ከቶውንም ድልን የሚያቀዳጀው አልነበረውም፤ ዳሩ ግን እርሱ በእግዚአብሔር ስላመነ፥ እግዚአብሔር ሽንፈትን ወደ ድል አድራጊነት ለወጠው። 

በመጨረሻም፥ ጳውሎስ እግዚአብሔር ሲመራው ሳለ እየተጠቀመበት እንደ ሆነ እርግጠኛ ነበር (2ኛ ቆሮ.2፡14-17)። የሮም ካህናት በሥርዓቱ ላይ ዕጣን በሚያጤሱበት ጊዜ፥ ከዚያ የሚመጣው ሽታ በተለያዩ ሰዎች ላይ የተለያየ ስሜት ያሳድር ነበር። ለድል-ነሺ ወታደሮች፥ ይህ የሕይወትና የድል ሽታ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ድል ለተመቱት ወታደሮች የሽንፈትና የሞት ሽታ ነበር። በአራዊት ተቦጫጭቀው የሚሞቱበት ጊዜ እየተቃረበ ነውና። 

ጳውሎስ ይህንን የዕጣን ምስል በመጠቀም፥ የክርስትናን አገልግሉት ገልጿል። አማኞችን በሕይወታቸውና በሥራቸው የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም መዓዛ እንደሚያመነጩ ዕጣኖች አድርጎ ይመለከታቸዋል። ለእግዚአብሔር አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም መዓዛዎች ናቸው። ለሌሎች አማኞች የሕይወት ሽታዎች ስንሆን፥ ዳሩ ግን ለማያምኑ ሰዎች የሞት ሽታዎች ነን። በሌላ አባባል፥ የክርስትና ሕይወትና አገልግሎት የሕይወትና የሞት ጉዳዮች ናቸው። የምንኖርበት ወይም የምንሠራበት ሁኔታ ዙርያችንን ለከበበን የተጎሳቆለ ዓለም የሕይወት ወይም የሞት ትርጉም ሊኖረው ይችላል። 

ጳውሎስ፥ «ለዚህ ነገር የሚበቃ ማን ነው?» (ቁ 16) ብሎ መጮኹ የሚያስደንቅ አይሆንም። በቀጣዩ ምዕራፍ ውስጥ የዚህን ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፡- «ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው» (3፡5)። ለቆሮንቶስ ሰዎች ልቡ ንጹሕ እንደ ሆነና አነሳሽ ዓላማዎቹም ታማኝ እንደ ሆኑ ይገልጽላቸዋል። እንደዚሁም የድል-ነሺውን አዳኝ ፈለግ ተከትሎ ሲመላለስ ሳለ በብልጠት ተጠቅሞ በእግዚአብሔር ቃል «የሚነግድበት» ምክንያት አልነበረውም። እነርሱ የእርሱን አሳብ ላይረዱ ቢችሉም፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ልቡን ያውቅ ነበር። 

«እወድቃለሁ» ብለን ተስፋ መቁረጥ የለብንም! ሁኔታዎች ተስፋ ሊያስቆርጡን፥ ሰዎች ሊቃወሙንና አሳባችንን ላይረዱልን ይችላሉ፤ ዳሩ ግን ውጊያውን ድል ለመንሣት በክርስቶስ መንፈሳዊ ሀብቶች አሉን፡- ንጹሕ ሕሊና፥ የሚራራ ልብና ድል የሚነሳ እምነት። 

«እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? … በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን» (ሮሜ 8፡31፥37)። 

Leave a Reply

%d