በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ምእመናን ሙታን ትንሣኤ የሚክዱ እንዳነበሩ ከአፃፃፉ እንረዳለን፡፡ የምእመናንን ትንሣኤ መካድ የክርስቶስን ትንሣኤ መካድ መሆኑን ያስረዳቸዋል። የክርስቶስንም ትንሣኤ መካድ ጠቅላላ የክርስትናን ሃይማናት መካድ እንደሆነ ያስረዳቸዋል። ስለዚህ ክርስቶስ ተነሥቷል፤ እርሱም ከተነሣ በእርሱ የሚያምኑትም ይነሣሉ!
ጥያቄ 23. ስለ ትንሣኤ ውይይት ሲጀምር በቁጥር 1 እና 2 ላይ ለምን ስል መሠረታዊ ወንጌል ይጠቅሳል?
ጥያቄ 24. ከቁጥር 3-11 ሁለት ዓይነት የክርስቶስ ትንሣኤ ማረጋገጫዎች ይጠቅሳል። ምንና ምን ናቸው?
ጥያቄ 25. ከቁጥር 12-19 ባለው ክፍል ውስጥ የምእመናንን ትንሣኤ በምን ላይ ይመሠርተዋል?
ቁጥር 1 እና 2:- ሐዋርያው ስለ ትንሣኤ ትምህርቱን ሲጀምር ስለ ወንጌል ያስታውሳቸዋል። የሰሙት ወንጌል ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ያበስራል። ለጳውሎስ አንድ ወንጌል ብቻ ነው ያለው፤ ይኸውም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ጳውሎስ ይህንን ወንጌል ሲያስተላልፍ የራሱን ሃሳብ ላለመጨመርና አሕዛቦች እንዳያምኑ ሊያደርግ የሚችለውን ነገር ላለማስቀረት ሲል በጣም ይጠነቀቅ ነበር። ጳውሎስ በጥንቃቄ የሰበከው ወንጌል በቆርንቶስ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሙሉ እምነታቸውንም በወንጌሉ ላይ በማድረግ ለመዳን ችለዋል። ይህም ቢሆን፥ ጳውሎስ የሰበከላቸውን ወንጌል አንድም ሳያስቀሩ በእምነታቸው መግፋት እንደሚገባቸው ያሳስባቸዋል። አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያናች ትንሣኤ የለም በማለት ወንጌልን ለመቀየር ሞክረዋል። ጳውሎስም ከወንጌል የሚገኘውን ደህንነት ሙሉ በሙሉ ለማገኘት አንድ ሰው እስከ መጨረሻው በእውነተኛው ወንጌል ማመን እንደሚገባው ይናገራል። ወንጌሉን ለመቀየር የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ የሰውዬውን የመጀመሪያ እምነት ውድቅ እንደሚያደርገው አበክሮ አስገንዝቧል።
ጥያቄ 26. አንዳንዶች ዛሬ እውነተኛውን ወንጌል ለመቀየር የሚሞክሩት እንዴት ነው?
ከቁጥር 9-11:- ይህንን አስታኮ ጳውሎስ ወንጌል ምን እንደሆነ ያብራራል። በመጀመሪያ፡- በኢየሱስ ሞት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለእኛ ኃጢአት ሲል ነው እንጂ ለራሱ ኃጢአት ሲል አይደለም። ሁለተኛ፡- ኢየሱስ ለመሞቱ ማረጋገጫ የሚሆነን የእርሱ መቀበር ነው። አንዳንዶች ዛሬ እንደሚያስተምሩት ራሱን ስቶ አይደለም በመጨረሻ ላይ የነቃው። ሦስተኛ፡- የኢየሱስ አካል እንዳለ ነው ከሙታን የተነሣው (ከመቃብር ውስጥ ሥጋው እንዳለ ነው የተነሣው)፡፡ ይህ ትንሣኤ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊም ጭምር ነው። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን ሞቶ ሲነሣ ለብዙ ሰዎች መታየቱ ነው።
በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ስለ ሁለት የክርስቶስ ትንሣኤ ማስረጃዎች ይናገራል። እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስና የዓይን ምስክሮች ናቸው። ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አስቀድሞ ብሉይ ኪዳን አስተምሮአል። ስለዚህ ሐዋርያው «መጽሐፍም አንደሚል» እያለ ይናገራል። ጌታችንም ስለዚሁ የተናገረውን ከሉቃስ 24፡44-47 ተመልከት።
ብሉይ ኪዳን ስለክርስቶስ ሞት በመዝሙረ ዳዊት 22 እና በትንቢተ ኢሳይያስ 53 ተናግሮአል። ስለትንሣኤውም ሐዋርያት ከብሉይ እንደጠቀሱ በሐዋ.2:25-28፤ 34 እና 35፤ 13:33ና 34 እናነባለን።
ለትንሣኤው የዓይን ምስክሮችም ሐዋርያትና ከ500 በላይ የሆኑት ምእመናን ናቸው። በስም የተሰበከውንም ወንጌል በልዩ ልዩ ተአምራት እያጀበ ለትንሣኤው መሰከረ። የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ይህንን ወንጌል ወይም የምሥራች ሰምተው አመኑ። ራሳቸው ለትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ ማለት ነው። ጳውሎስ ምናልባትም ከሰብዓዊነቱ የተነሣውን ክርስቶስን ያየ የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። እስጢፋኖስ በድንጋይ እየተወገረ ሳለ ነበር ኢየሱስን ያየው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ኢየሱስን ያየው! (የሐዋ.9)።
ጳውሎስ ኢየሱስ ከመረጣቸው ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት እኩል ሥልጣን እንደነበረው ያውቅ ነበር። ይህም ቢሆን በእግዚአብሔር መመረጡን ሲያስብ በጣም ነበር የሚገረመው። እንዲህ የሚገረምበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን ብዙ ያሠቃየና ለብዙ ክርስቲያናት ሞት መንስኤ በመሆኑ ነው። እግዚአብሔር በጸጋው ወደ ራሱ ጠራው። በዚህም ምክንያት እንደሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እርሱም ከሙታን የተነሣውን የጌታ የኢየሱስን ወንጌል መስበክ ጀመረ።
ከቁጥር 12-19፡- ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ እንግዲያስ የአማኛችም ትንሣኤ አለ በማለት የክርስቶስን ትንሣኤ ከአማኞች ትንሣኤ ጋር ያያይዘዋል። የክርስቶስ ትንሣኤ ከሌለ የክርስትና እምነት ራሱ ከንቱ እንዳሆነ ያስረዳል። የክርስትና እምነት ዋና ዋጋው በዚህ ሕይወት ሳይሆን በሚመጣው ሕይወት ስለሆነ ክርስቶስ ካልተነሣ የሚመጣውም ሕይወት አይኖርም፤ እኛም ያን ተስፋ ያደረግን «ከሰው ሁሉ ምስኪኖች ነን»።
እንገዲህ በቆሮንቶስ ያሉ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ትንሣኤ በማመን ወንጌልን ተቀብለዋል። ግን የአማኞችን የወደፊት ትንሣኤ ክደው ነበር። ሐዋርያው ግን የክርስቶስን ትንሣኤና የአማኞችን ትንሣኤ መለያየት እንደማይችሉ ያስረዳቸዋል።
ጥያቄ 27. ሀ/ በኢየሱስ ትንሣኤ ማመን ለምን አስፈለገ?
ለ/ ለምን ኢየሱስ ለኃጢአታችን መሞቱን ብቻ አናምንም?
ሐ/ ዛሬ ለእኛ የቅዱሳን ትንሣኤ ለምን ማበረታቻ ሆነ?