ጥያቄ 1. በቁጥር 23 ላይ ሐዋርያው በመሐላ ነገሩን ሲያረጋገጥ እናነባለን፤ ይህን ከማቴ.5፡37 ጋር በማስተያየት አስታራቂ ሃሳብ ጻፍ።
ጥያቄ 2. ሐዋርያው ጉብኝቱን የሰረዘው ለምንድነው ይላል?
ቁጥር 23፡- በምዕራፍ 1 ቁጥር 15 እና 16 ላይ አንደጠቀሰው ሐዋርያው ያሰበውንና የሰጣቸውን ሁለት ጊዜ የምጎብኘት ተስፋ እንዳልጠበቀ በማስታወስ ይህንን ያደረገው ለጥቅማቸው እንጂ ቃልን ያለመጠበቅ ጉዳይ እንዳልሆነ እንዲረዱለት በመሐላ ያረጋግጥላቸዋል።
“በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ”። ይህ የመሐላ አነጋገር ነው። መሐላ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት በዓለም ውስጥ በኃጢአት ምክንያት ውሸት ስለበዛ ነው። እንኳን ሰው ቀርቶ እግዚአብሐርም ራሱ ነገሩን በመሐላ እንደሚያረጋግጥ በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ እናነባለን፤ (ሉቃ.1:73፤ ዕብ. 6፡13-16)። በማቴ 5፡37 ላይ ጌታ መሐላን ይከለክላል። ይህም በፊት የተፈቀደውን መከልከሉ ሳይሆን በእርሱ ዘመን የነበሩ ፈሪሳውያን በመሐላ ካልተናገሩ በቀር መዋሽት የተፈቀደ ነው ይሉ ነበርና፤ እንዲሁም መተማመን ስለጠፋ በትንሽ ነገር እንኳ ይምሉ ስለነበር ነው።
ቁጥር 24፡- «በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደልንም። በእምነታችሁ ቆማችኋል» ። እንኳን ሌላ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀርቶ ሐዋርያው እንኳ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ማገልገል እንጂ የመግዛት መብት እንዳልነበረው ያስረዳል። የቤተ ክርስቲያንም ሸማገሌዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ማዘዝ የሚችሉት የክርስቶስን ትእዛዝ በማስተላለፍ ብቻ እንጂ ራሳቸው ትእዛዝ እያወጡ አለመሆኑን ይህ ቃል ያስተምረናል።
ጥያቄ 3. ሀ/ መሪነትን እንደ አገልገሎት ሳይሆን እንደ መግዛት የሚያዩ አንዳንድ መሪዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ይገኛሉ? ለ/ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሕዝቡን በጭካኔ ከሚገዛ አብሮ በስምምነት ቢያገለግል የሚሻለው ለምንድነው?
2:1:- ሐዋርያው ከዚህ በፊት በሃዘን እንደጕበኛቸው እንረዳለን። ይህም ጉብኝት የመጀመሪያው አልነበረም። ግን በመጀመሪያ ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ተመልሶ እንደጎበኛቸውና ያም ጉብኝት የሃዘን ጊዜ እንደበር ይናገራል። በጉብኝቱም ፋንታ በሃዘን ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህም ደብዳቤ 1ኛ ቆሮንቶስ ነው። አሁን ግን ንስሐ መግባታቸውን ስለተረዳ ጉብኝቱ የሃዘን ሳይሆን የደስታ ስለሚሆን ለሦስተኛ ጊዜ ሊጎበኛቸው እንደተዘጋጀ ይጽፋል (7:6-13፤ 12:14)።
እንደ ወላጅ ወይም እንደ ቤተ ክርስቲያን መሪ ለወንጌል ቅድስናና ለሰውዬው ዕድገት ስንል ጠንከር ያሉ የሥነ ሥርዓት እርምጃዎችን መውሰድ አለብን። በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 ላይ ክፉው ሰውዬ ከቤተ ክርስቲያን ሕብረት ውጪ መሆን ነበረበት። እንደዚህ ዓይነት ውሣኔ በምንወስንበት ጊዜ ይህንን ውሣኔ እንድናደርግ የገፋፋንን በስተጀርባ ያለውን ሃሳባችንን መመርመሩ ተገቢ ነው። ከቅናት፥ ከጥላቻ ወይም ከንዴት የተነሣ መሆን የለበትም። በምትኩ የዚህ የሥነ ሥርዓት እርምጃ መሠረት ፍቅር መሆን አለበት። ልክ እንደ ጳውሎስ እርምጃው በእንባና በሃዘን የታከለ መሆን ይገባዋል። ሁሌ አንድ የሥነ ሥርዓት እርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳን ምክንያት ከፍቅር የመነጨ መሆን አለበት እንጂ ከንዴት የመነጨ መሆን የለበትም።
ጥያቄ 4. ይህ ዓይነቱ ቅጣት ብዙ ጊዜ ወላጆችም ሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚወስዷቸው የሥነ ሥርዓት እርምጃዎች ለየት የሚለው እንዴት ነው?