1ኛ ቆሮ.12:12-13

ጥያቄ 13. በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ምን ሆንን ይላል? 

ቁጥር 12:- የአማኞችን አንድነት ለማስረዳት የሰውን አካል ምሳሌ ይሰጣል። የሰውነት ክፍሎች ብዙም ቢሆኑ በአንድ ኅብረት አብረው እርስ በርስ ይገለገላሉ። መንፈስ ቅዱስም የዋላባቸው ምእመናን በአድመኛነት መሰሎቻቸውን ብቻ በመጥቀስ ሌሎችን ከቡድናቸው የማያስገቡ ሳይሆኑ በተሰጣቸው ሥጦታ ሌሎችን ያገለግላሉ። 

ቁጥር 13፡- በክርስቶስ አንድ አካል ተደርገናል። ይህም አንድነት የተመሠረተው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰጠ። በዚያ የነበሩት አይሁዶች ነበሩ። አይሁዳውያን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተካፋዮች በመሆን በክርስቶስ አካል በቤተ ክርስቲያን ገቡ። ከዚያ በኋላ ያመኑት (የሐዋ.2:41-42፤ በተጨማሪ ቁጥር 33ን ተመልከት ) በተደጋጋሚ መንፈስ ቅዱስ እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሳይሆን ያው በመጀመሪያው የወረደውን መንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች ሆኑ፤ ያም በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት ባመኑ ጊዜ ነበር ማለት ነው። 

የሰማርያ ሰዎች በመጀመሪያ ሲያምኑ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የሐዋርያት እጅ መጫን አስፈላጊ ነበር፤ (የሐዋ.8፡14-18)። ከዚህ በኋላ የሰማርያም ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተካፋዮች ስለሆኑ ከመጀመሪያዎቹ ተከትለው ያመኑትም ባመኑ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ጋር በመንፈስ ቅዱስ ይተባበራሉ እንጂ እንደገና የሐዋርያት ወይም የሌላ ሰው እጅ መጫን አላስፈለገም። እንዲሁም አህዛብ (የሐዋ.10፡44-48) በመጀመሪያ ሲያምኑ አሕዛብም የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ተካፋይ መሆናቸው ተረጋገጠ። ከዚህ በኋላ አህዛብ ሲያምኑ ወዲያውኑ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ይቀበሉና የክርስቶስ አካል ማህበረተኞች ይሆናሉ፤ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ለመቀበል ልዩ ሥርዓት አይደረገም! (የሐዋ.13:48፤ 14:21-22 ወዘተ )። በሐዋ.16 ላይም የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የዚሁ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተካፋዮች ሆኑ። 

እነዚህ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት የአንዱ አካል ክፍሎች ሆኑ። እንግዲህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በመጀመሪያ ስናምን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሚያደርገን ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ ሙላትም ለመጀመሪያ ጊዜ ባመንንና በመንፈስ ቅዱስ በተጠመቅን ጊዜ ተሰጥቶናል። ይህ ቁጥር 13 ላይ «አንዱን መንፈስ ጠጥተናል» ሲል መንፈስ ቅዱስን በመጠጣት መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ሞልቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ.7:37-39፤ ቲቶ 3:5-7)። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ተደጋጋሚ ልምምድ መሆን አለበት፤ ሁልጊዜ ደጋግመን በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ ያስፈልጋል፤ (ኤፌ.5፡18)። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ባመንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር አንድ ያደረገን መሣሪያ ስለሆነ አይዳጋገምም። 

ጥያቄ 14. እንደዚህ የማያምኑ ክርስቲያን ቡድኖች እነማን ናቸው? ምን ያምናሉ? በጥናታችን መሠረት እንዴት ትመልስላቸዋለህ?

Leave a Reply

%d bloggers like this: