2ኛቆሮ.2:14-17

ጥያቄ 9 ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 10. የሞት ሸታና የሕይወት መዓዛ መሆን ምን ማለት ነው?

ጥያቄ 11. በቁጥር 17 የእግዚአብሔርን ቃል መሸቃቀጥ ማለት ምንድነው? 

ቁጥር 14:- «ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን» ይህ አነጋገር ግልጽ አይደለም። መሆን ያለበት «ድል በመንሣት ለሚያዞረን» ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ሐዋርያትን በድል ከቦታ ወደ ቦታ ያዞራቸዋል ማለት ነው። ይህ አነጋገር በዘመኑ የነበረውን የነገሥታትን ልማድ ይመረኮዛል። አንድ ንጉሥ ድል ሲያደርግ ለድል ያበቁትን ጃግኖች በክብር አሰልፎ በድል ሰልፍ ይመራቸዋል። ሐዋርያው ያን ተመርኩዞ ክርስቶስ በተጕናጸፈው ድል እግዚአብሔር ሐዋርያቱንና የወንጌልን አገልጋዮች በክብር ሰልፍ ይመራቸዋል ማለቱ ነው። 

በዚህም ሰልፍ በየሄዱበት ቦታ የእግዚአብሔርን እውቀት ሽታ ያሰራጫሉ። አሁንም ሐዋርያው የጥንትን ባህል ተመርኩዞ ነው ስለዚህ ሽታ የሚናገረው። በዘመኑ በድል ሰልፍ ላይ ጣፋጭ ሽታ ያለው እጣን ይጤስ ነበር። ይህን ምሳሌ ተመርኩዞ ሐዋርያው የወንጌል አገልጋዮች የአሸናፊው የክርስቶስ እጣን ናቸው ይላል። ይህም እጣን “የእግዚአብሔር እውቀት” ነው። በዞሩበት ቦታ ሁሉ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር እውቀት ይመራሉ። 

ጥያቄ 12. የአንተ ሕይወት የእግዚአብሔርን እውቀት ለሌሎች የሚገልጽ ጣፋጭ ሽታ የሆነው እንዴት ነው? 

ቁጥር 15 እና 16፡- ይህ ሽታ ሁለት ዓይነት ነው። ወንጌላውያንን የሰሙ ሁሉ ወደ እምነት አይመጡም። አንዳንዶች ሲቀበሉ ሌሎች ይክዳሉ። የሚያምኑት ሕይወትን ሲቀበሉ ወንጌላውያን የሕይወት ሽታ ይሆኑአቸዋል። የማያምኑት ደግሞ ባለመቀበላቸው ለፍርድ ሲቀሩ ወንጌላውያን ለማያምኑት የዋት ሽታ ይሆኑባቸዋል። ከዚህ ጋር የሚከተሉትን ጥቅሶች አስተያይ፤ ሉቃስ 2:34፤ ዮሐ.3፡36። 

ለዚህ ሥራ መሰለፍ ከባድ ነገር እንደሆነ ተረድቶ ሐዋርያው «ስለዚህ ነገር የሚበቃ ማነው?» ይላል። ለዚህ ሥራ አገልጋዮቹን የቀባ እግዚአብሔር ስለሆነ ብቃትንም የሚሰጥ እርሱው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን ያለ እግዚአብሔር ረዳትነት ሙሉ በሙሉ ጥሩ ሽታ እንደማይኖረው ተረድቶ ነበር። ታዲያ እኛ ምን ያህል ነው እግዚአብሔር የሰጠንን ሥራ ለመሥራት በእርሱ ላይ መደገፍ ያለብን? 

ወንጌላዊ የሥራውን ታላቅነት ተረድቶ በእምነት በእግዚአብሔር ብቻ ተደግፎ አንደመቆም ቃሉን ለማሳመን የተለያዩ ዘዴዎችን እንዲጠቀም ይፈተናል። አንዳንዶች በእኛም ዘመን በሰው ዘንድ መከበርን ፍለጋ የሥጋ ጥበቦችን ሲጠቀሙ ይታያሉ። ሰው በጌታ ቃል ላይ ምንም ዘዴ መቀላቀል አያስፈልገውም፤ ቃሉ ራሱን የቻለ ኃይል ነውና። ስለዚህ ሐዋርያው «የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚሸቃቅጡ እንደብዙዎች አይደለንምና» ይላል። የእግዚአብሔርን ቃል መሸቃቀጥ ማለት ሰዎች ወንጌልን እንዲቀበሉ የሰዎችን ዘዴ በወንጌል ላይ መጨመር ማለት ነው። ይህን መሸቃቀጥ የተባለውን ቃል ሐዋርያው በዘመኑ ከነበሩ የወይን ጠጅ ነጋዴዎች ሥራ ተበድሮአል። በዘመኑ የነበሩ ሌቦች የሆኑ የወይን ጠጅ ነጋዴዎች በማታለል ገንዘብ ለማትረፍ በወይኑ ላይ ውኃ ይቀላቅሉ ነበር። ይህም ወይኑን ርካሽ ወይን ያደርገዋል። በእግዚአብሔርም ቃል ላይ የግል ጥቅምን አስምርኩዞ የሰውን ዘዴና ጥበብ መጨምር ትርፉ ንጹሑን ቃል ማራከስ ነው። 

ጥያቄ 13. የሰዎችን የአሠራር ዘይቤ በመጠቀም እንዴት አድርገን ወንጌልን ማስተላለፍ እንደምንችል ምሳሌ በመስጠት አስረዳ። 

ሐዋርያው ግን «በቅንነት» ወንጌልን ምንም ሐተታ ሳይቀላቅል ይናገር ነበር። ይህም ውጭን አይቶ በሚፈርድ ሰው ፊት የሚደረግ ጥንቃቄ ሳይሆን ልብን በሚመረምር በእግዚአብሔር ፊት የሚደረግ ጥንቃቄ ነው። «በእግዚአብሔር እንደተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን»። ወንጌላዊ ሁልጊዜ አስቀድሞ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሰለፍ አለበት። በእግዚአብሔር እንደተላከ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ካህን መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ወንጌልን በተገቢው መንገድ ለማስተላለፍ ሁለት ነገር ያስፈልገናል። 

አንደኛ:- ወንጌል ምን እንደሆነ በደንብ ማወቅ ይገባናል፤ ምክንያቱም የሰዎችን ሃሳብ በውስጡ ላለመጨመር ስንል ነው። ይህ ማለት ወንጌልን በተመለከተ ሰዎች ጥሩ ትምህርት ማግኘት አለባቸው። 

ሁለተኛ፡- ወንጌልን በምንሰብክበት ጊዜ ከውስጥ ይህንን እንድናደርግ ያነሳሳን ሃሳብ ንጹሕ መሆኑን ማየት ይገባናል። ገንዘብን ከመውደድ ወይም ታዋቂነትን ለማግኘት ስንል መስበክ አይኖርብንም። በምትኩ ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅርና ታዛዥነት የተነሣ መሆን ይገባዋል። 

ጥያቄ 14. ህ/ እውነተኛውን ወንጌል ለማስተላለፍ አንድ ሰው ማወቅ ይገባዋል ብለህ የምታምንባቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። ለ/ አንዳንድ ሰዎች ወንጌልን ለመስበክ በሚነሡበት ጊዜ ሊኖራቸው የሚችለውን የተሳሳተ አመለካከት አብራራ። ሐ/ ወንጌልን ለመስበክ የሚያነሣሡን ትክክለኛ የሆኑ አስተሳሰቦች ምን መሆን ይገባቸዋል?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.