ጌታን አስቡ (1ኛ ቆሮ. 6፡9-20)

በቆሮንቶስ ከተማ ከፍተኛ ልቅ ወሲብ ነበር። የዛሬው ዓለም እንደተያያዘው ይህ ማኅበረሰብ ወሲብን ልቅ የሚያደርግ፡- ወሲብ ጤናማ አካላዊ ተግባር ነው፥ ታዲያ ለምንድን ነው እንደፈለግን የማንጠቀመው? የሚል ፍልስፍና ነበረው። እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ሲያበጅ ወሲብን ፈጠረ፤ ስለሆነም እንዴት መጠቀም እንዳለብን ሊነግረን መብት ያለው እርሱ እንደሆነ ጳውሎስ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ «ባለ ንብረት መመሪያ» ስለሆነ ሰዎች ሊታዘዙት ይገባል። 

እግዚአብሔር ወሲባዊ ኃጢአቶችን ያወግዛል፤ ጳውሎስ አንዳንዶቹን በቁጥር 9 ዘርዝሮአል። በዚያን ዘመን ጣዖት ማምለክ እና በሥጋ መደሰት የማይነጣጠሉ ነበሩ። በግብረ ሰዶማዊ ግንኙነት ወንድ እና ወንድ አንዱ እንደ ባል ሌላው እንደ ሚስት ይሆኑ ነበር። (ጳውሎስ ይህንና ሴት ለሴት ስለሚተኙት በሮሜ 1፡26-27 አውስቶአል።) በቁጥር 10፥ ጳውሎስ የመንፈስ ኃጢአት ሰለባ በመሆን፥ በስግብግብ አመለካከታቸው እርስ በርስ በሚካሰሱ አባላት ላይ ጣቱን ቀሰረ። 

ሆኖም ግን እግዚአብሔር የወሲብ ኃጢአትን በማንጻት ኃጢአተኞቹን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሊያደርጋቸው ይችላል። «ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል» (ቁ 1)። የእነዚህ ግሦች ጊዜ የሚያመለክተው የተጠናቀቀ ሥራን ነው። እንግዲህ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ ካደረገላቸው ሁሉ የተነሣ፥ ሰውነታቸውን ለእርሱ አገልግሎት እና ክብር የመጠቀም ግዴታ ነበረባቸው። 

እግዚአብሔር አብን አስቡ (6፡12-14)። ሰውነታችንን ፈጥሮአል እናም አንድ ቀን ለክብሩ ያስነሣዋል። (ስለ ትንሣኤ በምዕራፍ 15 በሰፊው ተወስቶአል።) ሰውነታችን እንዲህ ያለ ድንቅ መነሻ፥ ይልቁንም ደግሞ ድንቅ የሆነ የወደፊት ዕድል እንዳለው ስንመለከት እንዴት አድርገን እንዲህ ላለ ክፉ ዓላማ እናውለዋለን? 

ቆሮንቶሳውያን በሥጋ መደሰታቸውን ለመከላከል ሁለት ክርክሮችን ያነሣሉ። አንደኛ፥ «ሁሉ ተፈቅዶልኛል» (ቁ 12)። ይህ ስለ ክርስቲያን አርነት የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ የሚነገር ተወዳጅ የቆሮንቶስ አባባል ነው። አርነት የወጣነው ወደ አዲስ ዓይነት ባርነት ውስጥ ለመግባት አይደለም! እንደ ክርስቲያኖች፥ «ይህ ነገር ባሪያ ያደርገኛል ወይ? ይህ ተግባር ለመንፈሳዊ ሕይወቴ ትርፋማ ነው ወይ?» ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። 

ሁለተኛ ክርክራቸው፥ «መብል ለሆድ፥ ሆድም ለመብል» የሚል ነበር (ቁ 13)። ወሲብን የሚደሰቱበት እና በጥንቃቄ የሚጠቀሙበት ስጦታ አድርገው ሳይሆን የፍላጎት ጥማታቸውን እንደሚቆርጥላቸው ነገር አስተናገዱት። በሥጋ መደሰት ለወሲብ እንደሆነ ሁሉ ከመጠን በላይ መጠጣት ወይም መብላት ለሆድ ነው፤ ሁለቱም ኃጢአታዊ እና አደገኛ ውጤቶችን ያስከትላሉ። የተወሰኑ ከፍጥረት በእግዚአብሔር የተሰጡን ጤናማ ፍላጎቶች አሉን ማለት፥ ለእነርሱ እጅ ሰጥተን ሁልጊዜ እናርካቸው ማለት አይደለም። ከጋብቻ ውጪ የሆነ ወሲብ አጥፊ ነው፤ በጋብቻ ውስጥ የሆነ ወሲብ ግን የሚለመልም እና ውብ ነው። 

ከጋብቻ ውጭ በሆነ ወሲብ በእርግጥ ደስታ ይገኛል፤ ነገር ግን መታነጽ የለበትም ከጋብቻ ውጭ የሆነ ወሲብ ባንክን እንደሚዘርፍ ሰው ነው፤ የሆነ ነገር ያገኛል፥ ሆኖም ግን የእርሱ አይደለም፤ ደግሞም አንድ ቀን ይቀጣበታል። በጋብቻ ውስጥ የሚደረግ ወሲብ ገንዘቡን በባንክ እንደሚያስቀምጥ ሰው ነው፤ በዚያ ደኅንነት፥ ዋስትና አለ፥ ትርፉን የሚካፈልበትም የለም። በጋብቻ ውስጥ የሚደረግ ወሲብ ለወደፊት ደስታን የሚያመጣ ግንኙነትን ይገነባል፤ ነገር ግን ማንኛውም የክርስቲያናዊ ጋብቻ አማካሪ እንደሚነግርህ ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ወሲብ የወደፊት ግንኙነቶችን የሚያዳክሙ አዝማሚያዎች አሉት። 

እግዚአብሔር ወልድን አስቡ (6፡15-18)። የአማኝ ሰውነት የክርስቶስ አካል ነው (12፡12 መጨረሻ ተመልከት።) ከክርስቶስ እና ከኃጢአት ጋር በአንድ ጊዜ መተባበር እንዴት ይቻላል? አንዳንድ ቆሮንቶሳውያን የቤተ መቅደስ ዘማውያንን (በአፍሮዳይት ቤተ መቅደስ እንድ ሺህ ያህል ነበሩ) መጎብኘት እና በዝሙት መገናኘት ጉዳት እንደሌለው አድርገው ይመለከቱ ነበር። 

ኢየሱስ ክርስቶስ በዋጋ ገዝቶናል (ቁ. 20)፥ ስለሆነም ሰውነታችን የእርሱ ነው። ከጌታ ጋር አንድ መንፈስ ስለሆንን ሰውነታችንን ሕያው መሥዋዕት አድርገን ልናቀርብለት ይገባል (ሮሜ 12፡1-2)። እያንዳንዱን ቀን ሰውነትህን ለክርስቶስ በማስረከብ ብትጀምር፥ ቀኑን ሙሉ በሰውነትህ በምታደርገው ነገር የምታመጣው ትልቅ ለውጥ አለ። 

ጳውሎስ የወሲብ ኃጢአትን ከባድነት ለመግለጽ ወደ ዝክረ ፍጥረት (ዘፍ. 2፡24) ያመለክታል። ወንድ እና ሴት ሰውነታቸውን በሚያዋህዱበት ጊዜ መላው ሁለንተናቸው ይካተታል። ወሲብ ከራሱ ጋር ጥልቅ እና ዘላቂ ውጤቶችን ይዞ የሚመጣ በጣም ሥር የሰደደ «የአንድነት» ልምምድ አለው። ጳውሎስ ሰው በአካሉ ሊፈጽመው ከሚችለው ኃጢአት ሁሉ የወሲብ ኃጢአት እጅግ በጣም ከባድ መሆኑን ያስጠነቅቃል። ምክንያቱም ሁለንተናን (ቁ. 18) የሚያካትት ተግባር በመሆኑ ነው። ወሲብ በአንድ የሰውነት አካል ላይ ብቻ የሚፈጸም ተግባር አይደለም። «ወንድ»ና «ሴት» መሆን መላ አካልን ያካትታል። የወሲብ ልምምድ በመላ ሁለንተና ላይ የሚሰራጭ መዘዝ አለው ማለት ነው። 

ጋብቻ ራስን የመስጠት ነገር ስላለበት፥ ጳውሎስ ከአመንዝራ ጋር በሥጋ መተባበር ከጋብቻ ጋር አቻ ነው የሚል አሳብ አልነበረውም። ወንድና ሴት አዲሱን ጎጆአቸውን ለመመሥረት የወላጆቻቸውን ቤት ይለቅቃሉ። መሠረቱ የእርስ በርስ መሰጠት ስለሆነ በጋብቻ ውስጥ የሚደረግ ወሲብ የሚያንጽ የእድገት ልምምድ እንዳለው እንድናስተውል ይህ ይረዳናል። ሁለት ሰዎች ፍቅራቸውንና ታማኝነታቸውን በቃል ኪዳን ሲያጸኑ፥ የሚገነቡበትን ጠንካራ መሠረት ይጥላሉ። ጋብቻ ወሲብን በመከላከል እርስ በርስ የተሰጣጡ ጣምራዎች፥ በዚህ አስደናቂ ልምምድ እንዲያድጉ ያስችላቸዋል። 

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አስቡ (6፡19-20)። እግዚአብሔር አብ ሰውነታችንን ፈጠረ፤ እግዚአብሔር ወልድ ደግሞ ተቤዥቶት የራሱ አካል ክፍል አደረገው፤ እግዚአብሔር መንፈስ በሰውነታችን ውስጥ በመኖር የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያደርገዋል። ሰውነታችንን አግባብ ለሌለው ወሲባዊ ተግባር በማጋለጥ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የምናረክሰው እንዴት ነው? 

የእናንተ የሚለው ቃል ብዙ ቁጥር ሲሆን፥ ነገር ግን ሰውነት እና ቤተመቅደስ ነጠላ ቁጥር ናቸው (ቁ. 19)። እዚህ ላይ ጳውሎስ እየገለጸ ያለው ስለ ግለሰብ አማኝ ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንም ጭምር ነው። እያንዳንዱ የአጥቢያ ጉባኤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተጣመሩ ሰዎች «ኅብረት» ነው። የእያንዳንዱ ግለሰብ አማኝ ፀባይ አጠቃላዩን የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት ይነካል። 

በሁለቱም ነጥቦች ትምህርቱ ግልጽ ነው። «በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ!» የሚል ነው። መንፈስ ቅዱስ የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስን ለማክበር ነበር (ዮሐ. 16፡14)። መንፈስ ቅዱስ እርሱ እንዲከብር እና እንዲታይ ብልቶቻችንን ሊጠቀም ይችላል (ፊልጵ. 1፡20-2)። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለን ልዩ ግንኙነት በራሱ ልዩ ኃላፊነት ያመጣል። 

ስለዚህ በብልቶቻችን የምናደርገው ማንኛውም ነገር እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። የእግዚአብሔርን ሕግ የምንጥስ ከሆንን ቅጣቱን መክፈል ይገባናል። 

ይህን ክፍል በምትከልስበት ጊዜ የወሲብ ኃጢአት ሁለንተናን እንደሚነካ ትመለከታለህ። ስሜትን በመውረር ወደ ባርነት ይመራል (ቁ. 12)። ሥጋን ከአግባብ ውጭ ለሆነ ወሲብ መጠቀም እንዴት ሰውን እንደሚገዛ እና ለአጥፊ ልማዶች ባሪያ በማድረግ መላ ሕይወትን እንደሚያረክስ ማየት የሚያስፈራ ነገር ነው። ደግሞም ሰውን በአካልም ይጎዳል (ቁ 18)። ዘማዊ እና አመንዝራ፥ እንዲሁም ግብረ ሰዶማዊያን፥ ኃጢአታቸውን ሊረሱት ይችላሉ፤ ነገር ግን ኃጢአቶቻቸው አይረሱአቸውም።

መጋቢ ሆኜ በምሰጠው የምክር አገልግሎቴ፥ ግንኙነታቸው በቅድመ-ጋብቻ እና ከጋብቻ ውጭ በሆነ ወሲብ ትዳራቸው እየፈረሰባቸው ያሉትን ባል እና ሚስቶች መርዳት ነበረብኝ። በሥጋ  የሚዘራ ዘር ፍሬው ቢዘገይም አይቀሬ ነው (ገላ. 6፡7-8)። ይቅርታን ካገኘንባቸው ኃጢአቶች መዘዞች ጋር መኖር ምንኛ አሳዛኝ ነው። 

ይህን ሁሉ ካልን በኋላ፥ ወሲባዊ ኃጢአት የሚለማመዱ ዘላለማዊ መዘዞች እንደሚጠብቁአቸውም መገንዘብ አለብን። ከ9-10 ባሉት ቁጥሮች፥ ጳውሎስ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶችን የሚለማመዱ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ ሁለቴ ተናግሮአል። አንድ ክርስቲያን እንደ ዳዊት በእነዚህ ኃጢአቶች ሊወድቅ እና ይቅርታ ሊያገኝ ይችላል፤ ነገር ግን ማንም ክርስቲያን እንዲህ ያሉትን ኃጢአቶች አይለማመድም (1ኛ ዮሐ. 3፡1-10)። 

በማጠቃለያም፥ ከወሲባዊ ኃጢአቶች ሌላ ሌሎች ኃጢአቶች እንዳሉም በቅንነት ማስተዋል አለብን። በሆነ ምክንያት፥ ቤተ ክርስቲያን የአባካኙን ልጅ ኃጢአት ማውገዙ ላይ ስትረባረብ የታላቅ ወንድሙን ኃጢአት ትረሳዋለች (ሉቃ. 15፡11–32ን ተመልከት)። የመንፈስ እንዲሁም የሥጋ ኃጢአቶች አሉ፤ ጳውሎስ በቁጥር 10 ላይ አንዳንዶቹን ይዘረዝራቸዋል። ዝሙት በቀላሉ ሰውን ወደ ገሃነም ሊሰድ እንደሚችል ሁሉ ገንዘብን መመኘትም እንዲሁ ያደርጋል። 

የእግዚአብሔር ጸጋ የኃጢአተኛውን ሕይወት ሊለውጥ እንደሚችል ማስታወስ አለብን። «ከእናንተም አንዳንዶቻችሁ እንደነዚሁ ነበራችሁ» (ቁ. 1)። እምነት አንድን ኃጢአተኛ በክርስቶስ «አዲስ ፍጥረት» እንዴት እንደሚያደርግ ሲታሰብ በጣም ያስደንቃል (2ኛ ቆሮ. 5፡17-21)። የእግዚአብሔር አዲስ ፍጥረት አንዱ አካል ሆነን መኖር አስፈላጊያችን ነው። እኛ የራሳችን አይደለንም። ያበጀን የእግዚአብሔር አብ፥ የተቤዠን የእግዚአብሔር ወልድ፥ እና በእኛ ውስጥ የሚኖረው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ንብረት ነን። ደግሞም የእግዚአብሔር ሕዝብ፥ የቤተ ክርስቲያን ንብረትም ነን፥ ስለሆነም ኃጢአታችን ምስክርነቷን ሊያዳክም ኅብረቷንም ሊበክል ይችላል። 

«እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ» (1ኛ ጴጥ. 1፡16)።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: