1ኛ ቆሮ.14፡1-25

ጥያቄ 9. ከቁጥር 1-5 ባለው ክፍል ውስጥ ከልሳን ይልቅ በትንቢት መናገርን የመረጠው ለምንድነው? 

ጥያቄ 10. ልሳን ቤተ ክርስቲያንን የማያንጽ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? 

ጥያቄ 11. ልሳን የሚናገር ሰው ዓላማ ምን መሆን አለበት? 

ጥያቄ 12. በቁጥር 22 ላይ ልሳን ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም የሚለውን አብራራ። 

ዛሬ እንዳሉት ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች፥ የቆርንቶስም ቤተ ክርስቲያን በልሳን የመናገርን ሥጦታ በማጋነን ቤተ ክርስቲያኗን ጎድተዋታል። በዚህ ጥናት ጳውሉስ በልሳን ስላመናገር የሰጠውን ተጨማሪ ትምህርት እንመለከታለን። 

ቁጥር 1-5:- ከልሳን ይልቅ ትቢት የሚመረጥበት፥ ትንቢት ማህበሩን ስለሚያንጽ ነው። እንደምታስታውሰው ትንቢት ማለት ሁሌ የወደፊቱን ብቻ መናገር ሳይሆን የአግዚአብሔርን መልእክት ለምዕመናኑ ማስተላለፍም እንደሆነ አይተናል። የትንቢት ሥጦታ የነበራቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚገኙትን ቃል ኪዳናት በማካፈል፥ ሌሎችን የማበረታታት፥ የማጽናናትና የመቀስቀስ ችሎታ አላቸው። ልሳን ግን ራስን ብቻ ስለሚጠቅም የፍቅርን መንገድ ይረሳል። በልሳን የሚናገሩ በነገሩ ከመደሰታቸው የተነሣ ሌሎችን የማንገዋለልና ለሌሎች ያለማሰብ ዝንባሌ ይታይባቸው ነበር። እንዲሁም ልሳን የማይናገሩትን አማኞች በመንፈስ አልተሞላችሁም ብሎ ማንገዋለል ያለ ፍቅር መጓዝ መሆኑን እናስተውል። 

ጥያቄ 13. ሀ/ ለምንድነው አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን መናገሩ ለአንድ ክርስቲያን አስፈላጊ ነገር ነው የሚሉት? ለ/ በልሳን ከመናገር ይልቅ ትንቢት መናገሩ የበለጠ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? 

ከቁጥር 6-12:- ልሳን ትርጉሙ ካልታወቀ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ጩኸት ይሆናል። ክርስቲያን ከዚህ ትርጉም የለሽ እርምጃ ራሱን መጠበቅ አለበት። እንኳን አእምሮ ያለው ሰው ቀርቶ የሙዚቃ መሣሪያ እንኪ ጩከቱ ትርጉም አለው። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን መመሪያው ፍቅር መሆን ስላለበት ሌሎችን ለማነጽ እንዲችል ለተሰጠው ልሳን ትርጉም ደግሞ አንዲሰጠው መጸለይ አለበት እንጂ እሰይ በልሳን ተናገርኩ ብሉ ረክቶ መቀመጥ የለበትም። 

እንዲሁም ትርጉሙን ካወቀው በልሳን መናገሩ ቀርቶ በሚታወቀው ቋንቋ መልእክቱን በቀጥታ ጉባኤው በሚያውቀው ቋንቋ ብቻ ያስተላልፋል። እንደ ትንቢት መናገር የመሳሰሉትን በቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንፁትን ስጦታዎች መመኘቱ ይሻላል። 

ጥያቄ 14. ሀ/ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች ሲናገሩ በልሳን ሰምተህ ታውቃለህ? ለ/ ልሳኑ ተተርጉሞ ነበር? ሐ/ ለምንድነው የተጠቀሙበት? ለማበረታታት፥ ለማጽናናት፥ ወዘተ። 

ከቁጥር 13-19፡- “ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ”። ይህ የፍቅር መንገድ ነው። ደግሞም በአእምር ሕፃን አለመሆንን ያሳያል። በማይጠቅም ነገር ረክቶ የሚቀመጥ ሕፃን ብቻ ነው። ዝቅ ብሎ በቁጥር 20 ላይ ይህንኑ ሃሳብ ይዞ «በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ» ይላል። 

በቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓታቸውም ጊዜ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን እራት ብቻቸውን በመብላት ሌሎችን መርሳት እንደለመዱ አሁንም በልሳን መናገር የየግል ደስታቸውን እንጂ ወንድሜ እንዴት ይሆን አላሉም። በማይገባው ቋንቋ በወንድሜ ፊት በምናገርበት ጊዜ መንፈሱን እረብሸበት ይሁን ብሎ አለማሰብ የፍቅርን መንገድ መርሳት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው በማህበር ውስጥ እልፍ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ በሚታወቅ ቋንቋ አምስት ቃላት መናገርን እመርጣለሁ ብሏል። ይህም የሚሰሙትን ለማነጽ ስለሚጠቅም ነው። 

ከቁጥር 20-25፡- በልሳን በማህበር በመናገር የማያምኑትንም ማሰናከል አለ። «አብደዋል» እስኪሉ ድረስ መልካሚቱን የጌታን መንገድ በሕፃንነታችን ማሰደብ ተገቢ አይቻልም። 

ሐዋርያው ስለ ልሳን ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ ትክክለኛውን ዓላማ ያስተምራል። በቁጥር 22 ላይ “እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው» ይላል። ይህ ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ ሐዋርያው ኢሳ.28፡11ና 12ን ይጠቅሳል። በዚያ ትንቢት ላይ የልሳን ዓላማ አምጸኞችን ለመቅጣት ነበር። የሚነገራቸው ቃል እንዳይገባቸው ሆኖ ማቅረብ መርገም እንጂ በረከት አልነበረም። እንዲሁም አሁን ልሳን ምልክት ይሁን ከተባለ ምልክትነቱ ለማያምኑ መርገም መሆኑ መዘንጋት የለበትም። 

ጥያቄ 15. ለምን ይመስልሃል ብዙ ክርስቲያኖች በተለምዶ ቋንቋ ከመናገር ይልቅ በልሳን መናገርን የሚፈልጉት?

Leave a Reply

%d bloggers like this: