ጥያቄ 16. በዚህ ክፍል ላይ ስንት ነጥቦችን እንደሚጠቅስ በአጭሩ ዝርዝር።
የደብዳቤው መደደሚያ ላይ በሆነው በዚህ ክፍል ሐዋርያው የተለያዩ ነጥቦችን ይጠቅሳል፤ በአጭሩ እንዘርዝራቸው።
1ኛ/ ከቁጥር 5-6፡- «በጉዞዬ እንድትረዱኝ» ሲል ገንዘብ መጠየቁ እንዳልነበረ ከ9፡15 እንረዳለን። ምናልባት አንዳንድ ለጉዞው የሚያስፈልገው ስንቅና ሸኚዎች የመሳሰሉ ነገሮች ይሆናሉ።
2ኛ/ ከቁጥር 7-9፡- በኤፌሶን ለአገልገሎት አንደሚሰነብት ይነግራቸዋል። «ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና» እግዚአብሔር የአገልገሉት በር ሲከፍት እድልን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ከሐዋርያው እንማራለን። ይህም በር ብዙ የተቃውሞ ግፊት የበዛበት እንደሆነ ይናገራል። የአገልገሎት በር መከፈት ማለት ተቃውዋ ጠፋ ማለትም እንዳልሆነ እንገንዘብ።
ጥያቄ 17. በአሁኑ ጊዜ የአገልግሎት በር ለቤተ ክርስቲያንህ ክፍት ነው ወይስ ዝግ ነው? እንደት ነው ይህንን የምታውቀው? በሚመጡት አጋጣሚዎችስ ይጠቀሙባቸዋል? ተቃውሞስ አለ? ካለ ተቃውሞው ከማነው?
3ኛ / ከቁጥር 10-11:- ጢሞቴዎስን በአክብሮት እንዲቀበሉት እንጂ እንዳይንቁት ያስጠነቅቃል። ምናልባት ጢሞቴዎስ አይን አፋር ሳይሆን አይቀርም፤ 1ኛ ጢሞ.4:11-12፤ 2ኛ ጢሞ. 1:7። ደግሞም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በአገልጋዮች መካከል ስለሚመርጡ ትዕቢተኞች እንደሆኑ ሐዋርያው ስላወቀ በአክብሮት እንዲቀበሉት ያስጠነቅቃቸዋል።
4ኛ/ ቁጥር 12፡- አጵሎስ አሁን ሊጉበኛቸው እንዳማይሄድ ያስታውቃቸዋል፡፡
5ኛ/ ቁጥር 13:- በእምነታቸው የበረቱ እንዲሆኑ ያበረታታቸዋል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች አምስት ዋና ዋና ሊጠብቋቸው የሚገቡ ትእዛዞች ይሰጣቸዋል።
1. ንቁ፡- ራሳቸውን ከኃጢአትና ከትዕቢት መጠበቅ ነበረባቸው። ራሳቸውን ከሐሰተኛ ትምህርት መጠበቅ ነበረባቸው። ሰይጣን በሚያገኘው አጋጣሚ ወይም ባለመስማማታቸው ተጠቅሞ ሊያጠፋቸው እንደተዘጋጀ መገንዘብ ነበረባቸው።
2. በሃይማኖት ቁሙ፡- ሃይማናታችንን ጠብቀን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ መቀበርና ትንሣኤ ላይ መመሥረታችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ለእምነታችን ከዚህ ሌላ ምንም ዓይነት መሠረት ሊኖረው አይገባም። በመከራ ውስጥ ቢሆንም በኢየሱስ ላይ ያለንን እምነት ለመጠበቅ ቁርጥ ውሣኔ መውሰድ ይገባናል።
3. ጎልምሱ:- እውነቱን ከሚቃወሙት ከብዙዎቹ ፊት ለመቆም ጎበዞች መሆን አለብን። ሰዎች በሚያላግጡብንና በሚያሳድዱን ጊዜ በግልጽ እምነታችንን መግለጽ ጉብዝናን ይጠይቃል። መታወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ክርስትና ሃይማኖት ሊሆን አይችልም።
4. ጠንክሩ:- ልክ እንደ ሁለተኛውና ሦስተኛው ትእዛዝ ይህም ትእዛዝ በእምነታችን ጠንካሮች እንድንሆን ይገፋፋናል። በተጨማሪም ይህ ማለት ኃይልህንና ሁለንተናህን በእግዚአብሔር ሥራ አውል ማለት ነው። አስተውል! ይህ ኃይል የእኛ ሳይሆን እግዚአብሔር የሚሰጠን ኃይል ነው።
5. በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን፡- የእግዚአብሔር ትእዛዞች በሙሉ ፍጻሜ የሚያገኙት በፍቅር ነው። ፍቅር ከምንሠራው ሥራና ድንቅ ከሆኑት ስጦታዎች ሁሉ የበለጠ ጠቃሚ ነገር ነው። ለምስክርነታችን ኃይል የሚሰጠው ፍቅር ነው።
ጥያቄ 18. እነዚህን አምስት ትእዛዞች እየጠበቅህ ያለኸው እንዴት ነው? በሕይወትህስ ውስጥ የሚታዩት እንዴት ነው?
6ኛ/ ከቁጥር 14-18፡- ስለ እስጢፋኖስ ቤተሰብ እንዴት ለወንጌል ሥራ የነቁ እንደሆኑ ይናገራል፡፡
7ኛ/ ቁጥር 19 ላይ፡- “በቤታቸውም ካለች ቤተ ክርስቲያን” በማለት ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሳትሆን የምእመናን ክምችት ወይም ጉባኤ መሆንዋን ይገልጻል።
8ኛ/ ቁጥር 21-24:- ስንብትና ቡራኬ