ሙታን የሚነሡት መቼ ነው? (1ኛ ቆሮ. 15፡20-28)

ጳውሎስ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሦስት ምሳሌዎችን ተጠቅሞአል። 

የመከር በኩራት (1ኛ ቆሮ 15፡20፡23)። ቀደም ሲል የዚህን ማጣቀሻ ከብሉይ ኪዳን በዓል ጋር ማያያዛችን ይታወሳል (ዘሌዋ. 23፡9-14)። ኢየሱስ በፋሲካ ዕለት የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ሞተ። እንደ በኩረ መከር ነዶ፥ ከሦስት ቀናት በኋላ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ከሙታን ተነሣ። ካህኑ የበኩር መከሩን ነዶ ከጌታ ፊት ሲወዘውዝ፥ መላው መከር የእርሱ ለመሆኑ ምልክት ነበር። ኢየሱስ ከሙታን መነሣቱ፥ እኛም አንድ ቀን የመጻኢው መከር አካል ሆነን እንደምንነሣ የእግዚአብሔር ማረጋገጫ ነበር። ለአማኞች፥ ሞት «እንቅልፍ» ብቻ ነው። ሥጋ ያንቀላፋል፤ ነገር ግን ነፍስ ከጌታ ጋር ናት (ፊልጵ. 1፡21-23፤ 2ኛ ቆሮ 5፡1-8)። በትንሣኤ ጊዜ ሥጋም «ይቀሰቀስና» ይከብራል። 

አዳም (15፡21-22)። ጳውሎስ በአዳም ውስጥ ክርስቶስን የሚመስል ምሳሌ በንጽጽር አየ (ሮሜ 5፡12-21ን ተመልከት።) የመጀመሪያው አዳም የተበጀው ከአፈር ነበር፥ ነገር ግን የመጨረሻው አዳም (ክርስቶስ፥ 15፡45-47) ከሰማይ መጣ። የመጀመሪያው አዳም እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም አመጣ። ነገር ግን የመጨረሻው አዳም እግዚአብሔርን በመታዘዝ ጽድቅንና ሕይወትን አመጣ። 

(በቁጥር 23 ተራ የሚለው ቃል መጀመሪያ ያመለክት የነበረው በጦር ሠራዊት ውስጥ ያለውን ተዋረድ ነበር። እግዚአብሔር በትንሣኤ ውስጥ ተራ፥ ቅደም ተከተል አለው። እንደ ዮሐንስ 5፡25-29 ያሉ ምንባቦች እና ራእይ 20 መጽሐፍ ቅዱስ «አጠቃላይ ትንሣኤ» ብሎ ነገር እንዳላስተማረ ያሳያሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ በአየር ውስጥ በሚመለስበት ጊዜ፥ ቤተ ክርስቲያኑን ወደ ሰማይ ይወስዳታል። በዚያን ጊዜ እርሱን ያመኑትንና በእምነታቸው ሆነው የሞቱትን ከሞት ያስነሣቸዋል (1ኛ ተሰ. 4፡13-18)። ኢየሱስ ይኸኛውን «የሕይወት ትንሣኤ» ብሎታል (ዮሐ 5፡29)። ኢየሱስ ወደ ምድር በፍርድ በሚመለስበት ጊዜ፥ የጠፉት «በፍርድ ትንሣኤ» ይነሣሉ (ዮሐ 5፡29፤ ራእይ 20፡11-15)። የመጀመሪያ ትንሣኤን ያገኘ ማንም አይጠፋም፥ ይሁን እንጂ በሁለተኛ ትንሣኤ የሚገኝ ማንም አይድንም። 

የእርሱ መንግሥት (15፡24-28)። ኢየሱስ ወደ ምድር ለመፍረድ በሚመጣበት ጊዜ፥ ኃጢአትን ለአንድ ሺህ ዓመት ያጠፋና መንግሥቱን ያቋቁማል (ራእይ 20፡1-6)። አማኞች ከእርሱ ጋር በመንገሥ ክብሩንና ሥልጣኑን ይጋሩታል። በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት ይህ መንግሥት በነቢያዊ አስተማሪዎች «ሺሁ ዓመት» የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ቃሉ በላቲን «ሚሊየን» የሚል ሲሆን፥ ሚሌ-ሺህ። አነም-ዓመት ማለት ነው። 

ነገር ግን ከሺሁ ዓመት በኋላም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ኃይሉ የሚያጠፋው አንድ የመጨረሻ ዓመፅ በእግዚአብሔር ላይ ይከሰታል (ራእይ 20፡7-10)። ከዚያ በኋላ የጠፉት ይነሣሉ፥ ፍርድ ተቀብለው ወደ እሳት ባሕር ውስጥ ይጣላሉ። ከዚያ በኋላ ሞት ራሱ ወደ ገሃነም ይጣልና የመጨረሻውም ጠላት ይደመሰሳል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች ያደርጋል! ከዚያም መንግሥቱን ለአብ ያስረክብና ዘላለማዊ መንግሥት- አዲሱ ሰማይና አዲስ ምድር– ይስተናገዳሉ (ራእይ 21-22)። 

መልካምና መንፈሳዊ የሆኑ የቃሉ ተከታዮች በእግዚአብሔር ትንቢታዊ መርሐ ግብር ዝርዝር ጉዳይ ሁልጊዜም አይስማሙበትም፥ ሆኖም ዋነኞቹ እውነቶች ግልጽ ይመስላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በሰማይ ነግሦ ይገኛል፥ ሥልጣንም ሁሉ ከእግሩ በታች ነው [መዝ. (110)፤ ኤፌ. 1፡15-23]። ሰይጣንና ሰው አሁንም ምርጫቸውን መፈጸም ይችላሉ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ በሥልጣኑ ላይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በሰማይ ዙፋኑ ነው (መዝ 2)። የዳኑ ሰዎች ትንሣኤ ገና አልተፈጸመም፥ የጠፉትም ትንሣኤ ቢሆን ገና ነው (2ኛ ጢሞ. 2፡17-18)። 

ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ የሚመለሰው መቼ ነው? ማንም አያውቅም፤ ግን በሚሆንበት ጊዜ፥ «በድንገት በቅጽበተ ዓይን» (15፡52) ይፈጸማል። መዘጋጀት ያስፈልገናል (1ኛ ዮሐ 2፡28–3፡3)።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: