ድጋፍን ያለመቀበል መብቱን ተከላከለ (1ኛ ቆሮ. 9፡15-27)

ጳውሎስ ቁሳዊ ድጋፍን የመቀበል ሥልጣን (መብት) ነበረው፤ ነገር ግን እንደ አንድ በሳል ክርስቲያን ሥልጣኑን ከሥነ ሥርዓት ጋር አጣጣመው። በክርስቶስ የነበረውን አርነት የመተው መብት አልነበረውም፤ ነገር ግን መብቶቹን የመተው አርነት ነበረው። አሁን ለምን እንደዚህ እንደጻፈ ይገባናል። ለቆሮንቶስ እማኞች ስለሚጽፋቸው መርሆች ሕያው ምሳሌ ለመስጠት ነበር። በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ብርቱ አማኞች ለደካሞች ቅዱሳን ሲሉ መብቶቻቸውን ወደ ጎን መተው አይገባቸውምን? ሥጋን መብላት ቤተ ክርስቲያንን ከማነጽ የበለጠ ተፈላጊ ነበርን? 

ጳውሎስ ይናገር የነበረው በሕይወታችን በእርግጥ አስፈላጊ ናቸው ስለምንላቸው ተቀዳሚ ጉዳዮች ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ግላዊ ቀዳሚ ጉዳዮቻቸው ስለሚምታቱባቸው የክርስቶስን ሥራ ሲያውኩ ማየት የሚያሳዝን ነው። እያንዳንዱ ማቴዎስ 6፡33ን የሚለማመድ ቢሆን ኖሮ፥ ለወንጌል መልእክተኞች በርካታ ገንዘብ፥ በአገልግሎት በርካታ የሰው ኃይል በተገኘ ና የጌታ ሥራም በሰፋ ነበር። ነገር ግን ማቴ 6፡33ን የሚለማመድ ሁሉም ክርስቲያን አይደለም። 

አንዲት ሴት በቤቷ ያለውን የኤሌትሪክ ውኃ ማሞቂያ በመዝጋት ለዚህ የምታወጣውን ገንዘብ አጠራቅማ ለአገልግሎት ስጦታ አድርጋ ላከች። የጌታን ሥራ የበለጠ መርዳት እንድትችልም ዕለታዊ ጋዜጣ መግዛትን አቆመች። ገላዋን ለመታጠብ ስትፈልግ ውኃውን በምድጃ ላይ ታሞቅ ነበር። ጌታ ሁላችንንም ለዚህ ዓይነት መሥዋዕትነት ላይጠራን ቢችልም የእርሷ ምሳሌ ክቡር ነው! 

ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ለምን እንዳልተቀበለ የሚያብራሩ ሦስት ምክንያቶችን ሰጠ። 

ለወንጌል ሲባል (9፡15-18)። ጳውሎስ «የክርስቶስን ወንጌል ለመከልከል» አልፈለገም ነበር (ቁ 12)። በዚያን ዘመን የግሪክ ከተሞች ገንዘብ ለማፍራት ብለው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በሚያስተምሩ ና በሚሰብኩ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች የተሞሉ ነበሩ። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ይጠቀሙ የነበሩትን ዓይነት ንግግር ና ክርክር (2፡1-5) ለመጠቀም አሻፈረኝ ማለቱ ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን ካገለገላቸው ገንዘብ መቀበልንም እምቢ አለ። የወንጌሉ መልእክት ለጠፉ ኃጢአተኞች አእምሮ ከማንኛውም ዓይነት መሰናክልና እንቅፋት ነፃ እንዲሆን ፈለገ። 

ለዚያውም፥ ጳውሎስ «እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጻፍሁም» (9፡15) ሲል እርሱን መደገፍ ይገባቸው እንደነበር «መጠቆሙን» አንባቢያኑ አሳቡን አላገኙትም ነበር! 

