1ኛ ቆር.12:1-11

በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጉባኤያቸው ብዙ ስሕተቶች ነበሩ። እስከአሁን እንኳ ሁለት ስሕተቶችን ሐዋርያው እንዳረመላቸው አይተናል፤ እነርሱም ስለ ሴቶችና ስለቅዱስ ቁርባን ነበሩ። አሁን በዚህ ምዕራፍ ስለመንፈሳዊ ሥጦታዎች ይፈጽሙ የነበሩትን ስሕተቶች ያርምላቸዋል። ይህ የመንፈሳዊ ሥጦታ ጉዳይ በዘመናችንም አከራካሪ ሆና ስለመጣ የሐዋርያውን መምሪያ በጥንቃቄ በመመልከት የእኛንም ስሕተት በቃሉ መሠረት ማረም ይኖርብናል። 

ጥያቄ 6. የመንፈሳዊ ሥጦታዎች ዋና ዓላማ ምንድነው? 

ጥያቄ 7. ከቁጥር 8-10 ውስጥ ስንት መንፈሳዊ ሥጦታዎች ተዘርዝረዋል? 

ጥያቄ 8. እነዚህ ሥጦታዎች ለምን ያህል አማኛች ነው የተሰጡት? 

በቁጥር 1 ላይ፡- «ስለመንፈሳዊ ነገርም» ሲል የቆሮንቶስ ሰዎች ከጠየቋቸው ጥያቄዎች አንዱ ይህ አንደነበር ያመላክታል። 

ቁጥር 2:- «አህዛብ ሳላችሁ» ከማመናቸው በፊት በተለያዩ የጣዖት አምልኮዎች ያለ አእምሮ ይነዱ ነበር። ጣዖት አእምሮን ያደነዝዛል። አሁን ግን በአእምሮ መጎልመስና በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን የሕያው አምላክ ተከታዮች ሆነዋል። በጣዖት ሥር በነበሩ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ከቁጥጥራቸው ውጭ በሰይጣን አስገዳጅነት ይፈጽሙ ነበር። አሁን ግን በመንፈስ ቅዱስ ሲመሩ አእምሮአቸውን ሳይለቁ በልባቸው መንፈስ ቅዱስ ያስተማራቸውን ረጋ ባለ መንፈስ ይናገራሉ በፈቃዳቸው ይናገራሉ፡፡ 

ጥያቄ 9. ከማመንህ በፊትና ካመንህ በኋላ በሕይወትህ ምን ዓይነት ለውጥ ታይቶአል? 

ቁጥር 3፡- ይህ እርግማን ወይም እውቀት እንዲሁ በቸልተኝነት የሚሠነዘረውን ሳይሆን ከልብ የመነጨ አጋርን ያመለክታል። ሰው በመንፈስ ቅዱስ ካልተመራ በስተቀር የኢየሱስን ማንነት ማወቅ አይችልም፤ ( 1ኛቆሮ.2፡6-13)። እንዲሁ ሰው በአጋንንት መንፈስ ተወስዶ ኢየሱስን ሊረገም ይችላል። 

ስለ ጸጋ ሥጦታዎቶ መወያየት ይጀምራል። ከቁጥር 4 እስከ 7 ድረስ ስለዚህ ነገር ያብራራል። የጸጋ ሥጦታዎች ሥላሴን ያመላክታሉ፡፡ ሥጦታዎችን እንደፈቃዱ ለእያንዳንዱ አማኝ የሚያድል መንፈስ ቅዱስ ነውና ብዙ ሥጦታዎች በአንዱ መንፈስ ይሰጣሉ፡፡ የሥጦታዎችም ዓላማ ጌታ ኢየሱስን ለማክበር ስለሆነ ብዙ ቢሆኑም አንድ ዓላማ አላቸው። የሥጦታዎች አሠራር የተለያየ ቢሆንም በእግዚአብሔር አስተዳዳር ሥር ናቸው። እነዚህ ሥጦታዎች በሙሉ ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማሳደግና ለማነጽ ነው እንጂ ለግል ጥቅም ወይም ክብር ተብለው የሚሰጡ አይደሉም። ለዚህም ነው አንዳንድ ሥጦታዎች ለጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሰጡት፤ ( 1ኛጴጥ.4:10-11)። 

ክቁጥር 8-11 ሥጦታዎችን ይዘረዝራል፡፡ 

ጥበብ፡- በተፈጥሮ ሊታወቁ የማይቻሉትን ጥልቅና መንፈሳዊ እውቀቶች መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች ይገልጣል፡፡ ሁሉም አማኞች ክርስቶስን የማወቅ ጥበብ ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ ጥበብ ግን የተለየ ሥጦታ ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች የሚሰጥ ማለት ነው። 

እውቀት:- ይህ በመሠረቱ ከጥበብ አይለይም። 

እምነት፡- ይህም ለእያንዳንዱ አማኝ የሚሰጠው በኢየሱስ የማመን የደህንነት እምነት ሳይሆን በተለይ በእምነት የመራመድ ሥጦታ የሚታይባቸው አማኞች አሉ ማለት ነው። 

የመፈወስ ሥጦታ፡- ይህ ሥጦታ ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ ነበረው፤ የልብሱን ጫፍ እንኳ የነካ ይፈወስ ነበር። 

ተአምራትን ማድረግ፡- ይህ ልዩ ኃይልን የመግለጥ ሥጦታ ነበር። ለምሳሌ፡- ጴጥሮስ በተግሣጽ ሐናንያንና ሰጲራን እንደገደለ፤ ጳውሎስ አስማተኛውን በእውርነት አንደመታው ዓይነት ያለ ኃይል ነው። (የሐዋ.5፡1-11፤ 13:6-12)። 

ትንቢት፡- የእግዚአብሔር አንደበት ሆና የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ ማለት ነው። ይህ የወደፊቱን መተንበይ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቃልም መስጠት ትንቢት ይባላል፤ (የሐዋ. 15፡32)። ደግሞም ጌታ ኢየሱስ ነቢይ ነበር፤ ግን ዋና ሥራው ማስተማር ነበር እንጂ የወደፊቱን ነገር መተንበይ ብቻ አልበረም። ነቢያት ሲተነብዩ ከአእምሮአቸው ተለይተው ዛር እንዳለበት በመንቀጥቀጥና በንግግር በመፈንዳት አልነበረም። ነገር ግን ዘና ብለው በጽሞና መንፈስ በማስተማር አቀራረብ ነበር። አንዳንድ ጊዜም በጥያቄና በመልስ በውይይት መልክ ትንቢታቸውን በትምህርት መልክ አቅርበዋል። ይህ አይሆንም ያለ የጌታን ትምህርት አሰጣጥ ከወንጌል አንብቦ ይረዳ!! 

መናፍስትን መለየት፡- አማኞች በሙሉ መናፍስትን እንዲመረምሩ ታዘዋል፤ ( 1ኛ ዮሐ.4፡ 1)። ነገር ግን ይህ የተለየ የስሕተትን መንፈስ ቶሎ የመለየትና ቤተ ክርስቲያንን የማስጠንቀቅ ሥጦታ ነው። ያልበሰሉ አማኞች ብዙ ጊዜ «እኔ ለዶክትሪን ገድ የለኝም» እያሉ ሲኩራሩ ይታያሉ። ዶክትሪን በመሠረቱ ትምህርት ማለት ነው። ክርስቲያን ምን ዓይነት ትምህርት መቀበል እንዳለበት መጠንቀቅ አለበት። የቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች ሕዝባቸው ሐሰተኛ ትምህርት እንዳይቀበሉና ከክርስቶስ መንገድ ፈቀቅ እንዳይሉ መንከባከብ አለባቸው። እነዚህ ተንከባካቢዎች እንገዲህ የመለየት ሥጦታ ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፤ (2ኛቆሮ.11:2-4፤ ገላ.1:6-9፤ 2ኛጴጥ.2:1-3)። 

ልሳን፡- ይህ ሥጦታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው በሐዋ. ምዕራፍ 2 ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደ እለት ነው። በ1ኛ ቆርንቶስ የተጠቀሰውና በሐዋርያት ሥራ ያለው የተለያየ ነው የሚሉ ማስረጃ የላቸውም። ልዩነት የተባሉትን ስንመረምር ልዩነት እንዳልሆኑ እንገነዘባለን። በመሠረቱ በግሪክ ቋንቋ በሁለቱም ቦታ የተጠቀሰው ያው ልሳን የሚለው ቃል ነው። ስለዚህ ትርጉሙን ሁለት አድርገን ለመስጠት በቂ ምክንያት ሊኖረን ይገባል፤ ምክንያትም የለንም። ስለዚህ ሥጦታ ዝቅ ብለን በተጨማሪ እንወያያለን። (የዚህ ዌብ ሳይት አዘጋጅ ከዚህ የተለየ ሃሳብ አለው)

ከዚያ በፊት ግን ጠቅላላ ሥጦታዎቹን በሁለት ወገን እናጠቃልላቸዋለን። ያም የእውቀትና የኃይል ሥጦታዎች በመባል። የእውቀት ሥጦታዎች የተባሉት፡- ጥበብ፥ እውቀት፥ ትንቢት፥ መናፍስትን መለየት፥ ልሳን መተርጉም ሲሆኑ! የኃይል ሥጦታዎች ደግሞ፡- ዕምነት፥ መፈወስ፥ ተአምእራት ማድረግ ናቸው። በሁለቱ መካከል ያለው ዝምድና ይኸ ነው። በቃሉ የተነገረው እውቀት እውነተኛ ለመሆኑ የኃይል ሥጦታዎች ማረጋገጫ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ዕብ.2፡3-4ን ተመልከት። ይህንን ክፍል ከኤፌ.4:11-12፤ ከ1ኛ ጴጥ.4፡10-11፤ ከሮሜ 12፡4-8 እና ከ1ኛ ቆሮ.12:28-30 ጋር ካነፃፀርነው ሌሎች መንፈሳዊ ሥጦታዎች እንዳሉ መገንዘብ እንችላለን። 

ጥያቄ 10. 1ኛ ቆሮ.12:8–10፤ 28-30ን ከኤፈ.4፡11-12፤ ከ1ኛ ጴጥ.4:10-11 እና ከሮሜ 12:4-8 ጋር አነፃፅር። በእዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተሰጡትን ሥጦታዎች በዝርዝር ጻፍ። 

ጥያቄ 11. ሀ/ የትኛው መንፈሳዊ ሥጦታ ይመስልሃል የተሰጠህ? ለ/ ይህንን ሥጦታ ያሰብከው ለምንድነው? ሐ/ አንድ ሰው መንፈሳዊ ሥጦታውን ሊያውቅ የሚችለው እንዴት ነው? መ/ ለቤተ ክርስቲያንህ ዕድገት ይህንን ሥጦታህን በምን ዓይነት መንገድ ነው የምትጠቀምበት? 

ጥያቄ 12. ሀ/ አንዳንድ አማኝ ከዚህ የተለየ ሃሳብ አለው። ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ምን ያምናሉ? ለ/ አሁን በተማርከው መሠረት እንዴት ልትመልሳቸው ትችላለህ?

1 thought on “1ኛ ቆር.12:1-11”

  1. በዚህ ድህረገፅ የሚለቀቀው ጥናት በጣም ጠቅሞኛል መፀሐፍ ቅዱስን ባግባብ እንድረዳው እየረዳኝነው ተባረኩ አመሰግናለሁ በርቱ

Leave a Reply

%d bloggers like this: