ጥያቄ 1. “ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆና ተነሥቷል” ማለት ምን ማለት ነው? (ቁጥር 29)
ጥያቄ 2. ክርስቶስ ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እርሱ ራሱ ለእግዚአብሔር በመገዛት መንግሥቱን ያስረክባል ሲል ምን ማለቱ ነው? (ቁጥር 25-28)
ጥያቀ 3. ስለሙታን መጠመቅ ማለት ምን ማለት ነው? (ቁጥር 29)
ቁጥር 20፡- የክርስቶስ ትንሣኤ በእርሱ ለሚያምኑት ትንሣኤ ዋስ (መተማመኛ) ነው። ክርስቶስ ስለተነሣ በእርሱ የሚያምኑትዎ በእርግጥ ይነሣሉ።
ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ “በኩር” ይባላል። በኩር የሚለው ቃል የተወሰደው ከብሉይ ኪዳን ከዘሌዋውያን 23:10 ላይ ነው፡፡ መከሩ ለመጀመሪያ ሲደርስ የተወሰነ ነዶ ወደ ቤተ መቅደስ ለምስጋና መስዋዕት ይቀርብ ነበር። ይህ የበኩር መሥዋዕት የቀረው መከር እንደሚሰበሰብ ዋስትና (መተማመኛ) ነበር። እንዲሁም የክርስቶስ ትንሣኤ በእርሱ ለሚያምኑት ትንሣኤ መተማመኛ ነው። እርሱ ከሙታን ስለተነሣ በእርሱ የሚያምኑትም እንደሚነሁ በፍጹም የተረጋገጠ ነገር ነው።
ከክርስቶስ ትንሣኤ በፊት ከመቃብር የተነሱ ብዙ ሲሆኑ (ለምሳሌ አልዓዛር ) ለምን ክርስቶስ የትንሣኤ በኩር (የመጀመሪያ) ተባለ? ከእርሱ በፊት የተነሱት ተመልሰው ሞተዋል። ክርስቶስ ግን ዳግመኛ ላለመሞት ተነሥቷል። የእኛም የአማኞች ትንሣኤ እንዲሁ ዳግመኛ ላለመሞት ነው። ስለዚህ በዚህ ዐይነት ትንሣኤ እስካሁን የተነሣ ክርስቶስ ብቻ ስለሆነ የትንሣኤ በኩር ተባለ።
ከቁጥር 21-23:- በዚህ ክፍል ሁለት አዳሞች እንዳሉ ይነገረናል። በመጀመሪያው አዳም አማካይነት ሞት ለሰው ሁሉ እንደመጣ ሁሉ ÷ አሁንም በሁለተኛው አዳም (በክርስቶስ ) ትንሣኤ ለአማኞች መጣ፡፡ ከዚህ ጋር ሮሜ 5፡12-14ን አስተያይ። ክርስቶስ የተነሣው በመጀመሪያው የፋሲካ ቀን ጠዋት ላይ ነበር። አሁን ለዳግም ምፅዓቱ ግን ባለፉት ዘመናት ውስጥ በእርሱ ያምኑ የነበሩትን በሙሉ ነው ከሙታን የሚያስነሣው።
ከቁጥር 24-28:- ሁሉ ከክርስቶስ እግር ሥር ከተገዛ በኋላ ክርስቶስ ራሱ ሥልጣንን ለእግዚአብሔር መልሶ እርሱ ራሱም ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ ተመርኩዘው ሐሰተኛ አስተማሪዎች የክርስቶስን አምላክነት ይክዳሉ። ይህ ክፍል ክርስቶስን በአምላክነቱ ሳይሆን የሚመለከተው በሰውነቱ ነው። አዎን! ክርስቶስ በሰውነቱ ለእግዚአብሔር ሲጸልይ እግዚአብሔርን ሲያመልክ እንደነበር በወንጌል ተጽፏል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ መልሶ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንዳሆነ እርሱ ራሱ አምላክ እንደሆነ ያስተምራል።
እንግዲህ ክርስቶስ አሁን በሰውነቱ በዓለም ላይ ነግሶ ስላለ ወደፊት ሥልጣን ሁሉ በእግሩ ሥር እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ሥልጣን ሁሉ ለክርስቶስ ቢሰጥም እስካሁን ድረስ ሁሉን ነገር በራሱ ቁጥጥር ሥር አላደረገም። ሁሉንም በቁጥጥሩ ሥር የሚያደርገው በመጨረሻው ዘመን ነው። በዚህ ጊዜ ሞትን ብቻ ሳይሆን ሰይጣንንና በጌታ ኢየሱስ የማያምኑትን መንግሥታት በሙሉ ያወድማል። ሁሉም ተንበርክከው የእግዚአብሔርን ልጅ ያከብራሉ፤ (ፊል.2:10-11)። ሁሉ ነገር በእግሩ ሥር የሚሆነው የመጨረሻው ጠላት ያም ሞት ከወደመ በኋላ ብቻ ነው። እስከዚያ ድረስ ክርስቶስ በሰውነቱ የዓለም ገዥ ነው። በዚህ ጥቅስ መሠረት ግን ሁሉን በእግሩ ሥር ከገዛ በኋላ ሥልጣንን ከሰውነቱ አሳልፎ ለእግዚአብሔር ይሰጣል። በአምላክነቱ ግን እርሱዎ ዘለዓለማዊ ወልድ ስለሆነ ይህን ሥልጣን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይካፈላል። በዚህ ክፍል ላይ በሥላሴዎች መካከል ያለውን ዘላለማዊ ግንኙነት እንመለከታለን። ምንም እንኳን አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ እግዚአብሐርም ቢሆኑ፥ በሰብዓዊ ባሕርያቸውም እኩል ቢሆኑም፥ የግንኙነት ቅደም ተከተል አላቸው። እግዚአብሔር አብ ዋነኛውና የመጨረሻ ባለሥልጣን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ እንደ ልጅ ሁሉ የአባቱን ፈቃድ ይፈጽማል። ስለዚህም የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም የሰውን ልጅ ፈጠረ! ከኃጢአትም አዳናቸው። በተመሳሳይ ሁኔታም ሁሉን ነገር በራሱ ቁጥጥር ሥር አደረገ። አሁንም ቢሆን በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ነው። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአብና የወልድ ወኪል ሆኖ ፈቃዳቸውን የሚፈጽም ነው። ስለዚህ የመጨረሻው ፕሮግራም ሁሉ ነገር በክርስቶስ አማካይነት ለሥላሴ ተጠቃልሉ መገዛት ነው።
ጥያቄ 4. ከሞት በስተቀር ሌሎች የክርስቶስ ጠላቶች እነማን ናቸው? መቼስ ያሸንፋቸዋል?
ቁጥር 29:- በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ለሙታን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ይካሄድ እንደነበር ከዚህ እንረዳለን። ምናልባት አምነው ሳይጠምቁ ለሞቱት ዘመዶቻቸው በእርሱ ምትክ ይጠምቁላቸው ነበር። ሐዋርያው ይህንን ሥርዓት አልደገፈውም አልተቃወመውም። ግን የሙታንን ትንሣኤ የሚክዱ ከሆነ «ታዲያ ለምን ለሙታን ትጠመቃላችሁ?» በማለት ራሳቸው እንኳ ለትንሣኤ በዚህ ሥርዓታቸው ምስክሮች እንደሆኑ ያስረዳቸዋል።
ከቁጥር 30-34:- ሙታን የማይነሡ ከሆነ ሐዋርያውም ለወንጌል ሥራ ብሉ ራሱን በየጊዜው ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ለምንድነው? እንግዲህ ሙታን የማይነሡ ከሆነ ሰው ከዚህ ዓለም የተሻለ ደስታ ስለማያገኘ «ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ» በሚል ፍልስፍና መመራት አለበት። ግን ክርስቶስ ከመቃብር ስለተነሣ የእኛም የአማኞች ትንሣኤ ተረጋግጧል። ስለዚህ በዚህ ዓለም ለክርስቶስ ክብር ሕይወታችንን ብንሠዋ በትንሣኤ ዋጋችንን አናገኛለንና በተስፋ አንሮጣለን።
ጥያቄ 5. ሀ/ አንዳንድ ሰዎች ወይም አማኞች በሥራቸው “ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ” የሚለውን ፍልስፍና መደገፋቸውን እንዴት ያሳያሉ? ለ/ በክርስቲያን ትንሣኤ ቢያምኑ ሥራቸውን እንዴት ይለወጡ ነበር?