ከአንባብያን ወይም ከሬድዮ አድማጮች ጠጠር ያለ ደብዳቤ ሲደርሰኝ፥ ብዙውን ጊዜ ለመልሱ በብቃት እንደ ተዘጋጀሁበት እስከሚሰማኝ ድረስ በተለየ ፋይል ውስጥ አስቀምጠዋለሁ። በጥቂት አጋጣሚዎች፥ ለደብዳቤዎች እጅግ ፈጣን መልሶችን ሰጥቻለሁ፤ በኋላ ግን ተጸጽቼአለሁ። ቆይታ በማድረግ፥ ለማሰብና ለመጸለይ፥ ብሉም የደብዳቤውን አሳብ በትክክል ለመረዳት ለራሴ በቂ ጊዜ እሰጣለሁ። ይህም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ምላሽ ለመስጠት ስለሚያስችለኝ ነው።
ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በሚጽፍበት ጊዜ፥ ጥበብ ያለበትን እርምጃ እንዲከተል የእግዚአብሔር መንፈስ መርቶታል። የሚጽፈው ለተከፋፈለች (1ኛ ቆሮ. 1 ከቁ 11 ጀምሮ)፥ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን እየተገፋች ለነበረችና በሐሰተኛ መምህራን በማመረክ ላይ ለነበረች ቤተ ክርስቲያን ነበር። በመሆኑም፥ እውነተኛነቱን እንዳይጠራጠሩ በመጀመሪያ አገልግሎቱን ይገልጽላቸዋል። ከዚያም፥ የሚያቀርብላቸው የእርዳታ ጥያቄ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዕድገት እንደሚረዳቸው ስለሚያውቅ፥ በመዋጮው ውስጥ እንዲካፈሉ ያበረታታቸዋል። በጸጋ መስጠትና በጸጋ መኖር ጎን ለጎን ይሄዳሉ።
አሁን በመጨረሻው የደብዳቤው ክፍል፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ጨምሮ፥ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከት የሚፈጥሩትን ሰዎች ይሞግታል – ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም ያጠናክረዋል። ከምዕራፍ 10-13 ያለውን በምታነብበት ጊዜ፥ ጳውሎስ በቀጥታ ከሳሾቹን ሲጠቅስ (ለምሳሌ፥ 10፡7፥ 10-12፤ 11፡4፥ 20-23) እና ለሐሰት ክሶቻቸውም ምላሽ ሲሰጥ ትመለከታለህ። እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የእግዚአብሔርን ሥራ ለማፍረስ የሚሠሩ የሰይጣን አገልጋዮች መሆናቸውን አልሸሸገም (11፡12-15)።
ጳውሎስ ከምዕራፍ 10-13 ውስጥ አንድን ቃል ሃያ ጊዜ ያህል ጠቅሶአል – መመካት ተብሎ የተተረጎመውን ቃል። እነዚህን ምዕራፎች በመጀመሪያ ስታነብ፥ ጳውሎስ ስለ ራሱ እንደሚመካ አድርገህ ታስብ ይሆናል፤ ዳሩ ግን አይደለም። ጳውሎስ «የተመካው በኢየሱስ ክርስቶስ» ነው እንጂ፥ በራሱ ወይም ባደረጋቸው ነገሮች አልነበረም (ሮሜ 5፡11፤ ገላ. 6:14፤ ፊልጵ. 3፡ 3)። እንዲሁም ስለ ቆሮንቶሶች ያለውን ትምክህት ለሌሎች ተናግሯል፤ ዳሩ ግን ትምክህቱ ከንቱ የሚቀር ይመስል ነበር (2ኛ ቆሮ. 7፡4፥ 14፤ 8፡24)።
ጳውሎስ ለአገልግሎቱና ለሐዋርያዊ ሥልጣኑ እንጂ፥ ለራሱ ሲል በግል እየተከላከለ እንዳልነበረ፥ ልብ በል። ከሌሎች አገልጋዮች ጋር «የዝና ውድድር» እያደረገ አልነበረም። ጠላቶቹ እርሱን በውሸት ለመክሰስ አልቦዘኑም ነበር፤ ራሳቸውንም ከፍ ከፍ ከማድረግ አልተመለሱም ነበር (11፡12)። ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ አገልግሎቱ በመግለጽ በግሉ እንዲከላከል ያስገደደው፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ዓለማዊ አመለካከት ነበር። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመናገር አያቅማማም፤ ዳሩ ግን በቂ ምክንያት እስከሌለው ድረስ፥ ስለ ራሱ አይናገርም ነበር፡፡
በመጨረሻም፥ ጳውሎስ በተመካበት ወቅት፥ እግዚአብሔር በሰጠው አገልግሎት ላይ ተወስኖ ነበር (10፡13)፤ ከዚያም አጽንኦቱን ያደረገው በመከራዎቹ ላይ እንጂ፥ በስኬቶቹ ላይ አልነበረም። ይህ ደብዳቤ በቆሮንቶስ ማህበረ-ምዕመናን ዘንድ በሚነበብበት ወቅት፥ ጳውሎስን በከሰሱት ሰዎች ልብ ውስጥ የኀፍረት ስሜት መጫሩ የማይቀር ነበር – የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎችንም ሞኝነት ይፋ ማድረጉ የማይጠረጠር ነበር።
ጳውሎስ አገልግሎቱን የገለጸበት የመጀመሪያው ዓላማ፥ ከሥራው ጋር በተያያዘ መንገድ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሰረፀውን ውዥንብር (አለመግባባቶች) ማስወገድ ነበር። እነርሱም አስፈላጊ የሆኑትን ሦስት የአገልግሎት ክፍሉች አልተረዱም ነበር።
መንፈሳዊ ውጊያን ስለ ማካሄድ (2ኛ ቆሮ. 10፡1-6)
1. የቀረበበትን ክስ (2ኛ ቆሮ. 10፡1-2) ለማግኘት የሚያዳግት አይደለም። (በአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የሚመሩ) የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዓመፀኞች፥ ጳውሎስ ከርቀት ሆኖ ደብዳቤ ሲጽፍ እንደሚደፍርና ዳሩ ግን ከቆሮንቶስ ሰዎች ጋር ፊት ለፊት በሚጋፈጥበት ጊዜ አልፈራም እንዲያውም በጣም ደካማ እንደ ሆነ አድርገው ያስወሩ ነበር (በተጨማሪም ቁ9-11 ተመልከት)። ከበስተጀርባ ሆነው የሚገፋፏቸው የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በአመለካከታቸው ላይ ያላቋረጠ ተፅዕኖ ቢያሳድሩባቸውም፥ ሕዝቦቹ ግን ወደዋቸው ነበር (11፡20)። «አንድን መሥመር ያልተከተለው» የጳውሎስ የሕይወት ዘይቤ «አዎን እና አይደለም። ከሚለው የተስፋ ቃሉ ጋር ተጓዳኝ ነበር (1፡15-20)።
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርት፥ ዓላማው ክርስቶስን እንጂ ራሱን ማስከበር አልነበረም (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5)። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የሚያድጉት በተወለዱበት መንገድ ነው። አምባገነናዊ አገዛዝ በበዛበት ክልል ከተወለዱ፥ በሰው ጥበብና ብርታት ላይ ተደግፈው ያድጋሉ። ትህትናና ፍቅር በሰፈነበት አካባቢ ካደጉ፥ በጌታ ላይ መደገፍን ይማራሉ። ጳውሎስ አዲስ አማኞቹ በጌታ እንጂ በአገልጋዩ ላይ እንዳይተማመኑ ስለሚፈልግ፥ ሆን ብሉ ሥልጣኑንና ችሎታውን ዝቅ ያደርገዋል።
ጳውሎስ ያንን ሁሉ ካስተማራቸው በኋላ እንኳ፥ ክርስቲያኖቹ ግን አሁንም አላዋቂዎች ነበሩ። እውነተኛ መንፈሳዊ ኃይል የሚገኘው፥ በ«የዋህነትና ገርነት» እንጂ (2ኛ ቆሮ. 10፡1)፡ «ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም» እንዳልሆነ ለመረዳት አልቻሉም ነበር። በእነዚህ የመግቢያ ቁጥሮች ላይ የተጠቀሰው የጳውሎስ አመለካከት ባላንጣዎቹን ትጥቅ ያስፈታቸዋል። (እንዲያውም ጳውሎስ ማለት «ትንሽ» ማለት ስለ ሆነ፥ በዚህ ስፍራ ስሙን መጥቀሱም አስፈላጊ ነበር።) ጳውሎስ ደካማ ከነበር፥ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ ነበር፤ ኢየሱስ ትሁትና ገር ነበርና (ማቴ. 11፡29)። ይሁንና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ፥ ጌታችንም ብርቱና ብሎም ተቆጪ ነበር (ማቴ. 15፡1-2፤ 23፡13-33፤ ማር. 11፡15-17፤ ዮሐ 2፡13-16 ተመልከት።) ጳውሎስ ፍቅር በተመላው መንገድ፥ «እባካችሁ መጥቼ እንዴት ደፋር ልሆን እንደምችል እንዳሳያችሁ አታስገድዱኝ!» በማለት እያስጠነቀቃቸው ነበር።
2. የሰጠው መልስ ደግሞ (2ኛ ቆሮ. 10፡3-6) መንፈሳዊ ውጊያ ምን እንደ ሆነ ይገልጻል። የቆሮንቶስ ሰዎች (በሐሰት መምህራን ተመርተው) በጳውሎስ አገልግሎት ላይ በውዊው ሁኔታው ስለ ፈረዱበት፥ ከውስጡ የነበረውን ኃይል አጥተው ነበር። ነገሮችን «ከሥጋ» አንጻር (ቁ2) እንጂ፥ ከመንፈስ አንጻር አልገመገሙም ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች፥ ዛሬ እንደምናያቸው «አንዳንድ ታላላቅ የሃይማኖት ሰዎች»፥ በመግዛት ብቃታቸው፥ በርቱዕ አንደበታቸውና ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚያገኛቸው «ሙገሳዎች» ያስደንቁዋቸው ነበር።
ጳውሎስ ምንም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ቢሆንም የተደገፈው በመለኮታዊና ከጌታ ዘንድ በሚመጡ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች እንጂ በሰብዓዊ ነገሮች ላይ ባለመሆኑየተለየ ፈለግ ተከትሏል። ከሥጋና ከደም ጋር ስለማይዋጋ፥ ውጊያው እንደ ሥጋ ፈቃድ አልነበረም (ኤፌ. 6 ከቁጥር 10 ጀምሮ ተመልከት)። ማንም ቢሆን መንፈሳዊ ውጊያዎችን በሥጋዊ የጦር ዕቃዎች ሊዋጋ አይችልም።
በቁጥር 4 ላይ የተጠቀሰው ጦር «ጦርነት» ወይም «ዘመቻ» ማለት ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ አነስተኛ ጦርነት እየተጋፈጠ አልነበረም፤ በዚያ የነበረው የጠላት ጥቃት ከፍተኛ የሆነ ሰይጣናዊ ዘመቻ አካል ነበር። አሁንም ቢሆን የገሃነም ኃይላት የእግዚአብሔርን ሥራ ለማኮላሸት እየተጣጣሩ ስለ ሆነ (ማቴ. 16፡ 18)፥ ለጠላት ምንም ዓይነት ስፍራ አለመስጠታችን አስፈላጊው ነገር ነው፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንኳ መልቀቅ የለብንም!
በሰዎች አእምሮ የተቃወሞ ግድግዳዎች የሚገኙ በመሆኑ፥ (እንደ ኢያሪኮ ግንብ) እነዚህ ግድግዳዎች መናድ አለባቸው። ለመሆኑ «የአእምሮ ግድግዳዎች» የተባሉት ምንድን ናቸው? ግድግዳዎቹ፥ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ጋር የሚቃረኑ ፍልስፋናዎችና ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው በእውቀት መታበይ ናቸው። ጳውሎስ የሚቃወመው እውቀትን ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ሰዎችን ከሚያውቁት በላይ እንደሚያውቁ አድርገው እንዲያስቡ የሚገፋፋቸውን የምሁርነት ወይም የሊቅነት አመለካከት ነው (ሮሜ 12፡16)። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚመሠርትበት ጊዜ ይህንን «የሰዎች ጥበብ» የተጋፈጠ ሲሆን (1ኛ ቆሮ. 1፡ ከቁ. 18 ጀምሮ)፥ አሁን ደግሞ በአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች መምጣት የተነሣ ትግሉ እንደ ገና ሲጧጧፍ እናያለን።
ትዕቢት በሰይጣን እጅ እንደሚጥል ለተረዳው ጳውሎስ ከከፍተኛ የውጊያ መሣሪያዎቹ ውስጥ አንዱ ትህትና ነበር። ትሁቱ የእግዚአብሔር ልጅ ከጲላጦስ እጅግ የበለጠ ኃይል ነበረው (ዮሐ 19፡11 ተመልከት)፤ ይህንኑም ደግሞ አረጋግጧል። ጳውሎስ ተቃውሞውን ለመጣል መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ተጠቅሞአል፡- ጸሎት፥ የእግዚአብሔር ቃል፥ ፍቅርና በሕይወቱ ውስጥ የሚሠራ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ናቸው። ጳውሎስ በራሱ ስብዕና፥ ወይም በችሎታዎቹ፥ ወይም በሐዋርያነቱ ሥልጣን ላይ አልተደገፈም ነበር። ይሁንና ማኅበረ-ምዕመናኑ አንድ ጊዜ ራሱን ለጌታ አስከ ሰጠ፥ ጳውሎስ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ አጥፊዎቹን ለመቅጣ ተዘጋጅቶ ነበር።
ዛሬ በርካታ አማኞች ቤተ ክርስቲያን በጦርነት ፍልሚያ ላይ እንዳለች አይገነዘቡም፤ የክርስትናን ጦርነት አደገኛነት የሚረዱትም ቢሆኑ፥ ብዙውን ጊዜ እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው አያውቁም። አጋንንታዊ ኃይላትን ለመርታት ሰብዓዊ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፤ እነዚህም ዘዴዎች ለውድቀት ይዳርጉዋቸዋል። ኢያሱና ሠራዊቱ የኢያሪኮን ግንብ ለሰባት ቀናት በዞሩበት ጊዜ፥ የኢያሪኮ ከተማ ታዛቢዎች አብደዋል የሚል አሳብ ነበራቸው። ይሁንና አይሁዶች በእግዚአብሔር ተማምነው ትዕዛዛቱን በመፈጸማቸው፥ ከፍ ያሉትን ቅጥሮች አፍርሰው፥ ጠላትን ድል ነሥተዋል (ኢያሱ 6፡1-20)።
በሺካጎ ከተማ በመጋቢነት ሳገለግል ሳለሁ፥ በየሳምንቱ ከሦስት መጋቢ ወዳጆቼ ጋር እየተገናኘን «በጸሎት ጦርነት» እንተባበር ነበር። ሰዎችን ለእግዚአብሔር ከመሰጠት የሚከላከላቸውን የተሳሳተ አሳብ ለማስወገድ የሚያስችለውን የተስፋ ቃል በማሰብ ደጋግመን ጸለይን፤ እግዚአብሔርም በማለድንላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን አደረገ። በአእምሮ ውስጥ የሚገኙ ግድግዳዎች ከፈራረሱ፥ ወደ ልብ የሚያደርሰው መንገድ ሊከፈት ይችላል።
በመንፈሳዊ ሥልጣን ስለ መጠቀም (2ኛ ቆሮ. 10፡7-11)
የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊማሩት ከሚገባቸው እጅግ አስቸጋሪ ትምህርቶች አንዱ፥ ምድራዊ ሥልጣንና ሹመት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ምንም ስፍራ እንደሌላቸው ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ላይ «ጌቶች» ተብለው ሊጠሩና ተፈላጊነታቸውን ሊያጋንኑ እንደማይገባቸውና የአሕዛብ ገዢዎችን ፈለግ በመከተል የመሪነት ተግባራቸውን በፈላጭ ቆራጭነት እንዳያከናውኑ አስጠንቅቆአቸዋል (ማር. 10፡35-45 ተመልከት)። ለእኛ ልንከተለው የሚገባን እንደ ባሪያ ሆኖ የመጣውንና ሌሉችን ያገለገለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነት ነው። ጳውሎስ ያንን ምሳሌነት ተከትሏል።
ዳሩ ግን የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ ያደርግ የነበረውን ነገር ለመመርመር በቂ መንፈሳዊ መረዳት አልነበራቸውም። የእርሱን ትህትና ከአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች «የባሕርይ ጥንካሬ» ጋር በማነጻጸር፥ ጳውሎስ ሥልጣን እንደሌለው አድርገው ደመደሙ። በመሆኑም ሥልጣኑን ለማረጋገጥ ኃይለኛ ደብዳቤ ጽፏል ፥ ዳሩ ግን ሥጋዊ ሁኔታው ደካማ ከመሆኑም ሌላ ንግግሩም «የሚማረክ» አልነበረም። እነርሱም ከውጫዊ ገጽታ አኳያ እየፈረዱ እንጂ፥ መንፈሳዊ የመለየት ተግባር እያከናወኑ አልነበሩም።
አንድ ጊዜ ከጥቂት ወዳጆቼ ጋር ሆነን፥ አንድ ሰው በማራኪ «ታላላቅ ቃላት» የተሞላ፥ ባብዛኛው (ከዓውደ መልእክቱ ባፈነገጡ) በጥራዝ ነጠቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተደገፈና በዓለም ላይ ስለሚከሰቱ ነገሮች በሚገልጹ በርካታ ማጣቀሻዎችና «በዘመኑ ምልክቶች» ሙሉ በሙሉ የተጣበበ ስብከት ሲያቀርብ አድምጠናል። ከጉባዔው ወጥተን ስንሄድ ሳለ አንድኛው ወዳጃችን፥ «የዛሬው ስብከት በእርግጥም (እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም) የሚለውን የ1ኛ ነገሥት 19፡11 ምንባብ በደንብ ይገልጸዋል» አለን። ይሁንና ካጠገባችን የነበሩ ሰዎች እስካሁን ከሰሙዋቸው ስብከቶች ሁሉ እንደሚልቅ «አስደናቂ ስብከት» አድርገው ይናገሩ ነበር። በበኩሌ እነዚያ ሰዎች ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ከሰባኪው መልእክት ውስጥ አንዲት ተጨባጭ ነገር ማስታወሳቸውን እጠራጠራለሁ።
ጳውሎስ ሥልጣን እንደ ነበረው አልካደም፤ ዳሩ ግን ያንኑ ሥልጣን መንፈሳዊነት በጎደለው መንገድ ሊጠቀምበት አልፈለገም ነበር። የሥልጣኑም ዓላማ እነርሱን ለማፈራረስ ሳይሆን፥ ለማነጽ ነበር፤ ማነጽ ደግሞ ማፍረስ ከሚጠይቀው እጅግ የላቀ ጥበብ ይጠይቃል። ማነጽ በተለይም ፍቅርን ይጠይቃል (1ኛ ቆሮ. 8፡1)፤ ይሁንና የቆሮንቶስ ሰዎች የጳውሎስን ፍቅርና ገርነት የደካማነት ምልክት አድርገው ወሰዱት።
በጳውሎስና በአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች መካከል የነበረው ዋናው ልዩነት፥ ጳውሎስ ሥልጣኑን ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ የተጠቀመበት ሲሆን፥ እነርሱ ግን ቤተ ክርስቲያን ሥልጣናቸውን እንድታንጽላቸው መጠቀሚያ በማድረጋቸው ነው።
የቤተ ክርስቲያናት መጋቢ በመሆንና ከስፍራ ወደ ስፍራ በመንቀሳቀስ ባገለገልሁባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ፥ አንዳንድ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መጋቢዎቻቸውን በሚያስተናግዱበት ሁኔታ ተደንቄአለሁ። አንድ ሰው ፍቅርና እውነተኛ ትህትና ካሳየ፥ መሪነቱን በመቃወም ልቡን ያደማሉ። ሌላው ሰው «ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚቆጣጠር» «አምባገነን» ይሆንና የሚፈልገውን ሁሉ ያገኛል። ሰዎችም ይወዱታል – ዝናውንም ያወሩለታል። ሆኖም ግን ጌታችንም የተስተናገደው በዚህ መንገድ በመሆኑ፥ በዚሁ ነገር ልንደነቅ አይገባም።
ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ ቢሆን ኖሮ፥ ሥልጣኑን በትክክል ባስመሰከረም ነበር በማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቃውሞ ያስነሡበት ሰዎች በሐሰተኛነት ከሰውት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ በእርግጥም በሥልጣኑ ቢጠቀም ኖሮ አላግባብ ጨቁኖናል በማለት በወነጀሉት ነበር። ጳውሎስ የትኛውንም እርምጃ ቢወስድ፥ ሊከሱት ተዘጋጅተው ነበር። የቤተ ክርስቲያን አባላት መንፈሳዊ መረዳት ሲጎድላቸውና አገልግሉትን በዓለማዊ አመለካከት ሲገመግሙ፥ ሁልጊዜም ቢሆን የሚፈጸመው ይኸው ነው።
ይሁንና ክሳቸው በእነርሱ ላይ ተመልሶ የሚፈርድ ነበር። እንደ እነርሱ አባባል ጳውሎስ ሐዋርያ ባይሆን፥ በአስመሳይነት ተመላልሶአልና ተራ አማኝ እንኳ ሊሆን አልቻለም። ዳሩ ግን የጳውሎስ ሐዋርያነት እውነት ከሆነ፡ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም ማለት ነው። ጳውሎስ ቀደም ብሎ ማንም ሰው አገልግሎቱንና የግል ሕይወቱን ሊነጣጥል እንደማይችል ገልጾአል (2ኛቆሮ.1፡12-14)። እርሱ አታላይ ከነበር፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ተታለው ነበር ማለት ነው።
ጳውሎስ በተጨማሪም፥ በስብከቱና በጻፈው መልእክት መካከል ልዩነት እንዳልነበረ ገልጾአል። የጊዜውን ሁኔታ በማጤን፥ ጳውሎስ ሰደብዳቤዎቹ ውስጥ ጠንከር ያለ መልእክት አስተላልፎአል። በገርነት ለመጻፍ ቢቻል ኖሮ ምንኛ በይበልጥ ደስ ባለው ነበር። ይኼ ግን የተፈለገውን ዓላማ ከዳር ለማድረስ አያስችለውም ነበር። በመሆኑም፥ «ከባድና ኃይለኛ» ደብዳቤዎችን ቢጽፍም፥ ዳሩ ግን ከአፍቃሪ ልብ የመነጨ ነበር። «አስፈላጊ ከሆነ፥ እንዴት ኃይለኛ ልሆን እንደምችል አሳያችኋለሁና ለቀጣዩ ጉብኝቴ ብትዘጋጁ ይሻላል» እያላቸው ነበር።
ክርስቲያን ሥልጣንን የሚጠቀምበት ሁኔታ መንፈሳዊ ብስለቱንና ባሕርዩን ያመለክታል። ያልበሰለ ሰው በሥልጣኑ በሚጠቀምበት ጊዜ በኩራት ያብጣል፤ ዳሩ ግን በሳሉ ሰው በሥልጣን በመጠቀሙ ሂደት ውስጥ ያድጋል – ሌሎችም ከእርሱ ጋር ያድጋሉ። እንደ ጥበበኛ ወላጅ ሁሉ፥ ጥበበኛ መጋቢ መቼ ትዕግሥት በሞላበት ፍቅር በዝምታ እንደሚጠብቅና መቼስ በተወሰነ ኃይል ተግባሩን እንደሚያከናውን ያውቃል። ተቻኩሎ ከማጥቃት ይልቅ ትዕግሥትን ተላብሶ መጠበቅ የበለጠ ኃይል ያስፈልገዋል። በሳል ሰው ሥልጣንን የሚጠቀመው አክብሮትን ለማትረፍ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን አክብሮቱ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ በማዋል ነው። በሳል መሪዎች እርምጃ ለመውሰድ ሲጠባበቁ ይሰቃያሉ፤ ያልበሰሉ መሪዎች ደግሞ ባለማስተዋል ቅጽበታዊ እርምጃ ይወስዱና ሌሉችን ለሥቃይ ይዳርጋሉ።
ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሥልጣን ለመጨበጥ «በድጋፍ ደብዳቤ» ላይ ቢመጡም፥ ጳውሎስ ግን ከሰማይ የሆነ መለኮታዊ ተልዕኮ ነበረው። የእግዚአብሔር እጅ በሕይወቱ ላይ እንደ ነበረች እሙን በመሆኑ፥ ጳውሎስ የኖረው ሕይወትና የፈጸመው ተግባር ራሱ በቂ ማረጋገጫ ነበር። ጳውሎስ ቀጣዩን ዓረፍተ ነገር ለመጻፍ የሚያስችል ድፍረት ነበረው፡- «በሰውነቴ ላይ ያለው የግርፋት ምልክት የኢየሱስ አገልጋይ መሆኔን ስለሚያመለክት ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ» (ገላ 6፡17 አዲስ ትርጉም)።
እኔና ባለቤቴ በእንግሊዝ አገር ባገለገልንበት ጊዜ፥ ሁልጊዜም ለንደንን ለመጎብኘት በሚያስችል መልኩ ፕሮግራማችንን እናዘጋጅ ነበር። በተለይ በለንደን ውስጥ ከታወቁት ሁለት መደብሮች ማለትም ከሴልፍሪጅ እና ከሃሮድ ዕቃዎችን መግዛት ያስደስተን ነበር። ስማቸው የተጻፈበትን ታላቅ መደብር የገነቡት ኤች ጎርደን ሴልፍሪጅ፡ ድርጅቱን ለስኬታማነት ያበቁት መሪ እንጂ «አለቃ» ባለመሆናቸው መሆኑን አዘውትረው ይናገሩ ነበር። መሪው «እንሂድ!» ይላል። አለቃው ግን «ሂድ!» ይላል። አለቃው እንዴት እንደሚሠራ ያውቃል፤ ዳሩ ግን መሪው እንዴት እንደሚሠራ ያሳያል። አለቃ በጨፍሮቹ ላይ ፍርሃትን ያሳድራል፤ መሪው ግን በአክብሮትና በመልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ የሥራ ፍላጎትን ያሳድራል። አለቃ ለተበላሸው ነገር ጥፋትን በሌሎች ላይ ያላክካል፤ እውነተኛ መሪ ግን የተበላሸውን ነገር ይጠግናል። አለቃ «እኔ» ሲል፥ መሪ ግን «እኛ» ይላል። የሚስተር ሴልፍሪጅ የአስተዳደር ፍልስፍና፥ ከሐዋርያው ጳውሎስ የመሪነት ፍልስፍና ጋር በትክክል ይስማማል።
መንፈሳዊ አገልግሎትን ስለ መለካት (2ኛ ቆሮ. 10፡12-18) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከማንኛውም እንቅስቃሴ በላይ «አገልግሎትን መለካት» በርካታ ችግሮችን እንዳስከተለ አስባለሁ። የቤተ ክርስቲያን ሥራ የእግዚአብሔር ከሆነና የእግዚአብሔርም ሥራ ተአምር ከሆነ፥ እንዴት አድርገን ተአምርን እንለካለን? ጌታችን ኢየሱስ በራእይ ምዕራፍ 2-3 ውስጥ የተጠቀሱትን አብያተ ክርስቲያናት ሲገመግም፥ እነርሱ ራሳቸውን ከለኩበት ሚዛን እጅግ ልዩ በሆነ መስፈርት ተጠቅሟል። ድሀ ነኝ ስትል የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን፥ ሀብታም ነሽ አላት በሀታምነቷ የምትመካውና ደግሞ ድሀ (2፡8-11፤ 3፡14-22)።
አንዳንድ ሰዎች አገልግሉትን በአኀዛዊ ስሌቶች ብቻ ይለካሉ። የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አኀዛዊ ዘገባዎችን መጠቀሟ እውነት ቢሆንም (የሐዋ. 2፡41፤ 4፡4)፥ በዚያን ጊዘ ከቤተ ክርስቲያን ጋር መተባበር ይበልጥ አስቸጋሪ (አደገኛ) መሆኑም እውነት ነው (የሐዋ. 5፡13 ተመልከት)። ከጥቂት ዓመታት በፊት፥ ከአሜሪካ ታላላቅ የእምነት ክፍሎች አንዱ፥ «በ64 ዓ.ም. ከሚሊዮን የሚልቁ ነፍሳችን አባላታችን እንጻርጋለን። እያንዳንዱም አሥራቱን ይከፍላል» የሚል መፈክር ነበረው። ከዋንኛ ሰባኪዎቻቸውም አንዱ፥ «አሁንም የምናገኛቸው ሚሊዮን ሰዎች ከዚህ በፊት እንዳገኘናቸው ሚሊዮን ሰዎች ዓይነት ከሆኑ እግዚአብሔር ይርዳን!» የሚል አስተያየት ሲሰነዝር ሰማሁ። ብዛት ለጥራት ዋስትና አይሆንም።
1. የሐሰት መስፈሪያ (2ኛ ቆሮ. 10፡12)። ከውስጣዊ ለውጥ ይልቅ ውጫዊ እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት ሃይማኖት ለመለካት እጅግ ስለሚቀል፥ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች አገልግሎታቸውን በመለካቱ ረገድ ብርቱዎች ነበሩ። ሕግ አጥባቂው የሚያደርገውንና የማያደርገውን ሊለካ ይችላል፤ ዳሩ ግን በአማኝ ልብ ያለውን መንፈሳዊ እድገት ሊመለከተው የሚችለው ጌታ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዘ ከፍተኛ ዕድገት ያስገኙ አገልጋዮች ራሳቸውን እጅግ ከሚያንሱትም እንዳነሱ አድርገው ይቆጥራሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፡ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች፥ መመዘኛዎቹን አውጥቶ በዚያው አንጻር ነገሮችን የሚለካ «የእርስ በርስ መሞካሻ ማኅበር» አባላት ነበሩ ለማለት ይቻላል። በመሆኑም የዚህ ቡድን አባላት የተሳካላቸው ተደርገው ሲቆጠሩ፥ ከዚያ ውጭ የሚገኙት ግን ተስፋ ቢሶች ተደርገው ይወሰዱ ነበር። ጳውሎስም ከዚህ ቡድን ውጭ ነበረና እንደ ውደቂ ተቆጠረ። የሚያሳዝነው ግን እነዚህ አጉል ተመፃዳቂዎች ራሳቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ አይለኩም ነበር (ኤፌ 4፡12-16 ተመልከት)። እንዲህማ ቢያደርጉ ኖሮ፥ ስህተታቸው ጎልቶ በታያቸውም ነበር።
2. እውነተኛ መለኪያ (2ኛ ቆሮ. 10፡13-18)። ጳውሎስ አገልግሉታችንን በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመለካት ስንሻ፥ ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባንን ሦስት ጥያቄዎች ያቀርባል።
እግዚአብሔር በሚፈልገኝ ስፍራ ነው ያለሁት? (ቁ 13-14) እግዚአብሔር ጳውሉ የሚሠራበትን «ዳርቻ ወሰነ»:- እርሱ የአሕዛብ ሐዋርያ ነበር (የሐዋ. 9፡15፤ 22፡21፤ ኤፌ 3)። ከዚህ በፊት ሌላ ሐዋርያ ወዳላገለገለበት ስፍራ ተላከ።
ጳውሎስ በመከላከያው ጽሑፍ ውስጥ አነስተኛ በሆነ «የተቀደሰ ምፀት» ይጠቀማል። «እግዚአብሔር የወሰነልኝ ዳርቻ እናንተን የቆሮንቶስ ሰዎች ጭምር ያካልላል» (2ኛ ቆሮ. 10፡13 ተመልከት)። ወደ ቆሮንቶስ ወንጌልን ያዳረሱት የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች አልነበሩም። ዛሬ እንደሚታዩ መናፍቃን ሁሉ፥ እነርሱም ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች በኋላ ብቅ ብቅ ያሉ ነበሩ (ሮሜ 15፡15-22 ተመልከት)።
አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች ከራሳቸው ጋር እንጂ፥ እርስ በርስ እየተወዳደሩ አይደሉም። እግዚአብሔር ለቻርልስ እስፐርጀን ወይም ለቢሊ ሳንዳይ በሰጣቸው ስጦታዎችና ዕድሉች አንፃር አይለካንም። የእኔን ሥራ የሚለካው ለእኔ ከወሰነው የሥራ ድርሻ አኳያ ነው። እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ ታማኝነትን ይሻል (1ኛ ቆሮ. 4፡2)።
የመጋቢያንን ጉባዔ ወይም የአንድን የእምነት ክፍል ስብሰባ ለመካፈል የሚያስፈራ አንድ ነገር አለ፤ ለዚህም ምክንያቱ በፕሮግራሙ ላይ የሚካፈሉት ሰዎች ከሁሉም የላቁ ውጤቶችን ያስመዘገቡ ታላላቅ ሰዎች በመሆናቸው ነው። ወጣት መጋቢያንና በዝቅተኛ የሥራ መደብ ላይ የሚያገለግሉ ሰዎች፥ በታማኝነት የሚያከናውኑት አገልግሎት የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች ያህል ፍሬ የሚያፈራ ስለማይመስላቸው፥ በየዕለቱ በጥፋተኝነት ስሜት ተሸብበው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ከእነዚህ ተስፋ ከቆረጡት ሰዎች ጥቂቶቹ ፍሬያማ ለመሆን ሲሉ ባገኙት ዓይነት ፕሮግራምና ዘዴዎች ለመጠቀም ይሞክራሉ፤ ውጤቱ ግን የላቀ ኃዘኔታ ይሆናል። ከዚያም በመቀጠል አገልግሎቱን ለመልቀቅ ያስባሉ። ዳሩ ግን እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን የሚለካው በያዙት የሥራ መደብ እንጂ፥ በሌላ የሥራ ክልል አንጻር እንዳልሆነ ቢረዱ፥ በሥራቸው ላይ ለመቆየትና በታማኝነት አገልግሎታቸውን ለመቀጠል መጽናናትን ያገኛሉ።
እግዚአብሔር በአገልግሎቴ ከብሯልን? (2ኛ ቆሮ.10፡15-17)። ይህ ጥያቄ በሌሎች ሰዎች አገልግሎት የዳኑትን ሰዎች ሰርቀው ከወሰዱ በኋላ፥ የራሳቸው ደቀ መዛሙርት እንደ ሆኑ አድርገው ለሚመኩ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የሚቆጠቁጥ ነቀፋ ነው። ጳውሎስ በሌላው ሰው ሥራ አይመካም፤ ወደ ሌላው ሰው ግዛትም ክስ አይገባም። ምንም ዓይነት ሥራ ቢሠራ፥ በእርሱ አማካኝነት የሠራው እግዚአብሔር ነው – ክብሩንም ሊወስድ የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
አንድ ጊዜ አንድ ሰው እንዴት ትልቅ የሰንበት ትምህርት ቤት መሥራት እንደሚቻል ሲያስተምር ሰምቼ ነበር። በትምህርቱ ውስጥ የሚገኘው አሳብ ሁሉ ትክክል ሲሆን፥ በተለይ በዩናይትድ እስቴትስ ውስጥ በሚገኙ በአንዳንድ ታላላቅ አገልግሎቶች አማካይነት በጥሩ ሁኔታ ከሥራ ላይ ውሏል። አንድ የሚያሳዝን ነገር ግን ሰውየው ራሱ ትልቅ የሰንበት ትምህርት ቤት ከዚህ በፊት ሠርቶ አለማወቁ ነበር። ትምህርቱን ለማበልጸግ ሲል ብዙዎቹ ታላላቅ የአገልግሎት ማዕከሉችን ጎብኝቷል፤ መጋቢዎችንና የሥራ ባልደረቦቻቸውን አነጋግሯል፤ በአጭሩ ትምህርቱ ሁሉ የተገኘው ከዚያ ነበር ለማለት ይቻላል። ታዲያ የዚያን ዕለቱን ሰበካውን ከፈጸመ በኋላ፥ ሰዎች ጥያቄ ለመጠየቅና ፊርማውን ለመቀበል ከበውት ነበር። እኔም በዚያን ጊዜ እንደ አጋጣሚ በአሜሪካ እጅግ ውብና ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ከሠራ አንድ መጋቢ አጠገብ ቆሜ ነበርና፥
«እነዚህ ሰዎች ካንተ ጋር ቢነጋገሩ ይሻላቸው ነበር» አልሁት፤ «ምክንያቱም የሰንበት ትምህርት ቤት አሠርተህ ስላየኸው፥ ከእርሱ ይልቅ የተሻለ ዕውቀት አለህ ብዩ ስለምገምት ነው» ስል አከልሁበት።
መጋቢውም ፈገግ ብሉ፥ «ተወው፤ እባክህ ይደሰት!» አለና በመቀጠልም «ሁላችንም አንድን ሥራ እንሠራለን፤ ቁም-ነገሩ ግን የእግዚአብሔር መክበር ነው» በማለት አጫወተኝ።
ጳውሎስ «ከዚያ አልፎ ወደሚገኙ ስፍራዎችእንዳይሄድ እንቅፋት የሆነው ብቸኛው ነገር የእነርሱ አለማመን እንደ ሆነ ሲናገር፥ አሁንም በሌላ መጠነኛ «የተቀደሰ ምፀት» እየተጠቀመ ነበር። ለመሪነቱ ቢገዙና ለቃሉ ቢታዘዙ ኖሮ፥ ሌሉችን ከደኅንነት የራቁ ነፍሳት ቀደም ሲል በወንጌል ለመድረስ ይችል ነበር፤ ዳሩ ግን በርካታ ችግሮች ስለ ፈጠሩበት፥ የቤተ ክርስቲያኗን የውስጥ ችግሮች ለመቅረፍ ሲል፥ የሚሲዮናዊነት አገልግሉቱን ጊዜ ማባከን ነበረበት። «የማቀርባቸው በርካታ አኀዛዊ ቀመሮች (ነፍሳት) ነበሩኝ – ዳሩ ግን እናንተው አግዳችሁኛል» እያለ ነበር።
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1፡31 ላይ የጠቀሰውን ኤርምያስ 9፡24 በቁጥር 17 ላይ በድጋሚ ይጠቅሳል። የቆሮንቶስ ሰዎች፥ በተለይም አሁን የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስላንተንሰራፉ፥ ሰዎችን ወደማክበር ያዘነብሉ ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች እነዚህ መምህራን ያደረጉዋቸውን ነገሮች የሚያስረዱ «ዘገባዎችን» ሲሰሙና የያዙዋቸውንም «የድጋፍ ደብዳቤዎች» ሲመለከቱ፥ ሙሉ ለሙሉ ተማረኩ። ከዚህም የተነሣ፥ ጳውሎስም ሆነ አገልግሎቱ እንደ ተናቀ ነገር ይቆጠር ጀምር።
ይሁንና የፍጻሜው ፈተና ውጤት የሚገለጸው ለዓመታዊ ስብሰባዎች ዘገባዎች ተዘጋጅተው በሚቀርቡበት ጊዜ አይደለም። የፍጻሜው ፈተና ውጤት የሚታወቀው በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ነው . «በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል» (1ኛ ቆሮ. 4፡5)። ሰዎች ክብሩን የሚወስዱ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ክብርን ሊቀበል አይችልም። «እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም» (ኢሳ. 42፡8)።
እንዲህም ሲባል ስኬታማ ተግባር የሚያከናውኑ እጅግ የታወቁ አገልጋዮች የእግዚአብሔርን ክብር እየወሰዱ ናቸው ማለት አይደለም። እያደግንና «ብዙ ፍሬ» እያፈራን ስንሄድ፥ አብን እናስከብራለን (ዮሐ 15፡1-8)። ይሁንና ይህ ከመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሚመነጭ «ፍሬ» እንጂ፥ በሰዎች ግፊትና በተጋነኑ አኀዛዊ ዘገባዎች ቀመር «ውጤት» እንዳለሆን መገንዘብ አለብን።
ጌታ ሥራዩን ሊያመሰግነው ይችላል? (2ኛ ቆሮ. 10፡18)። ራሳችንን የምናመሰግን ወይም ሌሎች ሰዎች የሚያመሰግኑን ልንሆን እንችላለን። የሚያሳዝነው ግን የእግዚአብሔር ምስጋና የማይገባን ሰዎች ልንሆን መቻላችን ነው። እግዚአብሔር የሥራችንን መልካምነት የሚያጸድቀው እንዴት ነው? በመፈተን ነው! በቁጥር 18 ላይ የተፈተነ የሚለው ቃል፥ «በመፈተን ማረጋገጥ» ማለት ነው። ወደ ፊት በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት የሚደረግ ፈተና አለ (1ኛቆሮ.3 ከቁጥር 10 ጀምሮ)፤ ጻሩ ግን አሁንም የምንሠራው ሥራ ይፈተናል። እግዚአብሔር ሥራቸው እንዲፈተንና እውነተኛነቱም እንዲረጋገጥ ሲል፥ ችግሮች ወደ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እንዲመጡ ይፈቅዳል።
ለብዙ ዓመታት ያህል እንዳጤንኩት፥ ክርስቲያናዊ አገልግሎቶች በመዋዕለ-ንዋይ እጦት፥ በሐሰት ትምህርት ጣልቃ-ገብነት፥ «ቤተ ክርስቲያንን ለመቆጣጠር» በሚፈልጉ ኩራተኛ መሪዎችና በአጓጉል የለውጥ ጥያቄ ሲፈተኑ ተመልክቻለሁ። ሥራቸው መንፈሳዊነት ከማጣቱ የተነሣ፥ ወድቀው ወደ መክሰም የተቃረቡ አብያተ ክርስቲያናትም ነበሩ። ሌሉች አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ከመከራዎቹ የተነሣ አድገው ተጠናክረዋል – በዚህም ሁሉ እግዚአብሔር ከብሯል።
በመሠረቱ የአገልግሎታችንን መረጃዎች ልንጠብቅና ዘገባዎችን ልንሰጥ ይገባል፤ ዳሩ ግን «በአኀዛዊ መረጃዎች ወጥመድ» ልንጠመድና አገልግሎት የሚለካው በአኀዞች ብቻ ነው ወደሚለው መደምደሚያ ልንደርስ አይገባም። እንደ እውነቱ እያንዳንዱን አብያተ ክርስቲያን የሚገጥመው ሁኔታ የተለያየ ሊሆን ስለሚችል፥ የአንዱን አገልግሎት በሌላው አገልግሎት መሠረት ለመገምገም አይቻልም። ቁም-ነገሩ፥ እግዚአብሔር ሰሚፈልገን ስፍራ መገኘታችንና እርሱ በሕይወታችን እንዲከብር፥ እናደርገው ዘንድ የሚፈልገውን ማድረጋችን ነው። መንስዔ የሆነን ምክንያት (ዓላማ) ልክ እንደምናስገኘው እድገት ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ለሥራችን መለኪያ በመሆን ያገለግላል። እግዚአብሔርን ብቻ ለማስከበር የምንሻ ከሆነና እርሱም በልባችንና በሕይወታችን ውስጥ የሚካሄደውን ግምገማ ያለ ፍርሃት ከተቀበልን፥ የሰዎች ግምቶች ወይም ትችቶች ጭንቀት አያሳድሩብንም። «የሚመካ ግን በጌታ ይመካ (ቁ 17)።