የመስጠት ጸጋ – ክፍል 2፣ (2ኛ ቆሮንቶስ 9፡1-15)

እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር አብዝቶ ከሰጠን በኋላ፥ ለሌሎች ለመስጠት የሚገፋፋን ሌላ ሰው መፈለጋችን ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። እግዚአብሔር የቆሮንቶስን ሰዎች በድንቅ ሁኔታ ቢያበለጽጋቸውም፥ ዳሩ ግን ያላቸውን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ያመነቱ ነበር። በጸጋ መስጠትን አልተለማመዱም ነበርና ጳውሎስ ይህንኑ አሳብ ለእነርሱ ማብራራት ነበረበት። ጳውሎስ በጸጋ መስጠትን ከገለጸላቸው በኋላ፥ በልዩ መዋጮው ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሊያነሣሣቸው ይሞክራል። ይህንንም ያደረገው በጸጋ ከመስጠት ጋር የተያያዙትን አምስት ማበረታቻዎች (መጽናኛዎች) በማቅረብ ነው። 

ያንተ መስጠት ሌሎችንም ያነሣሣቸዋል (2ኛ ቆሮ. 9፡1-5) 

ክርስቲያኖች ለክርስቶስ በምናቀርበው አገልግሎት እርስ በርስ መወዳደር ባይኖርብንም፥ ጳውሎስ «ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ» (ዕብ 10፡24) እንዳለው ልንፈጽም ይገባል። እግዚአብሔር በሌሉች አማኞች ውስጥና በእነርሱም በኩል የሚሠራውን ነገር ስንመለከት፥ እኛም በበለጠ ለማገልገል መጣጣር አለብን። በሥጋዊ አድራጎት ኩረጃና በመንፈሳዊ ሕይወት ቅጂ መካከል እስከዚያ ልዩነት እንደሌለ ልንገነዘብና በዚህም በኩል ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። በመሆኑም ቀናተኛ ክርሲትያን ቤተ ክርስቲያንን ለማነቃቃትና ምዕመኑንም ለጸሉት፥ ለሥራ፥ ለምስክርነትና ለስጦታ ለማነሣሣት መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። 

የሚያስገርመው ነገር ግን የሚከተለው ነው፡- ጳውሎስ የመቄዶንያን አብያተ ክርስቲያናት ለማበረታታት በቆሮንቶስ ሰዎች ቅንዓት ተጠቅሞ ነበር፤ ግን አሁን ደግሞ የቆሮንቶስን ሰዎች ለማበ ረታታት በመቄዶንያ ሰዎች ይጠቀማል። ከአንድ ዓመት በፊት፥ የቆሮንቶስ ሰዎች በመዋጮው ውስጥ ተካፋይ እንደሚሆኑ በከፍተኛ ፍላጎት ገልጠውለት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ምንም አላደረጉም ነበር። የመቄዶንያ ሰዎች ደግሞ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተው ነበርና ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ሰዎች የተናገረው ትምክህት ከንቱ እንዳይሆንበት ሠጋ። 

ስለ ሆነም የቆሮንቶስ ሰዎች በመዋጮው አሰባሰብ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ያነቃቋቸው ዘንድ፥ ጳውሎስ ቲቶንና ሌሎች ወንድሞችን ወደ ቆሮንቶስ ላከ። ከገንዘቡ ይልቅ እጅግ የሚልቀው፥ በሕይወታቸው ውስጥ ላለው የእግዚአብሔር ጸጋ ምላሽ በመስጠት ያላቸውን በሚያካፍሉበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ የምታገኘው መንፈሳዊ በረከት ነበር። ጳውሎስ አስተዋጽኦውን ስለሚያሰባስቡበት ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስቀድሞ ስለ ጻፈ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-4)። ለመዘግየታቸው የሚያመካኙበት ነገር አልነበራቸውም። ጳውሎስ ባለቀ ሰዓት ላይ ተሰብስበው ችግር የሚፈጥሩ መዋጮዎች እንዳይኖሩ ሲል፥ እርሱና «የመዋዕለ-ንዋይ ኮሚቴው» በሚደርሱበት ጊዜ ሁሉም ነገር ተሰናድቶ እንዲጠብቀው ይፈልግ ነበር። 

ጳውሎስ ለማስወገድ የፈለገው ነገር ምን ነበር? የፈለገው መዋጮው ካልተሰናዳ በራሱና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ኀፍረት ለማስወገድ ነበር። በይበልጥም ኀፍረቱ ያሳሰበው ከመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተውክለው ከልዩ ኮሚቴው ጋር የሚሄዱ በርካታ ሰዎች በመኖራቸውም ጭምር ነበር (የሐዋ.20፡4 ተመልከት)። ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ሰዎች ለመቄዶናውያን ተናግሮ ስለ ነበር የነገራቸው ነገር ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር በእርግጥም ፍርሐት ገብቶት ነበር። 

ጳውሎስ ሰዎች ለመስጠት ቃል እንዲገቡ መጠየቅን፥ ስህተት ወይም መንፈሳዊነት የጎደለው ተግባር አድርጎ ያልተመለከተ ይመስላል። እያንዳንዳቸው ምን ያህል መስጠት እንደሚገባቸው አልተናገራቸውም፤ ዳሩ ግን የተስፋ ቃላቸውን መፈጸማቸውን ይጠብቅ ነበር። አንድ ሰው ለቤቱ ስልክ ሲያስገባ፥ በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ቃል ይገባል። እንደ ስልክ፥ መኪናና የዱቤ መውሰጃ መዝገብ ለመሳሰሉ ነገሮች ገንዘብ ለመስጠት ቃል መግባቱ ተቀባይነት ካለው፥ ለጌታም ሥራ ቃል የምንገባው ቅሬታ የሚያሳድርበት ምክንያት አይኖርም። 

ጳውሎስ ስለ መዋጮው ሲጽፍ ምን እንዳለ ተመልከት። ይህ «ለቅዱሳን የሚሆን አገልግሎት» ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ስጦታው «በረከት» (2ኛ ቆሮ. 9፡5) ማለትም «የልግስና ስጦታ» ነበር። ምናልባት ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ካቀዱት በላይ እንዲሰጡ እየገፋፋቸው ይሆን? 

ጳውሎስ ምንም ዓይነት ጫና ላለማሳደር ይጠነቀቅ ነበር። ጳውሎስ ስጦታቸው «እንደ በረከት (ልግስና) ሆኖ ከስስት (ከውጥረት) ነጻ» እንዲሆን ይፈልግ ነበር። ከፍተኛ ጫና የታከለባቸው የስጦታ ልመናዎች በጸጋ ከመስጠት ጎን ሊሰለፉ አይችሉም። 

ለመስጠት ከሁሉም በላይ የሚያበረታታን ነገር ስጦታችን ጌታን የሚያስደስት መሆኑ ነው፤ ይሁንና ሌሎችን ለመስጠት የሚያነሣሣ ዓይነት የስጦታ ልምምድ ማድረጉም ስህተት አይደለም። እንዲህም ስለ ተባለ በግል የምንሰጠውን ነገር እንደማስታወቂያ ለሁሉም ማወጅ አለብን ማለት አይደለም . ይኸውም የዚህ ዓይነቱ መስጠት ከመስጠት መሠረታዊ መመሪያዎች አንደኛውን ስለሚያፋልስ ነው (ማቴ. 6፡1-4)። ይሁንና ጳውሎስ የሚጽፈው ለአብያተ ክርስቲያናት ስለ ሆነ፥ ማኅበረ – ምዕመናን የሰጡትን ነገር ቢያሳውቁ ስህተት አይሆንም። ዓላማችን ያደረግነውን ለሌሎች በመግለጽ ለመመካት ከሆነ፥ በጸጋ የመስጠትን ልምምድ እያደረግን አይደለም። ዳሩ ግን መሻታችን ሌሎችም ያላቸውን እንዲያካፍሉ ለማነሣሣት ከሆን፥ የእግዚአብሔር ጸጋ ሌሎችን ለመርዳት በእኛ በኩል ሊሠራ ይችላል። 

ያንተ መስጠት ለራስህ በረከት ይሆናል (2ኛ ቆሮ. 9፡6-11) 

የጌታችን የተስፋ ቃል «ስጡ፤ ይሰጣችሁማል» የሚል ነበርና ይህ ቃል አሁንም በእውነትነቱ ጸንቶ ያለ ነው (ሉቃ. 6፡38)። መልሶ የሚሰጥበትም «መልካም መስፈሪያ» ሁልጊዜም ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ነገር የተመለከተ ባይሆንም፥ ዳሩ ግን ሁልጊዜም እኛ ከሰጠነው አብልጦ የሚልቅ ነው። መስጠት የእኛነታችን ማረጋገጥ እንጂ፥ እኛ የምናደርገው ነገር አይደለም። የእግዚአብሔርን ጸጋ ለሚገነዘብ ክርስቲያን፥ መስጠት የሕይወት ዘይቤ ነው። ዓለም እንደ ምሳሌ 11፡24 የመሳሰለውን አሳብ አትረዳም፡- «ያለውን የሚበትን ሰው አለ፤ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፤ ይደኸያልም።» በጸጋ በምንሰጥበት ጊዜ ዓላማችን «አንድን ነገር ማግኘት» አይደለም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን በረከት ማግኘት «እናገኛለን» ብለን የማናስበው ምርቃት ነው። 

መስጠታችን እንዲባርከንና እንዲያንጸን ከተፈለገ፥ ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ የገለጻቸውን መመሪያዎች ለመከተል ልንጠነቀቅ ይገባል። 1. የዕድገት መመሪያ – የምንዘራውን ያህል እናጭዳለን (2ኛ ቆሮ. 9፡6)። ይህ መመሪያ በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚንጸባረቅ ስለ ሆነ፥ በመጠኑ ማብራራት አስፈላጊ ነው። ብዙ ዘር የሚዘራ ገበሬ ብዙምርት ለመሰብሰብ የሰፋ ዕድል ይኖረዋል። በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ ያስቀመጠ ባለ ሀብት፥ ብዙ ወለድ ያገኛል። በጌታ ሥራ ውስጥም ብዙ ትርፋማ ተግባር ባከናወንን መጠን፥ በመዝገባችን ውስጥ የበለጠ «ፍሬ» ይገኛል (ፊል. 4፡10-20) 

ይህን መመሪያ ለመዘንጋት በምንፈተንበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር በስጦታው ቁጥብ እንዳለሆነ ልናስታውስ ይገባል። «ለገዛ ልጁ ያልራራለት፥ ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው፥ ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? » (ሮሜ 8፡32)። በተፈጥሮም ይሁን በጸጋ፥ እግዚአብሔር ለጋስ ሰጪ ነው፤ እንዲሁም ፈሪሃ-እግዚአብሔር የነገሠበትን ሕይወት ለመምራት የሚፈልግ ሰው መለኮታዊውን ምሳሌ መከተል አለበት። 

2. የመሻት መመሪያ – በትክክለኛ ልብ እንደ ዘራን እንዲሁ እናጭዳለን (2ኛ ቆሮ. 9፡7)። ለአንድ ገበሬ ግብርናውን ለማካሄያድ ልዩ የሆኑ አነሣሽ ምክንያቶች እምብዛም ፋይዳ አይኖራቸውም። ጥሩ የዘር እህል ካለውና በጥሩ ወቅት ላይ ከዘራ፥ ለትርፍም ይሁን ለብልጽግና፥ ወይም ለኩራት ቢሠራ፥ ዞሮ ዞሮ ፍሬ ማግኘቱ አይቀርም። ከምርቱ የሚያገኘውን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያቅድበትም ሁኔታ በምርቱ ላይ ልዩነት አይፈጥርም። እንደ ዘመኑ ሁኔታ ምድሪቱ ያፈራችለትን ሰብል ይሰበስባል። 

ዳሩ ግን ለክርስቲያን ነገሩ እንዲህ አይደለም – በመስጠት (ወይም በሌላ በማንኛውም እንቅስቃሴ) ውስጥ፥ አነግሱ ምክንያት «ዓላማው፥ መንስኤው) ወሳኝ ነው። የምንሰጠው ከልባችን መሆን አለበት፤ ከልባችን ውስጥ ያለው አነሣሽ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔርን ሊያስደስተው ይገባል። የልብ ፈቃደኛነት ሳይታከል «በኃዘኔታ እንደሚሰጡ» ወይም «በእብደት ያላቸውን እንደሚበትኑ» ሰዎች መሆን የለብንም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ጸጋ ስለ ተለማመድን፥ ያለንን በደስታ የምናካፍል «ደስተኛ ሰጪዎች» መሆን አለብን። እንዲህ ያለው «ርኅሩኅ የተባረከ ይሆናል» (ምሳ 22፡9)። 

በደስታ መስጠት አቀበት ከሆነብን፥ ልባችንን ወደ አምላካችን አንሥተን፥ ጸጋውን እንዲሰጠን መጠየቅ አለብን። በርግጥ እግዚአብሔር በኃላፊነት ስሜት የተሰጠውን ስጦታ ሊባርክ ይችላል፤ ዳሩ ግን ልቡ እስካልተስተካከለ ድረስ፥ ሰጪውን ሊባርክ አይችልም። በጸጋ መስጠት ማለት እግዚአብሔር ስጦታውንም ሰጪውንም ይባርከዋል ማለት ነው – ሰጪውም ለሌሎች በረከት ይሆናል። 

3. የፈጣን ውጤታማነት መመሪያ – እየዘራን ሳለ እንኳ ልናጭድ እንችላለን (2ኛ ቆሮ. 9፡8-11)። ገበሬ የመከሩን ጊዜ መጠባበቅ አለበት፤ ዳሩ ግን በጸጋ መስጠትን የሚለማመድ አማኝ ወዲያውኑ መከሩን መሰብሰብ ይጀምራል። ከስጦታችን የሚገኙ የረዥም ጊዜ ጥቅሞች ቢኖሩም፥ ዳሩ ግን ወዲያውኑ የሚከሰቱ በረከቶችም አሉ። 

አስቀድሞ እግዚአብሔር ከሚያበዛልን ጸጋው መካፈልን እንጀምራለን (ቁ 8-9)። በዚህ ጥቅስ መሠረቱ «ሁሉም» የቃሉ አጠቃቀም ሁላችንም ከምናስተውለው በላይ ነው፤ በጸጋ ሁሉ፥ ሁልጊዜ፥ ብቃትን ሁሉ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ ይላል። ይህም ማለት እግዚአብሔር ሁሉንም ክርስቲያን በቁሳዊ ነገሮች ያበለጽገዋል ማለት ሳይሆን፥ ዳሩ ግን በጸጋ መስጠትን የሚለማመድ ክርስቲያን ሁልጊዜም በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ የሚያስፈልገው ነገር ይኖረዋል ማለት ነው። በተጨማሪም፥ የእግዚአብሔር ጸጋ በግብረ-ገባዊና በመንፈሳዊ ሁኔታው ስለሚያበለጽገው፥ በክርስቲያናዊ ባሕርዩ ያድጋል። በአካሄዱና በሥራው ሁሉ፥ ሙሉ ለሙሉ በእግዚአብሔር ብቃት ላይ ይደገፋል። 

በዛሬው ጊዜ ምን ያህል ሰዎች ላመንፈሳዊ ጽናታቸው በሌሉች ሰዎች ላይ ሙሉ በሙሉ እንደሚደገፉ ማየት ከማስደነቅም የሚያሳዝን ነገር ነው። ሰባኪዎቹ የሚሰብኩትን ትምህርት ከመጽሐፍ ወይም ከካሴት እስካልተዋሱ ድረስ የሚያስተላልፉት ስብከት አይኖራቸውም። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ምክር ፍለጋ ለሁለት ወይም ለሦስት እውቅ ሰባኪዎች እስካልደወሉ ድረስ፥ ችግራቸውን እንዴት እንደሚፈቱት አያውቁም። እጅግ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባላት በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ ከመጋቢያቸው ምክር መጠየቅ ያስፈልጋቸዋል – አለበለዚያ ግን መንፈሳዊ ውድቀት ይደርስባቸዋል። 

ብቃት የሚለው ቃል «ከውስጥ የሚገኘውን በቂ ሀብት» የሚያመለክት ነው (ፊልጵ. 4፡11 ተመልከት)። በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት፥ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት የሚበቃ ሀብት አለን። ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን፥ እርስ በርሳችን መረዳዳትና መበረታታት አለብን፤ ዳሩ ግን አንዳችን በሌላችን ላይ መደገፍ (ጥገኛ መሆን) የለብንም። ጥገኛነታችን በጌታችን ላይ መሆን አለበት። ለሕይወት ብቁ የሚያደርገንን ያንን «የውኃ ምንጭ» ከልባችን ሊያመነጭ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው (ዮሐ 4፡14)። 

የእግዚአብሔር ጸጋ መጋራት ብቻ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ጽድቁንም ደግሞ እንካፈላለን (2ኛ ቆሮ. 9፡9)። ጳውሉላ አሳቡን ለማረጋገጥ መዝሙር (112)፡9ን ይጠቅሳል። መዝሙሩ ልቡ ለጌታ እውነተኛና ታዛዥ በመሆኑ ምክንያት ሥጋት ስለሌለበት ሰው ይናገራል። ጽድቅን የማግኛ ብቸኛው መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደ ሆኑ፥ ጳውሎስ በመስጠታችን ጽድቅን እናገኛለን አላለም። ይሁንና ልባችን ቅን ከሆነ፥ እግዚአብሔር ባሕርያችንን ለማቅናት በመስጠታችን ይጠቀማል። በጸጋ መስጠት ክርስቲያናዊ ባሕርይን ያንጻል። 

የምንዘራውን ያንኑ ስለምናጭድ፥ ለምንሰጠውና ለምናደርገው ነገር የእግዚአብሔርን የተአምራት ብዛት እንጋራለን (2ኛ ቆሮ.9፡10)። ገበሬው ምን ያህል ዘር ለምግብነት እንደሚያውልና ምን ያህሉን እንደሚዘራ መወሰን አለበት። ምርቱ ከቀነሰ፥ ለምግብነትም ሆነ ለቀጣዩ የአዝመራ ወቅት የሚኖረው እህል አናሳ ይሆናል። ዳሩ ግን በጸጋ በመስጠት የሚያምን ክርስቲያን፥ ስለዚህ ውሳኔ ከቶውንም መጨነቅ የለበትም – እግዚአብሔር የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሞላለታል። ሁልጊዜም ለምግብነት የሚውል መንፈሳዊና ቁሳዊ «እንጀራ» አለ፤ ሁልጊዜም ለመዝራት የሚያገለግል መንፈሳዊና ቁሳዊ «ዘር» አለ። 

ጳውሎስ በዚህ ስፍራ፥ የእግዚአብሔርን ቃልና የእርሻውን መስክ የመከር ፍሬ ለማመልከት «ዘር» እና «እንጀራ» የሚሉትን ቃላት የሚጠቀመውን የኢሳይያስ 55፡10-11 የምንባብ ክፍል ይጠቅሳል። በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ «ዓለማዊ» እና «የተቀደሰ» የሚባል ነገር የለም። ገንዘብን መስጠት፥ መዝሙር የመዘመርን ወይም የወንጌል ስርጭት በራሪ ወረቀት (ትራክት) የማከፋፈልን ያህል የሚቆጠር መንፈሳዊ ተግባር ነው። ገንዘብ ዘር በመሆኑ፥ በጸጋ መመሪያዎች አንጻር እስከ ሰጠነው ድረስ፥ ለእግዚአብሔር ክብርን ሊያበረክትና ብዙ ጉድለቶችን ሊሞላ ይችላል። ከዚህ ዓላማው ውጪ ከተጠቀምንበት ግን የዘራነው አዝመራ ፍሬ-አልባ ይሆናል። 

በመጨረሻም፥ ስንዘራ ለራሳችን እንበለጽጋለን፤ ሌሎችንም እናበለጽጋለን (2ኛ ቆሮ. 9፡11)። ገበሬው በእርሻ ቦታው ላይ ሲሠራ፥ ወዲያው ሥጋዊ ጥቅሞችን ያገኛል፤ ይሁንና የመከሩን ጊዜ መጠበቅ አለበት። በጸጋ የተነሣሣ ክርስቲያን በራሱ ሕይወት ውስጥ ለግል ብልጽግናው የሚጠቅሙትን በረከቶች ያጭዳል፤ ይህም ብልጽግና ለሌሎች ይተርፋል። የዚህም ነገር የመጨረሻ ውጤት ሌሎች በሚያመሰግኑበት ጊዜ ለእግዚአብሔር የሚመጣው ክብር ነው። ጳውሎስ በጸጋ መስጠት እግዚአብሔርን ከሚያስከብር በቀር፥ ለእኛ የሚያስገኝልን ምስጋና እንደሌለ በጥንቃቄ ይገልጻል። እኛ እግዚአብሔር የሌሎችን ጉድለት ለመሙላት የሚጠቀምብን አሸንጻዎች እንጂ፥ ማንም ምንም አይደለንም። 

ይሁንና ቁጥር 11 ሌላም እውነት ያስተምረናል – እግዚአብሔር የሚያበለጽገን ከዚህ አብልጠን እንድንሰጥ ነው። በጸጋ ከመስጠት ደስታዎች አንዱ አብልጦ መስጠት ነው። ገቢያችን ብቻ ሳይሆን፥ ማንኛው ያለን ንብረት ሁሉ የእግዚአብሔር፥ ለእግዚአብሔር የተሰጠና ሥራውን ይፈጸምበት ዘንድ እርሱ የሚጠቀምበት ነው። ሁሉንም ነገር ከእርሱና ከሌሉች ጋር ስለምናካፍል፥ በነገር ሁሉ በልጽገናል ማለት ነው። 

መጋቢ እንደ መሆኔ፥ ወጣት ክርስቲያኖች እነዚህን በጸጋ የመስጠት መመሪያዎች ተከትለው ማደግ ሲጀምሩ ተመልክቻለሁ። የመስጠት ተግባራቸው በጸጋ እንደ መነሣሣቱ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ሲታመኑ መመልከት እጅግ ደስ ያሰኘኝ ነበር። ሆኖም በዚያው በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ፥ ሌሎች በእነዚህ መመሪያዎች ላይ በማፈዝ፥ ቀስ በቀስ ወደ ጉስልቁልና አዘቅት ሲያመሩ ተመልክቻለሁ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የመዋዕለ-ንዋይ «ሀብት» ቢያገኙም፥ ገቢያቸው ግን ውድቀታቸው ነበር – እውነተኛውን ብልጽግና አልለገሳቸውም። ዋጋቸውን (ሽልማታቸውን) እዚሁ ተቀብለዋልና መንፈሳዊ ባለጸግነት የሚያገኙባቸውን ዕድሉች አጥተዋል። 

በጸጋ መስጠት ማለት እግዚአብሔር ታላቁ ሰጪ መሆኑን በትክክል በመረዳት፥ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን በተመሳሳይ መንገድ ለሌሉች ጥቅም ማዋል ማለት ነው። ዳሩ ግን የእኛ ስጦታ በእግዚአብሔር ስጦታዎች ዓይን ምን ያህል አናሳ ነው! 

ያንተ መስጠት የሌሎችን ጉድለት ይሞላል (2ኛ ቆሮ. 9፡12) 

አሁን ደግሞ ጳውሎስ መስጠትን አገልግሎት በሚለው ሌላ ቃል ሲገልጸው እንመለከታለን። ይህም አገልግሎት «የክህነት አገልግሉት»ን የሚመለከት ሲሆን ጳውሎስ የስጦታን ገጽታ እጅግ ከፍ ወዳለው ደረጃ አሳድጎታል። ጳውሎስ ይህንን መዋጮ፥ አንድ ካህን ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበትን መሥዋዕት በመሠውያ ላይ እንደሚያቀርበው፥ ለእግዚአብሔር እንደ ቀረበ « መንፈሳዊ መሥዋዕት» አድርጎ ተመልክቶታል። 

ክርስቶስ በመስቀል ላይ የፈጸመው ሥራ የሌዋውያንን ሥርዓት ከፍጻሜ ስላደረሰው (ዕብ 10:1-14)። ክርስቲያኖች ከእንግዲህ እንስሳትን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው አያቀርቡም። ይሁንና ለጌታ የምናመጣቸው ቁሳዊ ስጦታዎች፥ በኢየሱስ ስም ከተሰጡ፥ «መንፈሳዊ መሥዋዕቶች» ይሆናሉ (1ኛ ጴጥ. 2:5፤ ዕብ. 13፡15-16፤ ፊልጵ. 4፡10-20)። 

ዳሩ ግን በ2ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 12 ላይ ትኩረት የተሰጠው፥ ስጦታቸው በይሁዳ የሚገኙትን ድሆች ጉድለት በሚሞላበት ሁኔታ ላይ ነው። «የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል» (ቁ. 12)። የአሕዛብ አማኞች ገንዘባቸውን ላለመስጠት የመሰላቸውን የማመካኛ ምክንያቶች ሊያቀርቡ ይችሉ ነበር። ከማመካኛዎቹም አንዱ፥ «ረሃብ የደረሰባቸውና የደኸዩት በእኛ ጥፋት አይደለም» የሚለው ሊሆን ይችላል። ወይም፥ «በይሁዳ አቅራቢያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሊረዷቸው ይገባ ነበር።» በሌላም በኩል፥ «መስጠት አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን፤ ዳሩ ግን በመጀመሪያ ደረጃ ለራሳችን ድሆች እንክብካቤ ማድረግ አለብን» ለማለት ይችሉ ነበር። 

አንድ ክርስቲያን ላለመስጠት ብሎ ማመካኛዎችን ማሰባሰብ ሲጀምር፥ ከመቅጽበት በጸጋ ከመስጠት ክልል ይወጣል። ጸጋ የሚፈልገው የሚያገለግልበትን ዕድል እንጂ፥ የሚያመካኝበትን ምክንያት አይደለም። መሸፈን የሚገባው ቀዳዳ ካለ፥ በጸጋ ቁጥጥር ሥር የሚመላለሰው ክርስቲያን ቀዳዳውን ለመድፈን የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። «እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ» (ኤፌ 6፡10)። ጳውሎስ ሀብታም ክርስቲያኖች፥ «በበጎም ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ» ይመክራቸዋል (1ጢሞ. 6፡18)። ብዙዎቻችን ራሳችንን «ሀብታሞች» አድርገን አንመለከትም፤ ዳሩ ግን የተቀረው ዓለም የሚመለከተን እንደ ባለጠጎች አድርጎ ነው። 

ይሁንና ክብሩን የምንወስደው እኛ ሳንሆን፥ የሚከበረው ጌታችን ነው (ማቴ. 5፡16)። ብዙ ሰዎች ጉድላታቸውን በመሙላቱ በኩል ተካፋዮች በመሆናችን በሰማይ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። ምናልባት ዛሬ ያንን የምስጋና ድምፅ ላንሰማ ብንችልም፥ ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን በምትሰባሰብበት ጊዜ እንሰማለን። 

እዚህ ላይ ጳውሎስ ይህንን መልእክት በሚጽፍበት ወቅት መብዛት የሚለውን ቃል ስለ ተጠቀመበት ሁኔታ መመልከቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል። መልእክቱን የጀመረው ከብዙ መከራ ጋር በተመጣጠነ ብዙ መጽናናት ነበር (2ኛቆሮ. 1፡5)። እንዲሁም ብዙ ጸጋን (4፡15)፡ ብዙ ደስታንና ልግስናን (8፡2) ገልጾአል። ከእግዚአብሔር ጸጋ ብዛት የተነሣ፥ ሁልጊዜም በመልካም ሥራ ሁሉ ልንበዛ እንችላለን (9፡8)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለማንኛውም ሁኔታ ብቁ ሊያደርገን ስለሚችል፥ ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወት ከመትረፍረፍ እንደ አንዱ አድርጎ ይመለከታል። 

መስጠታችን መሠረታዊ ጉድለቶችን ለማቅረብ እንጂ፥ ለተቀናጣ ሕይወት ማሟያ ሊውል አይገባም። ልንቋቋማቸው የሚገባ ብዙ ችግሮች እያሉ፥ ውስን የሆነውን ሀብታችንን ለሆነ ላልሆነው ማባከን አይገባንም። ችግር በራሱ ለመስጠት ብቸኛው ምክንያት አለመሆኑ የታወቀ ከመሆኑም፥ ደግሞም ማንኛውም አንድ በጎ አድራጊ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን ሊሸፍኗቸው የማይችሏቸው የችግር ዓይነቶችም አሉ። ይሁንና ለመስጠት፥ የችግር መኖር አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ችግሮች ከሌሉች የላቁ ሲሆኑ፥ አንዳንዶቹ ችግሮች ደግሞ በመሟላታቸው ከሌሎቹ የተለየ ብዙ ጥቅም ይሰጣሉ። ዛሬ የሚጫኑን በርካታ ችግሮች ለመወጣት በምንነሣሣበት ጊዜ፥ ስለ ችግሮቹ ትክክለኛ መረጃና መንፈሳዊ መረዳት ሊኖረን ይገባል። 

ያንተ መስጠት እግዚአብሔርን ያስከብራል (2ኛ ቆሮ. 9፡13) 

ጌታችን፥ «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ» ብሏል (ማቴ.5፡16)። ይህ ከቤተ ክርስቲያን የመስጠት ውብ ገጽታዎች አንዱ ነው – ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን ክብር የሚቀበል ግለሰብ የለም። 

መልካም ነገር የተደረገላቸው የአይሁድ አማኞች እግዚአብሔርን ስለ ምን ያመሰግኑ ነበር? የሚያመሰግኑት የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሥጋዊና ቁሳዊ ጉድለቶቻቸውን ለእግዚአብሔር ሲሉ በማሟላታቸው ነበር። እንዲሁም ደግሞ ለአሕዛብ መንፈሳዊ መገዛትንና የመስጠትን ፍላጎት በልባቸው ስላሳደረው የእግዚአብሔር መንፈስ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። «እነዚያ አሕዛብ ወንጌሉን መስበክ ብቻ ሳይሆን፥ በወንጌሉ ይኖራሉ» ለማለት ይችሉ ነበር። 

በዚህ ቁጥር ውስጥ (2ኛ ቆሮ. 9፡13) 

«ሁሉንም» የምትለው ቃል አስፈላጊ ነች። የአይሁድ አማኞች ሌሉችም በአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ስለ መረዳታቸው እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። እርዳታ የተደረገላቸው አነስተኛ ማኅበረ ምዕመናን ሁሉ ስለ እርዳታውና እርዳታው ለሌሉች ስለ መሰጠቱ ጭምር ያመሰግኑ ነበር። «ለእኛ ለምን ብዙ አልተሰጠንም?» በማለት ፈንታ፥ በችግር ውስጥ ያሉት ሌሉችም እየተረዱ በመሆናቸው፥ እግዚአብሔርን ለማመስገን ይችሉ ነበር። በጸጋ መስጠት የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው። 

እያንዳንዳችን ስለ መታዘዛችንና ስለልግስናችንም እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ እንዳሉ እንደሌሉ ለመረዳት አብያተ ክርስቲያናት ግምገማ ቢያካሂዱ መልካም ነው። የቱንም ያህል የጎላ የወንጌል አገልግሎት ቅንዓት ቢኖረን፥ ወይም የአምልኮ ተግባራትን ብናከናውን እነዚህ በራሳቸው ሌሎችን ለማገልገልና ተጨባጭ ችግሮቻቸውን በማስወገድ ረገድ ያመለጡንን አጋጣሚዎች ሊተኩ አይችሉም። በእኛ ዘንድ አንዱን የመምረጥና ሌላውን የማግለል ጉዳይ ሊኖር አይገባም። ብርሃናችን ያለ ማቋረጥ በድምቀት እንዲያበራ ከተፈለገ፥ ወንጌል የማካፈልንና ሰዎችን ከችግራቸው የማላቀቅን ኃላፊነት ሚዛናዊ ልናደርጋቸው ይገባል። ለተራበ ሰው ወንጌል መስበኩ አስቸጋሪ ነው የሚለው አባባል ትክክለኛ ነው። (ያዕ.2፡15-16 ተመልከት።) 

አንድ ሀብታም ሰው በቤተሰቡ የግል የጽሞና ጊዜያት ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያኑ ለምትረዳቸው ሚሲዮናውያን ስለሚያስፈልጉ ነገሮች፦ በየዕለቱ ጸሎት ያደርግ እንደ ነበረ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ታዲያ አንድ ቀን የጠዋት ጸሎታቸውን እንደ ጨረሱ ትንሽ ልጁ፥ «አባባ፥ የአንተ የባንክ ሒሳብ ደብተር የእኔ ቢሆን ኖሮ፥ ጸሎትህን ያለ ምንም ችግር በመለስሁልህ ነበር!» አለው ይባላል። እውነትም እንዴት ያለ አስተዋይ ልጅ ነው! 

ያንተ መስጠት የእግዚአብሔርን ሰዎች አንድ ያደርጋል (2ኛ ቆሮ. 9፡14-15)። 

ጳውሎስ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት የአይሁድን አማኞች እንዲረዱ ሲጠይቅ፥ በልቡ ውስጥ ከነበሩት አበይት ዓላማዎች አንዱና መሠረታዊም ምክንያት ይህ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ዋንኞቹ ሕጋውያን ጳውሎስን ፀረ-አይሁዳዊና ብሎም ፀረ-ሕግ አድርገው ይከሱት ነበር። የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ከአገሩ ርቀትና ከባሕል ልዩነት የተነሣ በኢየሩሳሌም ውስጥ ከምትገኘው «እናት ቤተ ክርስቲያን» ተለይተው ነበር። ጳውሎስ ግን የቤተ ክርስቲያንን መከፋፈል ለመከላከል ይፈልግ ነበር፤ «እርዳታውም» የዚህ መርሐ-ግብር አካል ነበር። 

ይህ እርዳታ የአይሁድና የአሕዛብ ማኅበረ-ምዕመናንን ሊያስተሳስር የሚችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? አንድኛው ነገር፥ ስጦታው የፍቅር መግለጫ መሆኑ ነው። (ምንም እንኳ ጳውሎስ ስጦታው «የመንፈሳዊ ዕዳ» ክፍያ እንደ ሆነ ቢናገርም – ሮሜ 15፡25-27) ይህንን ያደረጉት አሕዛብም ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ እንጂ፥ ግዴታቸው ስለ ነበረ አይደለም። አይሁዶችም በበኩላቸው፥ ለአሕዛብ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ባለውለታነትና አንድነት ይሰማቸው ነበር። 

ሌላው በመንፈስ የሚያስተሳስራቸው ጸሎት ነው። «ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው የእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል» (2ኛ ቆሮ. 9፡14)። የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት የአይሁድ አብያተ ክርስቲያናትን የጸሎት ድጋፍ «እየገዙ» ይሆን? አይደለም! ጳውሎስ ስጦታውን ወደ ይሁዳ ሲያደርስ ሊስተዋል የሚችለውን ቅጽበታዊ የፍቅር፥ የምስጋናና የጸሎት መግለጫ በእዝነ-ሕሊናው ተመለከተ። 

በርካታ የሚሲዮን ጣቢያዎችን የመጎብኘትና በዚያ የሚገኙ አማኞች፥ «እየጸለይንልህ ነበር» ሲሉ የመስማት ልምምድ ነበረኝ። ከምሥራቅ አውሮፓ ከመጣው አንድ መልካም ክርስቲያን ጋር ስንጫወት፥ «በአንዳንድ በኩል መንፈሳዊ ክርስቲያኖች ለመሆን ከእኛ የበለጠ ችግር ስላለባችሁ፥ በዩናይትድ እስቴትስ ለምትኖሩ ወገኖች እየጸለይንላችሁ ነበር» አለኝ። አሳቡንም እንዲያብራራልኝ በጠየቅሁት ጊዜ ፈገግ አለና፥ «ይህን ማለቴ ባንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀለል ያለ ሕይወት ስልምትኖሩና ምቾት ደግሞ የመንፈሳዊ ሕይወት ባላንጣ ስለ ሆነ ነው። በምሥራቅ አውሮፓ እነማን ወዳጆቻችን እንደ ሆኑና እነማንስ ጠላቶቻችን እንደ ሆኑ ጠንቅቀን እናውቃለን። እናንተ በምትኖሩበት ስፍራ ግን ለመሞኘት መንገዱ ቀላል ነው። በመሆኑም እንጸልይላችኋለን» አለኝ። 

ሁለቱም የአይሁድና የአሕዛብ አብያተ ክርቲያናት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይበልጥ ይቀርቡ ነበር። «ስለማይነገር (ስለማይገለጽ) ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን» (ቁ. 15)። በኢየሱስ ክርስቶስ የሰብዓዊ ልዩነቶች በሙሉ ስለ ተወገዱ፥ ከእንግዲህ እርስ በርሳችን እንደ አይሁዶች ወይም አሕዛቦች፥ ድሆች ወይም ባለጠጎች፥ ሰጪዎች ወይም ተቀባዮች አንተያይም። «ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና» (ገላ. 3፡28)። 

ዳሩ ግን መስጠታችን የሕይወታችን ምትክ ሲሆን መመልከቱ አሳዛኝ ነገር ነው። አንድ ጊዜ አንድ የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን፥ «ለሚሲዮን አገልግሎት የምትፈልጉትን ያህል ገንዘብ እሰጣችኋለሁ። የሚሲዮናዊን ንግግር ብቻ አታሰሙኝ!» ሲል አጉረምርሞብኛል። አንድ ክርስቲያን በጸጋ መስጠትን በሚለማመድበት ጊዜ፥ ገንዘቡ ለሌሎቹ ለማሰቡ ሆነ ለአገልግሎቱ ምትክ አይሆንም። በመጀመሪያ ራሱን ለእግዚአብሔር በመስጠት (2ኛ ቆሮ. 8፡5) – ቀጥሉም ያለውን ይሰጣል። ስጦታው የልቡን በቅድሚያ መሰጠት የሚያመለክት ነው። ስጦታው በእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣሣ ከሆነ፥ ሰጪውንና ስጦታውን ለመለየት አይቻልም። 

ወደ ኋላ ተመልሰህ 2ኛ ቆሮንቶስ 8 እና 9ን እንድታነብና በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የተደረገውን አጽንኦት እንድታስተውል እጠይቃለሁ። አብያተ ክርስቲያኖቻችንና ሌሎችም አገልግሉቶች በጸጋ ወደ መስጠት ቢመለሱ ኖሮ፥ በከፍተኛ ጫና የሚካሄዱት የስጦታ ልመናዎች፥ ገንዘብ ለማከማቸት የሚደረጉ የማታለያ ጥረቶችና ከእግዚአብሔር ሰዎች ዘንድ የሚደመጡ ማጉረምረሞች በእጅጉ በተቀነሱ ነበር። በምትኩም፥ የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነተኛ መንገድ ለሚያበለጽጉ አገልግሎቶትች በቂ ገንዘብ በኖረም ነበር። እንደ እኔም ግምት፥ በዓለም ያለው ያልዳነው ሰው የምንሠራውን ተአምር በአድናቆት በተከታተለም ነበር። 

እግዚአብሔር በጸጋ በመስጠት በማመኑ፥ እኔና አንተ ድነናል። እኛስ በጸጋ በመስጠት ምን ያህል እናምናለን?

Leave a Reply

%d bloggers like this: