ሐዋርያው ስለ መንፈስ ቅዱስ የከፈተውን ውይይት ያቋርጥና ስለ ፍቅር በምዕራፍ 13 መዘርዘር ይጀምራል። ዋና ነጥቡ አንድ ሰው ብዙ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ቢኖሩት ነገር ግን በፍቅር ካልተመላለሰ ለእግዚአብሔር መንግሥት ምንም የማይጠቅም እንደሆነ ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታን መቀበልና በክርስትና ሕይወት በስሎ መገኘት አብረው ላይሄዱ እንደሚችሉ ነው። አንድ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታን በሥራ የሚያሳይ ሆኖ ሕይወቱ ግን ፍጹም ሥጋዊ ሊሆን እንደሚችል ነው። የቆርንቶስ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች በሙላት ነበሯቸው፤ ነገር ግን በጣም ሥጋውያን እንደነበሩ ሐዋርያው ይመሰክራል፤ ( 1ኛ ቆሮ.1:4-6፤ 3:1-4)።
ጥያቄ 1. የ12:31 ላይ «ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ» ባላውና በምዕራፍ 13 መካከል ያለውን ግንኙነት አስረዳ።
ጥያቄ 2. ከቁጥር 1-3 የፍቅርን አስፈላጊነት ዘርዝር።
ጥያቁ 3. ከቁጥር 4-7 የፍቅርን ፀባይ ዘርዝር።
ጥያቄ 4. ከቁጥር 8-13 የፍቅርን ጽናት ዘርዝር፡፡
ሐዋርያው ስል ፍቅር በሰፊው ይጽፋል። በቆርንቶስ የነበሩ እማኞች በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች በመመካት ምን ያህል ፍቅር የተጎደላቸው ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያስንዘባቸዋል። ያለ ፍቅር ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ይጽፋል። ሰው ብዙ ነገርን በክርስትና ስም ቢፈጽም ያ ሁሉ ነገር ያለ ፍቅር ከሆነ ዋጋ ቢስ እንደሆነ ያስጠነቅቀናል። በ1ኛ ቆሮ. 12:31 ላይ ጳውሎስ አንደተናገረ ይህንንም የፍቅር መንገድ ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ ይለዋል።
ከቁጥር 1-3:- የፍቅር አስፈላጊነት! ያለ ፍቅር አስደናቂ ልሳን ቢሆን፥ እውቀት ቢሆን፥ እምነት ቢሆን፥ ምጽዋት ቢሆን ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ነው። የእግዚአብሔርን መንግሥት አይገነባም። የእግዚአብሔርን መልክና ፀባይ ባለማሳየት ለጸጋውና ለፍቅሩ መሣሪያ አይሆኑም። ስለዚህ ፍቅርን ላለመርሳት ታላቅ ጥንቃቄ እናድርግ።
ጥያቄ 5. በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አንዳንድ ነገሮች ያለ ፍቅር ስለተሠሩ የእግዚአብሔርን ሥራ ከመሥራት ይልቅ ሥራውን ሲያበላሹ አይተሃል? እንዴት?
እዚህን መንፈሳዊ ሥጦታዎች በመጥቀስ፡- (በልሳን መናገርን፥ ትንቢት መናገርንና፥ እውቀትና እምነት) ጳውሎስ ብዙ ሰዎች ሥጦታዎቹን አንደሚመኙአቸው፥ ነገር ግን የእነዚህ ሥጦታዎች በአንድ ሰው ውስጥ መኖር የእርሱን መንፈሳዊነት እንደማያሳዩና በሥጋ ሊደረጉ እንደሚችሉ ያሳየናል። ሰዎች ዛሬም ቢሆን እነዚህንና ሌሎችን መንፈሳዊ ሥጦታዎች ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ክብር ሲያውሏቸውና ሲጠቀሙባቸው እናያለን።
ከቁጥር 4-7:- የፍቅር ፀባይ! ክርስቲያን በፀባዩ ክርስቶስን ካልመሰለ በአገልግሎቱ ፍሬቢስ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ የክርስቶስ ፀባይ ተዘርዝሮአል። በሮሜ 8፡29 ላይ እዚአብሔር ልጁን እንድንመስል ወስኗልና በፍቅር ፀባይ ፀባያችን ካልተለወጠ ክርስቶስን መምሰል አንችልም።
እነዚህን የፍቅር ፍሬዎች በምናጠናበት ጊዜ፥ አንድ ልናስተውል የምንችለው ነገር ቢኖር፥ ብዙዎቹ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸው ነው። ፍቅር እንዲሁ በልባችን ውስጥ የሚሰማን ስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሊታይ የሚገባው ነገር ነው። ስለዚህም ጳውሎስ ፍቅርን በአንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ያብራራዋል፡-
1. ሌሎችን መታገሥ፡- እኛ እንደምንፈልገው ባይሆኑልንም፥ እንደምን ፈልገው ባያደርጉልንም፥ …ወዘተ መታገሥ።
2. ለሌሎች ቸርነት ማድረግ (ቸር መሆን):- የሰዎችን ችግር ለመፍታት መጣር።
3. በሌሎች አለመቅናት:- ከእኛ የበለጠ ክብር ወይም ገንዘብ ቢያገኙም አለመቅናት።
3. ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፡- በምንታበይበት ጊዜ ራሳችንን ከሌሎች የተሻልን ነን ብለን ከፍ ከፍ ማድረጋችን ነው። ይህንንም ብዙ ጊዜ የምናደርገው ራሳችንን ከሌሎች ጋር አወዳድረን እነርሱን ዝቅ በማድረግ ነው።
5. ፍቅር የማይገባውን አያደርግም፡- በልጆች ወይም በተናቁት ወይም በድሆች ላይ እንከን የማይገባውን አያዳርገም።
6. ፍቅር የራሱን አይፈልግም:- ከራሱ ችግሮች ይበልጥ ለሌሎች ሰዎች ችግር ያስባል፤ (ፊልጵ.2:4)
7. ፍቅር አይበሳጭም፡- ብስጭታችንን ብዙ ጊዜ የምንገልጸው ሌሎችን የሚያናደድ ንግግር በመናገር ነው።
8. ፍቅር በደልን አይቆጥርም፡- በቀልን ለመበቀል ሳይሆን ለመታረቅ ነው የሚያስበው።
9. ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፡- ስለ ክፉ ሰዎች የሚነገር ወሪን መስማት አንዳንዴ ያስዳስተናል! በዚህም ምክንያት ደጉን ነገር ከማውራት ሰዎች የሚሠሩትን ክፉ ሥራ ለሌሎች የምናወራ ወሬኞች እንሆናለን። በምትኩ ግን ጥሩ የሆነውን ነገር መውደድ ይገባናል። የአመፃ ወሪ ሲደርሰን ይህንን ወሬ ላለመስማት ወስነን እውነት የሆነውን ለመስማት መወሰን አለብን።
10. ፍቅር ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል፡- ሌሎች መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ይመኛል እንጂ ያጋጥማቸዋል ተብሎ የሚገምተው መጥፎ ነገር እንዲደርስባቸው አይፈልግም።
11. ፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ለዘወትር አይወድቅም።
ጥያቄ 6. ከላይ የተዘረዘሩትን በመመልከት በሕይወትህ ውስጥ ፍቅርን ታሳይ የነበረው በየትኛው ዓይነት መንገድ ነው? ፍቅርስ ሳታሳይ የቀረኸው እንዴት ነው?
ጥያቄ 7. በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በመሪዎቹ መካከል ፍቅር የሚታይባቸው ሥፍራዎች የትኛዎቹ ናቸው? የፍቅር ፍሬዎች የሉበትም የምትለውስ ሥፍራ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የትኛው ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ቀዳሚው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ፀባይ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንዲቀይር እንጂ በአገልግሎት እንዲያሠልፈን አይደለም። አገልገሎት ሁለተኛ ደረጃ ነው። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ላይ ከማተኮራችን በፊት በመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ላይ እናተኩር፤ (ገላ.5፡22-26)።
ከቁጥር 8-13:- የፍቅር ጽናት! የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ፈጽመው የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጌታ ሲመለስ ይሆናል። የአሁኑ ሁኔታችን እንደሕፃንነት ጊዜ ይታያል፤ እንደመስታወት መልክ ይቆጠራል። ግን ጌታ ሲመለስ በከፊል የነበረን ሁሉ ሙሉ ይሆናል። እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር ግን ጸንተው ይኖራሉ። ፍቅር ከእነዚህ ከሁለቱም ይበልጣል። ስለዚህ የቆሮንቶስ አማኞች በፍቅር ማተኮር እንዳለባቸው እንደተነገራቸው እኛም እንዲሁ የፍቅር ሕልውናችንን እናጠናክር፡፡
ጥያቀ 8. ፍቅር ከእምነትና ከተስፋ ይበልጣል የተባለው ለምንድነው?