ጳውሎስ ወንጌልን ለመስበክ ከእግዚአብሔር የተጠራ ስለነበር ለአገልግሎቱ ምንም ዓይነት ዋጋን አለኝታ አላደረገም ነበር። «ግድ ደርሶብኝ ነው እና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ!» (ቁ. 16) እግዚአብሔር የመለኮታዊ መጋቢነትን «ልዩ ፈቃድ» ሰጥቶት ነበር። ደግሞም «በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል» (1ኛ ቆሮ. 4፡2)። የጳውሎስ ደመወዝ ጉዳይ በእግዚአብሔር ኃላፊነት ሥር ነበር መጋበሉቃስ 107 ደመወዝ ተብሎ ተተረክ… ነበር («ዋጋ»በሉቃስ 10፡7 ደመወዝ ተብሎ የተተረጎመው ጋር አንድ ቃል ነው)። 

የጳውሎስ ዋጋ ምን ነበር? ወንጌልን ያለ ክፍያ የመስበክ ሐሴት! ይህም ማለት የኢየሱስ ክርስቶስን የምሥራች በሚያካፍልበት ጊዜ፥ ሽረኛ አቋመ ልቡና ወይም ዘዴ አለው ብሎ ሊከስስ የሚችል ማንም አልነበረም ማለት ነው። 

ለገንዘብ ከመጠን ያለፈ አጽንኦት ከመሰጠቱ የተነሣ አንዳንዴ የወንጌል አገልግሎት መደናቀፍ አሳዛኝ ክስተት ነው። ያልዳነው ዓለም፥ አብዛኞቹን ሰባክያን ና ሚሲዮናውያንን፥ ከየዋህ ሰዎች ገንዘብን በመሰብሰብ «ሃይማኖታዊ ምዝበራ» ለማካሄድ እንደተሰለፉ አድርጎ ያምንበታል። ሃይማኖታዊ «ንዋየ መዝባሪዎች» ዛሬም በዓለም መኖራቸው ጥርጥር የለውም (1ኛ ጢሞ. 6፡3-16)። እነዚህ ሃይማኖትን ሌሎችን ለመበዝበዣ ና ለመቆጣጠሪያ «የሚጠቀሙ» ናቸው። እኛ በእርግጥ ከእነዚህ ዓይነቶቹ በዓላማም ሆነ በተግባር አንስማማም። በገዛ አገልግሎቶቻችን የምናደርገው ምንም ነገር ከእነርሱ ጋር የሚያስፈርጀንን ገጽታ እንደማያንጸባርቅ እርግጠኞች መሆን አለብን። 

በገንዘብ ላይ የሚደረግ የተሳሳተ አመለካከት ከጥንት የቤተ ክርስቲያን ዘመናት አንሥቶ እስካሁን ድረስ ለወንጌል ዕንቅፋት ሆኖአል። ሐናኒያ ና ሰጲራ እውነትን ከሚወዱት በላይ ገንዘብን ስለወደዱ፥ እግዚአብሔር ቀሰፋቸው (የሐዋ. 5)። ጠንቋዩ ሲሞን የመንፈስ ስጦታን ገንዘብ የሚገዛ መሰለው (የሐዋ. 8፡18-24)። ስሙ ዛሬ በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተካትቶአል። ሲሞኒ (simony) የሃይማኖት ሹመቶችን እና ጥቅሞችን የመግዛት እና የመሸጥ ተግባር ነው። 

ዶክተር ኤች. ኤ. አይረንሳይድ ለ 18 ፍሬያማ ዓመታት በቺካጎ የሙዲ ቤተ ክርስቲያንን ስመጋቢነት አገልግለዋል። መባ እንዲሰበሰብ ሲያውጁ ስሰማ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር፥ አሁን ሁኔታውን አስታውሰዋለሁ። እንዲህ አሉ፥ «የእግዚአብሔር ሕዝብ በልግሥና እንዲሰጥ እንጠይቃለን። በኢየሱስ ክርስቶስ የማታምን ከሆነ እንድትሰጥ እንጠይቅህም። እኛ ለእንተ ስጦታ አለን-ይኸውም በክርስቶስ በኩል የሚገኝ የዘላለም ሕይወት ነው!» መባ መስጠት ለአማኞች መሆኑን በግልጽ አሳወቀ፤ ይህም በጉባኤው የነበሩ ሰዎች በገንዘብ ምክንያት ተሰናክለው ወንጌልን እንዳይተዉት ነው። 

ለኃጢአተኞች ሲባል (9፡19-23)። ምንኛ የሚጋጭ ነገር ነው። ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን፥ ለሰው ሁሉ ባሪያ ነኝ! ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን» (2ኛ ቆሮ. 4፡5)። አርነት የወጣ ስለነበር፥ ጳውሎስ ሌሎችን ለማገልገል ና ስለ እነርሱ ሲል መብቱን ለመተው ቻለ። 

«ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ» (ቁ 22) የሚለው ሐረግ ጳውሎስ ለማለት ከፈለገው ውጭ ና ያለ አግባብ በዓለም ጥቅም ላይ ሲውል መታየቱ አሳዛኝ ነገር ነው። ጳውሎስ መልእክቱን ና ዘዴዎቹን ከእያንዳንዱ አዲስ ሁኔታ ጋር የሚቀያይር እስስት አልነበረም። አድማጮቹን ለማስደሰት ሲል መልእክቱን የሚያመቻምች አድርባይም አልነበረም። አምባሳደር እንጂ ፖለቲከኛም አልነበረም! 

ጳውሎስ ለራሱ ሕዝብ ታላቅ ሸክም የነበረው አይሁዳዊ ነው (ሮሜ 9፡1-3፤ 10፡1)። ነገር ግን የእርሱ ልዩ ጥሪ እሕዛብን ማገልገል ሆነ (ኤፌ. 3፡8)። ወደ ከተማ በሄደ ቁጥር (ሁልጊዜም ወንጌል ወዳልተሰበከበት ይሄድ ነበር- ሮሜ 15፡20)፥ ምኵራብ በአካባቢው ካለ በቀጥታ ወደዚያው ያመራና በድፍረት ወንጌልን ያካፍል ነበር። አይሁዶች የማይቀበሉት ከሆነ ወደ አሕዛብ ፊቱን ያዞር ነበር። 

በዚያን ዘመን አይሁዶችን ና አሕዛብን የሚለያየው ምን ነበር? ሕግ ና ቃል ኪዳን ናቸው (ኤፌ. 2፡11-15)። በግል ሕይወቱ ጳውሎስ እይሁድንም ሆነ አሕዛብን ሳያስቀይም ኖሮአል። አርነቱን በአይሁድ ፊት ለታይታ አላሽሞነሞነውም፤ በአሕዛብ ላይም ሕግን አልጫነም። 

ጳውሎስ አቋሙን የመቀያየር ባሕርይ ነበረውን? ለተለያዩ ቡድኖች በሚስማማ ሁኔታ አቀራረቡን እስተካከለ እንጂ በእርግጥ እንዲህ ያለ ባሕርይ አልነበረውም። በሐዋርያት ሥራ ስብከቶቹን በምታነብበት ጊዜ ይህን ከሁኔታዎች ጋር የማጣጣም ብልህ ስልቱን ታያለህ። ለአይሁድ በሚሰብክበት ጊዜ፥ በብሉይ ኪዳን አባቶች ይጀምራል፤ ነገር ግን ለአሕዛብ በሚሰበክበት ጊዜ፥ በፍጥረት አምላክ ይጀምራል። ጳውሎስ ሁኔታዎችን ሳያገናዝብ ሁልጊዜ የሚጠቀምበት አንድ የተወሰነ ስብከት አልነበረውም። 

ጌታችንም የነበረው አቀራረብ ይኸው እንደነበረ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ከከበረ ሐረግ ለተመዘዘው አይሁዱ ኒቆዲሞስ፥ ስለ መንፈሳዊ ልደት አወሳለት (ዮሐ 3)፤ ነገር ግን ለሳምራዊቷ ሴት፥ ስለ ሕያው ውኃ ተናገረ (ዮሐ 4)። ኢየሱስ ግትርነት የማያጠቃው ና ሁኔታዎችን የሚያጣጥም ነበር፤ ጳውሎስም የተከተለው የእርሱን ፈለግ ነበር። ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ድርቅ ያለ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ የሚሠራ «የወንጌል ቀመር» አልነበራቸውም። 

ግንኙነት መፍጠር ብልሃትን ይጠይቃል። የምመሰክርላቸው ሰዎች ስለ ሥርዓተ ቅበላ (አንድ ሰው የአንድ ክርስቲያናዊ ቤተ እምነት ሙሉ አባል የሚደረግበት ሥነ ሥርዓት) ልምምዳቸውን በሚነግሩኝ ጊዜ፥ እኔም በዚያ ውስጥ ያለፍሁ መሆኔን እነግራቸዋለሁ። በዚያን ወቅት ላስተማረኝ ና ለጸለየልኝ መጋቢ አድናቆቴን እገልጽላቸዋለሁ። ከዚያም «ሥርዓተ ቅበላን ካለፍሁ ከአንድ ዓመት በኋላ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን በግሌ ተገናኝቼ ዳግም ተወለድሁ» እላቸዋለሁ። ጥሩ ምስክር ድልድይን እንጂ ግድግዳን ለመገንባት አይጥርም። 

ላልበሰሉ ሰዎች የጳውሎስ የሕይወት ዘይቤ ምናልባት ተለዋዋጭ ይመስል ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እርሱ በጣም አቋመ-ጽኑ ሰው ነበር፤ ዓቢይ ዓላማው ሰዎችን ለክርስቶስ መማረክ ነበር። አንድ ሰው በሰው ሠራሽ ደንቦች ና መለኪያዎች ታስሮ ለማገልገል ነጻነት እስከሚያጣ ድረስ አቋመ-ጠባቃና ለሕግ አጎብዳጅ ሊሆን ይችላል። ይህ በሳዖል ልብስ ውስጥ ሆኖ ለመዋጋት እንደሞከረው ወጣት ዳዊት ነው። 

ጳውሎስ ያሰኘውን ሁሉ የመብላት መብት ነበረው፤ ነገር ግን አይሁዶችን ይማርክ ዘንድ ያን መብቱን ተወ። ጳውሎስ ሕግን አከበረ (ሮሜ 7፡12ን ተመልከት)። የጠፉትን አሕዛብ ይደርስ ዘንድ ግን ሕግን ወደ ጎን አደረገ። ይህ አቋምን የመሸቃቀጥ ነገር ላይሆን ለላቀው የፍቅር ሕግ ሲሉ ፍጹም ራስን መተው ነው። ጳውሎስ የአዳኙን ምሳሌ በመከተል የሁሉም አገልጋይ ለመሆን ራሱን ዝቅ አደረገ። 

ስለ ራሱ ሲል (9፡24-27)። ጳውሎስ የሩጫ (የአትሌትክስ) ምሳሌዎችን ይወድድ ነበርና ብዙ ጊዜ በመልእክቶቹ ውስጥ ተጠቅሞባቸዋል። ቆሮንቶሳውያን ከግሪክ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች እና ከራሳቸው ኢስሚያን ጨዋታዎች ጋር የሚተዋወቁ ነበሩ። ጳውሎስ ይህን በማወቁ ከልምምዳቸው ጋር በጣም የሚቀራረብ ዘይቤያዊ እገላለጽን ተጠቀመ። 

አንድ ሯጭ የሽልማቱ ባለቤት ለመሆን ከፈለገ ለሥነ ሥርዓት ራሱን ማስገዛት አለበት። ሥነ ሥርዓት ማለት ከሁሉ ለላቀው መልካሙን ና የተሻለውን መተው ነው። ሯጭ አመጋገቡን ና ጊዜውን መቆጣጠር አለበት። ሰዎች የሚያወፍሩ ምግቦችን ና የረፋድ ሌሊት ፓርቲዎችን ሲጋብዙት ፈገግ ብሎ «የለም፥ አመሰግናለሁ» ማለት መቻል አለበት። ምግብና መዝናኛ ችግር አለባቸው ማለት እይደለም፤ ነገር ግን ከከፍተኛ ግቦችህ ጋር የሚጋጩ ከሆነ፥ ያኔ ዕንቅፋቶች እንጂ ደጋፊዎች አይሆኑም። 

ክርስቲያን ሩጫውን የሚሮጠው መንግሥተ ሰማይ ለመድረስ አይደለም፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመኑ ምክንያት ያለው በሩጫ ውስጥ ነው። በዘመኑ በጨዋታዎች መሳተፍ የሚችሉት የግሪክ ዜጎች ብቻ ነበሩ፤ እነርሱም በሥልጠናውም ሆነ በውድድሩ ወቅት የሚታዘዙአቸው ሕጎች ነበሯቸው። የሥልጠና ሕጎችን የሚጥስ ማንኛውም ተወዳዳሪ ወዲያውኑ ውድቅ ይደረግ ነበር። ዝነኛው የሕንድ አትሌት፥ ጂም ቶርፔ ቀደም ሲል ለፕሮፌሽናል ቡድን መጫወቱን ኮሚቴው ስለደረሰበት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያውን መመለሱ የሚታወስ ነው። 

ጳውሎስ መብቱን በመተውና የጠፉትን ሰዎች በማዳን እርካታን ለማግኘት ሲል ራሱን ለሥነ ሥርዓት አስገዛ። የዚህ ምዕራፍ አጠቃላይ አጽንኦትም ይህ ነው፡- ሥልጣን (መብቶችንና ሥነ ሥርዓት መጣጣም አለባቸው። ጌታን ለማገልገል እና ከእርሱም ዋጋን ና ተቀባይነትን ለማግኘት፥ መሥዋዕትነት መክፈል አለብን። 

የተጣልሁ የሚለው ቃል (ቁ 27) የግሪክ ጨዋታዎችን ለሚያውቁት ቴክኒካዊ ቃል ነው። «ውድቅ የሆነ፥ ተቀባይነት ያጣ» ማለት ነው። በግሪክ ውድድሮች የውድድሩን ሕጎች፥ የተወዳዳሪዎችን ስሞች ና የአሸናፊዎችን ስሞችና ከተሞች የሚያውጅ ለፋፊ ሰው ነበር። ውድቅ የተደረጉትን ተወዳዳሪዎች ስምም ይለፍፍ ነበር። 

ጳውሎስ ራሱን እንደ «ለፋፊ»ም እንደ «ሯጭ»ም አድርጎ ቆጠረ። በሩጫው ሌሎችን ለመርዳት በመጣር ከሚገባው በላይ ተጠምዶ ራሱን ውድቅ ሆኖ እንዳያገኝ በጣም ይጨነቅ ነበር። እንደገና፥ ይህ የግል ደኅንነትን የማጣት ጉዳይ አልነበረም። (ውድቅ የተደረገው የግሪክ አትሌት ዜግነቱን አላጣም፤ ያጣው ሽልማት የማግኘት ዕድልን ነው።) አጠቃላይ አጽንኦቱ በዋጋው ላይ ነበር፤ ስለሆነም ጳውሎስ ዋጋውን ለማጣት አልፈለገም። 

በግሪክ ጨዋታዎች የወይራ አክሊልን መሸለም የሚችለው አንድ ሯጭ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን ማንኛውም አማኝ ከክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት በሚቀርብበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ሊያገኝ ይችላል። ይህ አክሊል ክርስቶስን በማገልገል እና የጠፉ ሰዎችን ለመመለስ ሲሉ ራሳቸውን ለሥነ ሥርዓት ለሚያስገዙ የሚሰጥ ነው። እነዚህ ሰዎች ሰውነታቸውን ከቁጥጥር ሥር አውለው ዓይኖቻቸውን በግባቸው ላይ ያደርጋሉ። 

በቅርብ ዓመታት ወንጌላውያን ክርስቲያኖች በአንድ በኩል የግል ሥነ ሥርዓት፥ በሌላ በኩል ደግሞ በሥነ ሥርዓት የተገዛ ሰውነት ና በመንፈስ የተሞላ ሕይወትን አስቀምጠው ሲያጤኑአቸው በመካከላቸው ስላለው ግንኙነት አዲስ ግንዛቤን ጨብጠዋል። በእርግጥ ጽንፎችን ማስወገድ ይገባናል። በአንድ በኩል ሃይማኖታዊ ብህትውና (ተድላን ና ምቾትን ለራስ ነፍጎ ተራ ሕይወት መምራት-የግድ ገዳም መግባትን አያመለክትም) ጤናማ ያልሆነና ምንም መንፈሳዊ እሴት የሌለው ነው (ቆላ. 2፡18-23)። ነገር ግን፥ በሌላ ወገን ሥርዓት ለጠበቀ አመጋገብ፥ የሰውነት እንቅስቃሴ፥ ዕረፍት እና በመንፈስ ለሚመራ ሚዛናዊ ሕይወት ጥቂት የሚባል አለ። ሲጋራ ስለማናጤስ ወይም አልኮሆል ስለማንጠጣ በኩራት ራሳችንን እናሞጋግሳለን፤ ነገር ግን ከመጠን በላይ መብላታችን ና መወፈራችን እንዴት ይታያል? አንዳንድ ክርስቲያኖች ጊዜአቸውን በሥነ ሥርዓት መጠቀም ስለማይችሉ የማይዋዥቅ የጥሞና ሕይወት ና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ የላቸውም። 

ጳውሎስ በሕይወቱ አንድ ትልቅ ዓላማ ነበረው፤ የጠፉትን በማዳን ና ቅዱሳንን በማነጽ ጌታን ማክበር። ወደዚህ ዓላማ ለመድረስ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር። የገዛ መብቱንም እንኳ ለመተው ፈቃደኛ ነበር! ጊዜአዊውን ጥቅም ለዘላለማዊው ዋጋ፥ ጊዜአዊውን ምቾት ለዘላለማዊ ደስታ ሠዋ። 

ሰማዕቱ ጂም ኤሊዮት የሚከተለውን ማለቱ ትክክል ነበር፡ «ለማሰንበት የማይቻለውን፥ ሊያጣው ለማይችለው የሚሠዋ ሰው ሞኝ አይደለም።»

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: