ገንዘብ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-4)

ጥያቄዎቻቸውን ለጳውሎስ በጻፉ ጊዜ፥ በኢየሩሳሌም ላሉት ድሀ ቅዱሳን ስለሚወስደው መዋጮ ገንዘብ መጠየቃቸው በቆሮንቶስ ያሉ አማኞች ዋጋ የሚያሰጣቸው ነበር። ጳውሎስ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሰጥቶ ስለ ግል ጉዞው ዕቅድ በመንገር ደብዳቤውን ዘጋው። 

ይህ ምዕራፍ ዛሬ እኛ ካሉን ችግሮች ጋር የሚዛመድ አይመስልም። ይሁንና እንደ እውነቱ ከሆነ በጣም ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሦስት የመጋቢነት እካባቢዎችን ይነካል። እነዚህም ገንዘብ (ቁ. 1-4)፥ ዕድሎች (ቁ 5-9)፥ እና ሰዎች (ቁ 10–24) ናቸው። እነዚህ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ምናልባት ያሉአት ታላላቅ ሀብቶች ስለሆኑ፥ መባከን የለባቸውም። 

ገንዘብ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-4) 

ጳውሎስ በሦስተኛ ጉዞው ከነበሩት ጠቃሚ እገልግሎቶች አንዱ ልዩ «የማቋቋሚያ መዋጮ» በኢየሩሳሌም ለነበሩ ድሃ አማኞች ማሰባሰቡ ነበር። በዚህ መዋጮ ጳውሎስ ብዙ ዓላማዎች ላይ ለመድረስ ፈለገ። ለነገሩ፥ አሕዛብ አይሁድ ስላመጡላቸው መንፈሳዊ በረከት ምላሽ በቁሳቁስ እርዳታ መክፈል ነበረባቸው (ሮሜ 15፡25-27)። ከዓመታት በፊት በኢየሩሳሌሙ ኮንፈረንስ ላይ፥ ጳውሎስ «ድሆችን እንደሚያስታውስ»። ተስማምቶ ስለነበር ቃሉን መጠበቁ ነበር (ገላ. 2፡10)። ጳውሎስ ወንጌልን ብቻ መስበክ ሳይሆን፥ ነገር ግን ሥጋዊና ቁሳዊ ችግር የነበረባቸውንም ለመርዳት ጥረት አድርጎአል። 

በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ችግር የተፈጠረው ለምንድን ነው? እነዚህ አማኞች በኢየሩሳሌም ጉብኝት ያደርጉ የነበሩና በጴንጠቆስጤ ዕለት ቃሉን ሰምተው ያመኑ በመሆናቸው ይመስላል። ይህም እነዚህ እማኞች እንግዶችና ሥራ አጦች፥ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን ልትንከባከባቸው የሚያስፈልጋቸው ነበር ማለት ነው። በጥንቱ የቤተ ክርስቲያን ዘመን፥ ምእመናን ያላቸውን በደስታ እርስ በርስ ይጋሩ ነበር (የሐዋ. 2፡41-47፤ 4፡33-37)፤ ሆኖም ግን የነበራቸው በጣም የተወሰነ ነበር። በወቅቱ ረሃብ ነበርና (የሐዋ. 11፡27-30) ወደዚያው የተላከ እርዳታ ረዘም ላለ ጊዜ ሊበቃ አልቻለም። 

ቃሉን ከመጠበቅና ከፍተኛ ችግርን ለማቃለል ከነበረው ፍላጎት ሌላ፥ የገንዘቡን መዋጮ ለማሰባሰብ ታላቅ አቋመ ልቦና የሰጠው የአይሁድና የአሕዛብ አማኞች አንድ እንዲሆኑ የመርዳቱ ጉዳይ ነው። ጳውሎስ ለአሕዛብ የወንጌል መልእክተኛ ነበር፥ ይህ ደግሞ ከአይሁድ እማኞች አንዳንዶቹን አሳስቦአቸው ነበር (የሐዋ. 17፡21-25)። ጳውሎስ ይህ ለአሕዛብ ፍቅር የመግለጹ ጉዳይ አንዳንድ ቁስሎች እንዲፈወሱ እና በአብያተ ክርስቲያናት መካከልም ድልድይ እንዲገነባ ይረዳል ብሎ ተስፋ አደረገ። (ስለዚህ የገንዘብ መዋጮ የበለጠ መረጃ ለማግኘት፥ 2ኛ ቆሮ. 8-9ን አንብብ።) 

ምንም እንኳ ይህ ልዩ ሚሲዮናዊ የገንዘብ መዋጮ ቢሆንም፥ ከጳውሎስ መመሪያዎች ለክርስቲያናዊ መጋቢነት ዝምድና ያላቸውን አንዳንድ መሠረታዊ መርሆች እንማራለን። 

መስጠት እንደ አምልኮ ተግባር። እያንዳንዱ ምእመን ለጌታ ቀን ስብሰባ (ለእሑድ አምልኮ) ለዚያ ሳምንት የድርሻውን ለመስጠት ተዘጋጅቶ መምጣት ነበረበት። ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትሰባሰብ የነበረው የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መታሰቢያ በማድረግ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ላይ ነበር። (መንፈስ ቅዱስም በቤተ ክርስቲያን ላይ የወረደው በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በጴጠቆስጤ ዕለት ነበር።) ስጦታዎቻችን ለጌታ የሚቀርቡ «መንፈሳዊ መሥዋዕቶች» (ፊልጵ. 4፡18) መሆናቸውን ዘንግተው ምእመናን እንደ ግዴታ ብቻ መስጠታቸው የሚያሳዝን ነው። መስጠት፥ ለተነሣውና ሳረገው አዳኝ የሚደረግ የአምልኮ ተግባር ነው። 

መስጠት በብልሃት መደረግ አለበት። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚያ ዘመን ታሪክ ብዙ ሰዎች በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እንደሚከፈላቸው አሳብ ሰጥተዋል። ይህም እንኳ ባይሆን ኖሮ፥ እያንዳንዱ አማኝ ስጦታውን (መባውን) በቤት ለብቻ ለይቶ ያቆየውና በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ወደ ጉባኤው ያመጣው ነበር። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በሚደርስበት ጊዜ ብዙ መዋጮዎችን ለማሰባሰብ አልፈለገም። አጠቃላይ መዋጮው ተዘጋጅቶ እንዲጠብቀው ፈለገ። የዛሬዎቹ አማኞች፥ ለሌሎች ገንዘብ–ነክ ጉዳዮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ሥርዓት የሚጠብቁ ቢሆኑ ኖሮ፥ አንዳንዴ እንደሚታየው የጌታ ሥራ ባልተስተጓጎለ ነበር። 

መስጠት የራስና ግላዊ ነበር። ጳውሎስ እያንዳንዱ ምእመን፥ ድሀም ሀብታምም እንዲሁ በመስጠት እንዲካፈሉ ይፈልግ ነበር። ማንም ገቢ ያለው ሰው ለማካፈልና በችግር ያሉትን መርዳት መብቱ ነበር። በበረከቱ ሁሉም ሰው እንዲሳተፍ ፍላጎቱ ነበር። 

መስጠት ተመጣጣኝ መሆን ነበረበት። «እንደ ቀናው መጠን» (ቁ 2) የሚለው ብዙ ያላቸው ብዙ እንዲሰጡ የሚያሳስብ ይመስላል። በቤተ ክርስቲያን የአይሁድ አማኞች አሥራትን የሚያውቁ ነበሩ፥ ሆኖም ግን ጳውሎስ እዚህ ላይ ምንም ዓይነት የተለየ መጠን አላስቀመጠም። በእርግጥ አሥራት (የአንድ ሰው ገቢ አንድ አሥረኛ) ገንዘብ የማውጣት አገልግሎታችንን ለመጀመር ጥሩ ቦታ ነው፥ ነገር ግን እዚያው ላይ መቅረት የለብንም። እግዚአብሔር ብዙ ሲሰጠን፥ ጨምረን ለመስጠት ማቀድ አለብን። 

ችግሩ ብዙ ቅዱሳን፥ የበለጠ ባገኙ መጠን፥ በሰፋ የገንዘብ ግዴታ ውስጥ ራሳቸውን ይስታሉ፤ ከዚያ በኋላ ለጌታ ጨምረው የሚሰጡት ነገር አይኖራቸውም። ተስማሚ ደረጃ » አግኝተው እዚያ ላይ መቆየት ሲገባቸው፥ «ከፍ ወዳለው» ለመድረስ ጥረታቸውን ይቀጥላሉ፥ ስለሆነም ገቢያቸው በሥራ ላይ ከመዋል ይልቅ ወጪ ሆኖ ይቀራል። ጥንታዊው አባባል እንደሚያስቀምጠው፥ «አተርፍ ባይ አጉዳይ» መሆን ይመጣል። 

ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ ከምዕ. 8-9 ላይ ክርስቲያናዊ መስጠት ጸጋ፣ በሕይወታችን የሚፈስስ የእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ የእድገት ወይም የጥበት ውጤት እንዳልሆነ ገልጾአል። የተከፈተ ልብ የታሰረ እጅ ሊኖረው አይችልም። ለእኛ የደረሰንን የእግዚአብሔር ጸጋ ዋጋ የምንሰጥ ከሆነ፥ ለሌሎች ካለን በማካፈል ያንን ጸጋ ለመግለጽ እንፈልጋለን። 

ገንዘብ በታማኝነት መያዝ አለበት በዚህ ልዩ ስጦታ የተሳተፉት ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጳውሎስን በገንዘብ አሰባሰቡ እንዲረዱና በደኅና ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱት ተወካዮችን ሾመው ነበር። (ጳውሎስን ስለረዳው «የገንዘብ ኮሚቴ» የበለጠ መረጃ ለማግኘት 2ኛ ቆሮ. 8፡16-24ን ተመልከት።) በአደራ ለተሰጣቸው ገንዘብ ትክክለኛ አስተዳደር አጥተው ምስክርነታቸው የሚበላሽባቸውን ክርስቲያናዊ አገልግሎቶች ማየት በጣም አሳዛኝ ነው። ማንኛውም አገልግሎት በገንዘብ ጉዳዮች ላይ የንግድን አሠራር ሊከተል ይገባል። ጳውሎስ ጠላቶቹ ገንዘብ ሰረቀ ብለው ለመክሰስ ዕድል የሚሰጣቸው ምንም ነገር እንዳይከሰት በጣም ጥንቁቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 8፡20-21)። 

ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናት ገንዘብ በማውጣቱ እንዲሳተፉና ገንዘቡን ለማስተዳደር ሁነኛ ተወካዮችን እንዲመርጡ የገፋፋው ለዚህ ነበር። ጳውሎስ ግለሰቦች በግል ስጦታ (ገንዘብ) መስጠታቸውን አልተቃወመም፤ በዚህ ምዕራፍና በሮሜ 16፥ በግል እርሱን የደገፉትን ልዩ ልዩ ሰዎች በስም ጠቅሶአቸዋል። ይህም በገንዘብ ፍላጎቱ የደገፉትን ጭምር መሆኑ አያጠራጥርም። ሆኖም ግን በአጠቃላይ ሁኔታ፥ ክርስቲያናዊ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ማዕከል ያደረገው ነው። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ምእመኖቻቸው በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ቤት በኩል የተወሰኑ ስጦታዎችን እንዲለግሡ ያበረታቱአቸዋል። 

ስለ ትንሣኤ ካወሳ በኋላ ጳውሎስ ወዲያው ስለ ስጦታ ማንሣቱ የሚያስደንቅ ነው። በመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት «የምዕራፍ መለያዎች» ስላልነበሩ አንባቢያን በቀጥታ ከጳውሎስ ድል ዝማሬ ወደ ገንዘብ ጉዳይ ይገቡ ነበር። ዶክትሪንና ኃላፊነት አብረው የሚጓዙ ናቸው። ልክ እንደዚሁም አምልኮና ሥራም አብረው ይሄዳሉ። ስጦታችን «በከንቱ» አይደለም፥ ምክንያቱም ጌታችን ሕያው ነውና። እንድንሰጥና እንድናገለግለው የሚያነሣሣን የእርሱ የትንሣኤ ኃይል ነው። 

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: