ጥያቄ 12. በቁጥር 1 ላይ ለቅዱሳንዎ ገዝብን ስለ ማዋጣት» ሲል ምን ማለቱ ነው?
ጥያቄ 13. በቁጥር 2 ላይ የገንዘብ ማጠራቀሚያው ቀን ለምን ከሳምንቱ የመጃመሪያው ቀን ይሁን አለ?
«ለቅዱሳን ገንዘብን ስለማዋጣት» ስለዚህም ጉዳይ ሳይጠይቁት አይቀሩም። ይህ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ክርስቲያኖች ገንዘብ አዋጥቶ መላክ ጳውሎስ ሥራዬ ብሎ የሚያካሄደው አገልግሉት ነበር። ለምሳሌ የሚከተሉትን የመድሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብንመለከት ይህንን እንገነዘባለን። የሐዋ /ሥራ 24:17፤ ሮሜ 15፡25-28፤ 2ኛ ቆሮ.8፡16-21 ተመልከት።
በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች በችግር ላይ ነበሩ። ለምን ችግር ላይ ወደቁ የሚል ጥያቄ ተነሥቶ አንዳንድ ግምቶች ተሠንዝረዋል። ከእነዚህም አንዱ ያላቸውን እርሻም ሆነ ሌላ ነገር ያለ ጥሩ ፕላን ይሸጡ ስለነበር (የሐዋ.4:32-37) ቆይቶ ይህ ድህነት አስከተለባቸው የሚል ነው። በእርግጥ የችግራቸው መነሻ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ሌሎች ክርስቲያናች ግን እንዲረጹ በሐዋርያው ታዘዋል።
የገንዘቡ አሰባሰብ ዘዴ እንደሚከተለው መሆን ነበረበት። ሐዋርያው እዚያ ከመድረሱ በፊት መዋጮው ተሰብስቦ ማለቅ ነበረበት። እያንዳንዱ አማኝ እግዚአብሔር እንዳስቻለው እሁድ እሁድ ካለው እየቆረሰ ማጠራቀም ነበረበት። ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን ማለት እሁድ ማለት ነው። እሁድ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ቀን ሆነ፤ (ዮሐ.19፡21፤ የሐዋ.20፡7፤ ራእይ 1:10)። ይህ ቀን ጌታ ከሞት የተነሣበት ቀን ስላበር የክርስቲያኖች ሰንበት ሆነ።
በአማርኛው ትርጉም ላይ «በቤቱ» የሚል ቃል በቁጥር 2 ላይ ገብቷል። በግሪኩ ላይ ግን ይህ የለም። እያንዳንዱ ክርስቲያን እግዚአብሔር እንዳበለጸገው ያስቀምጥ ይላል እንጂ የት ማስቀመጥ እንዳለበት አልተናገረም። ሆኖም እሁድ ቀን ክርስቲያኖች በአንድነት ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ቀን ስለነበርና መዋጮውም በዚሁ ቀን ይሰብሰብ ስላል በቤተ ክርስቲያን ይሰብሰብ ማለቱ ነው ብለን እንገምታለን፡፡ ይህ ከብሉይ ኪዳን ጋር ይስማማል። በብሉይ ኪዳን መዋጥ መጠራቀም የነበረበት በየግል ቤት ሳይሆን በቤተ መቅደስ ወይም አንድ የሕዝብ ማጠራቀሚያ በሆነ ቦታ ነበር።
እግዚአብሔር እንዳስቻለው ይላል እንጂ እያንዳንዱ ክርስቲያን ስንት ማዋጣት እንደነበረበት ባይናገርም በብሉይ ኪዳን እነአብርሃም አሥራት ይሰጡ እንደነበር መዘንጋት የለበትም። እንዲሁዎ ጌታ በማቴ.23፡23 ላይ አሥራትን ደግፎ ተናግሮአል። ስለዚህ እኛም ለክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዳበለጸገን እንስጥ፤ ያም አሥራትን። በጥንቃቄ አሥራት መስጠት በስሜት ተገፋፍቶ በድንገተኛ ሰጥቶ ከመጸጸትና እንዲሁም በቂ ባለመስጠት የእግዚአብሔርን ሥራ ከመበደል ይጠብቀናል።
ጥያቄ 14. ከምታገኘው ነገር 10% ለእግዚአብሔር ትሰጣለህ? ሌሎች ቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ሰዎች 10% የሚሰጡ ይመስልሃል? ብዙ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ አሥራት የማይሰጡት ለምን ይመስልሃል?
ይህ የተዋጣው ገንዘብ በጥንቃቁ የተባለበት ቦታ እንዲደርስና ሐሜት እንዳይነሣ ራሳቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከራሳቸው ሰዎች መርጠው ስጦታውን እንዲልኩ ያዛል እንጂ፥ ሐዋርያው «እኔ አደርስላችኋለሁ» ብሎ እንዳልወሰደ ግልድ ነው። ገንዘብ ንጽሕናንና ጥንቃቄን ይጠይቃልና አጉል «እንተማመን» በሚል ሞኝነት ሐሜትና ጥርጣሬ አንፍጠር፤ (ቁጥር 3)።
ጥያቄ 15. ይህ ክፍል የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በምን ዓይነት መንገድ ማስተደደር እንዳለብን ነው የሚያስተምረው?