Site icon

ሰዎች (1ኛ ቆሮ. 16፡10-24)

ብዙ ጊዜ ጳውሎስ በደብዳቤው መዝጊያ ላይ፥ የሕይወቱና የአገልግሎቱ ተካፋይ የነበሩትን ሰዎች በስም ይዘረዝር ነበር፤ አቤት ዓይነታቸው መብዛቱ! እርሱ ነፍሳትን – እጥማጅ ብቻ ሳይሆን ወዳጅ አፍሪም ነበር፤ ብዙዎቹ ወዳጆቹ በእርሱ ምክንያት የተሰጡ የጌታ አገልጋይ ሆነዋል። ወንጌላዊ ድዋይት ኤል. ሙዲ ወዳጅን የማፍራትና ያፈሩአቸውንም ወዳጆች ለጌታ አገልግሎት የመመልመል አንድ ዓይነት ስጦታ ነበራቸው። ከታወቁ የ19ኛው ምእተ ዓመት እና የ20ኛው ምእተ ዓመት መጀመሪያ ሰባኪዎችና ሙዚቀኞች መካከል እንደ እነ ወይራ ሳንኪ፥ ጂ. ካምፕቤል ሞርጋን፥ ሔንሪ ድሩሞንድ፥ እና ኤፍ ቢ. ሜይር የመሳሰሉት በ ሙዲ «የተገኙ» ነበሩ። 

ገንዘብና ዕድሎች ያለ ሶው ዋጋ የላቸውም። የቤተ ክርስቲያን ታላቅ ሀብቷ ሕዝቦቿ ናቸው። እንዲህም ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በጣም ብዙ ጊዜ ሰዎቿን እንደ ነገሩ ትቆጥራቸዋለች። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ገንዘብ አልሰጠም፥ ነገር ግን የሚሰጣቸውን ዕድሎች ይቀበሉ ዘንድ ሦስት ዓመት ለአገልግሎት ሲያሠለጥናቸው ቆየ። ሰዎች ከተዘጋጁ፥ እግዚአብሔር ሥራው ይከናወን ዘንድ ዕድሎቹንም ገንዘብንም ይሰጣል። 

ጢሞቴዎስ (16፡10-11)፥ ከቲቶ ጋር ብዙ ጊዜ እጅግ ከባድ ወደሆኑ ቦታዎች ከሚላኩት የጳውሎስ ልዩ ረዳቶች መካከል ነበረ። ጢሞቴዎስ እግዚአብሔርን በሚፈራ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ነበር (2ኛ ጢሞ. 1፡5)፥ ነገር ግን ይህን ወጣት ወደ ክርስቶስ የመራው ጳውሎስ ነበር። ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ጢሞቴዎስን «በእምነት ልጄ» (1ኛ ጢሞ. 1፡2) ብሎ ይጠራዋል። ዮሐንስ ማርቆስ ጳውሎስን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ፥ የጳውሎስ ረዳት ሆኖ እንዲሠራ የተጠራው ጢሞቴዎስ ነበር (የሐዋ. 16፡1-5)። 

ጢሞቴዎስ ትምህርቱን በደንብ ተምሮ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ታላቅ እድገትን አገኘ (ፊልጵ. 2፡20-22)። በኋላም፥ ለማገልገል በጣም ከባድ የነበረውን የኤፌሶኑን የጳውሎስ ስፍራ ወሰደ። (የጳውሎስ ወራሽ መሆን ቀላል አልነበረም!) ጳውሎስ በአንድ ደረጃ ላይ ከተማይቱን ለቅቆ ለመሄድ የፈለገበት ጊዜ ነበር፥ ነገር ግን ጳውሎስ እንዲቆይ አበረታታው (1ኛ ጢሞ. 1፡3)። 

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር (16፡10) ወጣቱ አንዳንድ አካላዊና ስሜታዊ ችግሮች እንደ ነበሩበት ይጠቁማል (1ኛ ጢሞ. 5፡23፤ 2ኛ ጢሞ. 1፡4)። ማግኘት የሚችለውን ያህል ማጽናኛ አስፈልጎት ነበር። ቁም ነገሩ የእግዚአብሔርን ሥራ እየሠራና ከእግዚአብሔር አገልጋይ ጋር እየደከመ መሆኑ ነበር። ቤተ ክርስቲያን ማንኛውም አገልጋይ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲሆን መጠበቅ የለባትም። አገልግሎት የሚጀምሩ ወጣቶች ከፍተኛ እምቅ ኃይል እሳቸው፤ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ልታበረታታቸው ይገባል። «ማንም ታናሽነትህን አይናቀው!» 

አጵሎስ (16፡12-24) በጵርስቅላና አቂላ (የሐዋ. 18፡24-28) አማካኝነት ወንጌልን ሙሉ በሙሉ ለማወቅ የበቃ በንግግር ችሎታው የታወቀ አይሁድ ነበር። በቆሮንቶስ በታላቅ ኃይል አገልግሎ ስለነበር ወደ እርሱ የተሳበ የቤተ ክርስቲያኒቱ እንድ ክፍል ነበረ (1ኛ ቆሮ. 1፡12፤ 3፡4-8)። ይህን ክፍፍል ጳውሎስ ያደፋፈረ አይመስልም፥ ምክንያቱም የጳውሎስ ትልቁ ጭንቀት የሚመስለው ክርስቶስን መስበክ ነበር። ክፍፍሉ እያለም እንኳ («የአጵሎስ ቲፎዞ») አጵሎስ ለተጨማሪ አገልግሎት ወደ ቆሮንቶስ እንዲመለስ ለማበረታታት ጳውሎስ አላቅማማም ነበር። በጳውሎስ በኩል ምንም ቅናት እንዳልነበረ ወይም በአጵሎስ በኩል የውድድር መንፈስ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ሰዎችን ከፈቃዳቸው ውጭ የማስቀመጥ ሥልጣን አልነበረውም። አጵሎስ በዚያን ጊዜ ወደ ቆሮንቶስ መሄድ ስላልታየው፥ ጳውሎስም በውሳኔው ተስማማ። እነዚህ የተለያዩ ሰዎች በጋራ የሠሩበት ሁኔታ አስደናቂ ነው። 

ምናልባት ጳውሎስ በቁጥር 3 እና 14 ላይ ያሉትን ተግሣጾች የሰጠው በቤተ ክርስቲያን ያሉትን ክፍፍሎች አስመልክቶ ሳይሆን አይቀርም። ንቁ ማለት «ተጠንቀቁ አደጋ ወይም ችግርን ተጠባበቁ!» ማለት ነው። ጠላት ሁልጊዜ ዝግጁ ስለሆነ ከቶውንም ነፃ አይደለንም። በእርግጥ ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን በማጥቃት የጢሞቴዎስንና የአጵሎስን አገልግሎት ለማደናቀፍ ጥረቱ ነበር። 

በሃይማኖት ቁሙ ማለት የብስለት መደላደል ይኑራችሁ ማለት ነው። ጳውሎስ ቀደም ብሎ ማደግ የሚያስፈልጋቸው ጨቅላ ሕፃናት እንደሆኑ አስጠንቅቆአቸዋል (3፡)። ስለዚህ ጳውሎስ ጎልምሱ ማለቱ የሚደንቅ አልነበረም። ጎልምሱ ማለት «እንደ አዋቂ እንጂ እንደ ልጆች አትሁኑ» ማለት ነው። ወቅቱ በሳል አመራርን በጠየቀበት ሰዓት ለጠንካራ ወኔ የተደረገ ጥሪ ነው። 

ነገር ግን አመራር አምባገነናዊ እንዳይሆን፥ ጥንካሬ ከፍቅር ጋር መጣጣም አለበት። ጳውሎስ የፍቅርን እሴትና በጎነት በምዕራፍ 13 አብራርቶአል። ካርል ሳንድበርግ ለአሜሪካ ኮንግረስ በሚናገሩበት ጊዜ አብርሃም ሊንከን «የብረት ጦር» ነበሩ በማለት አድንቀዋቸው ነበር። ይህ ለክርስቲያን መዋስ የሚገባው ጥሩ ምሳሌ ነው፥ እውነተኛ ጥንካሬ ልስላሴንም ያጣመረ ነው። 

የእስጢፋኖስ ቤተሰዎች (16፡15-18) በአካይያ ካሉት ክርስቶስን በማመን የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። ከረዳቶቹ ለእንዱ በመተው ፈንታ (1፡16) ያጠመቃቸው ራሱ ጳውሎስ ነበር። ለክርስቶስ አገልግሎት «ራሳቸውን ስለ ሰጡ»፥ በቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ መሪዎች ለመሆን በቁ። ራሳቸውን ሰጡ የሚለው «ራሳቸውን ሾሙ» ማለት ሲሆን፥ ነገር ግን ይህ ማለት ገፈታትረው አመራርን ያዙ ማለት አይደለም። ይልቅ ጉድለት በሚያዩበት ጊዜ እስኪጠየቁ ሳይጠብቁ በሥራው ውስጥ ይገቡ ነበር። የጳውሎስ ረዳት ሆነው እስኪዝሉ ድረስ ለጌታ ይደክሙ ነበር። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መላው ቤተሰብ በታማኝነት ጌታን ሲያገለግል ምንኛ አስደናቂ ነው። 

እስጢፋኖስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ችግር እንዲነጋገሩ ከቆሮንቶስ ወደ ኤፌሶን ከተላኩ ፈርዶናጥስና አካይቆስን ከያዘ ኮሚቴ ጋር ተባበረ። ጳ ውሎስ በእነርሱ ውስጥ የመላዋን ቤተ ክርስቲያን ውክልና አየ፤ ለጳውሎስ የነበራቸው ፍቅር የእርሱን በቆሮንቶስ አለመገኘት አካክሶታል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የጳውሎስን ችግሮች ከመካፈል በላይ ነበር ያደረጉት፤ በተጨማሪም መንፈሱን ለማደስና በረከትም ሊሆኑለት ችለዋል። 

ይህ ምእመናን መጋቢዎቻቸውን እንዲያድሱአቸውና እንዲያጽናኑአቸው ለማበረታታት ጥሩ ስፍራ ነው። ብዙ ጊዜ፥ አማኞች ለመንፈሳዊ መሪዎቻቸው የሚያካፍሉት ችግሮቻቸውንና ሸክሞቻቸውን ነው፥ በረከቶቻቸውን ግን ከስንት አንዴ ነው የሚያካፍሉአቸው። የመጋቢው መጋቢ ማን ነው? ማንኛውም ምእመን ፈቃደኛ ከሆነ መጋቢው እንዲታደስ እና ሸክሙም እንዲቀል መርዳት ይችላል። 

ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ይህን ልዩ ቤተሰብ እንድታከብር እና ለመንፈሳዊ አመራራቸውም እንድትገዛ አበረታታ። እግዚአብሔር ክብርን የሚያገኝበት ከሆነ ታማኝ ክርስቲያኖችን ማክበር ትክክል ነው። 

አቂላ እና ጵርስቅላ (16፡19) ሕይወታቸውና አገልግሎታቸው ከጳውሎስ ሕይወትና አገልግሎት ጋር የሚያያዝና የሚጣመር የተሰጡ የባልና የሚስት ቡድን ናቸው። እንደ እርሱ ድንኳን ሠሪ ስለነበሩ (የሐዋ. 18፡1-3) ጳውሎስ ያገኛቸው በቆሮንቶስ ነበር። በእግዚአብሔር ታዛዥ የነበሩቱ ባልና ሚስት፥ አቂላ አይሁድ በመሆኑ ምክንያት ከሮም ተባርረው ወጡ፤ ነገር ግን ጳውሎስን ለመርዳት ወደሚችሉበት ቆሮንቶስ መምጣታቸው የእግዚአብሔር ጥበቃና ክብካቤ አንዱ አካል ብቻ ነበር። 

ጵርስቅላ ተደናቂ የነበረች ሴት ናት። የእነዚህ ባልና ሚስት ስም በአዲስ ኪዳን ስድስት ጊዜ ተነሥቷል፥ ከእነዚህ በአራቱ ጎልቶ የታየው የጵርስቅላ ስም ነበር። (የታወቁ ጽሑፎች ጵርስቅላን በሐዋርያት ሥራ 18፡26 የመጀመሪያ ስፍራ ይሰጡአታል። ከሁለቱ ጠንካራ፥ ራሷን የሰጠች መሪና መስካሪ እንደነበረች ፍንጭ እናገኛለን። ጌታን በማገልገልና ጳውሎስን በመርዳት በአንድነት ይሠሩ ነበር። 

ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ወደ ኤፌሶን በተንቀሳቀሰበት ጊዜ፥ አቂላና ጵርስቅላ ጓዛቸውን ጠቅልለው ሥራቸውን እርሱ ወደሚሆንበት በማዛወር በዚያች ጎስቋላ ከተማ የሚካሄደውን የቤተ ክርስቲያን ምሥረታ አገዙት (የሐዋ. 18፡18)። ከፍተኛ ብቃት ስለነበራቸው ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ በተመለሰ ጊዜ አገልግሎቱን እንዲከታተሉት አደራ የሰጠው ለእነርሱ ነበር። እጵሎስ የወንጌልን እውቀት የበለጠ እንዲያውቅ የረዱት በኤፌሶን በነበሩ ጊዜ ነበር። 

እንደ አቂላ እና ጵርስቂላ ላሉ፥ እግዚአብሔርን በማገልገልና ሰባኪን በመርዳት አብረው ለሚሠሩ ባልና ሚስቶች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምስጋና ማቅረብ ይገባታል። አቂላ ባለቤቱ የተሻለች መሪ የመሆኗ ጉዳይ በተባበረው እገልግሎት አብሮእት እንዳይቆም አላገደውም። (ጵርስቅላ ለባለቤቷ ራሷን ያስገዛችና ተፈላጊ ለመምሰል ወይም ለመመጻደቅ እንዳልሞከረች እርግጠኛ ነኝ።) የእስያ ጉባኤ የሚሰበሰበው በእነርሱ ቤት ውስጥ ነበር፥ ይህም ለእንግዳ ተቀባይነት የተሰጡ መሆናቸውን ያሳያል። ሮሜ 16፡14 እነዚህ ራሳቸውን የሰጡ ባልና ሚስት አንድ ጊዜ ጳውሎስን ለማዳን ሲሉ ሕይወታቸውን የአደጋ ጫፍ ላይ እንደጣሉ ይገልጻል (ይህ የማዳን ሥራ ተፈጽሞባቸው ይሆናል ስለተባሉ ሁኔታዎች የሐዋርያት ሥራ 19፡29-30 እና 20፡19ን ተመልከት።) 

ነገር ግን ጵርስቅላና አቂላ በኤፌሶን አልቆዩም፤ ምክንያቱም ጳውሎስ በሮም ለነበሩ ቅዱሳን በጻፈ ጊዜ ለእነዚህ ባልና ሚስት ሰላምታ አቅርቦላቸዋል (ሮሜ 16፡3)። እንደገናም በቤታቸው የቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ተደርጎ ነበር (ሮሜ 16፡5)። በዝውውር አገልግሎቴ፥ በግለሰብ ላሎን ውስጥ ለተመሠረቱ ጉባኤዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ሰብኬአለሁ። 

ጳውሎስ በመጨረሻ ደብዳቤው ያኔ በኤፌሶን ይካሄድ የነበረውን ሥራ በሚከታተለው በጢሞቴዎስ (2ኛ ጢሞ 4፡19) በኩል ለጵርስቅላና አቂላ ሰላምታ ልኳል። እነዚህ ልዩ የሆኑ ባልና ሚስት ቀደም ሲል ጳውሎስን እንዳገዙት ሁሉ በዚህ ጊዜ ጢሞቴዎስን ለመርዳት ሮምን ትተው ወደ ኤፌሶን ተመልሰው ነበር። 

ዛሬ እንደ ጵርስቅላና አቂላ፥ ጌታን የበለጠ ለመርዳት ሲሉ አዘውትረው የሚጓዙ ባልና ሚስት ስንቶች ናቸው? ጵርስቅላና አቂላ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ሥራቸውንም አብረው ማዛወር ነበረባቸው። እንዲህ ያለ መሰጠትና መሥዋዕትነት ያላቸውን ሰዎች ማግኘት ቀላል አይደለም፥ ቢገኙ ግን ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ሀብት ናቸው። 

የጳውሎስ የመዝጊያ ቃላት የሚገድቡን ሊሆኑ አይገባም። «የተቀደሰ አሳሳም» በጊዜው የተለመደ የአሳሳም ዘይቤ ነበር። በዚህ ጊዜ ወንዶች ወንዶችን፥ ሴቶች ደግሞ ሴቶችን ነበር የሚስሙት (ሮሜ. 16፡16፤ 2ኛ ቆሮ. 13፡12፤ 1ኛ ተሰ. 5፡26፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡14)። ጳውሎስ ለምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት እየጻፈም ቢሆን ኖሮ፥ «እጆችን በመጨባበጥ እርስ በርስ ሰላምታ ተለዋወጡ» ይል ነበር። 

ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ደብዳቤዎቼን በቃል ይጽፍና ብዕሩን ወስዶ ፊርማውን ያሰፍር ነበር። በተጨማሪም ደብዳቤው እውነተኛ መሆኑን ለማመልከት «የጸጋ ቡራኬውን» ያስገባ ነበር (ገላ. 6፡11፤ 2ኛ ተሰ. 3፡17ን ተመልከት)። 

አናቴማ የሚለው ቃል አራማይክ ቃል ሲሆን «የተረገመ» (12። ተመልከት) ማለት ነው። ክርስቶስን አለመውደድ ማለት በእርሱ አለማመን ማለት ነው፥ የማያምኑ ደግሞ የተረገሙ ናቸው (ዮሐ 3፡16-21)። ማራን-አታ የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን «ጌታችን ይመጣል» ወይም (እንደ ጸሎት) «ጌታችን ሆይ፥ ና!» ማለት ነው (ራእይ 22፡20ን ተመልከት)። እንድ ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወድድ ከሆነ መምጣቱንም ይወድዳል (2ኛ ጢሞ. 4፡8)። 

ጳውሎስ በቆሮንቶስ አማኞች ላይ ጠበቅ ያለ ነበረ፥ ነገር ግን ደብዳቤውን በሚዘጋበት ጊዜ ለእነርሱ የነበረውን ፍቅር በማረጋገጥ ነበር። ለነገሩ፥ «የወዳጅ ማቁሰል የታመነ ነው» (ምሳሌ 27፡6) እኮ። ጳውሎስ ታላቅ መንፈሳዊ ጥበብን አካፍሎናል። በየዋህነት ተቀብለነው ለእግዚአብሔር ክብር በተግባር እናውለው!

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Exit mobile version