ድጋፍ ለመቀበል መከላከያን አቀረበ (1ኛ ቆሮ. 9፡1-14)

ይህ ምዕራፍ ስለ ጳውሎስ የገንዘብ እርዳታ መመሪያ የሚያወሳ ሲሆን፥ «ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ» በሚናገርበት በዚህ ስፍራ መቅረቡ ጣልቃ የገባ ነገር ሊመስል ይችላል። እውነቱ ግን፥ ጣልቃ ሳይሆን በምዕራፍ 8 እና 10 ለሚያቀርባቸው መርሆዎች መግለጫ ነው። ጳውሎስ የበሰለ የአርነት አጠቃቀምን ለመግለጽ ራሱን በምሳሌነት ተጠቅሞአል፡- ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ድጋፍን ለመጠቀም መብት ነበረው፤ ሆኖም ግን የላቀ ግብ ላይ ለመድረስ ሲል ያን መብቱን ወደ ጎን አስቀመጠ። 

በአብዛኛው ግሪኮች የጉልበት ሥራን እንደሚንቁ ልብ በል። የግሪክ ዜጎች የጉልበት ሥራ የሚሠሩላቸው ባሪያዎች ስለነበሩአቸው፥ በስፖርት፥ በፍልስፍና ና በመዝናኛዎች ይደሰቱ ነበር። አይሁድ በእርግጥ ጥሩ ገቢ እስካስገኘ ድረስ ሥራን ያከብሩ ነበር። የተማሩ የሃይማኖት መሪዎቻቸውም (ራቢዎች) እንኳ ሳይቀሩ ንግድን ይለማመዱ እና «ልጁን እንዲሠራ የማያስተምር፥ ሌባ እንዲሆን ያስተምረዋል» በማለት ትምህርት ይሰጡ ነበር። ጳውሎስ የድንኳን ሥራን እና የቆዳ ሥራን ጥበብ የተማረ ነበር። 

ክርስቲያናዊ የግል መብት አጠቃቀም በምሳሌ ለመግለጽ፥ ጳውሎስ እንደ ክርስቶስ አገልጋይነቱ ስለሚከተለው ባለ ሁለት ገጽታ የገንዘብ ፖሊሲው መከላከያን አቀረበ። 

ድጋፍ ለመቀበል መከላከያን አቀረበ (1ኛ ቆሮ. 9፡1-14) 

በዚህ ምዕራፍ አጋማሽ ላይ፥ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት መብት እንደነበረው አረጋገጠ። ይህን አሳቡን ለመደገፍ አምስት መከራከሪያ ነጥቦችን አስቀምጧል። 

ሐዋርያነቱ (9፡1-6)። ሐዋርያ ማለት «በሹመት የተላከ» ማለት ሲሆን በቀዳሚነት የሚያመለክተው አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት እና ጳውሎስን ነው። እነዚህ ሰዎች ከአዲስ ኪዳን ነቢያት ጋር የቤተ ክርስቲያንን መሠረት ለመጣል (ኤፌ. 2፡20) ልዩ ተልዕኮ ነበራቸው። ሐዋርያ የመሆን አንዱ መመዘኛ የተነሣውን ክርስቶስ በግል ማየት ነበር (የሐዋ. 1፡21-22)። ጳውሎስ ጌታን ያየው ክርስቲያኖችን ለማሰር ወደ ደማስቆ በሚሄድበት ወቅት ነበር (የሐዋ. 9፡1-9)። ሐዋርያት የክርስቶስ ትንሣኤ ምስክሮች ነበሩ (የሐዋ. 2፡32፤ 3፡15፣ 5፡32፣ 10፡39-43)። 

የስበኩትን መልእክት ለማስረገጥ ሐዋርያት ተአምራትንና ድንቆችን የመሥራት ልዩ ችሎታ ተሰጥቶአቸው ነበር (ዕብ 2፡4)። ጳውሎስ እንዲህ ያሉ ተአምራቶችን በቆሮንቶስ አገልግሎቱ (2ኛ ቆሮ. 12፡12) ፈጽሞአል። እንዲያውም፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንን በጣም ልዩ የሆነች የአገልግሎቱ «ማኅተም» (ማረጋገጫ) አድርጎ ቆጥሮአት ነበር። ቆሮንቶስ ለማገልገል በጣም አስቸጋሪ ከተማ ብትሆንም፥ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ኃይል ታላቅ ሥራ ሠርቶአል (የሐዋ. 18፡1-17ን ተመልክት)። 

በመሆኑም፥ እንደ አንድ ሐዋርያ ጳውሎስ ካገለገላቸው ሰዎች ድጋፍ የማግኘት ኃይል ነበረው። (በዚህ ምዕራፍ ኃይል የሚል ቃል በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ስድስት ጊዜ ተጠቅሶአል፤ ይህም «ሥልጣን» ማለት ነው)። ሐዋርያው የክርስቶስ ወኪል ነበር፤ ስለሆነም ሊስተናገድና ክብካቤ ሊደረግለት የተገባው ነበር። ጳውሎስ ያላገባ ሰው ነበር፤ ነገር ግን ሚስት ኖሮት ቢሆን ኖሮ፥ እርሷም በቤተ ክርስቲያን የመረዳት መብት ይኖራት ነበር። ጴጥሮስ ያገባ ሰው ነበረ (ማር. 1፡30)፥ እናም ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትጓዝ ነበር። ጳውሎስም ይኸው መብት የነበረው ሲሆን አልተጠቀመበትም። 

ጳውሎስ ሙሉ ጊዜውን ለቃሉ አገልግሎት የመመደብ መብትም ነበረው። ድንኳን መሥራት አልነበረበትም። ሌሎች ሐዋርያት ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ለቃሉ አገልግሎት ስለ ሰጡ ራሳቸውን ለመደገፍ መሥራት አልነበረባቸውም። ይሁን እንጂ፥ ጳውሎስና በርናባስ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ከእነርሱም ጋር አብረው የሚደክሙትን ለመደገፍ በገዛ እጆቻቸው ይሠሩ ነበር። 

ሰብአዊ ልምምድ (9፡7)። አንድ ሠራተኛ ለሥራው የሆነ ጥቅም ማግኘት እንዳለበት የየዕለቱ ልምምድ ያስተምረናል። አንድ ሰው ለውትድርና ከተመለመለ፥ መንግሥት ደመወዙን ይከፍለዋል፤ የተወሰኑ አቅርቦቶችንም ይሰጠዋል። እረኛ ወይም አርቢ ከእንስሳቱ ወተታቸውን የመጠቀም መብት እንዳለው ሁሉ፥ ወይን የሚተክል ሰውም ፍሬውን መብላት አለበት። 

ምናልባት ጳውሎስ በ«አእምሮው ጓዳ» ውስጥ፥ ቤተ ክርስቲያንን ከጦር ሠራዊት፥ ከወይን እርሻና ከመንጋ ጋር ያነጻጸረ ይመስላል። ሐዋርያ እንደ መሆኑ መጠን ጳውሎስ በጦር ሜዳው ግንባር መስመር ላይ ነበር። ቀደም ብሎ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንን ከለማ ማሣ (3፡6-9) አነጻጽሮ ነበር። ጌታም ራሱ የወይን ግንድንና ቅርንጫፍን ምሳሌ (ዮሐ 15)፥ እንደዚሁም የመንጋን ምሳሌ (ዮሐ 10) ተጠቅሞአል። ትምህርቱ ግልጽ ነበር። ክርስቲያን ሠራተኛ ለሥራው ጥቅምን የመጠበቅ መብት አለው። ይህ “በቁሳዊው” ዓለም እውነት ከሆነ በመንፈሳዊው ዓለምም እውነት ነው። 

የብሉይ ኪዳን ሕግ (9፡8-12)። ብሉይ ኪዳን የጥንቲቱ ቤተ ክርስቲያን «መጽሐፍ ቅዱስ» ነበር፤ ምክንያቱም አዲስ ኪዳን ገና በመጻፍ ሂደት ላይ ነበር። ምንም እንኳ የሕግን ትእዛዛት ከመታዘዝ ነፃ የወጡ ቢሆኑም የመጀመሪያዎቹ እማኞች በሕግጋቱ መንፈሳዊ መርሆች ይመሩ ነበር። ቅዱስ አውግስቲን እንዲህ ብለዋል፥ «አዲስ በብሉይ ውስጥ የተደበቀ፥ ብሉይ በአዲስ የተገለጠ ነው»። 

ጳውሎስ አሳቡን ለማስረገጥ ዘዳግም 25፡4ን ጠቀሰ። (ለጢሞቴዎስ ሲጽፍና ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿን በበቂ ሁኔታ ደመወዝ እንድትከፍል ባበረታታበት ወቅት ይኸንኑ ነው የጠቀሰው፥ (1ኛ ጢሞ. 5፡17-18።) በሬዎች ስለማያነብቡ ይህ ጥቅስ የተጻፈው ለእነርሱ አይደለም። ገበሬ የበሬዎቹን አፍ በማሰር በፊታቸው ካለው እህል እንዳይበሉ ቢያደርግ ጭካኔ ነው። እንደ እውነቱማ ሥራውን እኮ የሚሠራው በሬው ነው። 

ጳውሎስ ለሠራተኛው ደመወዙ ይገባዋልና በሚለው ትእዛዝ ውስጥ በትክክል መንፈሳዊ መርህን አይቶአል። መሬቱን ለዘሪ ያዘጋጀው በሬ አሁን ደግሞ የተመረተውን ምርት በእግሩ እየረገጠ ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስን አፈር አርሶአል፤ ሌት ተቀንም ደክሞአል። ከዘራው ዘር የተገኘውን መከርም አይቶአል። ከዚያ መከር አንዳንዶቹን ፍሬዎች መጠቀም መብቱ ነበር። 

ቁጥር 11 የክርስቲያናዊ ሕይወት መሠረታዊ መርህን በግልጽ ያስቀምጣል። መንፈሳዊ በረከቶችን ከተቀበልን በምላሹ ቁሳዊ በረከቶችን ማካፈል ይገባናል። ለምሳሌ፥ አይሁድ ለአሕዛብ መንፈሳዊ በረከትን ይሰጡ ነበር፤ በመሆኑም አሕዛብ ቁሳዊ በረከቶችን ለአይሁድ የማካፈል ግዴታ ነበረባቸው። ቃሉን የሚያስተምሩን እንድንደግፋቸው ከእኛ ሊጠብቁ መብት አላቸው (ገላ. 6፡6-10)። 

ጳውሎስ ከሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች የገንዘብ ድጋፍ መቀበሉን ለማመን ምክንያት አለን። ወደ ተሰሎንቄ በሄደ ጊዜ የፊልጵስዩስ አማኞች ሁለት ስጦታዎችን ልከውለት ነበር (ፊልጵ. 4፡15-16)። «እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ» (2ኛ ቆሮ. 11፡8) በማለት ጳውሎስ ቆሮንቶሳውያንን አሳሰበ። ሌሎች አገልጋዮች ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ የተቀበሉ ይመስላል (1ኛ ቆሮ. 9፡12)፤ ነገር ግን ጳውሎስ «የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል» በማለት ከዚህ ዓይነት ድጋፍ እራሱን ነፃ አድርጎ መቆየትን መረጠ። ለሌሎች አማኞች የላቀ ምሳሌ ለመሆን ፈለገ (2ኛ ተሰ. 3፡6-9)። 

የብሉይ ኪዳን ልምምድ (9፡13)። ካህናት ና ሌዋውያን የሚኖሩት ወደ ቤተ መቅደስ በሚመጣው መሥዋዕት እና ስጦታዎች ነበር። የሚቀበሉአቸውን ስጦታዎች እና ልዩ እሥራቶችን በተመለከተ የወጡት ደንቦች በዘኁልቁ 18፡8-32፥ በዘሌዋውያን 6፡14-7፡36፥ እና 27፡6-33 ላይ ይገኛሉ። የዚህ ተዛምዶ ግልጽ ነው። በሕግ ሥር የነበሩ የብሉይ ኪዳን አገልጋዮች በሚያገለግሉት ሕዝብ ይደገፉ ከነበረ፥ በጸጋ ሥር ሆነው የሚያገለግሉ የእግዚአብሔር ባሪያዎችስ መደገፍ የለባቸውምን? 

የኢየሱስ ትምህርት (9፡14)። ጳውሎስ ያጣቅስ የነበረው በሉቃስ 10፡7-8 እና በማቴዎስ 10፡10 ላይ ያሉትን የጌታ ቃላት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ቆሮንቶሳውያን የሚያጣቅሱባቸው ከሁለቱ ወንጌሎች የየትኛውም ቅጂ አልነበራቸውም። ነገር ግን የጌታ ትምህርት በሐዋርያት ይተላለፉ የነበረው አፍአዊ ትውፊት አካል በመሆን ተሰጥቶአቸው ነበር። ቤተክርስቲያን ችላ ልትለው የማይገባት መሠረታዊ መርህ ሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል የሚል ነው። 

ጳውሎስ ያለጥርጥር አሳቡን አስመስክሮአል። አምስቱ መከራከሪያዎቹ በማጠቃለያ የሚያረጋግጡት አብሮእቸው በነበረበት ወቅት በአገልግሎቱ ይደግፉት ዘንድ ከቆሮንቶስ አማኞች መጠበቅ መብቱ እንደሆነ ነው። እንዲሁም ሆኖ ድጋፋቸውን ሆን ብሎ ሳይቀበል ቀረ። ለምን? ይህንን በመከላከያው ሁለተኛ ክፍል ላይ ያብራራል።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: