አባት ከሁሉም በላይ ያውቃል (2ኛ ቆሮንቶስ 11፡1-15)

ለምሳሌ አንተ ክርስቲያናዊ አገልጋይ ብትሆን፥ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙትን ምዕመናን በርግጥ የምትወዳቸው መሆኑን እንዴት አድርገህ ልታሳምናቸው ትችላለህ? 

ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ በሚጽፍበት ጊዜ ያጋጠመው ከዚህ ተመሳሳይ የሆነ ችግር ነበር። በመካከላቸው የፈጸመውን ሥራ ቢያስታውሳቸው፥ «ጳውሎስ በትምክህት እየተናገረ ነው» የሚሉ ዓይነት ሰዎች ነበሩ። በቆሮንቶስ ስለ ነበረው አገልግሉት ምንም ባይናገር ደግሞ፥ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎቹ፥ «ተመልከቱ፥ ጳውሎስ ምንም ነገር እንዳልሠራ ነግረናችሁ አልነበር?» ማለታቸው የማይቀር ነው። 

ስለዚህ ጳውሎስ ምን አደረገ? በግሩም መግለጫ ማወዳደርያ እንዲጠቀም የእግዚአብሔር መንፈስ መራው፤ ይህም ወደ ቆሮንቶስ አማኞች ልብ ጠልቆ እንደሚገባ የማያጠራጥር ነበር። በዚህም መግለጫው ውስጥ ያደረገው ራሱን ለቤተሰቡ ከሚጠነቀቅ «መንፈሳዊ አባት» ጋር በማወዳደር ማቅረብ ነበር። ከዚህ በፊት፥ እንደ «አባት» በወንጌሉ አማካኝነት እንደ ወለዳቸውና አስፈላጊ መስሎ ከተሰማው ሊቀጣቸው እንደሚችል ለማስታወስ፥ ይህንኑ ምሳሌ ተጠቅሟል (1ኛ ቆሮ. 4፡14-2)። እነርሱ የተወደዱ መንፈሳዊ ልጆቹ ነበሩና የሚመኝላቸው ሁሉ ከሁሉም የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ ነበር። 

ጳውሎስ ለነርሱ ስለ ነበረው አባታዊ ፍቅር ሦስት መረጃዎችን ይሰጣል። በቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረው ቅንዓት (2ኛ ቆሮ. 11፡1-6፥ 13-15) እውነተኛ ፍቅር ከቶውንም አይመቀኝም፤ ዳሩ ግን በሚወዳቸው ላይ የመቅናት መብት አለው። ባል በሚስቱ ይቀናል፤ እርስ በርስ የሚኖራቸውን ፍቅር ለማሻከር በሚፎክር በማንኛውም ተቀናቃኝ ላይ ደግሞ ጥላቻና ተቃውሞ የማቅረብ መብቱን ማንም የማይነፍገው ነው። አንድ እውነተኛ የአገር ፍቅር ያለው ዜጋ በነጻነቱ ላይ የመቅናትና ይህንኑም ለማስጠበቅ የመዋጋት ሙሉ መብት አለው። እንደዚሁም ማንኛውም አባት (ወይም እናት) በልጆቹ ላይ ስለሚቀና፥ ከሚጎዳቸው ከማንኛውም ነገር ሊጠብቃቸው ያላቋረጠ ክትትል ያደርጋል። 

በዚህ ስፍራ የቀረበው መግለጫ፥ ለጋብቻ የታጨች ልጃገረድ ልጅ ያለችውን አፍቃሪ አባት የሚያመለክት ነው። እርስዋን በንጽሕና መጠበቅና ለባሏ በኃዘን ሳይሆን በደስታ ማስረከቡ፥ መብቱና ሃላፊነቱ እንደ ሆነ ይሰማዋል። ጳውሎስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግባት እንደ ታጨች ሙሽራ አድርጎ ይመለከታል (ኤፌ. 5 ከቁጥር 22 ጀምሮ እና ሮሜ 7፡4 ተመልክት)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሙሽራዪቱ እስኪመጣ ድረስ ያ ጋብቻ አይፈጸምም (ራእይ 19፡1-9)። እስከዚያው ድረስ፥ ቤተ ክርስቲያን ( ማለትም ክርስቲያኖች) ወዳጄን ለመገናኘት ራስዋን አዘጋጅታ በንጽሕና መጠበቅ አለባት። 

እንግዲህ ይህን በመሰለው ግንኙነት ላይ አደገኛ ሁኔታ የሚፈጠረው፥ ልጃገረዲቷ ለእጮኛዋ ሳትታመን ስትቀር ነው። የታጨች ሴት ፍቅሯንና ታማኝነቷን ሁሉ ለአንድ ሰው ብቻ ትሰጣለች . ለእጮኛዋ። ከሌላ ሰው ጋር ስትዳራ ብትገኝ፥ ታማኝነቷን ባለመጠበቋ በደለኛ ትሆናለች። በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡3 ላይ ቅንነት ተብሎ የተተረጎመው ቃል፥ «ታማኝነት፥ ለአንድ ወገን ራስን መስጠት» የሚል ትርጉም ይሰጣል። የተከፋፈለ ልብ ወደ ተበላሸ ሕይወትና ወደ ረከሰ ግንኙነት ያመራል። 

የፍቅርና የጋብቻ መግለጫ፥ እንዲሁም የታማኝነት አስፈላጊነት፥ ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል። ነቢዩ ኤርምያስ የእስራኤል ሕዝብ ለእግዚአብሔር የነበረውን ፍቅር እያጣ ሲሄድ ተመለከተና አስጠነቀቃቸው። «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡ የብላቴንነትሽን ምሕረት፥ የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተለኝ አስቤአለሁ» (ኤር. 2፡2)። የይሁዳ ሕዝብ «የጫጉላ ቤት ፍቅሩን» አጥተ ጣዖታትን በማምለክ በደል ውስጥ ወደቀ። ኢየሱስም በኤፌሶን የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲያስጠነቅቅ፥ በተመሳሳይ መግለጫ ተጠቅሟል – «ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና» (ራእይ 2፡4)። 

ጤናማውን ግንኙነት ከበስተጀርባ ሆኖ ያደፈረሰው ሳይጣን ሲሆን፥ በጥቅሱ ውስጥ በእባብ መልክ ተገልጾአል ። ይህም የሚያመለክተው ወደ ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ነው። ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ ለቆሮንቶስ ሰዎች በሚጽፍበት ጊዜ፥ ስለ ከሳሹ ዲያብሎስ ብዙ የሚለው ነገር እንደ ነበር መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ሰይጣን አማኞችን ለማጥቃት በርካታ መሣሪያዎች እንደ ነበሩት በመግለጽ ያስጠነቅቃል። ኃጢአት የፈጸሙትን አማኞች ሕሊና ሊያከብድ (2ኛ ቆሮ. 2፡10-11)፥ የማያምኑትን አእምሮ ሊያሳውር (4፡4)፥ ወይም የአማኛችን አእምሮ ሊያሳስት (11፡3)፥ ብሉም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ሰውነት ሊጎስም (12፡7) ይችላል። 

ሰይጣን ሐሰተኛ ስለ ሆነና ሐሰቶቹን እንድንሰማ፥ እንድናሰላስልና ከዚያም እንድናምንባቸው ስለሚፈልግ፥ ያለ የሌለው ትኩረቱ ሁሉ የአእምሯችንን አስተሳሰብ በመለወጥ ላይ ነው። ስለዚህም ነው በዚህ ክፍል ውስጥ በተለይ በአእምሯችን ላይ ለሚደርሰው ፈተና ልዩ ክብደት የተሰጠው ሰይጣንም በሔዋን ላይ የፈጸመው ይህንኑ ነበር። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔርን ቃል እንድትጠራጠር አደረገ («እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአልን .?)፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ካደ («መሞትን አትሞቱም! » )፤ ቀጥሎም የራሱን ውሸት ምትክ አድርጎ አቀረበ («እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ …») (ዘፍ. 3፡1፥ 4-5)። 

በመሠረቱ ሰይጣን አታላይ ነው። አማኞች ውሸትን ወዲያው እንደማይቀበሉ ስለሚያውቅ፥ «ወጥመዱን በሚማርክ ነገር ማበጀትና» የሚሰጠንን ነገር እንድንቀበል ማድረግ መቻል አለበት። ከሰይጣን መሠረታዊ ባሕርያት አንዱ አስመሳይነት ነው – እግዚአብሔር የሚያደርገውን ነገር ይቀናና የእርሱ ስጦታ በማስመሰል ከእግዚአብሔር እንደሚበልጥ አድርጎ ሊያሳምነን ይጣጣራል። ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ መስለው ሰይጣንን በሚያገለግሉ አስመሳይ ሰዎች በመጠቀም ነው። 

ሰይጣን፥ ሌላ አዳኝና ሌላ መንፈስ የሚገኝበት አስመሳይ ወንጌል አለው (ገላ 1፡6-12)። የሚያሳዝነው የቆሮንቶስ ሰዎች የጸጋና የሕግ ድብልቅ የሆነውንና ከቶውንም እውነትነት የሌለበትን ይህንኑ «አዲስ ወንጌል» «መቀበላቸው» ነው። አንድ ወንጌል ብቻ ስላለ፥ ሊኖር የሚችለው አንድ አዳኝ ብቻ ነው (1ኛ ቆሮ. 15 ከቁጥር 1 ጀምሮ)። ስለዚህ አንተም በአዳኙ በምታምንበት ጊዜ በልብህ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ገብቶ ያድራል፤ ያለውም አንድ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። 

የዚህ የሐሰተኛ ወንጌል ሰባኪዎች (ዛሬም በእኛ መካከል የሚገኙ)፣ በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡13-15 ውስጥ ተገልጸዋል። እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች መለኮታዊ ሥልጣን እንዳላቸው ይናገሩ ነበር፤ ይሁንና ሥልጣናቸው ውሸት ነበር። እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋዮችንም አስመሳዮች ናቸው ብለው በማሳጣት ወነጀሉ። ጳውሎስንም የከሰሱት በተመሳሳይ ሁኔታ ነበር። ራሳቸውንም ከጳውሎስ እጅግ ልቀው እንደሚገኙ «የመጠቁ-ሐዋርያት» አድርገው ያቀርቡ ነበር። በተራቀቀው የአነጋገር ችሉታቸው፥ አላዋቂ አማኞችን ሳቡዋቸው፤ ጳውሎስንም የመናገር ስጦታ የለውም በማለት ያሳጡት ጀመር (ቁ 6፤ 10፡10)። በመሆኑም በእምነታቸው ወላዋይ የሆኑት አማኞች በታማኝ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች በተሰጧቸው የወንጌሉ መሠረታዊ እውነቶች ጸንቶ በመቆም ፈንታ፥ በሰይጣን አገልጋዮች «ማራኪ ንግግር» መደለላቸው ምን ያህል የሚያሳዝን ነገር ነበር! 

ጳውሎስ፥ «እነርሱ ከቶውንም የመጠቁ-ሐዋርያት አይደሉም። በማለት ሕዝቡን ያስጠነቅቃል። «እነርሱ የውሸት ሐዋርያት ናቸው!» አነሳሽ ምክንያታቸውም እግዚአብሔርን ማስከበር ሳይሆን፥ ያመኑትን ሰዎች በማጥመድ የግል ጥቅም ማግኘት ነው። ዘዴዎቻቸው የማታለያ ብልሃቶች ናቸው (2፡17፤ 4፡2)። በዚህ ስፍራ ላይ የተመለከተው ዋንኛ አሳብ ዓሣን ለማጥመድ በወረንጦው ላይ የሚንጠለጠለው መታለያ ምግብ ነው። ለቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተገለጸው «የበለጠ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዳለ በማስመሰል ያቀርባሉ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሌለው የሕግና የጸጋ ድብልቅ ሕይወት ይሰብካሉ። 

እነዚህ አገልጋዮች የሚሠሩት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሳይሆን በሰይጣን ኃይል ነው። ጳውሎስ ሥራቸውን በማስመልከት፥ ለሦስት ጊዜ ያህል መለወጥ በሚለው ቃል ተጠቅሟል (11፡ 13፥ 14፥ 15 ተመልከት)። የዚህ ቃል የግሪኩ ትርጉም «ማንነትን ላለማስነቃት በአልባሳት መጀቦን፥ ጭምብል ማጥለቅ» የሚል ነው። ከውጭ ለውጥ ይታያል፤ ዳሩ ግን ከውስጥ የተለወጠ ነገር የለም። እንደ ሰይጣን ሁሉ፥ የሰይጣን ሠራተኞችም እውነተኛ ባሕርያቸውን ይዘው አይቀርቡም፤ ሁልጊዜም እነርሱነታቸውን የሚሸሽግ አልባሳት ደርበውና በመጋረጃ ውስጥ ተጠልለው ይመጣሉ። 

ይህን መጽሐፍ በምጽፍበት ወቅት፥ በርካታ «የሰይጣን አስመሳይ አገልጋዮች» ወደ ቤቴ መጥተው ነበር። ከነዚህ ሰዎች መካከል፥ አንዲት ውብ ወጣት ሴት፥ ለዓለም ሰላም እንደምትሠራ ልትነግረኝ ሞክራ ነበር። ጻሩ ግን ማንነቷን ስነግራት፥ የኑፋቄ ቡድን አባልነቷን አመነች። ሁለት አለባበሳቸውን ያሳመሩ ወጣት ወንዶች፥ «እኛ በዚህ ስፍራ የተገኘነው ኢየሱስ ክርስቶስን በመወከል ነው» በማለት ራሳቸውን አስተዋወቁኝ። እኔም የትኛውን ቡድን እንደሚወክሉ የማውቅ መሆኔን ወዲያውኑ ነገርኋቸውና በሩን ዘጋሁ። «ደህና ሁኑ» እንኳ አላልኋቸውም። ይህን በማድረጌ ትርነት የጎደለብኝ የሚመስላችሁ ከሆነ፥ 2ኛ ዮሐንስ 5-11ን አንብቡና እንደ ትእዛዙ ፈጽሙ። 

ጳውሎስ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጥቃት በመጠበቅ ለቤተ ክርስቲያን የነበረውን ፍቅር አረጋግጧል፤ ይሁንና የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ለአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ተታልለው በመቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲገቡ በር ከፈቱላቸው። የቆሮንቶስ ሰዎች «የመጀመሪያ ፍቅራቸውን ስለ ተዉ»፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከሙሉ ልብ የመነጨ አምልኮ እያቀረቡ አልነበረም። ፊታቸውን የመለሱት ከጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስም ጭምር ነበር፤ ይህ ደግሞ እጅግ የከበደ ጥፋት ነበር። 

ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው የልግስና ስጦታ (2ኛ ቆሮ. 11፡7-12) አፍቃሪ አባት ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያሟላል፤ ጳውሎስም በቆሮንቶስ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል መሥዋዕትነት ከፍሏል። ጳውሎስ እዚያ በነበረ ጊዜ፥ በእጆቹ ድንኳን የመሥራቱን ተግባር ከማከናወኑም በላይ(የሐዋ. 18፡1-3)፥ የቆሮንቶስ ሰዎች የዚህን ታላቅ የእግዚአብሔር ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማግኘት ምንም ዋጋ አልከፈሉም ነበር ማለት ነው። 

የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ የከፈለላቸውን መሥዋዕት አደነቁት ይሆን? የለም . አብዛኛዎቹ አላደነቁትም። እንዲያውም የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ጳውሎስ ለገንዘብ የነበረውን አመለካከት ትክክለኛ ሐዋርያ አይደለም ለሚለው ክሳቸው «ማረጋገጫ» አድርገው ተጠቅመውበታል። እውነተኛ ሐዋርያ ቢሆን ኖሮ፥ ለመተዳደሪያው የገንዘብ አስተዋጽኦ በጠየቀና በተቀበለ ነበር ብለው ደመደሙ። 

ጳውሎስ ግን ይህን በተመለከተ የነበረውን እምነት አብራርቷል (1ኛ ቆሮ. 9)። ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ስለ ተመለከተና በእርሱም ስለ ተላከ፥ እውነተኛ ሐዋርያ መሆኑን ገልጾአል። ዛሬ ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደሚያደርጉት፥ ጳውሎስ የመዋዕለ-ንዋይ ድጋፍ የመጠየቅ መብት ነበረው፤ ይሁንና ማንም ሰው ወንጌሉን የገንዘብ ማግኛ ምንጭ አድርጎ እንደሚጠቀምበት በመቁጠር እንዳይነቅፈው፥ በመብቱ ሊገለገልበት አልፈለገም። እርሱም ለወንጌል ትምህርት ደኅንነትና ብሉም ከደኅንነት ርቀው የጠፉ ኃጢአተኞች በ«ሃይማኖታዊው ንግድ» የመሳተፍ ዝንባሌ እንዳያደናቅፋቸው ከመስጋቱ የተነሣ «የመዋዕለ-ንዋይ መብቱን» ለመተው መረጠ። 

በሌላ በኩል ግን የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች «ወንጌሉን» ለግል ጥቅማቸው እየተዘዋወሩ «ይሸቅሉበት» ነበር። ጳውሎስ በነጻ (2ኛ ቆሮ. 11፡7፥ ያለ ምንም ክፍያ) ወንጌሉን ሰብኮላቸዋል፤ ዳሩ ግን የሐሰት አስተማሪዎች ሐሰተኛ ወንጌል እያስተማሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘርፉአታል (ቁ 20)። ጳውሎስ በቁጥር 8 ላይ መጠነኛ ውስጠ ወይራ ቅኔ ይቀኛል – «አዎን፥ «ዘራፊ› ነኝ። ሆኖም እናንተን (እንዳልዘርፍ ስል ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን (ዘረፍሁ» ብሏል። አሁን ግን የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በእርግጥ እየዘረፉዋቸው ነበር። 

አፍቃሪ አባት ሸክሞችን በልጆቹ ላይ አይጭንም። ይልቁንም፥ ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲሟላላቸው መሥዋዕትነትን ይከፍላል። ለልጆች በ«ዋጋዎች» እና «እሴቶች» መካከል የሚገኘውን ልዩነት ማስተማር አስቸጋሪ ነው። ለልጆች የወላጆቻቸው ወደ ሥራ መሄድና ለቤተሰቡ መሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ገንዘብ ማግኘት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት የሚከብዳቸው ይመስላል። ከወንድሜ ልጆች አንድኛው በጣም ትንሽ ሳለ፥ ወላጆቹ ለቤታቸው አንድ ትልቅ መገልገያ ዕቃ መግዛት እንዳለባቸው ሲወያዩ ቢሰማም፥ ዳሩ ግን በቀጥታ በመሄድ የማይገዙበትን ምክንያት አልተረዳም ነበር። በመሆኑም፥ ወደ አባቱ የቼክ ደብተር እያመለከተ፥ «ለምን የምትፈልገውን ገንዘብ ያህል በአንድኛው ወረቀት ላይ ዝም ብለህ አትጽፍም?» በማለት ጠየቀ። በእነዚያ የደብተሩ «ወረቀቶች» ላይ የሚጻፈውን የገንዘብ ጥያቄ ተአማኒ ለማድረግ በቅድሚያ በባንክ ቤት ውስጥ ገንዘብ መቀመጥ እንደ ነበረበት አልተረዳም ነበር። 

ጳውሎስ የገንዘብን ጉዳይ ያነሣው፥ የአይሁድን ሃይማኖት አስፋፊዎች ትምክህት ለማቀዝቀዝ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ለማድረግ እንጂ፥ ራሱን ለማሞካሸት ሲል አልነበረም። ጳውሎስ አንድም ሰው እንኳ በስግብግብነት ወይም በራስ-ወዳድነት እንደማይከሰው ያውቅ ነበር (ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ምስክርነት ከሐዋርያት ሥራ 20:33-35 ተመልከት)። እጆቹ ንጹሐን ነበሩ። ጠላቶቹ የሚከሱበትን ማንኛውንም መዘዝ ለማስወገድ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርግ ነበር። 

በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡9 ላይ መከበድ የሚለው ቃል በተለየ መንገድ መታየት የሚገባው ነው (12፡13-14ንም ተመልከት)። በግሪኩ፥ « መደንዘዝ» ማለት ነው። ቃሉም የተወሰደው ከውስጡ ከሚያስተላልፈው የኮረንቲ ኃይል ሳቢያ የሚበላቸውን ነገሮች አስቀድሞ ከሚያደነዝዘው «ኢል» ከሚባለው ዓሣ ምሳሌ ነው። ዓሣው ላጠመደው እንስሳ በኤሌክትሪክ ኃይል የደነዘዘው የአካል ክፍል ከባድ ሸክም ይሆንበታል። ጳውሎስ አማኞችን በማስደነቅ፥ በማጥቃት፥ ወይም በመዝረፍ ለመያዝ ምንም ዓይነት የማታለያ ብልሃቶችን አልተጠቀመም ነበር። በወንጌል ሰበካውም ሆነ በገንዘብ አያያዙ ግልጽና ታማኝ ነበር። 

በራሴ የአገልግሉት ጉዞዎች ወቅት በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እጅግ የሚያሳዝኑ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። ቤተ ክርስቲያኒቱ አድጋ ለማየት በመሥዋዕትነት ለሚሠሩ ታማኝ መጋቢዎች ማኅበረ-ምዕመናን ምንም ምስጋና ሲያቀርቡ አላየሁም። ከእነዚህ አገልጋዮች አንዳንዶቹ ጥቂት ደመወዝ እየተከፈላቸው ብዙ ሥራ የሚሠሩ ቢሆኑም፥ ዳሩ ግን አብያተ ክርስቲያናት ምንም ፍቅር የሚያሳዩዋቸው አይመስሉም። የእነርሱ ተተኪዎቻቸው ግን እንደ ነገሥታት ይታዩ ነበር። እዚህ ላይ የምንጽናናበት ነገር ቢኖር በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ሁሉም ትክክለኛ ፍትሕና ዋጋ ማግኘቱ ነው። 

በአንድ ወቅት ለአደን ወደ አፍሪካ መጥተው የነበሩት ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት በመርከብ ወደ አሜሪካ በሚመለሱበት ጊዜ ስላጋጠሟቸው ሁለት ሐቀኛ ባልና ሚስት ሚሲዮናዊያን ታሪክ፥ ዶክተር ክሪስዌል ያጫወቱኝን አስታውሳለሁ። በርካታ ዜና ዘጋቢዎችና ፎቶግራፍ አንሺዎች በአደን ላይ የከረሙትን ለማግኘትና ቃለ-ምልልስ ለማድረግ በወደቡ ላይ ይጠባበቁ እንጂ፥ እነኛን ክርስቶስን በአፍሪካ በማገልገል ዘመናቸውን አሳልፈው ለተመለሱት ጀግና ሚሲዮናውያን ግን አቀባበል የሚያደርግላቸው አንድም ሰው አልተገኘም ነበር። 

በዚያኑ ምሽት ባልና ሚስቱ በተከራዩበት መለስተኛ ሆቴል መኝታ ክፍላቸው ውስጥ ሆነው በኒው-ዮርክ ከተማ ወደብ ሲደርሱ ስለ ነበረው ሁኔታ በቴሌቭዥን ተመለከቱ። ባልዮዎም ባየው ነገር ኃዘን ተሰምቶት፥ «ትክክል አይደለም» አለ ለባለቤቱ፤ አክሉም፥ «ሚስተር ሩዝቬልት የተመለሱት ከአደን ጉዞ ነበር፤ እናም አገሩ በሙሉ እርሳቸውን ለማግኘት ወጣ። እኛም ከብዙ ዓመታት የአገልግሎት ጊዜ በኋላ ወደ ቤት ተመለስን፤ ሰላም ሊለን የቀረበ ሰው ግን አልነበረም» አላት። 

ባለቤቱ ግን ለዚህ ቅሬታው ትክክለኛ መልስ ነበራት፡- «ፍቅሬ፥ እኛ ገና ወደ ቤታችን አልደረስንም» አለችው። 

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረውን ፍቅር ለማረጋገጥ ሁለት መረጃዎችን አቅርቧል፡- ለቤተ ክርስቲያን የነበረው ቅንዓት – እነርሱን «ከመንፈሳዊ አለመታመን» መጠበቅና ለቤተ ክርስቲያን የነበረው ልግስና . ከእነርሱ የገንዘብ ድጋፍ አለመቀበል። ሦስተኛ መረጃም አቅርቦላቸዋል። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: